>

ጽሑፉ ስለ እስራኤል አይደለም! ስለ ኦሽዊትዝ ካምፕ መዘጋትም አይደለም! ስለ እኛ ነው!  (ልኡል አምደጽዮን ሰርጸድንግል)

ጽሑፉ ስለ እስራኤል አይደለም! ስለ ኦሽዊትዝ ካምፕ መዘጋትም አይደለም! ስለ እኛ ነው! 

 

 

ልኡል አምደጽዮን ሰርጸድንግል
ችግር በተፈጠረ ቁጥር መጮህና ማልቀስ ይሰለቻል! ለምኞት ጊዜ አላባክንም! የታገቱትን ተማሪዎች ጉዳይም ከላይ በፃፍኩት አውድ ተመልከተው! ዘላቂ መፍትሄ ካልፈለግህ ነገ ደግሞ እገታው ከጥቂት ተማሪዎች ወደ ሕዝብ ይሸጋገራል፡፡ ያኔም ‹‹ኢትዮጵያ አትፈርስም … ጠባቂዋ ከላይ ነው!›› እያልክ እንደምንገናኝ በፍጹም አልጠራጠርም…
ናዚ ጀርመን በርካታ ሰዎችን በተለይም አይሁዶችን ሲያሰቃይበት የነበረውና ከ1.1 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን (960ሺ አይሁዶች፣ 74ሺ አይሁድ ያልሆኑ ፖላንዳውያን፣ 21ሺ ሩማንያውያን፣ 15ሺ የሶቭየት ኅብረት ምርኮኛ ወታደሮች እንዲሁም 15ሺ ሌሎች አውሮፓውያን) የገደለበት ‹‹የኦሽዊትዝ ካምፕ (Auschwitz Concentration Camp)›› ነፃ የወጣው/የተዘጋው/ ከዛሬ 75 ዓመታት በፊት (ጥር 18 ቀን 1937 ዓ.ም) ነበር፡፡
– – –
የኦሽዊትዝ ካምፕ ነፃ የወጣበት/የተዘጋበት 75 ዓመት መታሰቢያም በስፋት ትንሽ (ጠባብ) በጥበብና በኃይል ግን ታላቅ በሆነችው በአይሁዶች አገር በእስራኤል እየታሰበ ነው፡፡ ኢየሩሳሌም ላይ በተከናወነው የዘንድሮው መታሰቢያ መርሃ ግብር ላይ ከተገኙት የአገራት መሪዎች መካከል አንዱ ያን ዘግናኝ ጥፋት በአይሁዶች ላይ ያደረሰችው የጀርመን ፕሬዝደንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማዬር ናቸው፡፡ ፕሬዝደንቱ በመታሰቢያ ዝግጅቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ‹‹ … ያ ድርጊት በፍጹም መደገም የለበትም! ከአይሁዳውያን ጎን እንቆማለን …!›› ብለዋል፡፡
– – –
አሜሪካ በወግ አጥባቂውና በነገር አዋቂው ምክትል ፕሬዝደንቷ በማይክ ፔንስ፣ ሩስያ በኃይለኛውና በአስፈሪው ፕሬዝደንቷ በቭላድሚር ፑቲን፣ ታላቋ ብሪታኒያ በንግሥቷ ታላቅ ልጅና በዌልሱ ልዑሏ በልዑል ቻርለስ … ተወክለው ኢየሩሳሌም ድረስ ሄደው ‹‹ … እስራኤል ሆይ ከጎንሽ ነን …!›› ብለዋታል፡፡ የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ደግሞ በኢየሩሳሌሙ ዝግጅት ላይ ከመገኘታቸው በተጨማሪ ፓሪስ ውስጥ ያለውንና የታደሰውን የዘር ጭፍጨፋው ሰለባ የሆኑ ሰዎች ስም ያለበትን ግድግዳ (Wall of Names) መርቀው ከፍተዋል፡፡
– —
ዛሬ እስራኤላውያን የዓለም ኃያል ሆነዋል፡፡ እስራኤላውያን በናዚ ጀርመንና በሌሎች ጠላቶቻቸው ከደረሰባቸው ጥቃትና መከራ ሁሉ ትልቅ ትምህርት ወስደዋል፡፡ የናዚ ጀርመን/ሂትለር ከስልጣን መባረርና መሞት አላዘናጋቸውም! ‹‹ናዚ ስለወደቀ፣ ሂትለር ስለሞተ … ከዚህ በኋላ መገፋት፣ መበደል፣ መሰቃየትና መሞት አይገጥመንም፤ አገር አልባ አንሆንም፤ ዘር ማጥፋት አይፈጸምብንም … ብለው በፍፁም አልተዘናጉም! በ ፍ ጹ ም! ምክንያቱም ማሰብ የሚችል ጭንቅላት ስላላቸው!
– – –
ግን እስራኤላውያን ይህን ሁሉ ማሳካት የቻሉት በምኞትና በጸሎት አይደለም! ‹‹እስራኤል አትፈርስም›› በሚል የጅል ስብከትም አይደለም! ደቪድ ቤንጎሪያንን፣ ሞሼ ዳያንን፣ ጎልዳ ሜየርን፣ ይስሃቅ ራቢንን፣ ቤንጃሚን ኔታንያሁን … በማምለክና ‹‹አሻጋሪያችን/አዳኛችን/የምትታደገን አንተ(ቺ) ብቻ ነህ(ሽ)፤እንደፈለግህ(ሽ) ሁን(ኚ)›› በሚል የሞኝ ዘፈንም አይደለም! ትናንት የደረሰባቸው ውርደትና መከራ ምንጩ ምን እንደሆነ በሚገባ አስበውና አሰላስለው ዘላቂ መፍትሄ መፈለግ ስለቻሉ ነው!
– – –
ቢሊየነሩና የልዕለ ኃያላኗ አሜሪካ መሪ ዶናልድ ትራምፕ ‹‹ኢየሩሳሌም የማትከፋፈል የአንቺ ብቻ ዋና ከተማሽ ናት›› ብለው የአገራቸውን ኤምባሲ ከቴል አቪቭ ወደ ኢየሩሳሌም ያዛወሩላት፣ የእስራኤል ልጆች የሆኑት አይሁዶች ላይ ያን ሁሉ መከራ ያደረሰችው የአንጌላ ሜርክሏ ግዛት፣ የአውሮፓ ኃያሏ ጀርመን ‹‹ … ያ አሳፋሪ ድርጊት በፍጹም መደገም የለበትም! ከአይሁዳውያን ጎን እንቆማለን …!›› ብላ የተፀፀተችላት፣ ሰላዩና ጦረኛው የሶቪየት ሰው ቭላድሚር ፑቲን ወዳጅነቷን አጥብቀው የሚፈልጓት፣ በስለላ፣ በጦር መሳሪያ፣ በቴክኖሎጂ … የዓለም ቁንጮ የሆነችው … ትናንት ልጆቿ አገር አልባ ሆነው በየደረሱበት ሁሉ ተይዘው እየተጎተቱ ወደ ማሰቃያ ካምፖች ተወስደው በግፍ ሲገደሉባት የነበረችውና ዛሬ ከዚያ ሁሉ መከራዋ ተምራ ራሷንና ልጆቿን አስከብራ፣ በጠላቶቿ ተፈርታ፤በወዳጆቿ ተከብራ ያለችው፣  በስፋት ትንሽ (ጠባብ) በጥበብና በኃይል ግን ታላቅ የሆነችው … እስራኤል !!!
– – –
ምናልባት ከተግባባን ዛሬም ልድገምልህ አንተ ያልታደልክ ሕዝብ! … 
በየቀኑ ማልቀስህ፣ አንዱ ችግርህ የተፈታ ሲመስልህ ሌላውን በደል ሁሉ ረስተህ ከገዳዮችህ ጋር መጨፈርህ፣ ‹‹ኢትዮጵያ አትፈርስም … ጠባቂዋ ከላይ ነው›› እያልክ በምኞት መሸወድህ፣ የሆነውንና እየሆነ ያለውን ዐይተህ ዕንዳላየህ፤ሰምተህ እንዳልሰማህ እያለፍክ እንዲሆን የምትፈልገውን ባዶ ምኞትህን በባዶ መኖርህ … ‹‹አትፈርስም፤ጠባቂዋ ከላይ ነው›› ያልካት አገር ይኸው ዛሬ ምን እንደሆነች ተመልከት (ለነገሩ በየትኛው ልብህና ዓይንህ ታየዋለህ?)
– – –
ችግር በተፈጠረ ቁጥር መጮህና ማልቀስ ይሰለቻል! ለምኞት ጊዜ አላባክንም! የታገቱትን ተማሪዎች ጉዳይም ከላይ በፃፍኩት አውድ ተመልከተው! ዘላቂ መፍትሄ ካልፈለግህ ነገ ደግሞ እገታው ከጥቂት ተማሪዎች ወደ ሕዝብ ይሸጋገራል፡፡ ያኔም ‹‹ኢትዮጵያ አትፈርስም … ጠባቂዋ ከላይ ነው›› እያልክ እንደምንገናኝ በፍጹም አልጠራጠርም! ምክንያቱም አንተ ያው ነህ! የማትለወጥ … ከስህተትህ የማትማር … ለቅሶን፣ ሐሜትን፣ ጊዜያዊ እርካታን፣ ተንኮልን፣ ማሽቃበጥን፣ ሴራን፣ ከእውቀትና ከጥበብ መራቅን … ብሔራዊ መገለጫዎችህ አድርገህ ለ3000 ዓመታት ያህል መልካቸውን እየቀያየሩ በሚመጡ ገዢዎች የጭቆና ቀንበር ስር ወድቀህ ስትረገጥ የኖርክ፣ ዛሬም የምትረገጥ ነገም ለመረገጥ ፈቃደኛ የሆንክ … ‹‹ፍጡር›› ነህ!
– – –
በሚቀጥሉት ቀናት ‹‹የታገቱትን ተማሪዎች አስለቅቀናል›› ተብሎ በገዢዎችህ ከተነገረህ በኋላ ሁሉንም ነገር ትረሳውና ወደተለመደው ማሽቃበጥህ/ማጨብጨብህ ትመለሳለህ!
– – –
ችግር በተፈጠረ ቁጥር መጮህና ማልቀስ ይሰለቻል! ለምኞት ጊዜ አላባክንም! (3X)
Filed in: Amharic