>

ኢትዮጵያ - በማጣሪያ ሽያጭ ላይ! (አሰፋ ሃይሉ)

ኢትዮጵያ – በማጣሪያ ሽያጭ ላይ!   

 

አሰፋ ሃይሉ
እነዚህን የገዛ ሕዝባቸው ፀር (‹‹ተውሳክ›› አይሉትም መቼም የሰውን ልጅ!) እነዚህን የገዛ ሕዝባቸው ፀር የሆኑ ሸቃላዎች አይቶ ምን ይባላል?! እያረሩ፣ እየተከኑ፣ ዝም – በቃ ዝምምምምም ማለት ነው እንጂ!!! በቃ ቃላት አፍህ ላይ ሲጠፉ ሌላ ምን ይባላል?!! ወዶ አይደለም ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ‹‹ኑ አብረን ዝም እንበል!!›› ያለው ለካ!! )    
22 ሰዓታት ደፍነውታል፡፡ የዓለማቀፉ ግዙፍ የዜና አውታር – የብሉምበርግ ዜና – ለድፍን ዓለም ከተሠራጨ፡፡ አርዕስተ ዜናው – የኖቤሉ አሸናፊ አብይ አህመድ – የተዳከመውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንዲያንሠራራ ለማድረግ – በኢኮኖሚ የደም ሥሮቿ ሁሉ – የነፍስ አድን ግሉኮዝ በመስጠት ላይ ተጠምዷል – የሚል አንድምታ ያለው ሆኖ አገኘሁት፡፡ “Ethiopia Pushes Privatization to Give Its Economy a Sugar Rush” ይላል፡፡ ያገሬ ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያችን ጉዳይ ነው፡፡ እና ቀልድ የለም፡፡
በድካም ካሸለብኩበት አልጋ እንዳለሁ – የራስጌ መብራቴን በደከመ እጄ ፈልጌ አበራሁት፡፡ እና መለመላዬን ወደ ኮምፒውተሬ አመራሁ፡፡ ሙሉ ዜናውን ለማንበብ፡፡ ካነበብኩት አይቀር ብዬ – ዜናውን – ሙልጭ አድርጌ አነበብኩት፡፡ እና መጀመሪያ እንዲህ አልኩ፡- “እንዴ?! ኢትዮጵያ በማጣሪያ ሽያጭ ላይ ነች እንዴ!?”፡፡ ያነበብኩትን አላመንኩም፡፡ ምክንያቱም የከሠረ መጋዘን የማጣሪያ ሽያጭ አውጥቶ ያለውን ዕቃ ላላፊው ለአግዳሚው ባገኘው ዋጋ ይሸጣል እንጂ – ሀገር ለማጣሪያ ሽያጭ አትወጣማ!!
ሀገር የቱንም ያህል ብትከስር፣ የቱንም ያህል ባይቀናት፣ የቱንም ያህል ብትናጋ፣ ሀገር – በምንም ተዓምር – የከሰረ መጋዘን አይደለችም፡፡ እና ሀገር በማጣሪያ ሽያጭ ልትቸበቸብ በአብይ አህመድ የተያዘውን ሩጫ ስመለከት ደነገጥኩ፡፡ እንዴ?!! ምን እየሆነ ነው?! የዜናውን ዝርዝር ትንታኔ – እንደ ዮሐንስ ወንጌል – ሁለት ሶስት ጊዜ ደጋገምኩት፡፡ ያው ነው፡፡ ለውጥ የለውም፡፡ ዕቅጩን፡፡ እና ደግሜ ለጭለማዬ አጉተመተምኩ፡- “እንዴ?! የምር ግን ይሄ ሰውዬ ሀገሪቱን ሙልጭ አድርጎ ሊሸጣት ነው ማለት ነው?”
ይሄ የሰሞኑ የአብይ የሽያጭ ሩጫ – ምን ለማግኘት ያለመ ነው? ብሎ የሚጠይቅ አይጠፋም፡፡ የውጪ ዕዳ አናታችን ላይ ወጥቷል፡፡ ሀገሪቱ በዕዳ ተነክራለች፡፡ የአብይ መንግሥት ግን የብድር አኪሩ ቆሞለታል፡፡ ወዳጆቹና አበዳሪዎቹ በዝተዋል፡፡ ከዓለም ባንክ፡፡ ከቻይና መንግሥት፡፡ ከሳዑዲ መንግሥት፡፡ ከዩናይትድ አረብ ኤሚሬትስ መንግሥት፡፡ ከዓለማቀፉ ሞነተሪ ፈንድ፡፡ ከተለያዩ ዶላር ዘነብ ተቋማት ብድሩ በቢሊዮኖች እየዘነበለት ነው፡፡
የሚዘንብለትን ደግሞ በላይ በላዩ ይለዋል፡፡ ብድሩን ወደ ሀገር ቤት እያዥጎደጎደው ነው፡፡ አብይ አህመድ ከመጣ ወዲህ (በእርግጥ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ) የኢትዮጵያ ዓለማቀፍ ብድር በ26 በመቶ ጨምሯል፡፡ 28 ዓመት ሀገሪቱን የገዛውና የመዘበረው የአብይ አህመድ የኢህአዴግ መንግሥት ከሀገሪቱ አጠቃላይ ብድር ሩብ ያህሉን የወሰደው (ሀገሪቱን እስከ አናቷ የነከራት) በዚህ በመጨረሻዎቹ የሀገር ማጣሪያ ሰሞናት ነው ማለት እኮ ነው፡፡
እና ሀገር በዕዳ ከእግር እስከ አናቷ ስትነከር – በዶላር ቆጥራ የተረከበችውን ገንዘብ በዶላር ለመመለስ ማጣፊያው ያጥራል፡፡ እና በተራው ከሀገር ወደ ውጭ የሚወጣ (እና ዶላር ወደ ሀገርቤት የሚያመጣ) ነገር ይፈለጋል፡፡ ግን ኢንጅሩ ነው፡፡ ብዙው ነገር የለም፡፡ ቄሮ የወረራት ሀገር፣ የጃዋር ብጥብጥና የአልሞት ባይ ተጋዳዩ ኢህአዴግ መንፈራገጥ ክፉኛ ያበሻቀጣት ሀገር – ዓለማቀፍ ኢንቬስተር መሳብ ቀርቶ – ሀገር ያሉትንም ባለሀብቶች አታፈናፍንም፡፡ የአልአሙዲ የወርቅ ማዕድናት የሚያመጣው ዶላር እንደ ድፍድፍ ነዳጅ በበርሜል ይሁን በሜትሪክ ቶን አይታወቅም ነበር፡፡ ቄሮ ሰጥ እረጭ አርጎታል፡፡ እና የአብይ መንግሥት የታየው ዓይነተኛ አማራጭ የታየው አማራጭ ምንድነው?
የአብይ መንግሥት የታየውማ አማራጭ አጭርና ቀላል ነው፡፡ ምንም አንጃ ግራንጃ የለውም፡፡ ለኢትዮጵያ እንደ ላሜ ቦራዎች ሆነው ያለማቋረጥ ገንዘብ ሲያመነጩ የቆዩ – በወያኔም ቅምቡርሶች እስኪነጥፉ ድረስ ያለማቋረጥ ሲታለቡ የቆዩ – የመንግሥት (ማለትም የሕዝብ) ተቋማትን፣ የአገልግሎት አቅራቢዎችንና ትላልቅ ኢንፍራስትራክቸሮችን ለውጪ ተቋራጮችና ኢንቬስተሮች በማጣሪያ ዋጋ ጆሮ ጆሯቸውን ብሎ – እንደ ደም ማነስ አላላውስ ያለውን የዶላሩን ማነስ – በማጣሪያ ሽያጩ ዋጋ – ወደ ሀገርቤት በማዳበሪያ ጠቅጥቆ ማምጣት ነው፡፡ መቸብቸብ፡፡
እና መንግሥት ሀገርን ሊቸበችበው ለዓለም የግዙኝ ማስታወቂያውን በትኖ የገዢዎችን በሰም በታሸገ ኤንቬሎፕ የሚሰጥ ዋጋ በተስፋ አንጋጦ እየተጠባበቀ ነው፡፡ ግን ይህ ሁሉ የማጣሪያ ሽያጭ ስንት እንዲያስገኝለት አቅዶ ነው? 7,500,000,000 (ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር)!! ኢትዮ ቴሌኮም እስከ 49 በመቶ ይሸጣል፡፡ የኢትዮ-ጂቡቲ ምድር ባቡር ድርጅትና መንገድ ሥራ ከነነፍሱ ይቸበቸባል፡፡ ቁጥራቸው ከደርዘን በላይ የሆኑ የስኳር ማምረቻ ፋብሪካዎች ይቸበቸባሉ፡፡ ሰባት ሰፋፊ ጅምር የፋብሪካ ማስፋፊያዎችና የአገዳ እርሻዎች ይቸበቸባሉ፡፡
እና በጣም ያሳቀኝም – ያሳዘነኝም ነገር ደግሞ የእነዚህ የስኳር ፋብሪካዎች ወደ ግል ይዞታ መዞር የተፈለገበት ምክንያት ነው፡፡ እነዚህ እነ አባይ ፀሐዬ ስኳሩ ስለተበላሸ አፈር ላይ በትነነዋል – እያሉ በዜሮ ሂሳብ ሲያወራርዷቸው የነበሩት የስኳር ፋብሪካዎች – በአብይ የማጣሪያ ሽያጭ ዶላር ወደያዙ ዓለማቀፍ ዲታዎች ከተሸጡ በኋላ – ቢያንስ በሀገር ውስጥ – የዕለት ስኳር ፍለጋ በየሸማቾች ሱቅ ተሰልፎ የሚያድረውን ሕዝብ ፍላጎት በመጠኑ ያረካሉ ተብሎ ይጠበቃል – የሚል ዕቅድ ስጠብቅ – የአብይ አህመድ እቅድ ግን ምን ብሎ ቢደሰኩር ጥሩ ነው? – የስኳር ፋብሪካዎቹ ወደውጪ ባለሀብቶች ከተላለፉ በኋላ – ኢትዮጵያ ለዓለማቀፍ ገበያ ስኳር በማቅረብ በአፍሪካ ቀዳሚ ሀገር ትሆናለች!!
(ኡኡኡኡይ…!! ኧረ የት ሄጄ በሞትኩት!! ወያኔዎች የህዳሴው ግድብ ሲጠናቀቅ – ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሀገሮች የኤሌክትሪክ ኃይል ኤክስፖርት ታደርጋለች…! ይሉን የነበረው ትዝ አለኝ!! ‹‹የማን ዘር… ጎመን ዘር›› ብሎ ዝም ማለት ነው!! በ24 ሰዓት ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል 24 ጊዜ የሚቆራረጥበት ህዝብን እየመሩ – የኤሌክትሪክ ኃይልን ወደ ውጪ ኤክስፖርት እናደርጋለን!! በየቤቱ ከህፃን እስከ አዋቂ ስኳር ስኳር የሚል ነዋሪ ስኳር በሬሽን በሚቀበልበት ሀገር ላይ – የመንግሥትና የሕዝብ ፋብሪካዎችን ለውጭ ሀገር ግለሰቦች እየሸጠ – ከዚያ በኋላ ስኳሩን ኤክስፖርት አድርጎ የውጭ ሀገሮችን ሻይና ኮካ ሊያጣፍጥ የሚያልም መሪ – የማን መሪ ነው ሊባል ነው?
እነዚህን የገዛ ሕዝባቸው ፀር (‹‹ተውሳክ›› አይሉትም መቼም የሰውን ልጅ!) እነዚህን የገዛ ሕዝባቸው ፀር የሆኑ ሸቃላዎች አይቶ ምን ይባላል?! እያረሩ፣ እየተከኑ፣ ዝም – በቃ ዝምምምምም ማለት ነው እንጂ!!! በቃ ቃላት አፍህ ላይ ሲጠፉ ሌላ ምን ይባላል?!! ወዶ አይደለም ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ‹‹ኑ አብረን ዝም እንበል!!›› ያለው ለካ!! )
ብቻ ሀገር የከሰረ መጋዘን የሆነችበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ ሀገር በማጣሪያ ሽያጭ ላይ ናት፡፡ የሚሸጠው ደግሞ እጅግ ብዙ ነው፡፡ ሌላ ቀርቶ ሜቴክ እንኳ መቸብቸብ አልቀረለትም፡፡ አብይ አህመድ በሜቴክ ላይ አህመድ ሀምዛ የተባለ የደህንነት ሹም ሾሞበታል፡፡ አህመድ ሀምዛ ደግሞ የሜቴክን ማምረቻ ድርጅቶች ቆጥሮ ሁለት ቦታ ከፍሏቸዋል – የሲቪል ማምረቻዎችና የሚሊቴሪ ማምረቻዎች፡፡ እና ሲቪሉ ሜቴክ ይቸበቸባል፡፡ (‹‹ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ – ስሟን ይሏታል ጅግራ›› ማለትስ ይሄኔ ነበር!?)፡፡
በጣም የገረመኝ ነገር ደግሞ የኤሌክትሪክ ማመንጫዎችም ሊሸጡ መሆኑ ነው፡፡ ሰሞኑን የኤልፓዋ ኢንጂነር የታሰረችው በምን ይሆን ግን?!! እና የገረመኝ – አብይ አህመድ – ሜቴክን በነካ እጁ ደግሞ – የተለያዩ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎችንና ጅምር ግድቦችንም ለሽያጭ እንደሚያቀርብ ዓለማቀፉ የዜና ዘገባ አስፍሮት ሳገኘው ነው፡፡ የትኛው (ማለቴ የትኞቹ) ማመንጫዎች በአብይ አህመድ የማጣሪያ ሽያጭ እንደሚካተቱ ግን የተገለፀ ነገር የለም፡፡
(እና እንዲህ የሚል የምሬት ሀሳብ መጣብኝ…!! ‹‹ለግድቡ ደፋ ቀና ያለው ኢንጂነር ስመኘው መቼም አንድያውን ሞቷል፡፡ ካልጠፋ ቦታ በህዝብ አደባባይ ሽጉጡን ጠጥቶ፡፡ እንደ ቴዎድሮስ! (አጉል ቀን፣ እና አጉል ቀልድ እኮ ነው!) እና በቃ ከጀመረው ላይቀር – አብይ አህመድ – እንዲያው ያንን ጦሰኛ ግድብ ሸጦ በገላገለን ጥሩ ነበር!! አባቴ ይሙት!! ምን ቀረን?!! በቁማችን እየተቸበቸብን አልቀናል እኮ ጎበዝ?!!!›› የሚል ከጨለማዬ የጠቆረ የምሬት ሀሳብ ድቅድቁን ጨለማዬን ዋጠው፡፡
የሀገርን ለማጣሪያ ሽያጭ መቅረብ ስሰማ የሀዘኑ ድባብ ጨለማዬን ራሱ ዋጠው ስል – ድንገት አንድ ነገር ትውስ አለኝ፡፡ ሟቹ የዓለም ሎሬት ሜይትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ትዝ አለኝ፡፡ አፈወርቅ አመዛኙን የሙያ ዕድሜውን የጃንሆይን በወርቅ ካባ የተንቆጠቆጠ ምስል ሲስልላቸው ቆይቶ – የኢትዮጵያ ህዝብ ረሃብ ውስጥ ውስጡን ከመብላላት አልፎ በይፋ መነገር ሲጀምር – ጃንሆይ አረፍ ካሉበት መኝታቸው በላይ ጥቁር ባለች ትልቅ ዝርግ ፀሐይ የተከደነ ጥቁር ሰማይ በላያቸው ላይ አጥልቶ ሳላቸው፡፡ (ይህ ስዕል ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ባሳተሙት የሎሬቱ የሕይወት ታሪክ ላይ ይገኛል)፡፡
እና ዘንድሮስ ሠዓሊው ጠፋ እንጂ – ጥቁር ፀሐይ በላያችን ላይ ያጠላብን ያጠላብን መስሎ ታየኝ፡፡ እና ክብድ አለኝ፡፡ አሻጋሪ የተባለ መንጁስ ሎሬት አብይ አህመድ – ሀገሪቱን ሸቅሏት ሳይሸበለል – አንድዬ ጣልቃ ይግባልን እንጂ – የሰውማ ነገር ዝም ሆኗል፡፡ ኑ አብረን ዝም እንበል ሆኗል፡፡ በቃ ዝም፡፡ ኤሎሄ ኤሎሄ፣ ላማ ሰበቅታኔ፡፡ አበቃሁ፡፡
ኢትዮጵያ ታበፅዕ ዕደዊአ ሀበ እግዚአብሔር፡፡  
ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ ፈጣሪዋ እግዚአብሔር ትዘረጋለች፡፡   
አምላክ ኢትዮጵያን አብዝቶ ይባርክ፡፡
የዜና ምንጭ
Filed in: Amharic