>
5:14 pm - Wednesday April 20, 8664

የሌንጮ ለታ ነገር. . .  (አቻምየለህ ታምሩ)

የሌንጮ ለታ ነገር. . . 

 

አቻምየለህ ታምሩ
የኦነጉ አምበል አዛውንቱ ሌንጮ ለታ ከሰሞኑ በኤ.ቲቪ. ላይ ቀርቦ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን የገዳ ሥርዓትን እንድንከተል በመምከር «የገዳ ስርዓት በደንብ ከተጠቀምንበት የዲሞክራሲን አሰራር በልብ ውስጥ ይተክካል» ሲል የ77 ዓመት እድሜ ያለው የሽማግሌ አስተያየቴ ያለውን ለግሶ ከተሰየመበት መድረክ ወርዷል። ሌንጮ ለታ እድሜ ዘመኑን ጥሮታ እስኪወጣ ድረስ በፖለቲካ ውስጥ ኖሮ ገዳ ስለሚባለው የወረራና ወታደራዊ ሥርዓት አለማወቁ የሚያስደንቅም የሚያስገርምም ነው።
እስቲ ይህ ገዳ የሚባለው ሥርዓት ከዲሞክራሲ ጋር የሚያገናኘው አንዳች ነገር እንዳለው እንመርምረው።
የዴሞክራሲ መርኅ ናቸው ከሚባሉት መካከል ዋናው «የብዙሐን አገዛዝ እና የጥቂቶች መብት» ወይም በእንግሊዝኛ «Majority Rule and minority Right» የሚለው ጽንሰ ሀሳብ ነው። በዚህ የዲሞክራሲ መርኅ የገዳ ሥርዓትን ስንመዝነው ገዳ የዲሞክራሲ ፍጹም ተቃራኒ ሆኖ እናገኘዋለን። ይህ ምን እንዴት እንደሆነ ላስረዳ!
በኦሮሞ ስነ ቃል ውስጥ Salgan Borana, sagaltamman Garba [Nine are the Borana [pure Oromo] and ninety the Garba [the assimilated] የሚል ታዋቂ ትውፊት አለ። [ምንጭ፡ 1ኛ. G.W.B Huntingford (1955). The Galla of Ethiopia. London: International African Institute፥ ገጽ 46; 2ኛ. Cerulli, E. (1933). Etiopia Occidentale (Dallo Scioa alla frontiera del Sudan): note del viaggio 1927-1928. Sindacato Italiano Arti Grafiche. Vol. I ገጽ 33]።
ይህ ትውፊት ኦሮምኛ ከሚናገረው ውስጥ «ገርባዎች ዘጠና፤ ቦረናዎች ግን ዘጠኝ ናቸው» ማለት ነው። ይህ ትውፊት ኦሮምኛ የሚናገረው ማኅበረሰብ ቦረናዎች [እውነተኛ ኦሮሞዎች] እና ገርባዎች [ተገደው ማንነታቸውን ወደ ኦሮሞ የቀየሩ] ተብለው በሁለት እንደሚከፈሉ የሚገልጽ ነው።
ከአስር ኦሮምኛ ተናጋሪዎች መካከል «ዘጠኙ ገርባ [ኦሮሞ ያልሆነ] አንዱ ኦሮሞ» ነው ከሚለው የኦሮሞ ትውፊት ተነስተን ኦሮሞ የሆነው በቁጥር እጅግ ጥቂት እንደሆነና ገርባው ደግሞ በቁጥር እጅግ አብዝሐ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።
የገዳ ሥርዓት መርኅ ናቸው ከሚባሉት መካከል ዋናው ማንነቱን እንዲቀይር የተደረገው ወይም ገርባው እንኳን መሪ ሆኖ ሊመረጥ የገዳ ስርዓት በሚካሄድበት አካባቢ ድርሽ እንዳይል ማድረግ ነው። በገዳ ሥርዓት መሰረት መሪ ወይም አባዱላ የሚሆነው ሰው የሚሰየመው እውነተኛ ኦሮሞ ወይም ቦረና ከሆኑት ብቻ የበለጠ የገደለውና ብዙ የወረረው ነው። በቁጥር አናሳ ከሆኑት እውነተኛ ኦሮሞዎች ወይም ቦረናዎች መካከል የበለጠ የገደለና ብዙ ገርባ ያስገበረ ጦረኛ አባ ዱላ ሆኖ ይሰየማል። ይህ የገዳ ስርዓት መርኅ ነው።
ጀርመናዊው ኡርሊች በርካምበር እንዳጠናው አርሲ ውስጥ ሁለት ሶስተኛው ሕዝብ የሐድያ ነገድ አባል የሆነና ኦሮምኛ በግድ የተጫነበት ነው። ሆኖም ግን አስተዳደሩን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረውት የነበሩት ጥቂቶቹ የቦረና ኦሮሞዎች ናቸው። በርካምበር እንደሚለው « አርሲ ውስጥ የኦሮሞ ጎሳ ከሆነው ከቦረና በስተቀር ከሁለት ሶስተኛ በላይ የሚቆጠሩት የሐድያ ጎሳዎች እንዲያስተዳድሩ አይፈቀድላቸውም፤ በማኅበራዊ ደረጃም የሐድያ ጎሳዎች የሆኑ አርሲዎች ከኦሮሞ ጎሳ ያነሰ ቦታ ይሰጣቸው ነበር።  [ምንጭ፡ Braukämper, U. (1980). Geschichte der Hadiya Sud-Athiopiens. A. Schröder፡ ገጽ 431]
የበርካምበት ጥናት የሚያሳየው የገዳ ሥርዓት አብዝሐነት የሆኑትን ገርባዎችን ለመግዛት በቁጥር አናሳ ከሆኑት ቦረናዎች መካከል በብዛት የገደለውና የወረረው አባ ዱላ ሆኖ በመሪነት የሚሰየምበት ሥርዓት እንደሆነ ነው። ዲሞክራሲ ግን የዚህ ተቃራኒ ነው። ዲሞክራሲ ብዝሐ ቁጥር ያላቸው ተገዥዎች ሙሉ በሙሉ ተገልለው ጥቂት ቁጥር ያላቸው ገዢዎች ብቻ እየተፈረራረቁ ተገዢዎችን ገርባና ባሪያ የሚያደርጉበት ስርዓት አይደለም። ገዳ የአንድ ኅብረተሰብ ግማሽ አካል የሆኑትን ሴቶችን ሙሉ በሙሉ እንደሚያገልል ስናስብ ደግሞ ስርዓቱ «የብዙሐን አገዛዝ እና የጥቂቶች መብት» የሚለውን ዋናውን የዲሞክራሲ መርኅ ጥርሱን እንዳረገፈው ማሰብ አይከብድም።
ምን ይሄ ብቻ። በገዳ ሥርዓት መሪ መሆን የሚችለው ኦሮምኛ ከሚናገሩት ከአስር አንድ እጅ ከሆኑት እውነተኞቹ ኦሮሞዎች ከሆኑት  ከቦረናዎቹ ውስጥም  ሴቶች ሙሉ በሙሉ ከገዳ ሥርዓት አመራር ውጭ ናቸው። በሌላ አነጋገር በገዳ ሥርዓት ሴቶች ሙሉ በሙሉ ከሥርዓቱ ውጭ ናቸው።
ከሴቶች በተጨማሪ አባቶቻቸው የገዢው  መደብ የሉባ መደብ አባላት ያልሆኑ ወንዶችም  መሪ ወይም የገዳ ሥርዓት አካል  መሆን አይችሉም። ይህን አስመልክቶ የገዳ ሥርዓትን በማጥናቱ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ የክብር ዶክትሬት የሰጠው ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሰ እንዲህ ይላል፤
“In the Gada system, there is a gap of forty years between a father and his son. According to the basic custom of the system, a son is admitted to Gada system, on the 40th year after the father joined the system… Class membership is open to men, whose fathers are already members [of the ruling class]” [ምንጭ፡Legesse, A. (1973). Gada: Three approaches to the study of African society. Free Press; Page 124 & Authority for Research and conservation of Cultural Heritage (ARCCH), 2015]
ትርጉም፡ 
“በገዳ ሥርዓትሥርዓት ውስጥ  በአባትና በልጅ እድሜ መካከል  ሁልጊዜ የአርባ አመት የእድሜ ልዩነት ይኖራል። በሥርዓቱ መሠረታዊ ሕግ መሰረት ገና የተወለደ ወንድ ልጅ ወደ ገዳ ሥርዓት የሚገባው አባቱ ወደ ገዳ ሥርዓት ከገባ ከአርባ አመት በኋላ ነው። ወደ ገዳ ሥርዓት መግባት የሚችሉ ወንዶች አባቶቻቸው የገዢ የገዳ መደብ አባል የሆኑት ናቸው።”
እንግዲህ! ሌንጮ ለታ «የገዳ ስርዓት በደንብ ከተጠቀምንበት የዲሞክራሲን አሰራር በልብ ውስጥ ይተክካል» የሚለን ከኦሮምኛ ተናጋሪው ውስጥ  አንድ አስረኛው ብቻ መሪ  ሊሆኑ የሚችሉበትን፣ ሴቶችን ሙሉ በሙሉ ያገለለውንና መሪ መሆን ከሚችሉት ከአንድ አስረኛው ኦሮምኛ ተናጋሪ ውስጥም አባቶቻቸው የገዢ መደብ አባላት የሆኑት ብቻ መሪ የመሆን እድል የሚሰጠውን የገዳ ሥርዓት ነው።
ባጭሩ ዲሞክራሲ «የብዙሐን አገዛዝ እና የጥቂቶች መብት»የሚከበርበት ስርዓት ነው። ገዳ ግን አብዝሐ ቁጥር ያላቸውን ገርባዎችን፣ ሴቶችን ሙሉ በሙሉና አባቶቻቸው በገዢው የገዳ መደብ ውስጥ የሌሉ ወንዶችን በገዳ ስርዓት ሙሉ በሙሉ እንዳይሳተፉ አግዶ በቁጥር አናዛ ከሆኑት እውነተኛ ኦሮሞዎች መካከል አብዝሐውን ለመግዛት በአባ ዱላነት የሚሰየሙበት ሥርዓት ነው።
ለዚህም ነው ጥቂቶቹ እውነተኛ ኦሮሞዎች አብዝሐ ቁጥር ያላቸውን ገርባዎች እንዲገዙ ተደርጎ የተዋቀረው የገዳ ስርዓት በኦነጋውያንና ደቂቆቻቸው እንደሚደሰኮረው እንኳን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት፣ እንኳን መንግሥታዊ ሥርዓት ፖለቲካዊ ሥርዓትም አልነበረም የወረራ ሥርዓት እንጂ። ባጭሩ የገዳ ሥርዓት ምንም አይነት ዲሞክራሲያዊነት የሌለበት ፍጹም የሆነ ወታደራዊ ሥርዓት ነው።
የገዳ ሥርዓትን የዲሞክራሲ ስርዓት ነው የሚለው ሌንጮ ለታ  Salgan Borana, sagaltamman Garba የሚለውን የኦሮሞ ትውፊት መሰረት አድርጎ  የገዳ ስርዓት የዴሞክራሲ መርኅ ናቸው ከሚባሉት መካከል ዋና የሆነውን «የብዙሐን አገዛዝ እና የጥቂቶች መብት» [Democracy is based on both majority rule and minority rights] እንደሚያሟላ እስቲ ያስረዳ?!
Filed in: Amharic