>

የመኢጠማ አባላት ጉድ ፈላብን! በብርጭቆ ድራፍት ከ40 በመቶ በላይ ዋጋ ጨመረ! (ዳግማዊ ጉዱ ካሣ)

የመኢጠማ አባላት ጉድ ፈላብን! በብርጭቆ ድራፍት ከ40 በመቶ በላይ ዋጋ ጨመረ!

 

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

 

“ሀገር እየታመሰች አንተ ስለድራፍት ዋጋ መጨመር ታወራለህ፤ የደላህ ነህ!” እንዳትሉኝ እንጂ የአቢይ መንግሥት ድል በድል እየተምበሸበሸ  መጥቶ አሁን ደግሞ ባለችን አንዲት መዝናኛ ላይ ውኃ እማያሰኝ ዱላውን አንስቷል፡፡ የፕሮቴስታንቶቹ መንግሥት አልቻል ብሏል፡፡ አብዛኞቹ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ከመጠጥ ጋር ያላቸው ፍቅር እስከዚህ መሆኑ ይነገራል – ቢያንስ ሲጠጡ በአደባባይ አይታዩምና፡፡ እዚህ ላይ “ውስጡን ለቄስ” የሚሉ ወገኖች እንዳሉ ግን አይካድም፡፡ ታላላቅ ፓስተሮች ሳይቀሩ በቤታቸውና በሥውር ዝጉብኞች በውስኪና በቢራ እንደሚራጩ  የሚወራ መሆኑን መደበቅ ተሸኮርማሚነት ነው፡፡ የሆኖ ሆኖ ሰው በወደደው ይቆርባልና በዋጋ ጭማሪ የሰውን ፍላጎት ለመግታት መሞከር ነውር ነው፡፡

ትናንት ማታ እንደወትሮየ ከሥራ ወጥቼ ሱክ ሱክ እያልኩ ጓደኞቼ ወደሚገኙበት የማታ ትምህርት ማዘውተሪያ ሥፍራየ እሄድላችኋለሁ – ለእናንተ ስል መሆኑ ነው፡፡ ከዚያ እንደደረስኩ የቀደሙኝ ጓደኞቼ “ዳጊ የምሥራች!” ይሉኛል፡፡ ምን ተገኝቶ እንደዚያ እንዳሉኝ ሳልጠይቅ “ምሥር ብሉ!” እላለሁ፡፡ አንዱ ለጠቀና “ያን የተለጠፈ ወረቀት አንብበው” ይለኛል፡፡ ሳነበው በዚያ የሕዝብ መዝናኛ የቀበሌ ክበብ 13 ብር የነበረው ድራፍት አምስት ብር ጨምሮ 18፣ 15 ብር የነበረው ትንሹ ጠርሙስ ቢራ 20 ብር መሆኑን እረዳለሁ፡፡ እውነቴን ነው የምላችሁ ጠላታችሁ ክው ይበልና እንደሎጥ ሚስት ክው ብዬ ቁሜ  ቀረሁ፡፡ ቁጭ እንድል ቢወተውቱኝም የሀዘኑ ብዛት ወደ ተረጋጋ ሰውነቴ ሊመልሰኝ አልቻለም፡፡ ሌላ ብሶታችንን የምንተነፍስበት ነገር የለንም፡፡ ከየትም ተሰባስበን ካለችን አነስተኛ ገቢም ቆንጥረን ቤተሰባችንን በመበደል የሆድ የሆዳችንን ተንፍሰን ወደየጎጇችን የምንገባው በዚሁ ድራፍትና ቢራ ነበር፡፡ በዚህም መጡብን፡፡ አምባገነኖች የማይመጡብህ አቅጣጫ የለም፡፡ አሁን የቀራቸው ባል ከሚስቱ፣ ሚስትም ከባሏ ለምታገኘው ተፈጥሯዊ እርካታ ግብር ማስከፈል ብቻ ነው፡፡ እንደዚያ ቢሉኝ ሲፈልጉ ያስመርምሩኝ እንጂ “የሜተር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ወንድም ከሆንኩ ሰነበትኩ!” ነው የምላቸው፡፡ ሆ! ሰው “በገዛ መንግሥቱ” እንደባብ እየተቀጠቀጠ ተሳቅቆ ይኖራል? ምን ዓይነት ውርጅብኝ ነው! በሣዳም ሁሴንና በጋዳፊ የወረደው መቅሰፍት በነዚህም ላይ ይውረድ፤ አሜን! የተባረኩ መንግሥታት ቀጭን ሰበብ እየፈለጉ ሕዝባቸውን ይጠቅማሉ፡፡ ከድህነት ሠፈር የመጡ የኢትዮጵያ መሪዎች ደግሞ ድህነት አንጎላቸው ውስጥ ቤቱን ስለሠራባቸው በህልማቸውም በእውናቸውም የሚያስቡት ስለማደህየት እንጂ ስለማክበር አይደለም፡፡ እናም ዕረፍት አጥተው የሚጨነቁት ሕዝብን ስለማቆርቆዝና አቆርቁዞም ስለነሱ እንዳያስብ ማድረግ ሆነ፡፡ በነሱ ተራ የፖለቲካ አስተሳሰብ ሕዝብ ከተመቸው ለመንግሥት አይመችም ነው፡፡ ዶሮ ብታልም ጥሬዋን፡፡

እርግጥ ነው መጠጥ ለማንም አይመከርም፡፡ መጠጥ ገዳይ ነው፡፡ ገዳይነቱ ግን በአወሳሰድ ይወሰናል፡፡ በልክ ከሆነ ደግሞ ያጫውታል፤ ሀዘን ትካዜን ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ያስረሳል፡፡ በዚያም ላይ ጓደኝነትን ያጠናክራል፤ ሰውን ያቀራርባል፤ ያወያያል – የዚህ ጭማሪ ዓላማም ይህን ለማስቀረት ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ጉዳት ብቻ ሳይሆን ጥቅምም አለውና በዚህ ማኅበራዊ ገመድ ላይ ይህን ያህል መጨከን የጤና አይመስልም፡፡

አንድ ጭማሪ ሲደረግ ጥንቃቄን ይሻል፡፡ የዱሮ ጭማሬዎችን ስናስታውስ የሚገርሙ ነበሩ፡፡ ሥንትና ሥንት ዓመት ቆይቶ የሚደረግ ጭማሪ ቢበዛ አሥር ሣንቲምና አሥራ አምስት ሣንቲም ነው፡፡ አሁን ግን የዛሬ 30 ዓመት ገደማ 1.70 ሣንቲም የነበረ ድራፍት አሁን በሕዝብ መዝናኛ ክበብ ብቻ ብር 18 ሲገባ ጭማሪው ዘግናኝ ነው፡፡ በመቶኛ ብትመቱት እጅግ ብዙ ነው፡፡ በአንድ ቢራ አምስት ብር መጨመር የጨማሪውን የቁጥር ችሎታ ገደል የሚከት ነው፡፡ ሃምሣ ሣንቲም መጨመር ወግ ነው፤ አንድ ብር መጨመርም ወግ ነው፤ አምስት ብር?! በግል ቡና ቤቶች ደግሞ “እንኳን ዘምቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ” እንዲሉ ናቸውና ይሄኔ ሰማይ ሰቅለውታል፡፡ ሌባው በዛ፤ ደህናው አነሰ፤ በኑሮ እየተገረፈ ያለው ደህናውና የወር ገቢው ለሁለት ቀናትም የማይበቃው ዜጋ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሆይ ወዴት አለህ?! እባክህን ሕዝብህን አስብ፣ ርስትህንም ባርክ፡፡ 

ለነገሩ ከፕሮቴስታንት ምን ይጠበቃል? ባለሥልጣኑ  ሁሉ ከላይ እስከታች ጴንጤ ወይም ሙስሊም ነው፡፡ እነዚህ ባለሥልጣናት ደግሞ ከኛ ጋር ወርደው ድራፍትና ቢራ አይሻሙም፡፡ ከፈለጉ ምን የመሰለ ምርጥ ሻምፓኝና ዊስኪ ከሎንዶን ቤታቸው ድረስ በቀጥታ ይመጣላቸዋል፡፡ ይህ ጨለማ የማይነጋ እየመሰላቸው ግና በኛ በድሆች ላይ ጢባጢቤ ይጫወታሉ፡፡ ለማየት ያብቃችሁ – አያያዛቸው ሁሉ ሌሊቱን የሚያሳጥር ነውና ተስፋችንን በአንድዬ ጥለን ከኃጢኣትና ከክፋትም ተቆጥበን የምንችለውን ሁሉ እናድርግ፡፡ ወሮበሎች ጋር አንተባበር፡፡ ደግሞም በርትተን እንጸልይ፡፡

በሶቭየት ኅብረት ዘመን ራሽያዎች ድንችና ቮድካ ርካሽ ይደረግላቸው ነበር፡፡ ያን ካገኙ ወደ መንግሥት አያስቡም፡፡ መጽሐፉም እኮ “ድሃ ድህነቱን ይረሳ ዘንድ የወይን ጠጅ ስጡት” ይላል፡፡ ጴንጤዎቹ መሪዎቻችን ግን ይቺን ጥቅስ አላነበቧም መሰለኝ፡፡ እንዲህ በአራቱም ማዕዘን አክረው አክረው የተበጠሰ እንደሆነ (መበጠሱም አይቀርም) እነሱን አያድርገኝ፡፡ አቢይ ከመጣ ወዲህ ኑሮው ከቀን ወደ ቀን እንደመንኮራኩር እየተወነጨፈ ነው፡፡ እርሱ ግን ምንም አልመሰለውም፡፡ የአንድ ሽህ ምናምን ብር ኩንታል ጤፍ አራት ሽህ ሲገባ አቢይን ስለማይርበው ቅንጣት አላሳሰበውም፡፡ የሃያ ብሩ የምግብ ዘይት 80 እና 90 ሲገባ የርሱ ምግብ በሕዝብ ቅቤና ዘይት ስለሚሠራ ጉዳዩ አይደለም፡፡ ወይ መንግሥት መሆን! በኢትዮጵያ መንግሥት መሆን እንዲህ ልበ-ድፍን ያደርጋል ማለት ነው? የነሱ ከርስ አይጉደል እንጂ ስለሕዝቡ የዕለት ከዕለት ኑሮ እኮ ቅንጣት አያስቡም፡፡ እነዚህን የአጋንንት ልጆች ከየትኛው የሲዖል መንደር አፍሶ እዚህች ኢትዮጵያ ውስጥ እንደዘረገፈብን እሱ ራሱ ይወቅ፡፡ ይሄ ሁሌ ይገርመኛል፡፡

ሀገር ቁና ሆናለች፡፡ ኑሮ ወደሰማየ ሰማያት በብርሃን ፍጥነት ተተኮሰ፡፡ በዚህ የመጠጥ ዋጋ ጭማሪ ደግሞ ለማየት ያብቃችሁ ሕይወት እንደኳስ ሽቅብ ትጉናለች፡፡ እያንዳንዱ የግል ተዳዳሪ ይህን የመጠጥ ውድነት ለመጋፈጥ ሲል በሚሸጠው ዕቃና በሚሰጠው አገልግሎት ላይ ዋጋውን ዕጥፍ ድርብ ሲያደርገው ነገሩ ሁሉ ቡሃ ላይ ቆረቆር ይሆናል፡፡ ይህን የሚፈልጉ አምስተኛ ረድፈኞች ሳይሆኑ አይቀሩም በዚህ የቀውስ ሰዓት በአላስፈላጊ ሁኔታ ይህን የዋጋ ጭማሪ እውን ያደረጉት፡፡ አለበለዚያማ ሀገር በብዙ ችግሮች እየተናጠች፣ የኑሮ ውድነቱ በተለይ ቅጥር ሠራተኛውን ከመኖር ወዳለመኖር እየለወጠው በሚገኝበት በዚህ አስጨናቂ ወቅት ይህን ያህል እጅግ የተጋነነ ጭማሪ አይደረግም ነበር፡፡ በአንዲት ብርጭቆ አምስት ብር መጨመር ማለት በራሱ እስካሁን በፍጹም ኪሣራ ነበር የሚሠሩት ማለት ነው፡፡ እንዲያ እንዳልሆነ ደግሞ እናውቃለን፡፡

ለማንኛውም በዱሮው አጠራር የመላው ኢትዮጵያ ጠጭዎች ማኅበር አባላትን በዚህ አጋጣሚ “እግዜር ያጥናችሁ፤ የጌሾ ጌታ ችግራችሁን ይስማችሁ” በማለት ላጽናናችሁ እፈልጋለሁ፡፡ እኔስ ዕድሜ ለቁንድፍት ወደታችኛውና ወደሚያዋጣኝ መንደር ጎራ እላለሁ – እሷም የወቅቱን ፋሽን ተከትላ አሁን ካለችበት በመለኪያ አራትና አምስት ብር ወደ ስምንትና ዐሥር ብር ልወርወር ካላለች፡፡ ተለያየን!

Filed in: Amharic