>

የሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን 14ኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ (ልኡል አምደጽዮን ሰርጸ ድንግል)

የሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን 14ኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ

 

ልኡል አምደጽዮን ሰርጸ ድንግል
አንጋፋው፣ ሁለገቡና ስመጥሩ የጥበብ ሰው ብላቴን ጌታ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን ያረፉት ከዛሬ 14 ዓመታት በፊት (የካቲት 18 ቀን 1998 ዓ.ም) ነው፡፡
ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ሁለገብ የጥበብ ሰዎች መካከል በቀዳሚዎቹ ተርታ የሚመደቡት ብላቴን ጌታ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን፣ በመላው ዓለም ሳይቀር ተደናቂነትና ከበሬታ ያላቸው ድንቅ ኢትዮጵያዊ የጥበብ ሰው ናቸው፡፡
– – –
ጸጋዬ የተወለዱት በ1929 ዓ.ም የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ በተጀመረ በስድስተኛው ወር ነው። የትውልዳቸው ቦታ ከአምቦ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ቦዳ አቦ በመባል የምትጠራው ስፍራ ናት፡፡ ቦዳ ተራራ ግርጌ የሚገኘው የአባታቸው ቤት ሲቃጠል እናታቸውና እህታቸው ከወራሪው ጦርና ከባንዳ ጋር ተታኩሰው በአርበኞች እርዳታ ሕይወታቸውን ካተረፉ በኋላ ወደእናታቸው የትውልድ ስፍራ ተሰደዱ፡፡
– – –
በግዕዝ፣ በአማርኛና በኦሮምኛ እየተማሩ ያደጉት ጸጋዬ፣ የኋላ ኋላ ዓለም ያደነቃቸው ገጣሚ፣ ፀሐፊ ተውኔትና ባለቅኔ ሆኑ፡፡ 52 የግጥምና የቅኔ ስራዎቻቸው የተካተቱበት ‹‹እሳት ወይ አበባ›› የተሰኘው መድብል እጅግ ተወዳጅና በብዙዎች ዘንድ ከሚታወሱላቸው ስራዎቻቸው መካከል አንዱና ዋነኛው ነው፡፡
ከተውኔቶቻቸው መካከል ደግሞ ‹‹የዳኒሲዩስ ዳኝነት››፣ ‹‹በልግ››፣ ‹‹የደም አዝመራ››፣ ‹‹እኔም እኮ ሰው ነኝ››፣ ‹‹የከርሞ ሰው››፣ ‹‹የእሾህ አክሊል››፣ ‹‹ቴዎድሮስ››፣ ‹‹ምኒልክ››፣ ‹‹ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት››፣ ‹‹ዘርዓይ ደረስ››፣ ‹‹ሀሁ በስድስት ወር››፣ ‹‹እናት ዓለም ጠኑ››፣ ‹‹መልእክተ ወዛደር›› ‹‹ሀሁ ወይም ፐፑ››፣ ‹‹ዐፅም በየገጹ›› ‹‹ትንሣኤ ሰንደቅ ዓላማ›› እና ‹‹የመቅደላ ስንብት›› ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
– – –
ለእናት ሀገራቸው ኢትዮጵያ የተለየና ጥልቅ ፍቅር የነበራቸው ብላቴን ጌታ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን፣ ካልተዘመረላቸው የሀገራችን ጀግኖች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ከተሰጣቸው ክብርና አድናቆት ይልቅ በውጭ አገራት የተሰጣቸው ክብር የተሻለ እንደነበርም ይገለፃል፡፡
– – –
ከጥበባዊ እውቀታቸው ባሻገር፣ ሰሚ አላገኙም እንጂ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ወደተሻለ ደረጃ ሊያራምዱ የሚችሉ ሃሳቦችንም በተደጋጋሚ ሰንዝረው ነበር፡፡ በርካታ አንጋፋ የሀገር ውስጥና የውጭ ጸሐፍትና ባለሙያዎች በብዕሮቻቸው ያሞገሷቸውና የመሰከሩላቸው ብላቴን ጌታ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን፣ ከፍተኛውን የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ስነ-ጽሑፍ ሽልማትን ጨምሮ በርካታ ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡
– – –
ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን የካቲት 18 ቀን 1998 ዓ.ም አሜሪካ ውስጥ አርፈው አስክሬናቸው ወደ አዲስ አበባ መጥቶ በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ስላሴ ቤተ-ክርስቲያን ቤተክርስቲያን አርፏል፡፡
Filed in: Amharic