>

ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ብሔራዊ ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ፤

ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ብሔራዊ ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ፤

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ብሔራዊ ምክር ቤት ጥር 16 እና 17፣ 2012 ዓ.ም 5ኛ መደበኛ ጉባኤውን በማካሄድ የንቅናቄያችንን አጠቃላይ ፓለቲካዊ እንቅስቃሴ፤ የምርጫ ዝግጅት፤ የታሠሩ የአብን አመራሮችና አባለትን፤ የታገቱ አማራ  ተማሪዎችን እና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ ውሳኔ እና አቅጣጫ በማስቀመጥ አጠናቋል።
በሀገራችን ኢትዮጵያ አማራ ጠል የተሳሳተ ትርክት በፈርጣጭ ብሔርተኞች መቀንቀን ከጀመረ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያሳለፈ ቢሆንም ለሦስት አስርት ዓመታት መዋቅርና ሕግ ሆኖ አማራን እንደ ህዝብ ለመጨቆን ሥራ ላይ ውሏል።
የአማራ ህዝብ የተገንጣይ ብሔርተኞች የተሳሳተ ትርክት እንዲቆም ብሎም ኢትዮጵያዊያን በሰላምና በአንድነት ተከባብረው እንዲኖሩ ሲታገል ቆይቶ በ2010 ዓ.ም ለውጥ እንዲመጣ ቢያድርግም ለውጡን እንመራለን እና እናሻግራለን የሚሉት ተረኛ ነን ባዮች የቆየውን ትርክት ለማስቀጠል በሚያደርጉት ልፊያ ህዝባችን በተደጋጋሚ ዋጋ እየከፈለ ይገኛል።
የአማራ ህዝብ በሰላምና በመተሳሰብ እሴቱ ከሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር ተዋዶና ተከባብሮ  የኖረ ወደፊትም የሚኖር ህዝብ መሆኑ በሁሉም ዘንድ የሚታወቅ ሀቅ ሆኖ ሳለ የኢትዮጵያዊያንን የቆየ እሴት የማይወክሉ ብሎም እንቆምለታለን ብለው የሚምሉለትን ህዝብ ዓላማና ፍላጎት የማያውቁ ተገንጣይ የፖለቲካ ቡድኖች በሚያቀነቅኑት የአማራ ጠል ትርክትና እንቅስቃሴ የተነሳ የአማራ ህዝብ ለከፍተኛ ጭቆና ተዳርጎ ቆይቷል።
የአማራ ህዝብ ትግል የህልውናና ፀረ ጭቆና መሆኑ የታወቀ ሲሆን ባለፉት ዓመታትም ጭቆናን ሲታገል የነበረው አንደኛው ጨቋኝ በሌላኛው ጨቋኝ እንዲቀየር አልነበረም፤ አይደለምም።
ሆኖም ግን “የአማራን ህዝብ ማህበራዊ ረፍት መንሳት” የሚለው ትህነጋዊ ትርክት በተረኛ መንግስት ነን ባይ ቡድኖችና ተቀፅላዎች በመተካቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት የአማራ ህዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ነው። በመሆኑም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ብሔራዊ ምክር ቤት በ5ኛ መደበኛ ጉባኤው በሚከተሉት ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔና አቅጣጫ አስቀምጧል።
የታገቱ አማራ ተማሪዎችን በተመለከተ፡- በደንቢዶሎ ዩንቨርሲቲ ይማሩ የነበሩ አማራ ተማሪዎች ታግተው ከጠፉ ሁለት ወራት አልፈውታል። ይህ የአሸባሪነት ተግባር በአስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጠውና የታገቱ ልጆች እንዲለቀቁ አብን መጠየቁ ይታወሳል።
የአማራ ህዝብ እና ሁሉም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ይህን ነውረኛ የአሸባሪነት ተግባር አውግዞ መንግስት ኃላፊነቱን እንዲወጣ በትዕግስት ሲጠይቅ ቆይቷል። የአብን ብሔራዊ ምክር ቤት በዚህ የአሸባሪነት ተግባር የታገቱ አማራ ተማሪዎች በአስቸኳይ እንዲለቀቁ አሸባሪዎችም ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ መንግስት ኃላፊነቱን እንዲወጣ እያሳሰበ፤ ለታገቱ አማራ ተማሪዎች ድምፅ ለማሰማት በተለያዩ ከተሞች በአማራ ወጣቶች የተጠራውን ሰልፍ አብን የሚደግፍ መሆኑን ያረጋግጣል። ሰላማዊ ሰልፉም ከየትኛውም ጥቃትና ጥፋት ነፃ በሆነ መንገድ በሰላም እንዲጠናቀቅ መንግስት አስፈላጊውን ጥበቃና ከለላ የማድረግ ኃላፊነቱን በሚገባ እንዲወጣ እናሳስባለን፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የአማራ “ክልል” መንግስትና ማዕከላዊ መንግስቱ ላሳዩት የበዛ ቸልተኝነት ተጠያቂነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ድርጊቱን ላልተገባ የፖለቲካ ቁማር ከማዋል ተቆጥበው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በጥብቅ እናሳስባለን፡፡ መላው የአማራ ህዝብ ቀጣይ በልጆቹ ዙሪያ መንግስት የሚሰጠውን ምላሽ እየተከታተለ ለቀጣይ ትግሎችም ራሱን እንዲያዘጋጅ አብን ጥሪውን ያቀርባል።
የፖለቲካና የህሊና እስረኛ የሆኑ የአብን አመራርና አባላትን በተመለከተ፡- የአማራ “ክልል” ከፍተኛ አመራሮች እና የፌዴራል የጦር መኮንኖች ግድያ ተከትሎ “የክልሉ”ም ሆነ ማዕከላዊ መንግስት ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ከመሆኑም በላይ ካላንዳች የፖለቲካ ትርፍ ስሌት ሃቁን በወቅቱ ለህዝብ ማቅረብ ሲገባቸው፤ በህዝብ ላይ የደረሰውን አሳዛኝ በደል እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም ይባስ ብሎ ንጹሃን የንቅናቄያችን አመራሮችና አባሎቻችንን በታሪክ አጋጣሚ መንግስት የመሆን እድል የገጠመው ቡድን ለአማራ ህዝብ ካለው የተሳሳተ የጥላቻ አመለካከት በመነሳት በግፍ አግቷቸው እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ገዢው መንግስት የንቅናቄያችንን አመራሮችና አባላት በቂ ባልሆነ ማስረጃ በፖለቲካ አስተሳሰባቸው ብቻ ላለፉት ሰባት ወራት በእስር ላይ አቆይቷቸዋል፡፡ የአማራን ህዝብ ሰላምና ደኅንነት ብሎም የሀገርን ህልውና ግምት ውስጥ በማስገባት ያለአግባብ የታሰሩ የአብን አመራሮችና አባላት በውይይት እንዲፈቱ ከ7 ወራት በላይ ኃላፊነት በተሞላበት እጅግ ከፍተኛ ትዕግስት የጠየቅን ከመሆኑም በላይ ጓዶቻችን ያልተገባ መስዋዕትነት እየከፈሉ ይገኛሉ፡፡ ይህንንም አስመልክቶ ንቅናቄያችን ለህዝብና ለመንግስት በተከታታይ ያሳወቀ ቢሆንም ከመንግስት በኩል ፍትህ በመነፈጉ ምክንያት ለህዝባችን በገባነው ቃል መሰረት ቀጣይ የሰላማዊ ትግል አማራጮችን ለመጠቀም ተገደናል፡፡ ስለሆነም መንግስት ያለአግባብ በአፈሳ የፈፀመውን እስር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ክሳቸው ተቋርጦ በአንድ ወር ውስጥ በአስቸኳይ እንዲፈቱ እያሳሰብን፤ በተቀመጠው ጊዜ የማይፈቱ ከሆነ በየደረጃው ያሉ የንቅናቄያችን አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ህዝባችንን በማስተባበር እንደሚከተለው በተገለጸው የጊዜ ቅደም ተከተል መሰረት ሁሉንም የሰላማዊ ትግል አማራጮች እንተገብራለን፡፡
የካቲት 22/2012 ዓ.ም፡- በተመረጡ የሃገሪቱ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ ይደረጋል፤
የካቲት 26 እና 27/2012 ዓ.ም፡- አድማ ይደረጋል፤
ከመጋቢት 3/2012 ዓ.ም ጀምሮ አመራሮቻችን እና አባሎቻችን እስከሚፈቱ ድረስ ለተከታታይ ቀናት ህዝባዊ እምቢተኝነት እንዲካሄድ ምክር ቤቱ በሙሉ ድምፅ የወሰነ ሲሆን ለዚህም ከወዲሁ አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች እንዲጠናቀቁ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
ከዩኒቨርሲቲዎች ስለተፈናቀሉ ተማሪዎች፡- መንግስት ሀገር የመምራት ኃላፊነቱን በአግባቡ ባለመወጣቱ ምክንያት በተለያዩ የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ተማሪዎች በሰላም ትምህርታቸውን መከታተል ካለመቻላቸውም በላይ አካላዊ፣ ስነ ልቦናዊና የሞት አደጋ ገጥሟቸዋል፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች የዩኒቨርሰቲ ትምህርታቸውን አቋርጠዋል፡፡ ይህ በአማራ ተማሪዎች ላይ የሚፈጸም በደል አማራ ላይ የእውቀት ሽግግር እንዳይኖር ሲደረግ የኖረው መንግስታዊ ጭቆና መገለጫ መሆኑን አብን ይገነዘባል፡፡ ስለዚህ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ተማሪዎቹ ደኅንነታቸው በተጠበቀ ሁኔታ ትምህርታቸውን የሚቀጥሉበትን መንገድ በአስቸኳይ እንዲያመቻች የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ያሳስባል፡፡
ሀገራዊ ምርጫን በተመለከተ፡-
 ንቅናቄያችን ያዘጋጀው የምርጫ ማኒፌስቶ ለብሔራዊ ምክር ቤቱ ቀርቦ የተገመገመ ሲሆን ምክር ቤቱም ተጨማሪ ጉዳዮች ተካተውበትና በተለያዩ አካላት ውይይት እንዲደረግበት እንዲሁም ንቅናቄያችን በቅርቡ በሚያካሂደው ጠቅላላ ጉባኤ እንዲፀድቅ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
በመጨረሻም በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጭም ያለ መላው የአማራ ህዝብና ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ በማንኛውም ቡድን የሚፈጸምን ኢሰብአዊና የአሸባሪነት ተግባር ተባብሮ እንዲያወግዝ ብሎም ለፍትህ፣ እኩልነትና ነጻነት እንዲሁም የህግ የበላይነት መረጋጋጥ እንዲታገል  ንቅናቄያችን ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
አማራ በልጆቹ ትግል ታሪኩን ያድሳል!
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ብሔራዊ ምክር ቤት
ጥር 17/2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ሸዋ፣ ኢትዮጵያ
Filed in: Amharic