>

ከ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ! ለመላው የአዲስ አበባ ነዋሪ

ከ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ!

 
ለመላው የአዲስ አበባ ነዋሪ
በምርጫ አስፈፃሚነት በንቃት በመሳተፍ የህጋዊ የስልጣን ባለቤትነትህን አረጋግጥ።
 የኢትዬጲያ ምርጫ ቦርድ በቀጣዩ ነሐሴ 10 ቀን 2012 ዓ/ም አገር አቀፍና ክልላዊ ምርጫ እንደሚካሄድ በማሳወቅ ዝርዝር መርሃ ግብሩን ይፋ ማድረጉ የሚታወቅ ነው። በዝርዝር ፕሮግራሙ ለመረዳት እንደሚቻለው ነገ ቅዳሜ ጥር 16 ቀን 2012 ዓ/ም በሁሉም ምርጫ ክልሎች የምርጫ አስፈፃሚ ምርጫ እንደሚካሄድ ለመረዳት ተችሏል።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በምርጫ ሂደት ውስጥ የምርጫ አስፈፃሚ አስፈላጊነት የሚመነጨው በምርጫው ህግ መሰረት ያለ አድልኦ መከናወኑን ወይም አለመከናወኑን ለማረጋገጥ የሕዝብ ዓይንን ጆሮ ለመሆን በገለልተኛ አካላት እንዲመራ ማድረግ ለእውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ አንዱ ምሰሶ እንደሆነ ይገነዘባል። ከዚህ አንፃር ፓርቲያችን የምርጫ አስፈፃሚን የምንመለከተው አንድን እግር ኳስ እንደሚመሩ ዳኞች አካል አድርገን ነው። የእግር ኳስ ዳኞች ገለልተኛ መሆን እንደሚጠቅባቸው ሁሉ የምርጫ አስፈፃሚዎችም ከዳኞቹ በላቀ ሁኔታ ገለልተኛ መሆን ይጠበቅባቸዋል።በመሆኑም የምርጫ አስፈፃሚ የዲሞክራሲያዊ ውድድሩ ሂደት በተገቢው መንገድ መከናወኑና ውጤቱም የእውነተኛ የሕዝብ ፍላጐት የተገለፀበት መሆኑን የሚያረጋግጥና የሚቆጣጠር አካል መኖር የግድ መሆኑን ፓርቲያችን ይገነዘባል።
ሆኖም ግን ኢህአዴግ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት የውሸትና የማስመሰል የምርጫ ዘመናት ለማጭበርበር ከፍተኛ ድርሻውን ከሚወስዱት አካላት አንዱ የምርጫ አስፈፃሚዎች ነበሩ። የምርጫ አስፈፃሚዎች ለኢህአዴግ ወገንተኛ የሆኑ የገዥው ፓርቲ አባላት፣ የፓርቲው ወጣትና ሴት ሊጐች እንዲሁም የፎረም አባላት የተካተቱበት በመሆኑ በሕዝቡ አመኔታና ተቀባይነት ያጡ ነበር። በዚህም ምክንያት ያለፉት ዘመናት ምርጫዎች ኢህአዴግን በይስሙላ ምርጫ ለማንገስ ባደረጉት ርብርብ ህዝቡ በነፃነት እና ዲሞክራሲያዊ መንገድ የሚመርጠው ተወካይ እንዳይኖር አድርገዋል። በተለይም በምርጫው ቀን የምርጫ አስፈፃሚዎች በየጣቢያዎቹ ሕዝቡ ተገቢዎቹን የድምፅ አሰጣጥ ሂደቶች ፍፁም አድሎአዊ በሆነ መንገድ በመፈፀም ኢህአዴግን እስከ መቶ ፐርሰንት የማንገስ ስራ በመስራት በታሪካቸው ጥቁር አሻራ አሳርፈዋል።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ እንዲህ አይነት ሕገ ወጥና ፀረ-ዲሞክራሲያዊ ተግባራት መድገም እንደሌለባቸው በጽናት ያምናል። ይህም ያለ አዲስ አበባ ህዝብ የነቃ ተሳትፎ ሊሳካ እንደማይችል ይገነዘባል። በአዲስ አበባ ሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ለእውነት እና ለእውነት ብቻ የሚቆሙ እንዲሁም የምርጫን ፋይዳ በቅጡ የተረዱ የምርጫ አስፈፃሚዎች መሳተፍ የግድ ይላል። በቀጣይ የሚካሄደው ምርጫ በአዲስ አበባ ብሎም በአገራችንና በሕዝባችን ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ያለውን ፋይዳ የሚገነዘቡ አስፈፃሚዎች መሳተፍ ይኖርባቸዋል።
ስለሆነም ጥር 16/2012 ዓ/ም በምርጫ ቦርድ መሪነት በሁሉም የምርጫ ክልሎች የሚደረግ የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ የአዲስ አበባ ነዋሪ በነቂስ ወጥቶ እንዲሳተፍ ፓርቲያችን ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ጥሪውን ያቀርባል።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ!
አዲስ አበባ
ድል ለእውነተኛዲሞክራሲ!
ይህን መረጃ በማሰራጨት አጋርነትዎን ያረጋግጡ
Filed in: Amharic