>

የወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ለጃዋር!!! (ጎልጉል)

የወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ለጃዋር!!!

ጎልጉል
ሕግን በማስከበር ስመጥር የሆኑትና ለዚህም የቀድሞው ታሪካቸው የሚመሰክርላቸው የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ለጃዋር መሃመድ የማስጠንቀቂና የማብራሪያ ደብዳቤ ሊልኩ መሆኑን ታወቀ። ጃዋር ለደብዳቤው በቂ ምላሽ ካልሰጠ ከምርጫ ጋር በተያያዘ የሚያደርጋቸው የፖለቲካ ተግባራት በሙሉ ሊታገዱ እንደሚችሉ አብሮ ለመረዳት ተችሏል።
የጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ በላከው መረጃ መሠረት ምርጫ ቦርድ ለጃዋር ለመላክ ያረቀቀው ደብዳቤ ጃዋር በየትኛው የሕግ አግባብ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ሳይኖረው በኢትዮጵያ የምርጫ ሒደትና የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ሊገባ እንደቻለ ማስረጃና ማብራሪያ በቀነ ገደብ እንዲሰጥ የሚጠይቅ ነው።
በምርጫ ቦርድ ውስጥ የሚገኙ የጃዋር ሰዎች ደብዳቤው ሊላክለት መሆኑን ያስታወቁት ሲሆን ጃዋርም ደብዳቤው ወጪ ከመደረጉ በፊት የቦርዱ ሰብሳቢዋን ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳን ለማግኘት ሙከራ እያደረገ መሆኑን ጎልጉል ያለው መረጃ ይጠቁማል። ይሁን እንጂ የሕግ የበላይነትን በማጽናትና ከፍ በማድረግ የሚታወቁት የቦርዱ ሰብሳቢ ከአቋማቸው ንቅንቅ እንደማይሉና ሕግን በማስከበሩ መንገድ እንደሚገፉት ለመረዳት ተችሏል።
በአገሪቱ ሕገመንግሥትና ሌሎች ህጎች መሠረት አንድ ሰው በምርጫ ለመሳተፍም ሆነ ማንኛውንም ከምርጫ ጋር የተያያዘ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግ ኢትዮጵያዊ ዜግነት እንዲኖረው ይደነግጋል። ይህ በበርካታ የዓለም አገራት የሚሠራበት ሕግ ሲሆን ጃዋር መሃመድ ደግሞ የአሜሪካ ዜግነት እንዳለው ይታወቃል። ሆኖም ይህንን እውነታ በመቃረን ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና የሚመሩት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ፓርቲ ጃዋርን በፓርቲው አባልነት ከመቀበል በተጨማሪ “ዜግነት ኢትዮጵያዊ” የሚል የመታወቂያ ካርድ ሰጥቶታል።
በወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የሕግ አካሄድ ከሆነ ጃዋር አቅርብ የሚባለውን መረጃ ለማቅረብ ስለማይችል ከኦፌኮ ሊታገድና እስካሁን ያለፈቃድ ስላከናወነው በሕግ ሊጠየቅ እንደሚችል ከቦርዱ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል። ከዚህ ጋር ተያይዞም ኦፌኮም እንደ ፓርቲ በዚህ ዓይነት ተግባር ውስጥ አባሉ እንዲሳተፍ ማድረጉ፣ “ኢትዮጵያዊ” የሚል የመታወቂያ ሰነድ መስጠቱ በህግ እንደሚያስጠይቀው ከወዲሁ የሚሰጡ አስተያየቶች ይጠቁማሉ።
ከጥቂት ቀናት በፊት ጃዋር መሃመድ ከኤልቲቪ ቤተልሔም ታፈሰ ጋር ባደረገው ጭውውት የዜግነቱን ጉዳይ እየሠራበት እንደሆነና በቀናት ጊዜ ውስጥ ይህንን ጉዳይ እንደሚጨርስ መናገሩ ይታወሳል። ሆኖም በዜግነት ጉዳይ ላይ ባለሙያ የሆኑ እንደሚናገሩት ከአሜሪካ ዜግነት ለመቀየር መሟላት ያለባቸው የግብርና መሰል በርካታ መሥፈርቶች ያሉ ሲሆን ሒደቱም እስከ አስራአምስት ወራት ሊፈጅ እንደሚችል ይናገራሉ።
Filed in: Amharic