>

የከማል ገልቹ ነገር...! (አቻምየለህ ታምሩ)

የከማል ገልቹ ነገር. . . !!!

አቻምየለህ ታምሩ
 
“ሁሉም በማንነቱ ተከብሮ በፌዴራሊዝም አብረን ለመኖር ጥረት እናደርጋለን ፣ ካልተሳካ ግን ኦሮሚያ እራሷን የቻለች አገር ለመሆን ትገደዳለች! ለዛ ደግሞ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርገናል!!!”
 ጀነራል ከማል ገልቹ
ከሰሞኑ እምቡር እምቡር ሲል የምንሰማው  ከማል ገልቹ  እጅጉን አስገራሚ ፍጡር ነው። ትናንትና በአርሲ ባደረገው ዲስኩር ማንነታችን ካልተከበረ ኦሮምያ የራሷ የሆነች አገር ለመሆን ትገደዳለች፤ ለዚህም አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርገናል። ይገርማል። ከማል ገልቹ ልክ  እንደ  ኦቦ ጂኔይዲ ሳዶ [Loodee የሚባል የሐድያ ጎሳ ተወላጅ]፣ የምዕራብ ሶማሊያው ጀኔራል ዋቆ ጉቱ [ Rayayitu የሚባል የሐድያ ጎሳ ተወላጅ]፣ ፕሮፌሰር አባስ ገነሞ [Assala/Akkiya የሚባል የሐድያ ጎሳ ተወላጅ]፣ ዶክተር ኑሮ ደደፎ [Assala የሚባል የሐድያ ጎሳ ተወላጅ]፣ ጠይባ ሐሰን [ኦሮምያ ክልል የሚባለው ምክትል ፕሬዝደንት የነበረች ስትሆን Saymannaa የሚባል የሐድያ ጎሳ ተወላጅ ናት]፣ አሚን ጁንዲ [ካናዳ ሲኖር የኦነግ ለአንድነት ዋና ፀሐፊ የነበርና በአሁኑ ወቅት  የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት አማካሪ ሆኖ በመስራት ላይ የሚገኝ  ሲሆን Shafila የሚባል የሐድያ ጎሳ ተወላጅ ነው] ወዘተ ሁሉ ሐድያ እንጂ ኦሮሞ አይደለም።  እነዚህ የዘረዘርኋቸው የሐድያ ጎሳዎች የኦሮሞ አባ ገዳ በኃይል ወደ ኦሮሞነት የለወጣቸው ኦሮሞ ያልነበሩ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የሚሻ ቢኖር ፕሮፌሰር በርካምበር «A History of the Hadiyya in Southern Ethiopia» በሚል በ1966 ዓ.ም. ባሳተሙት መጽሐፍ ውስጥ ከገጽ 459-462 ያለውን ማንበብ ይችላል።
ከማል ገልቹ ዛሬ ኦሮምኛ ተናጋሪ የሆነው  የኦሮሞ የገዢ መደብ የሐድያን ምድር ወርሮ ማንነታቸውን ተገደው እንዲተው፣ ቋንቋቸውን እንዳይጠቀሙና ባሕላቸውን በኃይል እንዲለውጡ ተደርገው የኦሮሞ ማንነት ከተጫነባቸው የሐድያ ቤተሰቦች በመወለዱ ነው። ከማል ካልተከበረልኝ እያለ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚለው ማንነት በኃይል የተጫነበርን የኦሮሞ ማንነት ነው። ከማል ማንነት እንዲከበር የምሩን የሚታገል ቢሆን ኖሮ ከሁሉ በፊት በኃይል የተጫነበትን የኦሮሞ ማንነት አሽቀንጥሮ ጥሮ የራሱን ማንነት ሐድያነትን ይላበስ ነበር። ግና ሰውዬው ያልሆነው የለምና በሰው ወርቅ ሊደምቅ ከኦሮሞ በላይ ኦሮሞ ለመሆን ያዙኝ ልቀቁኝ ያላል።
ከማል ገልቹ እ.አ.ኤ. በ2016 ዓ.ም. በአትላንታ ጆርጂያ በተካሄደው «የኦሮሞ ትግል መሪዎች ኮንቬንሽን» ያስቀመጠውን ግብ እንዲያሳካ ስብስቡ በወያኔ ቋንቋ አንድ «ኮማንድ ፖስት» ሰጥቶት ነበር። «የኦሮሞ ምሑራንና ብሔርተኞች ስብሰባ» በተባለው የጆርጂያው «የኦሮሞ ትግል መሪዎች ኮንቬንሽን» ባወጣው መግለጫ «የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ለነጻነት የሚበቃው እንደ ኤርትራ፣ ትግሬ እና ደቡብ ሱዳን ሲኾን ነው!» ይላል።
ያገራችን ሰው «ቸር ተመኝ ቸር እንድታገኝ» ይላል። ፈረንጅም “Aim to the stars! If you miss, you will hit the top of the tree” ይላል። «የኦሮሞ ምሑራንና ብሔርተኞች ስብሰባ» የተመኛት የኢሳይያስ አፈወርቂ ኤርትራ መላው ዓለም ማዕቀብ ያደረገባት፣ የአፍሪካ ሰሜን ኮርያ፣ ዜጎቿ በዓለም ላይ በየዓመቱ በገፍ የሚሰደዱባትና ያልተሰደዱትም የምድር ሲኦል ኑሮን የሚገፉባት፣ መሪዋ ከዛሬ ነገ የዓለም ጦር ፍርድ ቤት ይቀርባል እየተባለ የሚባንን ጉድ ያለባት ሀገር ናት። ሌላው «የኦሮሞ ምሑራንና ብሔርተኞች ስብሰባ» የተመኛት የወያኔዋ ትግራይም ገዢዋ ወያኔ ጭንቅ ላይ ነው፡፡ ደቡብ ሱዳንም ሀገር ሳይኾን የከሸፈ ሀገር (failed State) ነው። የተሻለ አድማስ ባይኖር ወይ መግዛት አልያም መዋስ ሲገባ «የኦሮሞ ትግል መሪዎች» ነን ያሉን ኦነጋውያን በቃላት እንኳን ቢኾን «ታላቅና ገራገር» ለሚሉት የኦሮሞ ሕዝብ የቀረጹለት አድማስ ግን የመከራ ዘመን እየገፉ ከሚገኙበት ከታሰሩበት የኑሮ ሰንሰለት፣ ከገቡበት ምድራዊ ሲኦል ነበልባላዊ እቶን የሚታደጋቸው መድኅን የሚፈልጉ ዜጎች ምድር እንዲኾኑ የተደረጉ ሀገሮችን ነው።
ከማል ገልቹ አስመራ ተከፍቶ የነበረው የኦ.ነ.ግ ቅርንጫፍ መሪ ነበር። ከማል የአስመራው ኦ.ነ.ግ መሪ ሆኖ የተመረጠው በኦ.ነ.ግ ጠቅላላ ጉባኤ ነበር። ኾኖም ግን ዳውድ ኢብሳ አሻፈረኝ ብሎ መፈንቅለ መሪ በማካሄድ ከሥልጣኑ አባረረው። በዚህም ከማል የዐባይ ፀሐዬ እድል ገጠመው። ዐባይ ፀሐዬ ከስብሓት ነጋ በኋላ በሕ.ወ.ሓ.ት ጠቅላላ ጉባኤ የሕ.ወ.ሓ.ት መሪ ሆኖ ተመርጦ ነበር። ኾኖም ግን በ1977 ዓ.ም. «ሕንፍሽፍሽ» ባሉት አውራጃዊ ክፍፍል ወያኔዎች ሲራኮቱ መለስ ዜናዊ በጠቅላላ ጉባዔ የተመረጠውን ዐባይ ፀሐዬን አውርዶ በመፈንቅለ መሪ በጉልበቱ የሕ.ወ.ሓ.ት መሪ ለመኾን በቃ። ዳውድ ኢብሳም ከማልን ያደረገው እንደዚያ ነው።
ዳውድ ኢብሳ በኦ.ነ.ግ ጠቅላላ ጉባኤ መሪ ተደርጎ በተመረጠው በከማል ገልቹ ላይ መፈንቅለ መሪ ያካሄደው ኢሳይያስን ተማምኖ ነው። ዳውድ ኢብሳ እንደ አንዳርጋቸው ፅጌ ኢሳይያስ የማይጠረጥረው የኢሳይያስ ታማኝ ነበር። ዳውድ አስመራ የተከፈተው የኦ.ነ.ግ ቅርንጫፍ መሪ ኾኖ በንግድ ሥራ ተሠማርቶ መካከለኛው ምሥራቅ ይመላለስ ነበር። ወዳጄ እንደነገረኝ አሥመራ ከተማ ውስጥ ቄንጠኛ መኪና ከሚነዱት ሰዎች መካከል አንዱ የሻዕብያ ሰላይና የቡርቃ ዝምታ ደራሲው ተስፋዬ ገብረአብ ነው። ቄንጠኛዋን መኪና ለተስፋዬ የሸጠለት ደግሞ ዳውድ ነበር።
ከማል ገልቹ ዐቢይ አሕመድ ከወያኔ እንዲያመልጥ ምሥጢር አሾልኮ ሰጥቶት ወደ ኤርትራ ሳይኮበልል በፊት ታማኝ የወያኔ አገልጋይ ነበር። ከማል በደርግ ዘመን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አንግቦ ሲዋጋ ሻዕብያ ማርኮት ለወያኔ በምርኮ ከተሰጡና ኦ.ሕ.ዴ.ድን እንዲመሰርቱ ከተደረጉት የሻዕብያ ምርኮኞች አንዱ ነው።
ወያኔን ፈርቶ ከፈረጠጠበት ሀገር የአማራ ልጆች ከወያኔ ጋር ተፋልመው በከፈሉት መስዕዋትነት ወያኔ መቀሌ ሲመሽግ፣ በግብዣ በኡጋንዳ አድርጎ በቦሌ በኩል ገብቶ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ቡራ ከረዩ የሚለው ከማል ከዚህ በፊት ሁለት ጊዜ በሻዕብያ በምርኮኝነት የተያዘ ሲኾን ሦስት ጊዜ ደግሞ ከድቷል። የአትላንታው ስብሰባ የደቡብ ኮማንድ ፖስት የተባለውን ቦረናን፣ ባሌንና አርሲን የሚያጠቃልለው ኮማንድ ፖስት አዛዥ ያደረገው ከማል ገልቹን ነበር። ከማል የአርሲ ልጅ ሲኾን መጽሐፉ «ብርሃን ይኹን አለ ብርሃንም ኾነ!» እንዳለው መለስ ዜናዊ ጀነራልነት ሲያድል ከምንም አስንቶ ‹ጀነራል› ያደረገው ‹ጀኔራል ኹን ተባለ፣ ጀነራልም ኾነ!› የሚባል ዓይነት ሰው ነው።
ከማል፣ አስመራ በዳውድ ኢብሳ መፈንቅለ መሪ ከተካሄደበት በኋላ አምባሳደር ኾኖ ነበር። ከማል አምባሳደር የኾነው ለሀገር እንዳይመስላችሁ። ከማል አምባሳደር የኾነው ለኢሳይያስ አፈወርቂ ነበር። ከማል የኢሳይያስ አፈወርቂ አምባሳደር ኾኖ ምሥራቅ አፍሪቃ ተልኮ ነበር። ኢሳይያስ ከማልን በዚህ አካባቢ አምባሳደር አድርጎ የላከው በአርሲ አካባቢ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ነበር። ይህ የከማል ሹመት ኋላ ላይ የአትላንታው ጉባዔ የሰጠውን «ኮማንድ ፖስት» ስለማጠቃለሉ እርግጠኛ አይደለሁም። ስለ ማጠቃለሉ ማጣራት ቢያስፈልግም የአትላንታው ጉባዔ ለኦሮሞ ሕዝብ ከቀረጸለት አድማስ መካከል ኤርትራ መኾኗን ስናስታውስ ግን የከማል የአምባሳደርነት ሹመት በአትላንታው ጉባኤ የተሰጠውን የኮማንድ ፖስት አዛዥነት የሚጠቀልል ቢኾን አያስደንቅም።
ኢሳይያስ አፈወርቂ ከማል ገልቹን ወደ ዩጋንዳ ከመላኩ በፊት ታማኝነቱን ለማረጋገጥ አንድ የበላይ አካል ተቆጣጣሪ ሰጥቶት ነበር። ኢሳይያስ ለከማል ያስቀመጠለት የበላይ ተቆጣጣሪ ከማል እንዲያገባት የተደረገች የአንድ የሻዕቢያ ጀነራል ልጅ ነበረች። በሌላ አነጋገር ኢሳይያስ ከማልን በአምባሳደርነት የላከው የአንዱን የሻዕብያ ጀነራል ልጅ ድሮለት፣ ሚስቱን አብራው እንድትሄድ በማድረግ ነበር። ‹ኢሱ› ከማል ገልቹን «የጴጥሮስ ታናሽ ወንድም» እያለ እንደሚጠራው አንድ ኮብላይ ጋዜጠኛ የጻፈውን ማንበቤን አስታውሳለሁ። እንደሚታወቀው የመጽሐፍ ቅዱሱ ጴጥሮስ ሦስቴ ከድቷል። ኢሳይያስም «የጴጥሮስ ታናሽ ወንድም» የሚለውን አምባሳደር ከማል ገልቹን ለማመን ተጨማሪ ጥንቃቄ አድርጎ ነበር። ‹ኢሱ› ለተጨማሪ ጥንቃቄ ሲል ከማል ገልቹ ሳያውቅ የከማል ገልቹን አንድ ልጅ ከኢትዮጵያ አስመጥቶ በመያዣነት ኤርትራ ውስጥ አስቀምጦ ነበር። ከማል የኢሳይያስ አምባሳደር ኾኖ ዩጋንዳ በነበረበት ወቅት ልጁ መያዣ መኾኑን ያወቅ አይመስለኝም። አሁን ማወቅ አለማወቁን እርግጠኛ አይደለሁምና አጣራለሁ።
ይታያችሁ! የሻዕብያው ምርኮኛ፣ የወያኔ ሎሌው እና ኢሳይያስ የዳረለት ሚስት የበላይ አለቃ፣ ልጁን ደግሞ በመያዟነት አሳግቶ የኢሳይያስ አምባሳደር የነበረው ከማል ገልቹ ነው እንግዲህ ታግሎ ነጻ እንደወጣ ሁሉ እስካፍንጫው ከታጠቀው ወያኔ ጋር ፊት ለፊት በመጋፈጥ በኢሳይያስ ምርኮ ከተያዘበት ሀገር አስፈትተው፣ ወያኔን ሸሽቶ እግሬ አውጭኝ ብሎ ከፈረጠጠበት የሰው ሀገር እንዲመለስ ባደረጉት የአማራ ልጆች ሲኩራራና ለስድብ ሲጋበዝ የምታዩት።
ያገራችን ገበሬ ክረምት ይዞት ይመጣል ብሎ የሚያስበውን በሽታ፣ ችግርና ተንከሲስ ሁሉ መስከረም ሲጠባ በችቦ የተስፋ ብርሃን እንጉሮጎባሽ እያለ በመተርኮስ ያባርራል። ሰኔ፣ ሐምሌና ነሐሴን በጎመን የባጀው ገበሬ፣ መስከረም ላይ ገብስ ሲደርስ ለነፍሱ ገብስ እንደደረሰለት ያስገነዝብና ተመልሶ ገብስ በዚህ እንዳይኮራ፣ የጎመን ውለታ እንዳይረሳ ሲል «ገብስ ስማ ስማ ነፍሴን አትርፎ ለአዲስ ዘመን ያደረሰኝ ጎመን ነውና አትንቀባረር» ለማለት «አትኩራ ገብስ፣ ጎመን ባወጣው ነፍስ» ብሎ ሸንቆጥ ያደርገዋል። እስካፍንጫቸው ከታጠቁ የወያኔ ነፍሰ በላዎች ጋር ተፋልመው ወያኔ መቀሌ እንዲመሽግ ከተገደደ በኋላ ወያኔን ፈርቶ ከፈረጠጠበትና ልጁን በማስያዝ የኢሳይያስ ጀኔራል ልጅ የበላይ ተቆጣጣሪ ተመድቦለት ከሚኖርበት የግዞት ሀገር በቦሌ በኩል እንዲገባ ያደረጉትን የአማራ ልጆች ሊሰድብ የሚጋበዘውን ከማልን «አትኩራ ገብስ፣ ጎመን ባወጣው ነፍስ» ልንለው ይገባል! «ማንነታችን ካልተከበረ. . . » እያለ በተጫነበት የሰው ማንነት ከሚፎክር መጀመሪያ የተጫነበትን  ማንነት አውልቆ የራሱን ማንነት ሐድያነትን  በማጥለቅ ለራሱ ማንነት ክብር እንዳለው ያሳይ!
Filed in: Amharic