>

ከኢትዮጵያ የተዘረፈው የ18ኛውን ክፍለ ዘመን የደጃች ወልደሥላሴ ዘውድ ሀገሩ ሊገባ ነው!!! (ሸገር FM)

ከኢትዮጵያ የተዘረፈው የ18ኛውን ክፍለ ዘመን የደጃች ወልደሥላሴ ዘውድ ሀገሩ ሊገባ ነው!!!

ሸገር FM
 
* ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ ተሰርቆ ኔዘርላንድ የተወሰደውን ዘውድ የቅርስ እና ጥበቃ ባለስልጣን በነገው ዕለት ልረከበው ነው አለ፡፡
 
* ቅርሱ በኔዘርላንድ ለ21 ዓመታት ተደብቆ እንደቆየም ታውቋል፡፡
 
* ከዚህ ቀደም የጨለቆት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን፣ የተዘረፈው ዘውድ የይመለስልኝ ጥያቄ አቅርባ ነበር፡፡
የባህልና ቱሪዝም ቀድሞ ከኢትዮጵያ በህገ-ወጥ መንድ ወጥቶ የነበረ ዘውድና ሌሎችንም ቅርሶች ለማስመለስ ከኔዘርላንድ መንግስት ጋር እየመከረ እንደነበር ሰምተናል፡፡
ኔዘርላንድ ከኢትዮጵያ የተዘረፈውን የ18ኛውን ክፍለ ዘመን የደጃች ወልደሥላሴ ዘውድን ለመመለስ ቃል ገብታ ነበር፡፡
በዚህ መሰረት የቅርስ እና ጥበቃ ባለስልጣን የተዘረፈውን ዘውድ በነገው ዕለት ተረክቤ ወደ ሙዚየም አስገባለሁ ማለቱን ለሸገር ነግሯል፡፡
ከዚህ ቀደም በኔዘርላንድ የሚኖሩት ትውልደ ኢትዮጵያዊ አቶ ሲራክ አስፋው የተባሉት ግለሰብ ይህንኑ ቅርስ ለ21 ዓመታት በመኖሪያ ቤታቸው ማቆየታቸውን ለስካይ ኒውስ፤ ለቢቢሲና ለሌሎችም ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን መንገራቸውን አንብበናል፡፡
ግለሰቡ በኔዘርላንድ ሀገር ይኸው ቅርስ በአጋጣሚ እጃቸው እንደገባና እሳቸው ጋርም 21 ዓመት እንደቆየ ተናግረዋል፡፡
ዘውዱንም 21 ዓመት ያቆዩት ለቅርሱ ደህንነት የተሻለ ጊዜ በመጠበቅ እንደሆነ ከዚህ ቀደም ተናግረዋል፡፡
በአፄ ፋሲለደስ እንደተሰራ የሚነገርለት የጨለቆት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የ400 ዓመት እድሜ አለው ተብሏል፡፡
ይህንኑ ቅርስም የቅርስና ጥበቃ ባለስልጣን ነገ በሚፈለገው ሥርዓት እና ደንብ እጄ አስገባለሁ ማለቱን ለሸገር ነግሯል፡፡
Filed in: Amharic