>

ከፋፍሎ መግዛት የገዢዎች ቅዠት (ሳዲቅ አህመድ)

ከፋፍሎ መግዛት የገዢዎች ቅዠት

ሳዲቅ አህመድ
• የጠ/ሚው የኤምሬትስ ንግግር የአፍ ወለምታ ወይስ ሆድ ያባውን ጭብጨባ ያወጣዋል?
***
በአብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ እምነት የለሽ ርዮተ-አለም ተምነሽንሸው ለአምባገነናዊው ልምሻ ምርኩዝ ሆነው ባደፈው ስርአት ውስጥ በስነ-ልቦናዊ መመረዝና መበከል ከልጅነት እስከ እውቀት ቆዩበት።ለስርአቱ ታማኝ በመሆን ከእግረኛ ወታደርነት የደህንነት ተቋምን እስከመምራት አሻቀቡ።በፈረንጆቹ መላኒየም አለማችን የገባችበትን የሐይማኖት አጣብቂኝ ተከትሎ እራሶን ለምእራቡ ገበያ ማዘጋጀት ነበረቦትና በሻሻ ከ«አሊፍ፣ባ፣ታ» ጀምሮ ያስታጠቀቾትን የእምነት ዘለበት በጠስኩ አሉንና የኢትዮጵያ መላኒየም ፍልቅልቅታ ሲበሰር እንደ አዲስ ተወለድኩ ( Born again ነኝ) አሉ። እምነት የግል ምርጫዎ ቢሆንም አደጋዉ በእምነቶች መካከል ዥዋዥዌ ለመጫወት መሞከሮ ነውና ትንሽ ማለቱን ፈለግን።
 
• ትላንትን በምልስት
በ«እርካብና መንበር» ስሌቶ ህወሃትን እርካብ አድርገዋት ሊሆን ይችላል።ለያኔው የርዮተ-አለም ተመላኪ አባቶ መለስ ዜናዊ ጠረጴዛ ላይ የጅማውን የሐይማኖት ግጭት የተመረኮዘው የርሶ ጥናት መቅረቡ ድብቅ አይደለም ።ዛሬም የሚያላምጡት መለሳዊ «ሱፊ፣ሰለፊ» ማስቲካ ካፎ አልጠፋም።ሆድ ያባውን ብቅል እንደሚባለው አንዳንዴ ምጡቅ የሐይማኖት ተንታኝ መሆን ሲቃጣዎቅ የሚያስወነጭፏቸው ቃላቶች ስጋትን ይፈጥራሉ።
የአወሊያው ትግል እንዲጀመር፣ድምጻችን ይሰማ እንዲወለድ፣ብዙዎች እንዲታሰሩ፣ብዙዎች እንዲሰደዱ ካደረጉት ሰዎች መካከል አንዱ መሆኖ ለምን ይዘነጋል? የአንድነትና የሰደቃ መርሃ ግብሮች «ህገመንግስትን በሐይል ለመናድ» በሚል ትርጓሜ ከሽኖ ለአለቆቹ እንካቹ ያለው ማን ሆነና? … ያ ንቅናቄ ገሰገሰና ቄሮን ወለደ።ንቅናቄው ፋኖንና ሌሎችን አስከትሎ በርሶ አጠራር «እርካብ» ሆኖት አራት ኪሎ አስገባዎት።ዘርማ ሲሉ ተደምጠዋል።ከአንደበቶ አንድም ቀን እንኳ «ድምጻችን ይሰማ» አለማለቶ ሆድ ሲይታውቅ ዶሮ ማታ መሆኑ ግልጽ ነው።ስለዚህ በርሶ ቀመር ህወሃትም ሆነ የሙስሊሙ ትግል ለርሶ መንበር እርካብ ነበሩ ማለት ነውን? የዋሁ ህዝባችን አብይ የሚባል አድብቶ ሰሪን ሳይሆን ፕሮፌሰር ሐጋይ ኤርሊክ እና ዶ/ር ሽፈራው ተክለማሪያም  የሚባሉ ስሞችን ይዞ ቀረ።
• ሐይማኖትን መቀየር ለምን?
በስልጣን ጥም ሐይማኖቴን ቀየርኩ ያሉት የቀድሞ ባልደረባዎ የሽመልስ አባት ሐጂ ከማል በአጼ ሐይለስላሴ ዘመነ-መንግስት ያሳረፉት ታሪካዊ ሰንበር በህይወት ካሉ አባቶች ህሊና ውስጥ አልጥፋም።በኢስላማዊ ታሪክ ውስጥ ሐይማኖቴን ቀየርኩ የሚሉ ሰዎች የሚያደርሱት ጥቃት በጉልህ ይታወቃል።ስለዚህ ሙስሊሙ ማህበረሰብ እርሶን በጥርጣሬ ነው የሚመለከቶት።ግን እድል እንስጣቸው፣እንያቸው (give the benefit of the doubt) በሚል ስሌት ሁለት አመት በአንክሮ ተመለከቶት።ስንዝር እየሰጡ ክንድ ይወስዳሉ።ባደባባይ ቃል ይገቡና በቢሮክራሲ ቀፍድደው ይይዛሉ።የማህበረሰቡን የለውጥ ፋላጎት በረጅም ገመድ እንዲታሰር አርገው እርሶ በፈጠሩት ርቀት ብቻ እንዲወራጭ ማድረጉን ቀጠሉ።ይህ ሳያንስ «ሙስሊሞች በተለያዩ መስጊድ ሱፊ፣ሰለፊ ብለው ይሰግዳሉ» ተብሎ ኤምሬትስ ውስጥ «በሬ ወለደ» መታወጁ  እምነቱን ካጨረተ ሰው መሰማቱ የንቃት ደወል ደወል ሆኗል።
• የአፍ ወለምታ ወይስ ሆድ ያባውን ጭብጨባ ያወጣዋል?
በኤምሬትሱ ንግግሮት ላይ የሙስሊምና የክርስቲያን መከፋፈል የተለያየ ነው በማለት አጋነዋል።በመሰረቱ በአለማችን ላይ ያሉት ሙስሊሞች መሰረታዊ በሆነ የእምነት ትግባሬ  የማይለያዩ ናቸው።አምስት የእምነት መሰረትንና ስድስቱን የእምነት መሰረቶች ተግባሪዎች ናቸው።የአለማችን ሙስሊሞች ከ90% በካይ የሚሆኑት ሱኒዎች ሲሆኑ 10% የሚሆኑት ደግሞ ሺአ በሚል መጠሪያ ይጠራሉ።ሁሉም ተመሳሳይ በሆነ ሰዓትና አቅጣጫ ይሰግዳሉ።ሺዓዎቹ ሱኒዎች ጋር መጥተው ሲሰግዱ ቢታይም ሱኒዎቹ ሺዓዎቹ ዘንድ ሔደው የሚሰግዱበት አጋጣሚ ውስን ነው። አይደለም ባንድ መስጊድ ውስጥ መስገድ ቀርቶ በቂ መስጊዶች በሌሉባቸው ቦታዎች ሙስሊሞች ቤተ-ክርስቲያንንና ሴኔጋግ ውስጥ ገብተው ይሰግዳሉ (ለምሳሌ ትላንት ጁመአ የሰገድኩት የአይሁድ ሴኔጋግ ውስጥ ነው)።ሱፊ የሚለው መጥሪያ በጥልቅ መንፈሳዊነት ወደፈጣሪነት የሚደረግ ቀረቤታ ሲሆን ሰለፊ የቀድሞውቹን ጻድቃን የህይወት ጎዳና በራስ ዘመን መተግበር ነው።ተመሳሳይ መዳረሻ ያለውን ትግባሬ በማደበላለቅ የኢትዮጵያው ሳያንሶ ሳኡዲ ድረስ ገስግሰው የሱፊ የሰለፊ መስጊድ ማለቶ ጥራዝ ነጠቅነቶን ፍንትው አርጎ የሚያሳይ ነውና እባኮትን የኢስላም ጉዳይ ለሙስሊሞች ይተው።
• ማጠቃለያ፦ ህዝቡ የአቡዳቢን የምነት ክትባት አይሻም
ሒሳቡን በዲሞክራሲ እንተሳሰቦታልን ብሎ ማህበረሰቡ ቢዘጋጅም ተከፋይ፤ወዶ-ገብና አጋጣሚን ጠባቂ ጥቅመኛ ካድሬዎቾ ዲሞክራሲ ላሳር የሚሉትን ፕሮፓጋንዳ ጀምረዋል።ህዝብ መስዋእትነት የከፈለበት ለውጥን አሻጋሪ እሆናለሁ ያለው ኢህአዲጋዊ  ተመራጭ ደርግ በመጨረሻ ሰአት ከሶሻሊዝም ወደ ቅይጥ ኢኮኖሚ ተሻጋርኩ እንዳለው አብዮታዊ ዲሞክራሲን በብልጽግና ወልውሎ ኢህአዴግን የማስቀጠሉ ስራ ተጧጡፏል።ስለዚህ የሚወጣ አቀበት መኖሩን ከወዲሁ ማየት ይቻላል።
 «ሱፊ፣ሰለፊ» በሚለው ስሌትና ከፋፍለህ ግዛው በመጅሊሱ ውስጥ አንጃ እንዲፈጠር እየተተደረገ መሆኑን እየታየ ነው።ማህበረሰቡ «የብስራት ዜና» ተሰማ ብሎ ተደስቶ ስሜቱን ባደባባይ አሳይቶ አገርን በለውጥ እርከን ለማበልጸግ ቢሰማራም የጓሮው ገመድ ጉተታ እንደቀጠለ ነው። ሙስሊምን ከፋፍሎ፣በተለያዩ ስያሜዎች ፈርጆ የተመናመነ ተቋም እንዲኖርው ህወሃት የጀመረው ሴራ ዛሬ ባይቆምም  የሞጣን ተጠቂዎች መልሶ ለማቋቋም በተደረገው ርብርብ የገዢዎች ሴራ ምኞት እንደሚሆን  ለማየት ትችሏል።
ኢኮኖሚያችን የአቡዳቢን እርዳታ ቢያገኝም መስጊዶቻችን የአቡዳቢ ጣልቃ-ገብነትን አይሹምና የአብዳቢውን መርፌ አስገድዶ መውጋቶን ያቁሙ።እጆትን ከመስጊዶቻችን ላይ ያንሱ።
ልብ ያለው ልብ ይበል!
Filed in: Amharic