>

የልጅ ኢያሱ ሚካኤል 127ኛ ዓመት የልደት መታሰቢያ!!! (ልዑል አምደጽዮን ሰርጸድንግል)

የልጅ ኢያሱ ሚካኤል 127ኛ ዓመት የልደት መታሰቢያ!!!

ልዑል አምደጽዮን ሰርጸድንግል
የንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ አልጋ ወራሽ የነበሩትና ኢትዮጵያን ከ1903-1909 ዓ.ም ‹‹ያስተዳደሩት›› ልጅ ኢያሱ ሚካኤል የተወለዱት ከዛሬ 127 ዓመታት በፊት (ጥር 25 ቀን 1885 ዓ.ም) ነበር፡፡
– – –
የልጅ ኢያሱ ሚካኤል አባት የ‹‹ወሎ››ው ንጉሥ የነበሩት ንጉሥ ሚካኤል አሊ ሲሆኑ እናታቸው ደግሞ ወይዘሮ ሸዋረጋ ምኒልክ ናቸው፡፡ የንጉሥ ሚካኤል አባት የሆኑት ኢማም አሊ አባቡላ፣ የነብዩ መሐመድ 36ኛ ትውልድ ናቸው ስለሚባል፣ ልጅ ኢያሱ ደግሞ የነብዩ መሐመድ 38ኛ ትውልድ ናቸው ተብሎ ይነገራል፡፡ (?)
– – –
የወይዘሮ ሸዋረጋ ምኒልክ እናት ወይዘሮ ደስታ የተባሉ የቤተ-መንግሥት አገልጋይ (ጠጅ ቤት/ክፍል ሰራተኛ) ነበሩ፡፡ ወይዘሮ ሸዋረጋ አድገው የዳግማዊ ምኒልክ ልጅ መሆናቸው ታወቀና የራስ ጎበና ዳጬ ልጅ ለሆኑት ለወዳጆ ጎበና ተዳሩ፡፡ ይህ ትዳር ብዙም ሳይቆይ ፈረሰና (ወሰንሰገድ ወዳጆ የተባለውን ልጃቸውን የወለዱት ከዚሁ ትዳር ነው) በመጨረሻም ንጉሥ ሚካኤል አሊን አገቡ፡፡ ከዚህ ትዳርም የታላቁ ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ አልጋ ወራሽ የነበሩትና ኢትዮጵያን ከ1903-1909 ዓ.ም ‹‹ያስተዳደሩት›› ልጅ ኢያሱ ተወለዱ፡፡
– – –
ልጅ ኢያሱ የተወለዱት በ‹‹ወሎ›› ጠቅላይ ግዛት ተንታ በሚባለው ቦታ ነው፡፡ የክርስትና ስማቸው ደግሞ ‹‹ክፍለያዕቆብ›› ይባላል፡፡ ልጅ ኢያሱ ከመወለዳቸው በፊት የ‹‹ወሎ›› ሸሆች እንዲህ የሚል ትንቢት ተናግረውላቸው ነበር …
‹‹ጌታው መሐመድ አሊ በአዳራሹ ገብተህ በእልፍኝ ብትወጣ፣
ወቀሳ ቢያገኝህ እኔ በጉድ ልውጣ፣
በዳግመኛው እግርህ ሸዋረጋን አምጣ፡፡
ከእመት ሸዋረጋ የሚወለደው ልጅ፣
እምብዛም አይከፋ እምብዛም አይበጅ፡፡››
(‹‹መሐመድ አሊ›› ተብሎ የተጠቀሰው ንጉሥ ሚካኤል ከመጠመቃቸውና በንጉሰ ነገሥት አጤ ዮሐንስ ፬ኛ ክርስትና ከመነሳታቸው በፊት ስማቸው መሐመድ አሊ መሆኑን ለማመልከት ነው … ‹‹እመት›› የሚለው ቃል በዚህ ጽሑፍ ‹‹እመቤት›› የሚለውን ቃል ለመግለፅ ጥቅም ላይ የዋለ ነው)
– – –
ልጅ ኢያሱ በተወለዱ በሦስተኛ ወራቸው እናታቸው ወይዘሮ ሸዋረጋ ምኒልክ ሞቱ፡፡ ሰባት ዓመት እስኪሆናቸው ድረስ ከአባታቸው ጋር በእንክብካቤ አደጉ፡፡ በኋላም በንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ፍላጎትና ጥያቄ መሰረት ወደ አንኮበር ሄደው በሞግዚት አደጉ፡፡ ገና የ12 ዓመት ልጅ ሳሉ እቴጌ ጣይቱ የወንድማቸውን የራስ ወሌ የልጅ ልጅ የሆነችውን ፅጌሮማን መንገሻ ዮሐንስን ድረውላቸው ነበር፡፡
– – –
ታላቁ ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ግንቦት 10 ቀን 1901 ዓ.ም ልጅ ኢያሱ ሚካኤል አልጋ ወራሻቸውና ተተኪያቸው እንደሆኑ አሳወቁ፡፡ ከወቅቱ የኢትዮጵያ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ ነባራዊ እውነታዎች ጋር መግባባት ያልቻሉት ልጅ ኢያሱ፣ በዙፋኑ ላይ ብዙም ሳይቆዩ ከነሕልማቸው ከስልጣናቸው ተሽረዋል፡፡
የልጅ ኢያሱ የአስተዳደር ዘመን ተብሎ የሚጠቀሰው ከ1906-1906 ዓ.ም ያለው ጊዜ ይሁን እንጂ፣ ልጅ ኢያሱ ብቻቸውን (ያለእንደራሴ) ማስተዳደር የጀመሩት እንደራሴያቸው ራስ ተሰማ ናደው ከሞቱ ከ1903 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡
– – –
ለልጅ ኢያሱ በዘመናቸው ከተገጠሙላቸው ግጥሞች መካከል …
ወዴት ነው ያለኸው ኢያሱ አባ ጤና፣
ችጋርግ ሊድለን ነው እባክህ ቶሎ ና፡፡ (በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ የአስተዳደር ዘመን ረሀብ ተከስቶባቸው የነበሩ አካባቢዎች ሰዎች የገጠሙት)
መቅደላ አፋፉ ላይ ያስካካል ፈረሱ፣
የዘጠኝ ንሥጉ ልጅ አስረኛው እሱ፣
እንኳን ሴቶቹና ወንዶቹ ቢነግሱ፣
አልጋውን አይለቅም አባጤና ኢያሱ፡፡ (ልጅ ኢያሱ ዙፋናቸውን ለማስመለስ መቅደላ ላይ ከማዕከላዊው መንግሥት ጦር ጋር በተዋጉበት ጊዜ የተገጠመ)
Filed in: Amharic