>

ቅ/ሲኖዶስ: በእነቀሲስ በላይ መኰንን ላይ ጥብቅ የርምጃ አማራጮች ይዞ እየተወያየ ነው!!! (ሐራ ዘተዋሕዶ)

ቅ/ሲኖዶስ: በእነቀሲስ በላይ መኰንን ላይ ጥብቅ የርምጃ አማራጮች ይዞ እየተወያየ ነው!!!

———
(ሐራ ዘተዋሕዶ ዛሬ እንደዘገበው):-
ክህነታቸው እንዲያዝና ሌሎችም የጥንቃቄ ርምጃዎች እንዲወሰዱ ሐሳብ ቀረበ፤
• በሕግ እንዲጠየቁ ያሳለፈው ውሳኔ ያለቅድመ ኹኔታ ተፈጻሚ እንዲኾን አዘዘ፤
• የ“ኦሮሚያ ቤተ ክህነት” በሚል የከፈቷቸው ጽ/ቤቶች እንዲዘጉ መመሪያ ሰጠ፤
***
በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች አስቸኳይ ስብሰባ የተጠራው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ ከትላንት ለዛሬ ባሳደረውና፣ “የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እናደራጃለን” በሚል ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ እያደረጉ በሚገኙት በእነቀሲስ በላይ መኰንን ላይ መውሰድ በሚገባው የርምጃ አማራጮች መወያየቱን ቀጥሎ ውሏል፡፡
ዛሬ ከቀትር በፊት በነበረው ውሎ፣ እነቀሲስ በላይ መኰንን፣ የቤተ ክርስቲያንን ሕግ እና መዋቅራዊ አንድነት በመፃረር እያደረጉ በሚገኙት እንቅስቃሴ በሕግ እንዲጠየቁ፣ በጥቅምቱ መደበኛ ስብሰባው አሳልፎት የነበረው ውሳኔ፣ ያለምንም ቅድመ ኹኔታ ተፈጻሚ እንዲኾን በድጋሚ ጥብቅ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡ “የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት” በማለት የከፈቷቸው ጽ/ቤቶችም እንዲዘጉና ይህንም ኹሉ፣ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ የሕግ አገልግሎት መምሪያ፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋራ በመኾን እንዲያስፈጽም፣ ምልአተ ጉባኤው በአጽንዖት መመሪያ ሰጥቷል፡፡
የሕግ ተጠያቂነቱ እንዳለ ኾኖ፣ የእንቅስቃሴው መሪ በኾነው ቀሲስ በላይ መኰንንና መሰሎቹ ላይ፣ ቤተ ክርስቲያን በራሷ መውሰድ የሚገባትን ቀኖናዊ እና ሥርዓታዊ ርምጃ በተመለከተ፣ ኹለት አካሔዶች በአማራጭነት ቀርበው ምልአተ ጉባኤው እየተወያየባቸው ይገኛል፡፡
የመጀመሪያው የርምጃ አማራጭ፥ ቀሲስ በላይ መኰንንን ጨምሮ በክህነት እና ምንኵስና ያሉት ግለሰቦች፣ ሥልጣናቸው አሁን እንዲያዝ፣ በዚህም እስከ ርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ ድረስ ይቅርታ ጠይቀው እንዲመለሱ የማሰላሰያ ጊዜ እንዲሰጣቸው፤ ይቅርታ ጠይቀው ከተመለሱ ሥልጣናቸው እንዲመለስላቸው፣ ካልተመለሱ እንዲወገዙ ሐሳብ የቀረበበት ነው፡፡
ኹለተኛው የርምጃ አማራጭ፥ የመጀመሪያውን አካሔድ በመሠረቱ የሚቀበል ኾኖ፣ ነገር ግን በቅድሚያ፣ በቤተ ክርስቲያን በኩል መሠራት ለሚገባቸው ተግባራት ትኩረት መሰጠት እንዳለበት የሚከራከር ነው፡፡ ይኸውም፣ በእነቀሲስ በላይ እና የዓላማ አጋሮቹ ስሑት መረጃ እና የፈጠራ ትርክት ተታለው ባለማወቅ አብረው የተሰለፉ ምእመናን በመኖራቸው፣ እኒህን ወገኖች አስቀድሞ በጥንቃቄ ለይቶ የሚያወያይና መክሮ የሚመልስ ኮሚቴ እንዲዋቀር ሐሳብ የቀረበበት ነው፡፡
ኮሚቴው ግለሰቦቹን ሲያነጋግር፣ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ በበኩሉ፣ ቀደም ሲል በተወሰነው የቋንቋዎች አገልግሎት ማስተባበርያ ማዕከል አማካይነት የችግሩን መነሻ ከመሠረቱ ለመፍታት ሥራውን እንዲያጠናክር፣ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ አህጉረ ስብከትም የድርሻቸውን እንዲወጡ ያስችላል በማለት ተከራክረዋል- አስተያየት ሰጪዎቹ፡፡
“ጉባኤው በኹለት መንፈስ ነው እየተወያየበት ያለው፤” ያሉ አንድ ተሳታፊ ብፁዕ አባት፣ የመጀመሪያው፥ “እስከ ርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ ድረስ፣ ክህነታቸው ተይዞ ይቆይና ይቅርታ ከጠየቁ እንመልስላቸዋለን፤” የሚል እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ ሌላው ደግሞ፣ “አይደለም፤ በመጀመሪያ በዙሪያቸው ባሉ ምሁራንና ምእመናን ላይ ሥራ መሥራት አለብን፤ በዚህ ምክንያት ብዙ ሰዎች እንዳይጎዱብንና ከቤተ ክርስቲያን እንዳይርቁብን፣ ሌላም ችግር እንዳይፈጠር የመለየት፣ የመነጠል ሥራ መሥራት አለብን፤ አስቀድመን ኮሚቴ አዋቅረን ጠርተን ማነጋገር፣ ኦሮሚያ ላይ ብዙ ሥራ መሥራት አለብን፤” የሚል እንደኾነ አስረድተዋል፡፡
ምልአተ ጉባኤው፣ ከቀትር በኋላ 9፡00 ላይ አስቸኳይ ስብሰባውን የሚቀጥል ሲኾን፣ በአማራጭነት በቀረቡት ሐሳቦች እና በይደር በተያዙት ሌሎችም ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ እንደሚያሳርፍ ተገልጿል፡፡
Filed in: Amharic