>

ሰቆቃ ወ ቤተ ክርስቲያን !!!! (ሊቀ ጉባኤ ጌታሁን ደምጸ) 

ሰቆቃ ወ ቤተ ክርስቲያን !!!!

ሊቀ ጉባኤ ጌታሁን ደምጸ 
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በኢህአዲግ ዘመነ መንግሥት በካቴድሬዎች ጣልቃ ገብነት ለኻያ ሰባት ዓመታት እንደ ወተት ዕቃ ስትናጥ ኖራለች፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች ከቤተ ክርስቲያን ህልውና ይልቅ ለፖለቲካ ህልውና የሚያደሉ ለጥቅማቸው ያደሩ የፖለቲካ የማገዶ እንጨት ሆነው መኖራቸው አንዱ ፈተና ነበር፡፡
የኢህአዲግ ካቴድሬዎችም ‹‹ክርስትና አሳዳጅና ጨቋኝ ሃይማኖት ነው፤ የነፍጠኛ ኮተት መጣያ ነው፤ ቤተ ክርስቲያን የፊውዳል ዓላማ አራማጅ ናት፤ ለኢትዮጵያ ድህነት ተጠያቂዋ ቤተ ክርስቲያን ናት›› እያሉ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶን ቤተ ክርስቲያንን ሲያዳክሟት ኖረዋል።
ቤተ ክህነትን በአቁጣሮ የዘር ሐረግ ጨምድደው ወንጌላዊ አገልግሎት በአግባቡ እንዳይሰራጭ የበከተ መሥዋዕት የረከሰ ዕጣን እናሳርጋለን የሚሉ ካድሬዎች ካህናትን ሰግስገው ሲያስለቅሷት ኖረዋል፤  በአንጻሩ የመናፍቅ መንጋ አሰማርተው መጋዘን እያከራዩ በየሴንቲ ሜትሩ የተዋሕዶ ቀበኞች እንዲፈነጩ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ እንዲሳለቁ አድርገዋል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስን እንደ አክርማ ለሁለት ሰንጥቀው ሲያበጣብጧትና ሲያንገላቷት ኖረዋል፡፡
ከዲያቆን እስከ ጳጳስ የሚገባውን ባይተዋር እያደረጉ ለፖለቲካቸው ብቻ የሚመቻቸውን እየመለመሉ ለሥልጣን የሚሻኮቱ ከአፍንጫቸው በላይ አርቀው ማሰብ የማይችሉ ያልተማሩ ሆድ አደሮችን ሰብስበው ቤተ ክህነቱ ሽባ አድርገዉት ኖረዋል፡፡
የኢህአዲግ ካድሬዎች (የህውሀት አባላት) ቢያውቁት ቢረዱት ለክርስትና ከእነርሱ በላይ ማን ይቀርብ ነበር፤ የክርስትና መፈጠሪያ ማኅፀን ነበሩ። እንኳን ለሰው ለእንስሳት የሚራሩ ክርስትናን በሁለት እግሩ ያቆሙ፤ አክሱም ጽዮንን በወርቅና በዕንቊ ያስጌጡ፤ የጀግኖች የነአብርሀ የነአጽብሐ የነዐፄ ገብረ መስቀል የነዐፄ ካሌብ ትውልድ ነበሩ። ማተብ ያላደረገ ማየት የሚያስከፋቸው፤ በሊቃውንት ጉባኤ ተገኝተው የሃይማኖት አድሀሪዎችን የቀጡ፤ ቀሳጥያን መናፍቃንን ያስደነገጡ፤ በሃይማኖታቸው የማይደራደሩ የዐፄ ዮሐንስ ትውልድ ነበሩ።
በተለይ ደግሞ በሃይማኖቱ የማይደራደር ያፈራውን ሲሳይ ተካፍሎ የሚኖር ቄጠማ ጎዝጉዞ ፍሪዳ አርዶ እንግዳ የሚቀበል ርኅሩኅ የደግ ሕዝብ አብራክ ልጆች ነበሩ፡፡
ግን ምን ይሆናል ለኦርቶዶክስ የበኵር ልጆቸ መሆናቸውን ረስተው ክርስትና የአማራ ዲስኩር ነው፤ ክርስትና ውኃ ከመቦጫረቅ ውጭ ምን ትርፍ አለው እያሉ በካድሬዎቻቸው ስብከት ኦሮሞውን፣ ጉራጌውንና ሌላውንም ከቀናች ከጸናች ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት እንዲኮበልል ደባ ሲፈጽሙ ኖረዋል። በአንድ በኩል መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ አይገባም እያሉ ወዲህ ፓርላማውን ሳይቀር ለካድሬዎቻቸው የሚጸልዩ የፓስተር መንጋ መመሰጊያ አድርገዉት ነበር።
በቤተ ክህነት ሌቦችና ዘረኞች ሴሰኞች ሰግስገው ቤተ ክርስቲያን እንድትጠላ እያደረጉ ከውጭ ተቀባይ አውሬ እያዘጋጁ እናት ቤተ ክርስቲያንን ለኻያ ሰባት ዓመታት አስለቅሰዋታል፡፡
የደሀ ዕንባ ይጠበቅ ፍርድ አይጓደል ብለው ኢፍትሐዊና አረማዊ ድርጊትን የተቃወሙ አባቶችን በቤተ ክህነት ካድሬ አሰማርተው በውድቅት ሌሊት የጳጳሳትን ቤት ሰብረው፤ ጳጳሳትን ሲደበድቡ ኖረዋል፡፡ በአዲስ አበባ ብቻ እንኳን ለዓመታት በይዞታነት ስትጠቀምበት የነበሩትን የደመራ ቦታና የበዓለ ጥምቀት ማክበሪያ ቦታ ለባለ ሀብት እየሸጡ የመቃብር ቦታ እያሳጡ ቤተ ክርስቲያንን ሲያስለቅሷት ኖረዋል።
ሕንጻዎች እንኳን ቢገነቡ አብያተ ክርስቲያናት ቢታነጹ በምእመናን ገንዘብና ላብ ነው፤ ያውም ዝረፉ ቅጠፉ ብለው ካሰማሯቸው ካድሬ አለቆች መንጋጋ እየተናጠቁ የተሠሩ ናቸው።
ሕዝብ ከሕዝብ ሲጋጭ ብሔራዊ መግባባት ሲጠፋ ሰላምን የሚሰጥ እግዚአብሔር ነውና ምሕላ ይያዝ ብለው አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ምህላ ሲያደርሱ ምን ተፈጠረ? ማን አዘዛችሁ? ብለው ዛቻና ማስጠንቀቂያ ሲሰጡ ኖረዋል፤ በተለይ በ1999 ዓም በጅማ ክፍለ ሀገር ክርስቲያኖች በግፍ ሲታረዱ ይህንን ግፍ በዐውደ ምሕረት እንዳይነገር ለሰባክያን ጥብቅ መመሪያ የሚሰጡ፣ መዋቅር የማይጠብቁ በአምባገነንነት ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ዘበኛ ድረስ ብቻቸውን ፈላጭ ቆራጭ የነበሩ፤ የምንሰበሰብበትን አጀንዳ በመንግሥት አካል ሳላስፈቅድ እንዲሁም የመንግሥት አካላት ካልተገኙ ስብሰባውን አላስጀምርም የሚሉ ፓትርያርክ አስቀምጠው ሲኖዶሱን የፖለቲካቸው የማገዶ እንጨት አድርገው እናት ቤተ ክርስቲያንን ሲያስለቅሷት ኖረዋል፡፡
ምእመናንን ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብተው ያስሩ ይገድሉ ነበር፤ ለምሳሌ በ1997 ዓም ወቅታዊ የፖለቲካ ግርግርን ተከትሎ ፈርተው ከቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የተጠለሉትን አፍሰው ወኅኒ ቤት የጣሏቸውንና የገረፏቸውን እንደ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቤተ ክህነት ሙስና የሚስፋፋበት መደላድል በመፍጠር፣ አስተዳደራዊ ብልሹነትን በማስፈንና መንደርተኛነትን በማስፋፋት ቤተ ክርስቲያንን ሲያስለቅሷትና ምእመናንን ሲያስመርሩ ኖረዋል፡፡
ርእዮተ ዓለማዊና የሐሰት ታሪኮችን ፈጥረው በመጻሕፍም ሆነ በሚዲያ እያሰራጩ ለሀገር ግንባታ፣ ለመልካም አስተዳደር፣ ለትምህርት ወዘተርፈ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ማንነት ትልቅ አሻራ ያሳረፈችውን ታላቋን ቤተ ክርስቲያናችንን ፖለቲከኞች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአሐዳዊ ሥርዓት ናፋቂና የአንድ ብሔር ሃይማኖት እንደሆነች በማስመሰል በሚያራግቡት የሐሰት ወሬ አንዳንድ ምእመናን እንዲደናገሩና ቤተ ክርስቲያንን እንዲጠራጠሩ ሲያደርጉ ኖረዋል፡፡
በቤተ ክህነት ብልሹ አሠራር የተበሳጨው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በአንድ ወቅት ‹‹ሦስቱ አርእስተ ኀጣውእ›› በሚል ርእስ በድረ ገጽ ከትቦ ያሰነበበንን እኔ በአጭሩ እንደ ማጠናከሪያ ሀሳብ ተጠቅሜበታለሁ፡፡
ይኸውም ዛሬ የአዲስ አበባ አብዛኞቹ ካህናት የመኖሪያ ቤት የላቸውም፡፡ እንዲያውም አዳዲስ በሚሠሩ ቤቶች የኋላ ክፍሎች ውስጥ (ሰርቪስ ቤቶች) ተጠግተው ዕቃ እየጠበቁ የሚኖሩ ናቸው፡፡ ካህናቱ ልጆቻቸውን የተሻለ ትምህርት ቤት መላክ አይችሉም፤ አንዳንዶቹ በመቃብር ቤት ነው የሚኖሩት፤ የአንዳንዶቹም ደመወዝ በየወሩ አይከፈላቸውም፡፡
በሌላ በኩል በአስተዳደር የሚመደቡት አካላት ቤትና መሬት የሚሸጡ፣ የንግድ ተቋማትን የሚያስተዳድሩ፣ መኪና የሚቀያይሩ፣ በውስኪ የሚራጩ፣ በጮማ የሚጫወቱ ናቸው፡፡ ዛሬ የብዙዎቹ ካህናት ልጆች አባቶቻቸው በቤተ ክህነቱ የሚደርስባቸውን በደል ስለሚነግሯቸው በእግራቸው ተተክተው ካህናት መሆን አይፈልጉም፡፡
አባቶቻቸው ለመቀጠር፣ ለማደግ፣ ለመዛወር፣ የደመወዝ ጭማሪ ለማግኘትና ለመሾም ጉቦ መስጠት ግዴታቸው መሆኑን ስለሚያውቁ ልጆቻቸው የዚህ ሰለባ እንዳይሆኑ የእኔ ይበቃል በሚል ሐሳብ ካህን እንዲሆኑ አይፈቅዱላቸውም፤ ትምህርቱንም አያስተምሯቸውም፡፡
የምእመናኑ ዕውቀትና ንቃት አደገ፤ የቤተ ክርስቲያኒቷ ሀብትና ንብረት ተትረፈረፈ፣ የካህናቱና አገልጋዮቹ ቁጥር ጨመረ፤ የዘመኑ ጥያቄዎች እየተቀየሩና እየበዙ መጡ፡፡ ይህን ማስተዳደር የነበረበት ቤተ ክህነት ግን እንደ ግመል ሽንት ወደ ኋላ ይሄዳል፡፡
መንግሥት እንኳን ሲቪል አስተዳደሩን ለማሻሻል በየዘመናቱ የአሠራር ማሻሻያዎችን ሲያደርግ ቤተ ክህነት ግን ላለፉት አርባ ዓመታት ባለበት እየረገጠ ነው፡፡ ዘመኑ የመረጃ ዘመን ነው፤ እንደ ጥንቱ ግመል ሰርቆ አጎንብሶ መሄድ አይቻልም እንዲሉ በየሠፈሩ የሚሠሩት ሕንጻዎች፣ በየገበያው የሚገዙት አክስዮኖች፣ በየሆቴሉ የሚረጩት ውስኪዎች፣ በየፓርኪንጉ የሚቆሙት መኪኖች፣ በየባንኩ የሚገቡት ገንዘቦች፣ በየአንገቱ የሚንጠለጠሉት ወርቆች ሙሰኛ ቤተ ክህነታውያን በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ምን እየሠሩ እንደሆነ ይነግሩናል፡፡
ገዳማቱ ተቸግረው፣ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት እየተዘጉ፣ የአብነት መምህራን እየተራቡ፣ የአብነት ተማሪዎች ቁጥር እያሽቆለቆለ ሄዷል፡፡ የሙሰኞች ሆድና ሀብት ግን እየጨመረ ነው፡፡ ብልሹ አስተዳደሩ ለሙሰኝነቱ የረሰረሰ መሬት ፈጥሯል፡፡ ሙሰኞች ሲጋለጡ ደግሞ መንደርተኝነቱ ይከላከልላቸዋል፡፡
ትግሬ ስለሆነ ነው፣ ሸዋ ስለሆነ ነው፣ ጎንደር ስለሆነ ነው፣ ጎጃም ስለሆነ ነው፣ ወሎ ስለሆነ ነው ይባላል፡፡ ሙስናው፣ ብልሹ አስተዳደሩና መንደርተኛነቱ እንዲህ ተጠላልፎ ከጠቅላዩ እስከ አጥቢያው ተሰናስሏል፡፡
በተለይ ደግሞ ለእውነትና ለእምነት የቆሙ አባቶች በጊዜ ነቅተው እንክርዳዱን ራሳቸው ካልነቀሉት፤ ጊዜ የሚያመጣው አጫጅ እንክርዳዱን ከነ ስንዴ መንቀሉ አይቀሬ ነው፡፡
የጨው ገደል ሲናድ ብልህ ያለቅሳል ሞኝ ይስቃል እንደተባለው ችግሩ የገባቸው አባቶችና ምእመናን እያለቀሱ ነው፡፡ ፍሬውን እየበሉ ከላይ የተቀመጡበትን ዛፍ እየቆረጡ ያሉት ሙሰኞች ደግሞ ይስቃሉ፡፡
መንፈሳዊ ኀዘን ከእግዚአብሔር ዘንድ ፍትሕ ይጠይቃልና ተገቢ ነው፡፡ ከዘመኑ መናፍቃን ጋር ተባብረው ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመግደል እያሤሩ የሚገኙትን የቤተ ክርስቲያን የውስጥ መዥገሮች ለመንቀልና ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን የሚተርፍ የእፎይታ ዘመን ለማምጣት ካህናት ምእመናንን በመያዝ በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ መታገል ይገባቸዋል፡፡
   “የእግዚአባሔርን ስራ በቸልታ የሚያይ ርጉም ይሁን ” ኤር 47፥10
Filed in: Amharic