>

የአገዛዙ ትልቅ ፋውል!!! (አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

የአገዛዙ ትልቅ ፋውል!!!

አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
* “ይሄ ሕገመንግሥት አንድ ብሔር ብቻውን ክልል መመሥረት ይችላል አይልም፡፡ የሚለው ብሔሮችና ብሔረሰቦች (ሕዝቦች የሚለውን ሆን ብሎ በመተው) ክልል መመሥረት ይችላሉ ነው የሚለው!”…  ይሄ እንግዲህ የሴራ ፖለቲካ ድምር ውጤት መሆኑ ነው።.!!!
—-
ወያኔ/ኢሕአዴግ ሕገመንግሥታቸው እራስን በራስ በማሥተዳደር መብት ሽፋን የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የትግሬ፣ የሐረሪ፣ የአፋር፣ የሱማሌ ወዘተረፈ. እያለ ሀገሪቱን በዘር ሸንሽኖ “ይሄ የዕከሌ ብሔረሰብ ክልል ነው!” ከማለት ጀምሮ “ይሄ የእከሌ ጎሳ ወረዳ ነው፣ ልዩ ወረዳ ነው!” እስከማለት ወርዶ ሀገሪቱን በዘር በጣጥቆ ማደሉንና የብሔረሰቡ ወይም የሕዝቡ ፍላጎት ከሆነ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ክልል የመሆን መብትን መስጠቱን ዐቢይ እረሳችውና ዛሬ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ተወካዮች ጋር ባደረገችው ውይይት ላይ ማምሻውን በብዙኃን መገናኛ ሲተላለፍ እንደሰማነው ምን አለች መሰላቹህ “ይሄ ሕገመንግሥት አንድ ብሔር ብቻውን ክልል መመሥረት ይችላል አይልም፡፡ የሚለው ብሔሮችና ብሔረሰቦች (ሕዝቦች የሚለውን ሆን ብሎ በመተው) ክልል መመሥረት ይችላሉ ነው የሚለው!” ብሎ እርፍ!!!
እዚህች ጋር ልብ ማለት ያለብን የአዲስ አበቤ አልያም የድሬዳዋ ህዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር የክልል ነት ጥያቄ ቢያነሱ ሀገ መንግስቱ የሚደግፋቸው “ህዝቦች” በሚለው ማእቀፍ ውስጥ ነው። ይህም ማለት ዛሬ የቃላት ግድፈት አስመስሎ ከብሄር ብሄረሰቦች ቀጥላ በጉልህ የተጻፈችውን “ህዝቦች” የምትለውን ቃል ገደፋት ነገ ከነገ ወዲያ ከህገ መንግስቱ ይፍቃታል። ይሄ እንግዲህ የሴራ ፖለቲካ ድምር ውጤት መሆኑ ነው።
ቀጠለና “እንዲህ ስላቹህ ከዚህ በኋላ የክልል ጥያቄን አናስተናግድም ማለቴ እንዳይመስላቹህ፡፡ እርግጠኛ ሆኘ የምነግራቹህ ግን 56 ክልል አንፈቅድም፡፡ አቅም የለንም!” በማለት ከፍትሐዊነትና ከዲሞክራሲያዊ መብት ጋር ፊትለፊት በኃይለኛው ተላትማ ቁጭ አላለችም???
አጭሉግ ዐቢይ ይሄንን ስትል “ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ዕኩል መብት የላቸውም!” ብላ እያወጀች መሆኗ አልገባትም!!! አንድ ሥርዓት “ዲሞክራሲያዊ ነኝ!” ካለ ለአንዱ የሰጠውን መብት የግድ ለሌላውም መስጠት ይኖርበታል ወይም ለሌላው መከልከል አይችልም፡፡ መብቱን ለሁሉም ዕኩል መስጠት አለበት፡፡ ካልሰጠ ያ ሥርዓት አንባገነንና አድሏዊ እንጅ ፈጽሞ ዲሞክራሲያዊ አይደለም!!!
ዐቢይ በደቡብ ክልል 56 የክልል ጥያቄ እንደማናስተናግድ “እርግጠኛ ሆኘ እነግራቹሃለሁ!” ያለበትን ምክንያት ሲናገር አቅም እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ለፍትሕ፣ ለዲሞክራሲና ለሰብአዊ መብት መርሕ ታማኝ የሆነ ሥርዓት በአቅም ውስንነት ለሁሉም ማጎናጸፍ የማይችለው መብት ካጋጠመው ሁሉንም ይነፍጋል እንጅ ፈጽሞ ለከፊሉ ሰጥቶ ከፊሎቹን “በጭራሽ አይሆንም!” አይልም!!!
ወያኔ/ኢሕአዴግ ለጥቂቶቹ ቋንቋንና ማንነትን መሠረት ያደረገ የክልል መብት ሰጥቶ ሲያበቃ ደቡብን እንደሌሎቹ በብሔረሰባዊ ማንነት ሳይሆን በአቅጣጫ ሠይሞ በአንድ ቋት ጀብሎ ያስቀመጣቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ቋንቋና ማንነት ላይ የተመሠረተ ክልል የመሆን መብት ለሁሉም መስጠት ፈጽሞ የማይቻልና ይደረግ ቢባልም ሰላም ስለማይሰጥ ማለትም ሀገሪቱን የድንበር ግጭቶች መተራመሻ የሚያደርግ በመሆኑ ነው!!! ስለሆነም ወያኔ “ራስን በራስ የማሥተዳደር የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት!” እያለች የምትደሰኩረውን የሐሰት ዲስኩር ወደጎን አለችውና “ደቡብ!” ብላ 56 ብሔረሰቦችን በአንድ ቋት አጎረቻቸው!!!
ቋንቋና ማንነት ላይ የተመሠረተ የፌዴራል አሥተዳደር ፈጽሞ እንደማይሠራና እንደከሸፈ ከዚህ በላይ ማሳያ የለምና ለዘጠኞቹ ወይም ለበጣም ጥቂቶች ተፈቅዶ ለ73ቱ ወይም ለብዙዎቹ መከልከል የለበትምና መፍረስ ወይም መከልከል አለበት!!! ይሄ ካልሆነ ግን ሥርዓቱ የዘር መድሎ (apartheid) ሥርዓት እንጅ ፈጽሞ ዲሞክራሲያዊም ፍትሐዊም አይደለም!!!
Filed in: Amharic