>

ቄሮ እና ኤጄቶ ከአማራው ክልል ሰልፍ ምን ይማራሉ? (ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ)

ቄሮ እና ኤጄቶ ከአማራው ክልል ሰልፍ ምን ይማራሉ?

 

ዶ¦ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ

 

ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ

 

 

ፍትህ ሲጓደል፣ ነፃነት ሲገደብ፣ እና መንግስት ኢ-ዲሞክራሲያዊ ሲሆን የማህበረሰቡን የውስጥ ብሶት፣ ቁስልና ምሬት በሰላማዊ ሰልፍ መግለፅ በዘመናዊ የመንግስት አስተዳደር የሚታይ ሁነት ነው፡፡ ከጥር 19 እስከ 24፣2012 ዓ.ም. ባሉት ቀናት በበርካታ የአማራ ክልል ከተሞች (እንዲሁም በውጭ አገራት በሚኖሩ ኢትዮጲያውያን) ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል፡፡ የእነዚህ ሰላማዊ ሰልፎች ዋና ምክንያት በደንቢዶሎ ዩኒቨርስቲ በታገቱ የአማራ ተወላጅ ተማሪዎች ያሉበትን ሁኔታ የሚጠይቅ ነበር፡፡

ሰላማዊ ሰልፉ እና በሰላማዊ ሰልፉ የተንፀባረቁ ጥያቄዎች ወቅታዊና ተገቢ ነበሩ፡፡ ሰላማዊ ሰልፉ ፍፁም ሰላማዊ እና በአማራው ህዝብ ላይ ሞልቶ የፈሰሰውን የግፍ መጠን የሚያሳይም ነበር፡፡ የሰላማዊ ሰልፉ ታዳሚዎች በጨዋ መልክ ጥያቄያቸውን በሥልጣን ላይ ላለው ለመንግስት አቅርበው፣ ብሶታቸውን እና ቅሬታቸውን ገልፀው  ወደ ቀያቸው በሰላም ተመልሰዋል፡፡ በሰላማዊ ትግል ሂደት ጥያቄዎችን እና ቅሬታን ሰላማዊ በሆነ ሰልፍ ማሳወቅ ስልጡን የሆነ ማህበረሰብ አንዱ መገለጫ ነው፡፡ በአማራው ህዝብ ላይ የሚፈፀመውን መፈናቀል፣ ሞት እና ሰቆቃ ለመግታት መደራጀት እና ቅሬታን በተከታታይ ሰላማዊ ሰልፍ መግለፅ ሊቀጥል ይገባል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በሰላማዊ ሰልፉ ወቅት በሁሉም ከተሞችና ወረዳዎች ውስጥ ምንም ዓይንት የግልሰቦችንና የመንግሥታዊ ተቋማትን ንብረት የማውደም አዝማሚያ አልተከሰተም ነበር፡፡ አንድ ሰላማዊ ሰለፍ እና ስልጡን የሆነ አካሄድ ምን መምሰል እንዳለበት ለቄሮና ለኤጄቶ (እንዲሁም ለመሰሎቻቸው) አስተማሪ የሆነ ክስተት ነበር፡፡ በቅርቡ በኦሮሚያ እና በሀዋሳ በተካሄዱ የተቃዉሞ ሰልፎች ቄሮ እና ኤጄቶ  ሰላማዊ እንቅስቃሴዎችን ቸል ብለው ወደ ውደመትና ግድያ ተግባራት ሲገቡ እንደነበር እና በኦሮሚያ ከ86 በላይ ሰዎች እና በሀዋሳ ደግሞ በርካታ ኢትዮጲያውያን እንደተቀጠፉ የቅርብ ጊዜ ትዝብታችን ነው፡፡ ስለዚህ ስንቃወምም ሆነ ስንደግፍ እንደ አማራ ክልል ወገኖቻችን ምክንያታዊ እንሁን፤ ሰልፍም ወይም ተቃዉሞ ስንወጣ ሰላማዊ መሆን ይጠበቅብናል፡፡ መንገድ መዝጋት፣ ዜጎችን መግደል ወይም በዜጎች ላይ አካላዊ ጉዳት ማድረስ፣ ማፈናቀል፣ ንብረት ማውደም፣ በመንግስት  ወይም በህዝብ ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈፀም ዘመኑን ያልዋጀ፣ ለዘመኑ የማይመጥን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ነው፡፡ 

እውቀት ከትክክለኛ የመረጃ ምንጭ  ይገኛል፤ እውነት ዕዳ የሆነባቸው ሰዎች እና የሀሰት ትርክትን ለሚፈለፍሉ ቅጥረኞች እውነት ቦታ የላትም፡፡  ስለዚህ ወጣት ኢትዮጲያውያን በደመ-ነፍስ መንቀሳቀስ፣ በጋራ መደገፍ፣ በርካሽ አሉባልታ እና በሀሰት ትርክት መመራት ፍፁም የሰው ባህሪ እንዳልሆነ በመረዳት ሰላማዊው ከሆነው ከአማራ ክልል ሰላማዊ ሰልፍ  በርካታ ቁም ነገሮችን መረዳት የሚያስችል ግብዓት ያገኛሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ 

የማይናወጡትን ሰላማዊ ሰልፎችን በሁሉም የአገራችን ክፍሎች አከናውነን አገዛዞቹ ተገቢውንና ፍትሐዊ እንቅስቃሴዎቻቸውን በተጠያቂነት መንፈስ እንዲያከናውኑ ለማድረግ የበኩላችንን እንወጣ፡፡

Filed in: Amharic