>

ማሰርም መፍታትም ፖለቲካዊ ቃና ከተላበሰ ፍርድ ቤት እና የፓርቲ ፅህፈት ቤት ልዩነታቸው ምን ይሆን? (መስከረም አበራ)

ማሰርም መፍታትም ፖለቲካዊ ቃና ከተላበሰ ፍርድ ቤት እና የፓርቲ ፅህፈት ቤት ልዩነታቸው ምን ይሆን?

መስከረም አበራ
ሃገር የሚፀናው በህግ የበላይነት ነው። በእኛ ሃገር የህግ የበላይነት፣በህግ መተዳደር ኖሮ አያውቅም። ያለው / የኖረው የሰው የበላይነት እና በህግ መግዛት (በህግ ማስተዳደር ሳይሆን) ነው፨ እስር ቤቱን የሚሞላው መንግስትን የሞገተው ነው።በጥፋቱ የሚታሰረው ጥቂቱ ነው።እኛ ሃገር ማወቅ ጥፋት ነው። ባወቁት መጠን መሞገት ፍርድ የሚያሻው ሃጢያት ሆኖ ዘብጥያ ያወርዳል!
 ዙፋን እስኪረጋጋ የታሰረ ሞጋች ዙፋን የተረጋጋ ሲመስል  “ነፃ ነህ በሰላም ሂድ ይባላል”፨ ያለ ሃጢያት በእስር ቤት ለመታጎሩ ፣የጉብዝና ወራትን በዘብጥያ በከንቱ ለመባከኑ ተጠያቂ የለም!ተጠያቂ መሆን የነበረበት አሳሪ “መፍታቴ ፅድቄ ነውና አመስግኑኝ” ብሎ ቁጭ ይላል። እንዲህ እንዲህ እየሆነ የህግ እና የፖለቲካ ድንበሩ ጠፍቷል! ቀን የወጣለትን ፖለቲከኛ ፍትህ ሽር ብትን ብላ ታገለግላለች።
 የፖለቲካ  ምህዳር ለማስፋት በወንጀል ጠረጠርኩት ተብሎ የታሰረ ሰው ተፈታ ይባላል። እዚህ ውስጥ እስሩ ውስጥ ፖለቲካዊ ምክንያት እንደነበረ ጠቋሚ ነገር አለ። በዚህ መልክ ፖለቲካችን ቆሻሻውን ፍትህ ላይ ይለቀልቃል! ማሰርም መፍታትም ፖለቲካዊ ቃና ከተላበሰ ፍርድ ቤት እና የፓርቲ ፅህፈት ቤት ምን ልዩነት አላቸው?
 ያለፈው አለፈ ለወደፊቱ ግን ማሰርም መፍታትም ከፖለቲካ ቃና ቢርቅ ደግ ነው።አስሮ ሰንብቶ ደሞ ክስ አቋረጥኩ ከማለት ይልቅ ከማሰሩ መቆጠብ የተሻለ ነው። ፖለቲካ ሲያስለው ፍትህ የሚያስነጥሳት ከሆነ ተስፋችን ምንድን ነው?!
Filed in: Amharic