>

በአድዋ ድል ማግስት የሮማው ሊቀ ጳጳስ ልመና ....! (ዮሀንስ ተካልኝ)

በአድዋ ድል ማግስት የሮማው ሊቀ ጳጳስ ልመና ….!!!

 

ዮሀንስ ተካልኝ
“በጣም ኃያል ለሆኑት ምኒልክ ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ ሰላምና ገናናነት ለርስዎ ይሁን!
 ዛሬ አንድ ንጉሳዊ ልግስና እንዲያደርጉ የምክር ቃላችንን ክርስቲያናዊና ንጉሳዊ ለሆነው ልብዎ ለመላክ አሰብን። ይህ ድል ብዙ ምርኮኞች በእጅዎ ጥሎልዎታል።እነዚህ ምርኮዎች በወጣትነት ዘመን የኑሮኣቸው ተስፋ ባበበትና የብርሃን ጎህ በቀደደበት ሰዓት ካገራቸው ከቤተሰቦቻቸው ተነጥለው ይገኛሉ።
የነርሱ ምርኮ የግርማዊነትዎን ዝናና ገናናነት ምንም ሊያስፋፋው አይችልም። ይልቅ የምርኮ ዘመን ጊዜ በረዘመ መጠን በሺ የሚቆጠሩት ቤተሰቦቻቸው የመንፈስ ሀዘን እየበዛ ሄዷል። ከእየሱስ ክርስቶስ በተቀበልነው የተቀደሰ መልእክት እንደ ልጆቻችን እንወዳቸዋለን።
ስለዚህ ያንድ ልብ በቅድስት ስላሴ በተባረከችይቱ ድንግል ወይም ከዚህ ዓለም በሚወዱት ስም የሚያቀርብልዎትን ልመና ይቀበሉና ሳይዘገዩ ነፃነታቸውን ይስጡዋቸው። ኃያሉ ንጉሠ ነገስት ሆይ ይኽን የደግነት ስራ ባለመስራት እምቢታዎን ባለም ነገስታት ዐይን ፊት አይግለፁ። በወንድማማችነት እና በሰብአዊ ተግባር አንፃር ያለው የጦር መብትዎ ምንድን ነው የዚህን ብድር ርኀሩኅ አባት እግዚያብሔር በብዙ ይክስዎታል። ይህን ክብር ያላትን ደብዳቤ በመንግስትዎ ዜና መዋዕል ያስመዝግቧት።
እስከዚያው ለንጉሳዊ ቤተሰብ እግዚያብሔር በረከት እንዲያወርድ እንለምናለን።
ሮማ ቅዱስ ጴጥሮስ አጠገብ
ግንቦት 11 ቀን 1896 ዓ.ም በ19ኛው ዘመነ ጵጵስና ተፃፈ “
ዋቢ፦ አፄ ምኒሊክና የኢትዮጵያ አንድነት
Filed in: Amharic