>

ውሸት እና ወንጀልን መደበቅ - የፖለቲካ ሞት ያመጣል!!! (መ/ር ኤፍሬም እሸቴ)

ውሸት እና ወንጀልን መደበቅ – የፖለቲካ ሞት ያመጣል!!!

 

መ/ር ኤፍሬም እሸቴ
• በአሜሪካ ፖለቲካ Watergate እየተባለ በሚጠራውና ፕ/ት ኒክሰንን (Nixon) ከሥልጣን ባወረደው ወንጀል ውስጥ የፕሬዚዳንቱ ትልቅ ወንጀል የነበረው የተፈፀመውን ወንጀል ለመደበቅ፣ ለማድበስበስ፣ መረጃ ለማጥፋት ይህን የሄዱበት መንገድ ነው። 
ማንም የዓለምን ፖለቲካ የሚከታተል ሰው “ዲሞክራሲያዊ መንግሥት” ለመሆን ለሚጥር መንግሥት ሁሉ  “ውሸት” እና “የተፈጠረ ስሕተትን/ወንጀልን ማድበስበስ/መደበቅ”
መውደቂያ ወጥመዱ ነው። ዓምባገነን ከሆንክ ማንንም ስለማትፈራና ስለማታፍር ከመጀመሪያውኑ ለመደበቅ አትሞክርም። ወጉ ይድረሰኝና ዲሞክራሲያዊ ልሁን ስትል ነው ውሸት፣ ማጭበርበር እና ማድበስበስ የሚመጣው።
ሌላውን ሁሉ እንተወው። ከደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ታገቱ። መታገታቸውን መንግሥት ሳይነግረን ዝም ብሎ ከረመ። ከዚያ የጠ/ም የኮሙኒኬሽን ኃላፊ በቲቪ ብቅ አሉና “እንኳን ደስ አላችሁ ልጆቹ ተለቀዋል” አሉ። መነሻውን ሳይነግሩን መድረሻውን አበሰሩን። ይሁን ዋናው የልጆቹ ደህና መሆን ነው አልን። በሚያሳዝን ሁኔታ ልጆቹ ብቅ ሳይሉ ቀሩ። አቶ ንጉሡም በዚያው ጠፉ።
ወንጀል ከተሠራ (ለምሳሌ የልጆቹ መጠለፍ) ጥፋቱ ሙሉ ለሙሉ የመንግሥት ላይሆን ይችላል። በርግጥ ዩኒቨርሲቲውና የአካባቢው መንግሥታዊ አስተዳደር የተማሪዎቹን ደኅንነት ባለማስጠበቃቸው ተጠያቂዎች ናቸው። የጠ/ሚ ቢሮ ይህንን ሁሉ ለማሸፋፈን እና ያልተለቀቁትን ልጆች “ተለቀዋል” ብሎ እስከመዋሸት ያደረሳቸው ምንድርነው? ወንጀል የትም ሀገር ይከሰታል። ነገር ግን ያንን መደበቅ የመንግሥት ተግባር አይደለም። ከደበቀ ደግሞ ወንጀሉን ከሠራው አካል ለይተን ልናየው አንችልም። “It is not the crime but the cover up”.
በአሜሪካ ፖለቲካ Watergate እየተባለ በሚጠራውና ፕ/ት ኒክሰንን (Nixon) ከሥልጣን ባወረደው ወንጀል ውስጥ የፕሬዚዳንቱ ትልቅ ወንጀል የነበረው የተፈፀመውን ወንጀል ለመደበቅ፣ ለማድበስበስ፣ መረጃ ለማጥፋት ይህን የሄዱበት መንገድ ነው። እርሳቸውን ከሥልጣን ለማውረድ በተካሄደው impeachment ወቅት እንደተገለፀው it is “not the crime but the cover up” (“ወንጀሉ ሳይሆን ወንጀሉን ለመደበቅ መሞከሩ ነው ጥፋቱ) ተብሏል። ይህ አባባል ዛሬም ድረስ ታዋቂ አባባል ሆኖ ዘልቋል።
የዶ/ር ዐቢይ ቢሮ እያካሄደ ያለው cover up ማድበስበስ ትልቅ ትልቅ ትልቅ ጥፋት ነው። ለዚህ ጥፋት ኃላፊነት መውሰድ ያለበት አካላት ራሱን ያዘጋጅ። ወንጀሉን ከፈፀሙት የልጆቻችን አፋኞች ባልተናነሰ ወንጀሉን ያድበሰበሰው የማንግሥት አካል፤ ከዩኒቨርሲቲው እስከ ክልሉ፣ ከክልሉ እስከ ጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ ሁላችሁም የልጆቹ ደም አለባችሁ።
Filed in: Amharic