>
5:13 pm - Thursday April 19, 7455

የዋቆ ጉቱ «አመጽ» እና የኦሮሞ ብሔርተኞች አመጹን አስመልክቶ  የፈጠሩት ትርክት ሲፈተሽ!  (አቻምየለህ ታምሩ)

የዋቆ ጉቱ «አመጽ» እና የኦሮሞ ብሔርተኞች አመጹን አስመልክቶ  የፈጠሩት ትርክት ሲፈተሽ! 

 

 

አቻምየለህ ታምሩ
ኢትዮጵያ ውስጥ የቆመው የአፓርታይድ አገዛዝ ቁንጮ የሆነው ዐቢይ አሕመድ  ጥር 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ወደ ባሌ በማቅናት እነ ዋቆ ጉቱን የነጻነት ታጋዮችና አርበኞች አድርጎ በማቅረብ በአማርኛ  ስለ ኢትዮጵያ በሚያሰማው ለጆሮ በሚስቡ ዲስኩሮቹ  የሚያጠልቀውን ጭንብሉን ሮቤ ላይ በኦሮምኛ  ስለነ ዋቆ ጀግንነት የኦነጋውያንን ዲስኩር ሲደግሞ  በድጋሜ አውልቆታል። ለመሆኑ ዋቆ ጉቱ የነጻነት ታጋይና አርበኛ ነበርን? እስቲ ዶሴው ይውጣና ዋቆ ጉቱ  በኢትዮጵያ ላይ በተለይም በቦረና የኦሮሞ ጎሳዎች ላይ ምን እንደሰራ ታሪኩ ይመርመር።
እንደሚታወቀው የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች ያለፉት አርባ አራት ዓመታት ፖለቲካ በፈጠራ ታሪክ ላይ ተመስርተው ኢትዮጵያን በቅኝ ገዢነት፣ ዳግማዊ ምኒልክን በወራሪነትና በጨፍጫፊነት፣ ሰፊውን የአማራ ሕዝብ ደግሞ በጨቋኝነት በመፈረጅ በነዚህ ጠላት ባደረጓቸው አካላት ላይ የዘር ማጥፋት እየፈጸሙ ከአማራ የጸዳ አገር የመመስረት ትግል ነው። በርግጥ በፈጠሩት የውሸት ትርክት ላይ ተመስርተው በአማራ ላይ የዘር ማጥፋት ሲያኬሂዱ ብቻቸውን አልነበሩትም። የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች እንደ ትግል አርአያነትና ታሪካዊ መነሻ ወደኋላ የሚያማትሩት የአርሲ ጎሳ ተወላጁ ዋቆ ጉቱ ባሌ ውስጥ የዚያድ ባሬ እንደራሴ ሆኖ ለኦሮሞ ሳይሆን የታላቋን ሶማሊያ ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ መሳሪያ ሆኖ የተንቀሳቀሰበት አመጽ ነው። ዋቆ ጉቱ በዚያድ ባሬ እየታገዘ በኢትዮጵያውያን ኦሮሞዎች ላይ ያካሄደውን ውጊያ እንደ ተራማጅ እንቅስቃሴ የሚቆጥሩት የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች ብቻ አይደሉም።
የኢትዮጵያ የግራ ፖለቲከኞች ሁሉ «ገበሬው በፊውዳሉ ሥርዓት ላይ በተለያየ ጊዜና ቦታ እያመጸ በመነሳት መብቱን ለማስከበር፣ ሥርዓቱንም ለመደምሳስ ታግሏል፤ በተለይ በባሌ ያካሄደው የነፃነት ትግል በአርአያነት የሚጠቀስ ነው» ብለው ያልነበረ የገበሬ አመጽ ፈጥረው እስካሁን ድረስ ሳያፍሩ ይናገራሉ፤ የሚጽፉት አልፎም መታሰቢያ እስከማቆም ሁሉ ደርሰዋል። የዚህ አይነቱ ትርክት ዋቆ ጉቱንም ሆነ የኢትዮጵያ ገበሬ ያልሆነውን ሆነ፣ ያልፈጸመውን ፈጸመ እያሉ ለማሞገስና ለሚቀጥለው ትውልድ ከዚህ በፊት እንደተደረገው ሁሉ ዛሬም ለነዋቆ አይነት የጠላት ዓላማ ተሰለፍ ብሎ ለመቀስቀስ ካልሆነ በስተቀር በባሌም ሆነ በሌላው የኢትዮጵያ አካባቢ ገበሬው በዘመኑ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ላይ አምጾ ለውጥ ለማምጣት ታግሎ ነበር የሚያሰኝ አንዳች እንቅስቃሴ አልነበረም።
በ1950ዎቹ ዛሬ ሶማሊያ የሆነው አገር በኢትዮጵያውያን ተጋድሎ ከቅኝ ግዛት ተላቆ  «የሶማሊያ ሕዝብ ሪፑብሊክ» ተብሎ ነጻነትን አግኝቶ ከተቋቋመ በኋላ «ታላቋን ሶማሊያ» እንመሰርታለን የሚል ዓላማ አዲሱ መንግሥት በመንደፉና «የሱማልኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሰዎች የሰፈሩበት አካባቢ ሁሉ የሶማሊያ መሬት ነው» ከሚል የተሳሳተ ዓላማ ላይ በመመርኮዝ ኦጋዴንና የባሌን ምስራቅና ደቡብ ክፍል ለማጠቃለል የተቀየሰውን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ እንዲረዳው የተወሰኑ የአካባቢው ተወላጅ የሆኑ ባላባቶችንና ልጆቻቸውን በገንዘብና በጦር መሳሪያ በመርዳትና በማደራጀት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ብረት እንዲያነሱ አደረገ። ለዚህ እንቅስቃሴ ጥሩ መሳሪያና አገልጋይ ሆኖ የተገኘውን ዋቆ ጉቱ የሚባልን የአርሲ ጎሳ ተወላጅ የባሌ ባላባት ሞቃዲሾ ድረስ ወስዶ በገንዘብ በመደለል በእሱ መሪነት የተወሰኑ ጭሰኞቹን አሰልጥነውና አስታጥቀው በሽፍትነት የቦረናና ጉጂን ጎሳዎች እንዲወጉና ሰላም እንዲደፈርስ ወደ ባሌ ጫካ አሰማሯቸው።
ይህ «የኢትዮጵያን መንግሥት በውጥ ሽፍቶች ተወሮ ሲያዝ ኃይሉ ስለሚዳከም በቀላሉ በኦጋዴን ላይ ወረራ በማድረግ በቁጥጥር ሥር እናደርጋለ። ታላቋንም ሶማሊያ እንመሰርታለን» ብለው የሶማሊያ መሪዎች የቀየሱትን የባዕድ የወረራ እቅድ ለማስፈጸም የተቀሰቀሰ ንቅንቅሴ ነበር እንጂ የኢትዮጵያ ገበሬዎች በተለይም ደግሞ ለኦሮሞ ገበሬዎች ለነጻነትና ለመብት መጠበቅ ያካሄዱት ትግል እንደነበር ሲነገረን የኖርነው። ታሪኩን የመረመረ ግን ሁሉን ያውቀዋል። የሶማሊያ መንግሥት አራት የማሰልጠኛ ጣቢያዎችን አቋቁሞ በዋቆ ጉቱ እየተመለመሉ የሚቀርቡትን የዋቆ ጭሰኞች እያሰለጠነና እያስታጠቀ የሶማሊያን ፍላጎት ለማሟላት ኢትዮጵያን በተለይም በጠቅላይ ግዛቱ የሚገኙ የኦሮሞ ጎሳዎችንና ዋቆ ከብቶቼን ወስደዋል ያላቸውን ቦረናዎች ወጋ፤ የባሌን አካባቢ ፀጥታ አደፈረሰ፣ በነዋሪው ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አደረሰ፣ በተለይ በሕዝበ ክርስቲያኑ  ላይ ከፍተኛ ፍዳና መከራ አስከተለ።
የባሌ ገበሬዎች አመጽ መሪ ተደርጎ የሚቆጠረው ዋቆ ጉቱ ምንም እንኳ ተወልዶ ያደገው ባሌ ቢሆንም በመሰረቱ ግን ትውልዱ የአርሲ ጎሳ ነው። ዋቆ ጉቱ የቃልቻ ዘር በመሆኑ የአርሲ ጎሳዎች ያመልኩበት ነበር። ተወልዶ ያደገው ባሌ ውስጥ ወለቦ ከምትባለው ወንደር ሲሆን ከወላጅ አባቱ ከአቶ ጉቱ ኡሶ ጋር አብሮ ሲኖር ይተዳደሩ የነበረው በከብት ርቢ ስለነበር ግጦሽ ፍለጋ ከአባቱ ጋር ወደ ቦረና አውራጃ ይዘዋወር ነበር። አባቱ ሲሞቱ ከወንድሙ ከግራዝማች ጨምሪ ጉቱ ጋር አብሮ ይኖር ነበር። ወንድሙ አባ ቆሮ የሚባል የጎሳቸው ባላባትነት ስለነበረው አንድ ወቅት የባላባትነቱን ሥራ እንዲሰራ ውክልና ሰጥቶት ነበር። ዋቆ ጉቱ በውክልና የባላባትነት ስራ ከያዘ በኋላ ውክልና የሰጠውን ወንድሙን ይቀማና ባላባትነቱን በስሙ አዛውሮ ለራሱ በማድረግ አሻፈረኝ በማለት እምቢተኛ ሆነ።
በዚህ ምክንያት ወንድሙ ክስ አቅርቦ ብዙ ጊዜ ከተሟገቱ በኋላ በገንዘብ ኃይል ዋቆ ጉቱ ስላሸነፈ የአባቆሮ ባላባትነቱን ይዞ መኖር ጀመረ። ነገር ግን ይዞታው በገንዘብ ኃይልና በተጭበረበረ ሁኔታ እንጂ በሀቅ ስላልሆነ ነገሩ በሽምግልና ታይቶ ሽማግሌዎቹም ባላባትነቱን ያላግባብ ለተነጠቀው ለወንድሙ እንዲመልስ ስለወሰኑበት በሽማግሌዎቹ ውሳኔ መሰረት ለወንድሙ ለማስገከብ ተገደደ። ይህ በሆነ ጊዜ ከወንድሙ ይለይና በከብት አርቢነት ዘመኑ ወደሚያውቀው ነገሌ አካባቢ ኩርኩር ወደሚባለው ቦታ ሄዶ መኖር ጀመረ። ስለሆነ ዋቆ ከወንድሙ በውክልና የተሰጠውን ባላባትነት ለመንጠቅ ሲል ይሟገት በነበረበት ወቅት ከብቶቹን ሽጦ ገንዘቡን በጉቦ አባክኖ ጨርሶ በድህነት ላይ ወድቆ ስለነበር ለመሸፈት በዝግጅት ላይ ሳለ እንዲያው ለመሸፈት የሚገፋፋው አንድ ነገር በመሀሉ ላይ ተፈጠረ። የዚህ ታሪክ እንደሚከተለው ነው።
ዋቆ ጉቱ የነበሩትን ከብቶች ሁሉ ሽጦ ይኖርበት ከነበረው ከቦረና  በታች በጠረፍ በኩል በከብት አርቢነት ኑሯቸውን የሚገፉ ሶማሌዎች ይኖሩ ነበር። እነዚህ የሶማሌ ጎሳዎች የኢትዮጵያ ሶማሌዎች ሲሆኑ ጎሳቸው የመሪሀንና የዲጎድያን ጎሳዎች ናቸው። እነዚህ ሁለቱ ጎሳዎች እንደ ማናቸው አርብቶ አዳሪ ማኅበረሰብ የጥንት ይዞታቸውን እያለፉ የቦረናዎች ይዞታ ወደሆነ መሬት እየገቡ ከብቶቻቸውን ሳር በማብላትና  ውኃ በማጠጣት ጭምር ነበር። ይህ እየተደጋገመ በመምጣቱና በመለመዱ ይህ እንዳሻቸው በፈለጉ ጊዜና ሰዓት እየወጡና እየገቡ ውኃ የሚያጠጡበትንና ሳር የሚያግጡበትን መሬት እንዳሻቸው መርገጥ የለመዱት ሁለቱ ጎሳዎች ከቦረናዎች ጋር መጋጨት ይጀምራሉ። በዚህ ጊዜ ቦረናዎች ስብሰባ አድገው «በላይ በኩል ጉጂ የሚባሉት ጎሳዎች ወደታች እየወረዱ ያጣብቡናል፤ በታች በቆላው ያሉት ሶማሌዎች ደግሞ ይዞታቸው ከፊልቱ በታች ሆኖ ሳለ አሁን ፊልቱን አልፈው የኛን ይዞታና እርስታችን ከሆነው ምድር ገብተው ከማስቸገር አልፎ ከርስታችን የሚፈልቀውን ውኃ እያጠጡና የበቀለውን ሳር ከብቶቻቸውን እያስጋጡ የኛ ከብቶች እንዲራቡና እንዲጠሙ አደረጉብን፤ ስለዚህ ሶማሌዎች ፊልቱን አልፈው ወደኛ መሬት እንዳይገቡ በጥንቱ ይዞታቸው ጸንተው እንዲኖሩ ይደረግልን» ሲሉ ለጠቅላይ ግዛት እንደራሴው ለራስ አንዳርጋቸው መሳይ አመለከቱ።
ጠቅላይ ግዛቱም ነገሩን በጉባዔ አይቶ ሱማሌዎቹ የጥንቱ ይዞታቸውን አልፈው ከቦረናዎቹ እርስትና ይዞታ ገብረው እንዳይሰፍሩ፣ የሰፈሩ ቢኖሩ እንዲለቁ ወደፊትም ፊልቱን አልፈው ወደ ቦረናዎች መሬት እንዳይገቡ ብሎ ወስኖላቸው ነበር። ይህ ውሳኔ በተሰጠበት ቦታ የሱማሌዎች ብቻ ሳይሆኑ የቦረና ጎሳዎችን ያልሆኑ አርሲዎች እነ ዋቆ ጉቱ ይኖርበት የነበረው ቦታጭምር ነው። ሶማሌዎቹ የጠቅላይ ግዛቱን ውሳኔ አክብረው የቦረና ጎሳዎችን መሬት ለቀው ወደቦታቸው ሲመለሱ የአርሲ ጎሳዎቹ እነ ዋቆ ጉቱ ግን «እኛ ሶማሌዎች አይደለንምና ልንለቅ አይገባም» በማለት ክርክር አቀረቡ። በዚህ ጊዜ የቦረና ጎሳዎች እነ ዋቆን ለጠቅላይ ግዛቱ ከሰሱ። ጉዳዩን የተመለከተው ጠቅላይ ግዛቱም በሰጠው መልስ «ቦረናዎች ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ተመስርቶ የተላለፈው ውሳኔ ጎሳ ሳይለው በሁሉም ላይ የተሰጠ ስለሆነ ባለርሥቶቹ ሳይፈቅዱ በሰው ቦታ ላይ ማንም ሊቀመጥ አይገባም፤ ስለሆነ  እናንተም ወደ ርስታችሁና ወደ ጥንት ይዞታችሁ ተመለሱ» ብሎ ወሰነባቸው።
ይህን ውሳኔ በመተላለፍ በዋቆ ጉቱ አደፋፋሪነትና ምክር ሰጭነት የተሰባሰቡ የተወሰኑ የአርሲ ጎሳ አባላትና ጭሰኞቻቸው ቦታውን አንለቅም በማለት ለቦረናዎች የተላለፈውን ውሳኔ በመጋፋት ተቀመጡ። በዚህ ጊዜ ቦረናዎችና ጀምጀሞች በአንድ ላይ ሆነው መንግሥት ለሰጠው ውሳኔ አንታዘዝም ብለው በተቀመጡ ሰዎች ላይ ጦርነት ከፍተው ከሀያ በላይ የሚሆኑ የአርሲ ጎሳ አባታትን ገደሉ። አሁን ዋቆ ጉቱ ፊትም የወንድሙን ባላባትነት ሊነጥቅ ባስነሳው ሙግት ሀብቱን ጨርሶ ከድህነት ላይ የወደቀ ስለሆነ አሁን ዳግም መንግሥት የሰጠውን ትእዛዝ አልቀበልም ብሎ በሱ ሐሳብ የሚመሩትን ባላገሮች አደፋፍሮ ከቦታው እንዳይነሱ አድርጎ በማቆየቱ ምክንያት ጦርነት ተከፍቶ ከሀያ በላይ ሰዎች እንዲሞቱ ስላደረገ በሙግቱ ጊዜ ከሺያጭ ተርፈው የነበሩትን ከብቶች ቦረናዎች ዘርፈው ስለወሰዱበትና በ1957 ዓ.ም. በመስከረም ወር በግልጽ ወደ ሺፍትነቱ ተሰማራ። ዋቆ ወደሽፍትነት ሲሰማራ አብሮ ይዟቸው ጫካ የገባቸው ሰዎች እየተሻገሩ የቦረናዎችን መሬት በመያዛቸው በጠቅላይ ግዛቱ እንዲለቁ ታዝዘው ቅሬታ የፈጠረባቸውን አንዳንድ የሶማሌ ጎሳ አባላት ጭምር ይዞ ነው።
በመስከረም ወር 1957 ዓ.ም. የዋቆን መሸፈት የሰማው የሶማሌ መንግሥት ዋቆ ጉቱ ሸፍቶ ከተቀመጠበት ገናሌ ወንዝ ድረስ መሐመድ ሰላ የተባለውን የመሪሃን ጎሳ የሆነ ሰው ልኮ ወደ ሶማሌ መጥቶ የፈለገውን ያህል የጦር መሳሪያ ወስዶ በጦር የወጉትን የቦረና ጎሳዎች እንዲወጋና መሀል ባሌ ድረስ ገብቶ ያሻውን እንዲዘርፍ ማደባፈሪያ ሰጠው። ዋቆም የመጣለትን ልመና ተቀብሎ ወደ ሱማሌ ገብቶ ከሱማሌ መንግሥት መጀመሪያ አርባ ሁለት፤ ለሁለተኛ ጊዜ አምስት መቶ፤ ለሶስተኛ ጊዜ ደግሞ ከስድንስ መቶ በላይ ጠመንጃ፣ አስምት ሞርታርና ሁለት ባዙቃ ከነ ሙሉ ጥይቱና አሰልጣኝ መኮነኖች ላከለት።
በመቀጠል የሱ ግብረ አበሮች የሆኑት አደም ጂሎና አልዬ ጭሪ ወደ ሲማሌ ሄደው ሶስት መቶ ጠመንጃ ተቀብለው እንዲመጡ አደረገ። ከዚህ በኋላ አደም ጂሎ ብቻውን ሄዶ አራት መቶ ጠመንጃና ልኩ ያልታወቀ ፈንጂ ተቀብሎ ወደ ዋቆ እዝ ተመለሰ። ለሶስተኛ ጊዜ ዋቆ ሎጉ የሚባል ግብረ አበሩ ሁለት መቶ ሰባ ጠመንጃና አምስት ሌጀራ መትረየስ ከሶማሌ መንግሥት ተቀብሎ ተመለሰ። የሶማሌ መንግሥት ይህንን ሁሉ ትጥቅና ስንቅ ለዋቆ ጉቱና ግብረ አበሮቹ ያስታጥቅ የነበረው በባሌ ጠቅላይ ግዛት ለሚያካሂዱት የወረራ ዘመቻው ነበር። እነ ዋቆ የሶማሌ መንግሥት የሚሰጣቸውን መሳሪያ የሚረከቡት ሱማሌ ግዛት ውስጥ ሊክ ከሚባለው ቦታ እየሄዱ ከጀኔራል አፊያ እጅ ነው። ከሶማሌ ግዛት እየተነሳ በጊዜው ወደ ኢትዮጵያ እየገባ እነዚህና ሌሎችን ትጥቆች የሶማሌ መንግሥት እንደሚሰጣቸው በማባበል እነዋቆን ወደ ጀኔራል አፊያ ይልካቸው የነበረው ከፍሲል ስሙ የተጠቀሰው መሐመድ ሳላ ነው። እንግዲህ! ለአርነትና ለነጻነት እንደተካሄደ ትግል ተቆጥሮ ላለፉት አርባ አራት አመታት ሲነገርለት የነበረው የነዋቆ አመጽ የቦረና ጎሳዎችን በመውጋት የሶማሌ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ያለውን የግዛት ጥያቄውን ለማሳከት በዚህ መልክ በቅንጅት ይሰራ በነበረበት ወቅት በመሳሪያነት ያገለገሉበትን ዘመን ነው።
ሱማሌ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት የጀመረችው በ1956 ዓ.ም. መሆኑና በዚህም ጦርነት ድል ሁና መመለሷ ቢታወቅም ዋቆ ጉቱ ኢትዮጵያና ሱማሌ በግልጽ መጣላታቸውን አይቶ የቀረበለትን ጥያቄ ሳያመነታ በመቀበል  የሶማሌ መንግሥት መሳሪያ ለመሆን ግብረ አበሮቹን ይዞ የገባው  በ1957 ዓ.ም. ነው። በሌላ አነጋገር በ1957 ዓ.ም. የተካሄደው የኢትዮጵያና የሶማሊያ ጦርነት ባይፈጠር ኖሮ ዋቆ የሚባል በታሪክ የሚወሳ አይኖርም ነበር። ዋቆ የሚባል ስም በታሪክ ሊነሳ የቻለው ሶማሊያ የኢትዮጵያን ግዛት ወርራ ከያዘች በኋላ ከኢትዮጵያ ግዛት በኃይል ተሸንፋ እንድትወጣ ስትገደድ የኢትዮጵያ ጠላትነቷ ጥያቄ ውስጥ ባለመውደቁ እሷን ተገን አድርጎ ጦርነት በመክፈቱ ነው። በፊት ለፊት ጦርነት የተሸነፈው የሶማሌ መንግሥት እነ ዋቆን በደስታ ተቀብሎ በሱ ስር ያሉትን የቦረና የኦሮሞ ጎሳዎችን ለመውጋት የሸመቁትን ግብረ አበሮቹን ሁሉ ስለጦር መሳሪያ አፈታትና አገጣጠም እንዲሁም ስለፈንጂ አጠማመድ ካሰለጠነ በኋላ «የምዕራብ ሶማሊያ ነጻነት ግንባር» የሚል ድርጅት መስርቶላቸው ዋቆ ጉቱን «የምዕራብ ሶማሊያ ጀኔራል» ብሎ የግንባሩ መሪ አድርጎ ማዕረግ ያደለው ሲሆን በስሩ የተሰየሙት አመጸኞች ደግሞ ሻለቃ የሚል ማዕረግ ተሰጣቸው።
ልብ በሉ! ዋቆ ጉቱ «ጀኔራል ዋቆ» እየተባለ የሚጠራውና አዲስ አበባ ውስጥ የጀኔራል ዋቆ ጉቱ ትምህርት ቤት ተብሎ የተሰየመለት የሶማሌ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ያለውን የግዛት ባለቤትነት ጥያቄ ለማስፈጸም «የምዕራብ ሶማሊያ ነጻነት ግንባር» የሚል ድርጅት ፈጥሮለት የዚህ ድርጅት መሪ አድርጎ ሲሾመውና የወራት የተሰጠውን ስልጠና አጠናቅቆ «የምዕራብ ሶማሊያ ነጻነት ግንባር»ን እየመራ ወደ ኢትዮጵያ ለግዴታ ሲሰማራ በተሰጠው ማዕረግ ነው።
ለወትሮው ጀኔራልነት ከተራ ወታደርነት እስከ ከፍተኛ ኃላፊነት፤ ከልጅነት እስከ አዛውንትነት ከአገር ጠላት ጋር ሲዋጉና ሲተናነቁ ለኖረ፣ እግሩን ለጠጠር፣ ግንባሩን ለጦር ለሰጠ የአገር ባለውለታ አገር የምትሰጠው ዋዕረግና የሚሰጥና የአገርን ዳር ድንበር ለማስከበር ለተከፈለ ማስዕዋትነት መታሰቢያነት ማሳያ ተደርጎ የሚቀርብ ነበር። እነ ዋቆ ግን ጀኔራል እየተባሉ የሚጠሩት ኢትዮጵያ በሰጠታቸው ማዕረግ ሳይሆን የኢትዮጵያ ጠላት አገር ያላትን የግዛት ጥያቄ በእጃዙር ለማግኘት ስትል «የምዕራብ ሶማሊያ ነጻነት ግንባር» መስርታ ላሰማራቸው ቅጥረኞች በሰጠታቸው ማዕረግ ነው። ጀኔራል ጃገማ ኬሎ ዋቆ ጉቱን በማረኩት ወቅት ዋቆ ይዞት የተገኘው የሶማሊያ መንግሥት የሰጠው ባለ ማኅተም መታወቂያ በእንግሊዝኛ ቋንቋ «General of Western Somalia» ይላል። ለዚህ የምዕራብ ሶማሊያ ጀኔራልነቱ ነው እንግዲህ  አዲስ አበባ ውስጥ «ጀኔራል» ተብሎ ትምህርት ቤት በስሙ የተከፈተለት።
እንደ ዋቆ ሁሉ ሞቃድሾ ቤተ መንግሥጥ የሰለጠነው ወያኔም የትግራይ ሪፑብሊክን ለመመስረት ጫካ ከገቡ በኋላ ሻዕብያን ተከትለው አዲስ አበባ ሲገቡ ኢትዮጵያን ሲያደሙ ለኖሩ የትግራይ የገበሬ ሽፍቶች  «ጀኔራል» ሲል የሚል ማዕረግ ያደለው በተመሳሳይ እሳቤ ነው። እነ ዋቆ ጀኔራል የተባሉበትና እነ ሳሞራ ጀኔራል የተባሉት አገልግሎት አንድ አይነት ነው። እነ ዋቆ ኢትዮጵያን ይወጉ የነበረው በምስራቅ ነው። እነ ሳሞራ ደግሞ ኢትዮጵያን ይወጉ የነበረው በሰሜን ነው። ሁለቱም ጀኔራል የተባሉት ከተራ ወታደርነት እስከ ከፍተኛ ኃላፊነት፤ ከልጅነት እስከ አዛውንትነት ከአገር ጠላት ጋር  ሲዋጉና ሲተናነቁ ስለኖሩ አይደለም። ጀኔራል የተባለው ዋቆ ጉቱም ሆነ ጀኔራል የተባሉት የፋሽስት ወያኔ የገበሬ ሽፍቶች ጀኔራል የተባሉት ለኢትዮጵያ ስለተዋጉ ሳይሆን ኢትዮጵያን ስለወጉ ነው። ኢትዮጵያን ሲወጉ ኖረው ለኢትዮጵያ የተዋጉላትን ማዕረግ የተላበሱት አገርና መንግሥት ስለሌለን ነው። ይህ ተግባር  የየካቱት 12 መታሰቢያ ሐውልት አፍርሶ በቦታው  ለፋሽስቱ መሪ ቤንቶ ሞሶሌኒና ለሩዶልፎ ግራዚያኑ ከማቆም አይተናነስም።
ወደነዋቆ ታሪክ ስንመመለስ ዋቆ ራሱ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በ1965 ዓ.ም. በተናገረው ቃል መሰረት ወደ ጫካ ከገባበው ጊዜ ጀምሮ በ1962 ምሕረት ጠይቆ በሌተናት ጀኔራል ጃገማ ኬሎ አማካኝነት ምሕረት ተደርጎለት እስከገባበት ድረስ በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ላይ ከፍያለ በደል ሲፈጽም የኖረ ሰው መሆኑን ስላመነ ከአገልግሎት ተቆጥሮ ጀኔራልነት ሊያሰጥ የሚያስችል ተግባር እንደሌለው ራሱ ምስክር ነው።
እንግዲህ ዋቆ ጉቱ ሸፍቶ በባሌ ጫካ ገብቶ ቦረናዎችን የወጋውና የሱማሌን መንግሥት የተስፋፊነት ፍላጎት ለማስፈጸም የረጋውን የኢትዮጵያ ፀጥታ ሲያደፈርስ የነበረው ከዚህ በላይ በተገለጠው ምክንያት እንጂ የኦሮሞ ብሔርተኞቹ እነ ዐቢይ አሕመድ እንደሚሉት የባሌ ሕዝብ በዐፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ተበድሎ ለሕዝቡ በደል ተቆርቋሪ ሆኖ አይደለም።
ባጭሩ ዋቆ ጉቱ የሱማሌ መንግሥት ቅጥረኛ ሁኖ በሀገሩ ላይ ለመዝመት የበቃው «የቦረናዎችን እርስት ይዘህ ለመኖር አይገባህም፤ ወደርስትህ ገብተህ ተቀመጥ» ተብሎ ሲበየንበት የቦረናዎችን ርስት ቀምቼ ካልተቀመጥሁ ብሎ በመቃወም ከቦረናዎች ጋር ጦር ገጥሞ ሲሸነፍ እነሱን ለመውጋት ሲል ነው ጫካ የገባው። ግብረ አበሮቹ እነ አደም ጂሎ፣ አልዩ ጭሪና ዋቆ ሌጉ ደግሞ የሸፈቱት በዋቆ ጉቱና ከሶማሌ መንግሥት ተወክሎ በመጣው በመሐመድ ሳላ ስብከት ተስበው ወዲያውም የጦር መሳሪያ ለማግኘት ሲሉ ነው። ከዚህ ውጭ በባሌ ምድር የወቅቱ ኢትዮጵያ መንግሥት ሕዝባዊ በደል አድርሶ እነ ዋቆ ያንን ለመቃወም የመሩት አመጽ የለም። ሆኖም ግን የምንኖርበት ዘመን የሚያኮሩን የነበሩ ነገሮች ሁሉ ተዋርደው፤ ልናፍርባቸው በሚገቡ ወራዳ ተግባሮች የምንኮራበት ዘመን ስለሆነ እንጂ ከፍ ሲል እንዳየነው የዋቆ ተግባር እንኳን ሐውልት ሊቆምለት ቀርቶ በሀገር ክሕደትና በፈጃቸው ቦረናዎች ነፍስ መጠየቅ የነበረበት ሰው ነበር። ከዚህ ውጭ የዋቆ ጉቱ ታሪክ የነጻነቱ አንዱ አካል የሆነውን የቦረናን የመሬት ባለቤትነት መብት ለመግፈፍ  እንጂ  ለሕዝብ መብት ለመታገል ጫካ እንድወረደ የሚያሳይ አንዳች ታሪክ የለውም።
ቀደም ብሎ የቀረበው ታሪክ ምንጮች  የሲ.ኤይ.ኤው ሰላይ ፖል ሄንዚ እ.ኤ.አ. በ1985 ዓ.ም. «Rebels and Separatists in Ethiopia: Regional Resistance to a Marxist Regime» በሚል ያሳተመው የራንድ ኮርፖሬሽን ሪፖርት፣ በሪሁን ከበደ በ1993 ዓ.ም. ያሳተሙት «የዐፄ ኃይለሥላሴ ታሪክ» መጽሐፍ፣ ጆን ማርካኪስ እ.ኤ.አ. በ1987 ዓ.ም. «National and Class Conflict in the Horn of Africa» በሚል ያሳተመው መጽሐፍ፤ ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ በ2006 ዓ.ም. ያሳተመው «እኛና አብዮቱ» የሚለው መጽሐፍ፣ ፍቅረ ማርቆስ ደስታ «ጃገማ ኬሎ የበጋው መብረቅ (የሕይዎት ታሪክ) በሚል ጀኔራል ጃገማ ኬሎን ቃለ መጠይቅ አድርጎ በ2001    ያሳተመው የታሪክ ማስታወሻ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበረው አበራ ቀጸላ ዋቆ ጉቱን አዲስ አበባ ውስጥ ቃለ መጠይቅ አድርጎ «The Rebellion in Bale (1963–1970)»  በሚል በ1963 ዓ.ም. ያዘጋጀው የዲግሪ ማሟያ ወረቀትና ማሪናና ዴቪድ ኦቶዋይ የተባሉ ተመራማሪዎች «Ethiopian Empire in Revolution» በሚል  እ.ኤ.አ. በ1978 ዓ.ም. ያሳተሙት መጽሐፍት ናቸው።
Filed in: Amharic