>
5:14 pm - Wednesday April 20, 4698

መንግሥትን እንደ በርጩማ ...! (አሰፋ ሃይሉ)

መንግሥትን እንደ በርጩማ …!

 

 

አሰፋ ሃይሉ
መንግሥት ለዜጎቹ የተመቸ እንዲሆን በሶስት የተለያዩ እግሮች ተደግፎ መቆም አለበት።
አንደኛው እግሩ ህጎችን የሚያወጣው ፓርላማ ነው። ይሄ እግር በሀገሩ ያሉ ዜጎችን ሁሉ የተለያዩ ፍላጎቶች ይዞ የቆመ እግር ነው። በውስጡ የዜጎች ሁሉ ድምፅ አለ። እነዚያ ድምጾች ተወያይተውና ተከራክረው ነው ለሁሉም የሚበጁ ህጎች የሚፀድቁት።
ሁለተኛው የመንግሥት እግር በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የወጡለትን ህጎች የሚያስፈፅመው አካል ነው። ይሄም እግር በአሸናፊ ፓርቲዎች፣ በባለሙያዎችና በፀጥታ ኃይሎች የተቀናጀ የመንግሥት አንቀሳቃሽ እግር ነው። ይህ እግር በህዝብ ለመወደድ (እና ለመመረጥ) ሲል በቻለው መጠን ዜጋው ቢሆንለት ደስ የሚለውን ሁሉ ያደርጋል። ህጎችን ያስከብራል። የዜጎችን ደህንነት ያስጠብቃል። ሀገሪቱን ዕለት በዕለት ለዜጎች ጠቃሚ ወደሆነ አቅጣጫ ይመራል።
ሶስተኛው የመንግሥት እግር ደሞ ፍርድ ቤት ነው። የፍርድ ቤት ዳኞች በሙያቸውና ገለልተኝነታቸው እየተመዘኑ በመጀመሪያው እግር (በፓርላማው) ዳኝነታቸው ፀድቆ ይሾማሉ። ፍርድ ቤቶች የዜጎችን መብቶች ያስጠብቃሉ። ተበደልኩ የሚልን ቅሬታ ሰምተው የፍትሕን ህመም ያክማሉ። ግዴታውን ባልተወጣ ተከሳሽ ላይ በሃቅና በግልፅ ችሎት መርምረው ብያኔ ይሰጣሉ። በሁለቱ እግሮች የተጣመመን እያቃኑ ይተረጉማሉ። ከመስመሩ የወጣን ያርቃሉ። ሚዛናዊነት መለያቸው ነው።
በብዙ የዓለማችን ሀገራት የመንግስት ገለልተኛ የሲቪል ሠራተኞችን የሚያስተዳድረው የሀገሪቱ የሰው ሀይል እንደ ተጨማሪ ራሱን የቻለ እግር፣ የመንግሥትን ሥህተቶችና ሸፍጦች በንቃት እየተከታተሉ የሚያጋልጡ ሚዲያዎች ደግሞ በበኩላቸው እንደ አምስተኛ የመንግሥት እግርም ተደርገው ይቆጠራሉ። እግሮቹ በየራሳቸው የተለያየ አቅጣጫ ቆመው መንግሥትን እስካቆሙ ድረስ መብዛታቸውና የትኩረት አቅጣጫቸው የተለያየ መሆኑ መንግሥትንም ዜጎችንም ይጠቅማቸዋል እንጂ ጉዳት አያመጣባቸውም።
ሁሉም እግሮች በአንዱ እግር አቅጣጫ ብቻ ተደራርበው ከቆሙ ግን በቃ መንግሥት ሚዛኑን ስለሚያጣ ተደላድሎ አይቀመጥም። ለዜጋውም የተደላደለ መቀመጫ አይሆንም።
የሥልጣን ክፍፍል በሌለበትና ሁሉም የመንግሥት እግሮች ከአንዱ ወደ ሌላው አቤት የሚባልበት ዕድል በሌለበት፣ ወይም ዋጋቢስ በሆነበት ሀገር ግን –  መንግሥት የሁሉም ዜጎቹ ሣይሆን የሆኑ ተመራርጠው የተቧደኑ ጉልበተኛ ቡድንተኞች መፈንጪያ ይሆናል።
ያ ከሆነ ሁሉም የመቀመጫው እግሮች በአንዱ አቅጣጫ ብቻ ተነባብረው ቆሙ ማለት ነው። ያ ማለት ደግሞ መቀመጫው ሚዛኑን ስቶ ወደቀ ማለት ነው። የጊዜ ጉዳይ ብቻ እንጂ የአንድ ቤት የብቻውን ጥቅም እያስጠበቀ መሠንበት አይችልም። ያዘምማል። ይወድቃል። ተቀማጭነታቸውን በእርሱ ያደረጉ ዜጎቹን ሁሉ ለአደጋ ያጋልጣል።
በሀገራችን የሆነውም ያ ነው። ሶስቱም የመንግሥት እግሮች በአንድ ተጠቃልለው እንዲገቡ በመደረጋቸው የተነሣ። የፓርላማው እግር የኢህአዴግ ነው። የአስፈፃሚው እግር የኢህአዴግ ነው። የዳኝነቱ እግር የኢህአዴግ ነው። ሌላ ቀርቶ አራተኛው የመንግሥት እግር – አስተዳደር ቢሮዎችና ተቋማት ሁሉ – የኢህአዴግ ናቸው። አምስተኛውም እግር ያው የኢህአዴግ ነው። ኢህዴግን መደገፍ – ካልሆነ እንደሰሊጥ መርገፍ – ዕጣፈንታው የሆነ የሚዲያ እግር።
እንግዲህ ምን ቀረ? ምን እግር ቀረ?! ምንም!!! ይሄ እውነት እስካሁንም ድረስ አለ። ትንሽ በመሐላቸው ልዩነት የናፈቃቸው ወገኖች አሁን ከመነሳታቸው በስተቀር – አሁንም ከፓርላማው እስከ ብዙሃን መገናኛ ሚዲያው ድረስ – ሁሉም የኢህአዴግ የግሉ መፈንጫ ነው። እንዳሻው ለመፈንጨት የሚያገለግሉት እግሮች ናቸው ሁሉም የመንግሥት እግሮች።
እንግዲህ እነዚህ የመንግሥት እግሮች የሁሉንም ዜጎችና የሁሉንም ፍላጎቶች ይዘው የቆሙ ሆነው ካልተገኙ – እግሮቹ እንደ ሶስት እንደ አራት አምስት ሣይሆን እንደ አንድ እግር ነው የሚቆጠሩትና ደንበርካው ከነአካቴው መውደቁ አይቀርም። እየሆነ ያለውም ያ ነው።
ለውጥ ሲባልም በዚህ 100 ፐርሰንት ፓርላማ እውን የሚሆን አይደለም። ለዚያ ገና ጊዜ አልደረሰም። ለውጡ የመንግሥትን ተዋናዮች የመቀያየር ለውጥ ብቻ ከሆነ ወንበሩንም ይዞ ይወድቃል።
ለውጡ መንግሥት የቆመበትንና የቆመበትን ሥርዓት በዜጎችና ለዜጎች የማድረግ ለውጥ ከሆነ ግን እግሮቹ ፀንተው ይቆማሉ። በማዕበሉ ከመስመጥም ይድናል። የሀገሪቱን ዜጎችም ወደተሻለ የመንፈስ ሠላምና ሥጋዊ መረጋጋት ያደርሳል ( – የሚል ፅኑ ዕምነት አለኝ)።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ።
Filed in: Amharic