>
5:13 pm - Saturday April 18, 4105

የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች አገዛዝ በተለዋወጠ ቁጥር አጋጣሚውን እየጠበቁ በአማራ ላይ የሚፈጽሙት ግድያ፣ ዝርፊያና ማሳደድ! (አቻምየለህ ታምሩ

የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች አገዛዝ በተለዋወጠ ቁጥር አጋጣሚውን እየጠበቁ በአማራ ላይ የሚፈጽሙት ግድያ፣ ዝርፊያና ማሳደድ!

[ክፍል ፩] 
አቻምየለህ ታምሩ
ያለፉት ሰማኒያ የኢትዮጵያ ዘመናት  ውስጥ አንድ በቋሚነት ሲካሄድ የኖረ ነገር ቢኖር የአገዛዝ ለውጥ በተከሰተ  ቁጥር የአማራ ሕዝብ በተለየ መልኩ ሲገደል፣ ሀብቱና ንብረቱ ሲዘረፍ እንዲሁም ቤቱ ሲቃጠል መኖሩ ነው። ፋሽስት ጥሊያን ኢትዮጵያን በወረረና የኢትዮጵያ መንግሥት ተቋርጦ የፋሽስት አገዛዝ በኢትዮጵያ ውስጥ በተተከለ ጊዜ  ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተው  ቀዳሚው ለውጥ  ነፍሰ ገዳዮች ሰላሳ ብር እየተከፈላቸው የአማራ ሕዝብ ማረድ ነበር። ከዚህ የአገዛዝ ለውጥ በኋላ በ1966 ዓ.ም. ደርግ የኢትዮጵያን መንግሥት ገልብጦ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ የተከሰረው ቀዳሚው ለውስጥም በተለይ በደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍል የሚኖሩ ዐማሮች በኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች  እንደ ፋሲካ በግ እየታረዱ መጣላቸው ነበር።
ከደርግ አገዛዝ መወገድ በኋላ የፋሽስት ወያኔ አገዛዝ ወደ ሥልጣን እንደመጣ አሁንም የተከሰተው የመጀመሪያው ለውጥ ዛሬ ኦሮምያ በሚባለው ክልል ውስጥ የሚኖሩ አማሮች አገራችሁ ካልሄዳችሁ ተብለው ከተራራ ላይ መወርወር፤ በእሳት መቃጠል፤ ከነ ነፍሳቸው በማይሞላ  ገደል መጣል፤ በትምህርት ቤት ሳይቀር ነፍጠኝነትን፣ ትምክህትንና በዝባዥነትን ለመስተማር በምሳሌነት  ቀርቦ  እንደ አደገኛ ርዕዮተ አለም  ኦሮሞዎች  ሁሉ  እንዲፋሟቸው  ተዘምቶባቸዋል። ካለፈው አመት ወዲህ ደግሞ የፋሽስት ወያኔ አገዛዝ ሄዶ የዐቢይ አሕመድ የአፓርታይድ  አገዛዝ ሲተካም  ባለፉት ሀያ ሰባት አመታት ውስጥ ስናይ የነበረው በአማራ ገበሬ ላይ ሲካሄድ የኖረ ጭካኔ ደረጃውን ከፍ አድርጎ ከየቤታቸው የራሳቸውን ቆሎ፣ ብርድ ልብስና አንሶላ ይዘው ወደ ትምህርት ገበታቸው የሄዱ አማራ የሆኑ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን  አማራ ጠል ኦነጋውያን እያረዱ፣ እያቃጠሉ፣ እያባረሯቸውና ጠልፈው ወስደው በማይታወቅ ቦታ እያሰቃዩዋቸው ይገኛሉ።
ባጭሩ የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞችና  አማራ የመግደል  የበቀል ፖለቲካን ለኦነግ ያወረሱ አገር በቀል የመንፈስ አባቶቻቸው [ይህ ከዐማራው ጋር ኢትዮጵያዊ ሆነው አብረው የተዋደቁትን ኢትዮጵያዊ  ኦሮሞዎችን አይመለከትም] አገዛዝ በተለወጠ ቁጥር በአማራ ላይ ሲያደርሱት የኖሩትና እያደረሱ ያሉት ግፍና በደል ተነግሮ አያልቅም። በዚህ ጽሑፍ ዐማራው በመካከሉ ያሉትን ኦሮሞዎች የተለመደ ፍቅርና አክብሮቱን ሳይነፍጋቸው የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች ግን  አገዛዝ በተለዋወጠ ቁጥር ሲገድሉ፤ ሲያሳድዱ፤ ሀብቱንና ንብረቱን ሲዘርፉ፤ ቤቱንና ገላውን  በእሳት ሲያቃጥሉ የኖሩበትን የታሪክ ቅብብሎሽ  ከነአብነቶቹ እናቀርባለን።
የፋሽስት ጥሊያኑን ወረራ የዘገበው ጆርጅ ስቲር የተባለው ደቡብ አፍሪካ የተወለደ እንግሊዛዊ ጋዜጠኛ Caesar in Abyssinia እ.ኤ.አ. በ1936 ባሳተመው መጽሐፉ የጦርነቱ ተካፋይ መሆኑ ቀርቶ አገር ለመውረርና ነፃነትን ለመግፈፍ፣ ሕዝብን ለመጨረ፣ ቤተ ክርስቲያንንና መስጅድን ለማቃጠል የመጣውን የጋራ ጠላት የሆነውን ፋሽስት ጥሊያን ለመመከት የዘመተው የኢትዮጵያ አርበኞች ጦር ተሸንፎ ወደ ቤቱ ሲመለስ የጅማው ንጉሥ የአባ ጅፋር ልጅ የሆኑት የአባ ጆቢር አባ ጅፋር ተከታይ አማራውን ብቻ እየለየ በየመንገዱ የፈጀው ዘማች ጥሊያን ከገደለው የማያንስ መሆኑን በዐይኑ ያየውን እውነት ነግሮናል። ለአብነትም ያህል የሰሜኑን ጦር መፈታት የሰማውና  ለመበቀል የነመረውን መንግሥት መውደቅ ሲጠብቅ የነበረው ተበቃይ  በደቡብ ክፍል ዘምተው የነበሩት ራስ ደስታ ዳምጠው፣ ደጃዝማች ነሲቡ ዘአማኑኤል፣ ደጃዝማች በየነ መርዕድ፣ ደጃዝማች መኮነን እንዳልካቸው፣ ደጃዝማች አምደሚካኤል፣ ደጃዝማች አበበ ዳምጠው በባላገሩ ብዙ ችግር እንደደረሰባቸው ይነግረናል።
እንዲሁም የአርሲ ባንዶች ከጣልያን ባንዳ ከደጃዝማች ተክሉ መሸሻ ጋር በመሆን ጎጌቲ ከተባለው ቦታ ላይ ከቦ ደጃዝማች በየነ መርዕድን፣ ደጃዝማች ገብረ ማርያም ጋሪን፣ ፊታውራሪ ሺመልስ ሀቤትን ገድሎ ራስ ደስታ ዳምጠውን አቁስሎ የንጉሠ ነገሥቱን ልጅ ልዕልት ሮማነ ወርቅ ኃይለ ሥላሴን ማርከዋል።  ራስ ደስታ ዳምጠው ከዚሁ ቦታ ቆስለው አምልጠው ቡታጅራ ገብተው ሳለ የሻሸመኔ ባንዶች ተከታትለው ይዘው ለደጃዝማች ተክሎ መሸሻ ስለአቀረቧቸው ደጃዝማች ተክሉ ግራዚያኒን አስፈቅደው ረሽነዋቸዋል።
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመውን በደል ለዓለም መንግሥታት ማኅበር ለማሰማት ኢትዮጵያን ለቀው ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ ባዶሊዮ ገብቶ እስኪረጋጋ ድረስ እነ አባ ጆቢር በዐማራው ሕዝብ ላይ ያደረሱት በደል ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም። በአርሲ የተደረገውን የዘመን ታሪክ የዐይን  ምስክሩ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛና የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ፓር አባል የነበሩት አቶ በሪሁን ከበደ «የዐፄ ኃይለ ሥላሴ ታሪክ» በሚል ባሳተሙት ባለ1333 ገጽ መጽሐፋቸው እንዲህ ይነግሩናል፤
በተለይም በአርሲ ክፍለ ሀገር በጭላሎች አውራጃ ገና ጣልያን ሳይገባ ድል አድርጓል መባሉ እንደተሰማ የአማራውን ቤተሰቦች እንግደላቸው ተብሎ ተመክሮ ከቀጠሮ ሳለ ከዘመቱት አንዱ ግራዝማች ኃይሌ ብሩ የተባሉ ቀድም ብለው  ከቀጠሮ በፊት ደረሱ። የተመከረውን ነገርና የተነገራቸውን ጥንቃቄ አድርገው ሲጠባበቁ ባላገሮቹ  ግራዝማች ኃይሌ ብሩ ከዘመቻው በደህና ተመልሰው መግባታቸውን ስላልሰሙ በቀጠሮው ቀን የአማራ ቤተሰብ ለመግደል መጥተው ጦርነት ከፈቱ። ስለሆነም በግራዝማች ኃይሌ ተመትተው ድል ሆነው ተመለሱ።  ባላገሩ ሊጨርሰው የነበረው ዐማራም ከእርድ ዳነ።
ፋሽስት ጥሊያን ከገባ በኋላ ዐማራውን መጨረስ አለባችሁ ብሎ የአርሲ ባላገሮችን ስላነሳሳቸው ወደ መንዝና  ወደ ተጉለት እያዘመተ ብዙ ዐማራዎች እንዲገደሉ አድርጓል። እንዲሁም ይደረግ የነበረው የፋሽስቱ መሪ የሞሶሎኒ እንደራሴ የነበረው ማርሻል ግራሲያኒ በነበረበት ወቅት ነው። በኋላ ግን በአማራው ላይ የሚደርገው የአገዛዝ ፈሊጥ ስለተቀየረ እሱ ተነስቶ ቪቼሬ ልዑል አማዲኦ ዲ ሳቮያ ዱክ ኦስታ ተሹሞ እንደመጣ የዐማራው እንደፋሲካ በግ በነ አባጆቢርና መሰሎቻቸው መታረድ  እንዲቆም ተደረገ። የዐማራው አንገት መታረድ ቢቆምም አገሩን መልቀቅ ይገባቸዋል ሲሉ የአርሲ ባላገሮች እነ ሐጂ ሁሴንን ነገረ ፈጅ አድርገው ክስ መሠረቱ። የፋሽስት ጥሊያን መንግሥትም የኢትዮጵያን ታሪክ የሚያውቁ ጥሊያኖችን መርጦ ዳኝነት እንዲታይ አደረገ።
በዚህ ጊዜ በአርሲ ለሚገኘው ለዐማራው ሕዝብ ዋና ነገረፈጅ ሁነው እንዲከራከሩ ፊታውራሪ መለስ እሸቱ የተባሉ የአማራ ተወላጅ ግራዝማች በያን አባ ጋሪ የተባሉ የሸሞ ኦሮሞ አርሲ ውስጥ ከጠላት በፊት በሹመት ይኖሩ የነበሩ ተመርጠው ክርክር ተደርጓል። ፊታውራሪ በያን አባ ጋሪ ያቀረቡትም መከራከሪያ  «አገሩ  እርስቱ የኛ ነው፤ ዐማሮቹ ይውጡልን፤ ታላቁ የፋሽስት ጥሊያን መንግሥትም  ሊወጉ የዘመቱና የተዋጉ ስለሆነ  ይቀጡልን» የሚል ነበር። ፊታውራሪ መለስ እሸቱ በበኩላቸው የሰጡት መልስ « ከጋላው በፊት አገሩና እርሥቱን ይዘን የቆየን እኛ ነን፤ ጋሎች የመጡት አሁን ትናንትና ነው፤ ስለዚህ አንዳችን መልቀቅ አለባችሁ ከተባለ መልቀቅ የሚገባን እኛ አይደለንም። ለርሥታችን፣ ለአገራችን ለመንግሥታችን፣ ለነጻነታችን ስንል ብንዋጋ ወንጀል አይሆንብንም» የሚል ነበር።
ዳኝነቱን ለማየት የተቀመጡት ጥሊያኖችም አርሲዎችን «እናንተስ ወደ ጦርነት ዘምታችኋልን ወይስ አልዘመታችሁም?» ተብለው ለተጠየቁት መልስ «አልዘመትንም» ብለው መልስ ሰጡ። በዚህ ጊዜ የመሐል ዳኛው  «እነሱ ማለትም ዐማሮች  ከአርሲ ተነስተው የዘመቱት በእርግጥ ለአገራቸው፣ ለርሥታቸው ብለው ስለሆነ እናንተ አለመዝመታችሁ አርሲ አገራችሁ ባለመሆኑ ስለሆነ አርሲ አገራችሁ አለመሆኑን የሚያስረዳ በመሆኑ ክሳችሁ ውድቅ ተደርጓል» ሲል ፋይሉን ዘግቶ አሰናብቷቸዋል።
ጅማ ፋሽስት ጥሊያን እንደገባ የጅማ ባላባት አባ ጆቢር አባ ጅፋር አንድ የአማራ አንገር ቆርጦ ለአቀረበ ሰላሳ ጠገራ ብር ይከፈለዋል ብሎ ስለአወጀ ሰላሳ የአማራ አንገት ተቆርጦ ቀርቦለታል። በዚህም ምክንያት በዘመኑ በዚሁ ክፍለ ሀገር የነበረው የዐማራው ሕዝብ ሁሉ አንገታችን እየተቆረጠ ከምናልቅ ጫካ ገብተን ብንሞት ይሻላል ብሎ በዘመኑ የጅማ ዙሪያ አስተዳዳሪ  የነበሩት ከንቲባ ጋሻው ጠና ሸሽተው ወደሄዱበት ጫካ ሀብቱን፣ ንብረቱን ሳይቀር በሙሉ ግልብጥ ብሎ ጠቅላይ ገዢው ወደ አሉበት ቦታ ተመመ። በአባ ጆቢር እንዳይታረድ  ከንቲባ ብስራት ጋሻው ጠና ተከትሎ የተመመውን ሕዝብ ሰቆቃ  የዐይን ምስክሩ ሐዲስ አለማየሁ «ትዝታ» በሚለው መጽሐፋቸው ከገጽ 166-167 እንዲህ ገልጸውታል፤
«በነከንቲባ ጋሻው ጠና ዙሪያ ተሰብስቦ ጫካውን ሞልቶት ያገኘነውና ከደረስን በኋላም እየመጣ በላይ በላዩ ላይ ይጨምር የነበረው ከያገሩ በየምክንያቱ እዬሄደ እዚያ ክፍለ ሀገር ይኖር የነበረ፤ ከልዩ ልዩ ዘር የተጠራቀመ ሕዝብ ሲሆን ከዚያ የሚበዛው ዐማራነት ያለው ነው። በጠቅላላው ከዚያ ስደተኛ ሕዝብ መካከል ሽማግሌው፣ ባልቴቱና ሕጻኑ ይበዛል። ታዲያ እጉዞ ላይ ራሳቸውን ካልቻሉ ሕጻናት በስተቀር ያሁሉ ወንዱ ከቤቱ ጋር ያልተወውን ለስደቱ የሚያስፈልገውን ቁሳቁስ ጠቅላሎ በራሱ ወይንም በትክሻው ተሸክሞ ፍዬሉን በጁ ስቦ ወይንም ዶሮውን በቅፉ ታቅፎ  ይሄዳል። ሴቷ ልጇን ወይንም ምጣዷን በጀርባዋ አዝላ አገልግሏን ወይንም ሌላ እቃዋን በእጇ አንጠልጥላ ትሄዳለች።  ታዲያ ለዚያ ሁሉ ሕዝብ መንገዱ አልበቃው ብሎ እየተተራመሰ ጫካ እየጣሰ የተጠፋፉት ሲጠራሩ፤ ሕጻናቱ ጫካ ግጧቸው ወይንም ርቧቸው  ወይንም አሟቸው ሲላቀሱ ያንን ረብሻ ያንን ጫጫታ ያንን ሁናታ በጊዜው በቦታው ላይ ተገኝቶ መመልከቱ ብቻ ሳይሆን ካለፈም በኋላ ትዝታው  የሚያሳዝን ነው።
ያ ሁሉ ሕዝብ አንዳንዱ ካባት ከናቱ ጀምሮ፤ አንዳንዱም ራሱ ሄዶ ስራ እየሰራ ቤት ንብረት መስርቶ ዘመድ ወዳጅ አበጅቶ የኖረበትን አገር አስለቅቆ እንዲህ ባለ ችግር ውስጥ ያጣለው ምንድን ነው? ተብሎ ሲጠየቅ ያን ጊሴ ሲነገር የሰማሁት ምክንያት ሁለት ነው። አንዱ ምክንያት «ያገሩ ሕዝብ ከሌላው አገር እየሄደ እዚያ የሚኖረውን በተለይም ዐማራውን እንዲለቅለት ስላስገደደው ነው» የሚል ሲሆን ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ «አባ ጆቢር የተባሉት የአገሩ ባላባት ያገሩ ተወላጅ ያልሆነ ሁሉ ካገራቸው እንዲወጣላቸው በተለይም ዐማራውን ግን ራስ ራሱን እየቆረጠ ለሚወስድላቸው በሽልማት መልክ ላንድ የአማራ ራስ ሰላሳ ብር እንደሚሰቱ ላገሬው በይፋ ስላስታወቁና የዐማራዎች ራስም ስለተቆረጠ፤ አማራው  ራሱ እንዳይቆረጥ፡ ሌላው ደግሞ «ዛሬ በዐማራው የደረሰ ነገ በኔ ይደርስ ይሆናል» ብሎ ፈርቶ መሸሹ ነው የሚል ነበር።»
ከሐዲስ ጋር የነበሩት ልዑል ራስ እምሩ ጎጀብ ከተባለው ቦታ ላይ ጦርነት ሳያደርጉ ለፋሽስት ጥሊያን እጃቸውን ለመስጠት የተገደዱት በነዚህ የአባ ጆቢርን እርድ  ሸሽተው የተሰደዱ ሕጻናት፣ ሴቶች፣ አሮጊቶችና ሽማግሌዎች ምክንያት ነው። ልዑል ራስ እምሩ በጥቅምት ወር 1929 ዓ.ም. ከጎሬ ተንቀሳቅሰው ወደ ጅማ ያቀኑት ከቄለም ወለጋ ገዢው ከደጃዝማች ሀብተ ማርያም ጋር ተገናኝተው ከተነጋገሩ በኋላ አንደኛ የጅማ አካባቢ ገዢ የነበሩት ከንቲባ ጋሻው ጠና፤ ሁለተኛ ከከፋው ጠቅላይ ገዢ ከደጃዝማች ታዬ ጉልላቴ እንዲሁም ሁለቱ ጠቅላይ ገዢዎች ባሉበት ቦታ እራቅ ብለው በሲዳሞ፣ በባሌ፣ በጎሙ ጎፋ ከሚገኙት ከራስ ደስታ፣ ከደጃዝማች ገብረ ማርያም፣ ከደጃዝማች በየነ መርዕድ ጋር  የደቡቡን ክፍል አርበኞች አስተባብረው ኃይላቸውን በማጠናከር  አዲስ አበባን የተቆጣጠረውን ፋሽትን ለመዋጋት በተስማሙት ምክር መሰረት ነበር።  ሆኖም ግን ከጎሬ ተነስተው ጉዟቸውን ወደ ወለጋ አድርገው ሲጓዙ የወለጋን ሕዝብ አስተባብረው ከኔ ጋር ሁነው ጠላትን ይወጋሉ ብለው የአሰቧቸውና የገመቷቸውን ደጃዝማች ኃብተ ማርያም ገብረ እግዚያብሔር ግን እንኳን እንዳሰቧቸው ሊሆኑ የርሳቸውን መምጣት እንደሰሙ ጉይ ከሚባል  ቦታ ላይ አድፍጦ  የሚወጋቸው ጦር ልከው እንዲወጋቸው አደረጉ።
ከዚህ ጦርነት በኋላ ልዑል ወደለቀምት መሄዱን ትተውና ከሞት የተረፈውን ሠራዊት ይዘው ወደ ጅማ ጉዟቸውን መቀጠልን መረጡ። ጅማም ሲደርሱ አስቀድሞ ጥሊያን ገብቶ ከተማውን ይዞ ስለቆያቸው አንገቱ አባ ጆቢር ባሰማራቸው ነፍሰ በላዎች እንዳይቆረጥ ቤቱን እየተወ ጫካ የገባውን አማራ እየጠበቁ  የጅማ አካባቢ አስተዳዳሪ የነበሩትን ከንቲባ ጋሻው ጠናን ጉማ በተባለው ጫካ ውስጥ አገኟቸው። የሳቸውን ወደዚህ ጫካ መምጣት የሰማው ፋሽስት እነ ዮሐንስ ጆቴን ልጆ እጃቸውን እንዲሰጡ አልያም ጫካ ውስጥ ያለውን ሕዝብ ጭምር እንደሚፈጀው ፋሽስት ላከባቸው። አማራጭ ስላልነበራቸው እጃቸውን ሰጡ። በዘመን ትውስታቸው ውስጥ እንዳሰፈሩትም ጅማ በሄዱ ጊዜ ለታጠቀ ወታደርና ጤነኛ ሰው እንኳ አስቸጋሪ በሆነው በዚያ በሕጻናት፣ በሴቶች፣ በደካሞችና በበሽተኞች በተጥለቀለቀው አብዛኛው ስደተኛ የአማራ ተወላጅነት ባለው ሕዝብ መካከል ከመዋጋትና ሕዝቡን ከማስፈጀት መማረክን መምረጣቸውን ጽፈዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት መፍረሱን እንደ ክፍተት በመጠቀም የፋሽስት አገዛዝ በተተከለበት ወቅት አማራው በጅማ ያን ሁሉ ግፍና መከራ ያየው፤ ቤት ሠርቶ፣ ንብረት አፍርቶ፣ ዘመድ ወዳጅ አበጅቶ፣ ከዘመናት በፊት ይኖርበት ከነበረው ከአገሩ እየለቀቀ ጫካ እንዲገባ የሆነበት ምክንያትና አባ ጆቢር የአንድ አማራ አንገት ቆርጦ ለአመጣ ሰላሳ ጠገራ ብር ይከፈለዋል ብለው  አዋጅ ያስነገሩት ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ አባ ጅፋርን በተደጋጋሚ ኦሮሞን ጭምር ባርያ አድርገው መሸጣቸውን እንዲያቆሙ ቢያዝዟቸው  ከድርጊታቸው አልቆጠብም በማለታቸው አስፈርደው  ለተወሰነ ጊዜ እንዲታሰሩ ስላደረጉ ልጃቸው  ባሪያ ሻጭ አባቱን ያሰረብኝ አማራ ነው የሚል ቂም ይዘው ያንን ለመበቀል  ነው።
Filed in: Amharic