>
5:13 pm - Wednesday April 18, 1488

የአባይን ውሃ ኢትዮጵያ እንዳትገድብ …ግብጽ፣ ሱዳን እና አሜሪካ ተስማሙ! (ዳዊት ከበደ ወየሳ)

የአባይን ውሃ ኢትዮጵያ እንዳትገድብ …ግብጽ፣ ሱዳን እና አሜሪካ ተስማሙ!

(ዳዊት ከበደ ወየሳ)
*  ግብጽ እና ሱዳን፤ አሜሪካ እና የአለም ባንክ በተናጠል ስብሰባ ካደረጉ በኋላ፤ ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ላይ ውሃ ማጠራቀም እንዳትጀምር ሲሉ በድፍረት መግለጫ አውጥተዋል። ይህ ስምምነት የተደረገው ደግሞ፤ 86% የናይል ውሃ የምታበረክተውን ኢትዮጵያን ሳያካትት ነው። ይህም በ1929 ኢትዮጵያን ሳያካትት የተደረገውን የቅኝ ገዢዎች ውል የሚያስታውስ፤ የአንድን አገር ሉአላዊ ነጻነት የሚጋፋ ተግባር ሆኖ አልፏል።  ይህ የሆነው ደግሞ፤ በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ጥቁር ህዝቦች፤ የአድዋን 124ኛ አመት የድል በአል ለማክበር በተዘጋጁበት ወቅት መሆኑ፤ ዜናውን ለየት ያደርገዋል
—–
በኦክቶበር 2019 – የራሺያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን ኢትዮጵያ እና ግብጽን ማደራደር ጀምረው ነበር። ይህን የታዘበችው አሜሪካ፤ “እኛ እንደታዛቢ እንሁን። እናንተም አሜሪካ መጥታቹህ ተነጋገሩ።” የሚል መልዕክት አስተላለፈች። ሁለቱ አገሮች ሱዳንን ጨምረው ለመነጋገር ወደ አሜሪካ አቀኑ። በውሃው አሞላል ላይ ግን መስማማት አልቻሉም። በቅርቡ አሜሪካ ከታዛቢነት ወደ ጉዳዩ ባለቤትነት ስትቀየር፤ ኢትዮጵያ ድርድር ማድረግ አቆመች።
በዚህ መሃል ግን… በ124ኛው የኢትዮጵያ አድዋ ድል ዋዜማ ላይ… የአሜሪካ መንግስት አስገራሚ መግለጫ አወጣ። “ስምምነት ሳይደረግ የአባይን ውሃ መገደብ ወይም ማጠራቀም አይቻልም!” በማለት ኢትዮጵያን አስጠንቅቋል።
የአሜሪካ ጠቅላይ አቃቤ ንዋይ – U.S. Department of Treasury  መስሪያ ቤት እንደገለጸው ከሆነ፤ “ፌብሩዋሪ 27 እና 28 በተደረገው ስብሰባ በአሜሪካ በኩል፤ የአቃቤ ንዋዩ ሃላፊ፤ ስቴቨን ኑቺን፤ ከግብጽ እና ሱዳን ተወካዮች ጋር ስብሰባ አድርገው ነበር።”
መግለጫው ሲቀጥል፤ የግብጽ፣ የኢትዮጵያ እና የሱዳን፤ እንዲሁም የአለም ባንክን ጥናት መሰረት በማድረግ፤ የህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሊት እና አሰራሩን በተመለከተ፤  ከስምምነት ላይ እንዲደረስ አሜሪካ የበኩሏን ስራ እንደተወጣች ይገልጻል።
 በተናጠል በተደረገው የሁለትዮሽ ስምምነት፤ ሚንስትሮቹ በስምምነቱ ላይ ያላቸውን አስተያየት ሰጥተዋል። ላለፉት አራት ወራት የተደረገው ውይይት እና የደረሱበት ስምምነት፤ ነገሮችን ሚዛናዊ እና ብቁ በሆነ ሁኔታ የቃኘ እና የሶስቱንም አገሮች ጥቅም ያስጠበቀ እንደነበር፤ መግለጫው አብራርቷል።
ላለፉት ሰባት አመታት በሶስቱ አገሮች መካከል የነበረው ውይይት፤ በተለይም በ2015 ግድቡ የታችኛውን አገሮች እንዳይጎዳ ተብሎ የደረሱበት ስምምነት መከበር እንዳለበት ገልጿል።
በአሁኑ ወቅት ግብጽ እና ሱዳን፤ ከአሜሪካ እና አለም ባንክ ፕሬዘዳንት ጋር ስብሰባ ተቀምጠው፤ የራሳቸውን ውሳኔ ሰጥተዋል። ኢትዮጵያ ይህን ውሳኔ ማክበር እንዳለባት ሊነግሩን ፈልገዋል። አልፈው ተርፈው፤  በግድቡ ላይ ምንም አይነት የውሃ ሙሊት ወይም ውሃ ማጠራቀም እንዳትጀምር ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ኢትዮጵያ ይህን ውል የማታከብር እና ውሃ መሙላት ከጀመረች፤ የአለም ባንክ ገንዘብ ይከለክላል። አሜሪካም እርዳታዋን ታቋርጥ ይሆናል። ግብጽ ደግሞ… በአሜሪካ የታገዘ የአየር ጥቃት ከመፈጸም ወደኋላ እንደማትል ይገመታል። ኢትዮጵያ በበኩሏ በምን አይነት ዝግጅት ላይ እንዳለች፤ ገና አልታወቀም። ወደጦርነት ከማምራት በፊት ግን ፊታችንን ወደ ራሺያ እና እስራኤል በማዞር፤ ወታደራዊ ምክክር ማድረግ ያስፈልግ ይሆናል።
በደርግ ዘመነ መንግስት – ከግብጽ ወይም ከሱዳን ተነስቶ በጣና በለስ መሰረተ ልማት ላይ የአየር ጥቃት የሚደርስ ከሆነ፤ በአጸፋው ከባህር ዳር ወይም ከአስመራ ተነስቶ፤ የሱዳኑን መሮወ… የግብጹን አስዋን ግድብ ለመምታት በኢትዮጵያ አየር ኃይል በኩል ዝግጅት ይደረግ እንደነበር ይታወቃል። ስለሆነም… የዲፕሎማሲው ስራ እንዳለ ሆኖ፤ ለመከላከልም ሆነ ለማጥቃት የተዘጋጀ አየር ኃይል ያስፈልገናል። ለዚህም ነው – የራሺያ እና የእስራኤልን በሮች በድጋሚ ማንኳኳት የሚኖርብን – ነገን እናስብ።
እንኳን ለ124ኛው የአድዋ ድል በአል አደረሰን!
Filed in: Amharic