>
5:13 pm - Thursday April 20, 7719

ፈተናው ዘርፈ ብዙ ነው።ይሁንና እናት ቤተክርስቲያን ታሸንፋለች እንጂ የሲኦል ደጆችም አያሸንፏትም።

ፈተናው ዘርፈ ብዙ ነው።ይሁንና እናት ቤተክርስቲያን ታሸንፋለች እንጂ የሲኦል ደጆችም አያሸንፏትም

ብርሃኑ ተክለያሬድ

ቅዱስ ሲኖዶስ ብዙ ነገር በትእግስት አልፏል። ዛሬም በትእግስት አጥፊዎች በይቅርታ እንዲመለሱ በጊዜያዊነት ስልጣናቸውን ይዞ ጊዜ ሰጥቶ አልፏል። አጥፊዎቹ በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ከጀርባቸው የነበሩ ሊቃነ ጳጳሳትን ተማምነው “ማነው አውጋዥ ማነው ተወጋዥ?”ሲሉ በእብሪት ሲመልሱ ነበር። ቅዱስ ሲኖዶሱ ያስተላለፈውን እግድ ተከትሎ ህገወጦቹ የመጨረሻ ጥይታቸውን ተኩሰዋል። እናም ቅድስት ተዋህዶ በሁሉም ግንባር ተኩስ ተከፍቶባታል።
ቤተክርስቲያን ከልጅነት ኮትኩታ “ብፁዕ” ብላ ሰማያዊ ዜግነት የሰጠቻቸው ጳጳሳት “የለም ጎጣችን ይሻለናል” ብለው ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በተቃራኒ ቆመዋል። 2 የተመረጡ ሚዲያዎች(?) ብቻ በተገኙበት “እጩ ፓትርያርኩ” ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስም ልዩ ወንበር ተዘጋጅቶላቸው በ2ቱ ሊቃነ ጳጳሳት መካከል ተቀምጠው “ከውጪ የሌሎችን አጀንዳ ለማስፈፀም ታጥቀው የተነሱ ሰዎች፣በኦሮሚያ፣በትግራይና በመሀል ያሉ አባቶች ውሳኔውን አልደገፉትም ከሌላ ወገን ያሉ ናቸው የወሰኑት”እያሉ የቅዱስ ሲኖዶሱን አባላት በዘር ሲከፋፍሉና ሲያቃልሉ ውለዋል። ሁሉን ከመናገራችን በፊት ግልፅ ሊሆኑ የሚገባቸውን ጉዳዮች እናጥራ
1.መግለጫው የተሰጠበት ቢሮ የት ነው? በላይ መኮንን መንግስት በሰጠው ስልጣንና ቢሮ በቤተክርስቲያን ላይ ሲታበይ እስከመቼ ዝም ይባላል?
2.በየመንደሩ መግለጫ ሲበትንና በተሰበሰቡ ምዕመናን ላይ ሲተኩስ የሚውል አስተዳደርስ ቅዱስ ሲኖዶስ ያገደው አካል ህገወጥ መግለጫ ሲሰጥ ምን እየሰራ ነው?
3. አንድ አባት ጵጵስና ከተሾመ በኋላ ወርዶ እነእከሌ የኛ ደጋፊ እነ እከሌ የሌሎች ማለቱስ ከቤተክርስቲያን ህግ አንፃር ተገቢ ነው?
በኔ እምነት ቤተክርስቲያን በዘመኗ ገጥሟት የማያውቅ “ዘረኝነት” የሚባል ፈተና ገጥሟታል። የቅዱሳኑ ቃል ኪዳን የግሁሳኑ እምባና የንፁሀኑ ፀሎት ከአባቶች ጥበብና ትእግስት ብሎም ከምእመናን በቁርጠኝነት መቆም ጋር ተደምሮ ፈተናውን እናልፈዋለን።ፈተናውን ለማለፍም
-ብፁዓን አባቶች ጉዳዩ ህገወጥ መሆኑን ገልፀው ለመንግስት አካላት በአስቸኳይ እንዲያስቆሙ ደብዳቤ መፃፍ በአካልም መነጋገር፣ ለሚፈጠረው ችግር ሁሉ መንግስት ሀላፊነት እንደሚወስድ ማሳወቅ
-ከነገሩ አንገብጋቢነት አንፃር በመዋዕለ ፆም ቅዱስ ሲኖዶስ ተገናኝቶ ራሱን ያጥራ ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የተለዩ አባቶችን ይመርምር ለቀኖና ወደተመረጡ ገዳማት ይላክ
-የገዳም አባቶች፣ ካህናትና ምእመናን መዋዕለ ፆሙን ከልብ በሆነ እንባና ልቅሶ እናሳልፍ በየአድባራቱ በነግህም ሆነ በሰርክ ምህላዎች ይደረጉ
-የምስካየ ህዙናን መድሃኔ አለም ገዳም መነኮሳትና ዲያቆናት፣የተምሮ ማስተማር አባላትና የአጥቢያው ምእመናን ገዳማቸውን በንስር አይን ይጠብቁ (ምክንያቴን በውስጥ መስመር ጠይቁኝ)
-እንደሁልጊዜው የቤተክርስቲያንን ድምፅ ብቻ ከሚያሰሙ አባቶች ጎን እንቁም ንስሀ ገብተንም ለሰማእትነት እንዘጋጅ!!!
“ይኼይሰነ ናድሉ ለእግዚአብሄር እምነ አድልዎ ለሰብዕ”
“ለሰው ፊት ከምናደላ ለእግዚአብሄር ፊት ማድላት ይሻለናል”
እግዚአብሄር ይርዳን
ወፀልዩ ሊተ
Filed in: Amharic