>
5:13 pm - Wednesday April 18, 2345

የሰላሌው የጦርነት ቅስቀሳ ዳንኤል ክብረት ለመተያያ የደረተው የውሸት አስተምህሮ ውጤት ነው!   (አቻምየለህ ታምሩ)

የሰላሌው የጦርነት ቅስቀሳ ዳንኤል ክብረት ለመተያያ የደረተው የውሸት አስተምህሮ ውጤት ነው!  

አቻምየለህ ታምሩ
በኦፌኮ የምርጫ ቅስቀሳ ሰላሌ ተገኝቶ ጦርነት ያወጀው  ሰውዬ የዳንኤል ክብረት የውሸት የታሪክ አስተምህሮ ውስጤት ነው። ባጭሩ ሰላሌ ላይ በታወጀው ጦርነት የዳንኤል ክብረት እጅ አለበት።  ዳንኤል ክብረት እናት መዝገብ የሌላቸውንና በታሪክ ምንጭነት ሊቀርቡ የማይችሉ የተሳሳቱ ድርሰቶችን በመጥቀስ የኢትዮጵያን ታሪክ እያዛባ የደረታቸው ድርሳናት እነሆ ጦርነት ለማሳወጅ በቅተዋል። ሰላሌ ላይ ጦርነት ያወጀው ሰውዬ ራሱ በአንደበቱ እንዳደጋገጠው «… ይኽ መሬት የአቡነ አኖሬዎስ መሬት ነው። ይኽ መሬት የአቡነ ፊሊጶስ መሬት ነው። . . .  መጤ ቄሶችን አብሯቸው. . . » እያለ ያስተጋባው  የነበረውን የውሸት ትርክት  ያገኘው ዳንኤል ክብረት ከጻፈው መጽሐፍ እንደሆነ ተናግሯል።
ዳንኤል ክብረት በጻፈው  አቡነ ቀውስጦስ በሸዋ፣ አቡነ አኖሬዎስ ደግሞ በባሌ ኦሮሞዎችን በኦሮምኛ አስተማሩ ብሎ ደርቷል። ሆኖም ግን እነዚህ ጻድቃን በዘመናቸው ያስተማሩት  ኦሮሞ በአካባቢው ሳይኖር ነው። ቅዱሳን ያላስተማሩትን ማኅበረሰብ እንዳስተማሩ አድርጎ በማቅረብ፣ ባላስተማሩበት ቋንቋ እንዳስተማሩበት አድርጎ በመጻፍ  ሥራቸውን ያራከሰውና ለዛሬ የፖለቲካ ቅስቀሳ እርሾ የሆነው ዳንኤል ክብረት ነው።
ዳንኤል ክብረት «አቡነ አኖሬዎስም በባሌ አካባቢ ሲያስተምሩ ኦሮምኛን ይጠቀሙ እንደነበር መዛግብቱ ይነግሩናል» ብሎ ታማኝነት በሌላቸው እቶፈንቶዎች ላይ በመመስረት የደረተው አንድም  የጥንት ቅጂ ወይም እናት መዝገብ ሳያቀርብ ነው። እስከሁን ድረስ ዳንኤል የቀረቡበትን ትችቶች አላስተባበለም፤ አልያም አቅርብ የተባለውን እናት መዝገብ ሊያቀርብ አልቻለም።
በመሆኑም ዳንኤል ክብረት ስላዛባው የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ጻድቃን ያልሰሩትን ሰርተዋል፣ ባላስተማሩበት ቋንቋ አስተምረዋል ብሎ ስላራከሰው ስራቸውና በቤተክርስቲያንና ሕዝበ ክርስቶያኑ ላይ ጦርነት እንዲታወጅበት ምክንያት ስለሆነው አስተምሮው  ከባድ ይቅርታ መጠየቅ ይኖርበታል፣ ሃይማኖተኛ ከሆነ ንስሐም መግባት አለበት!
ኃላፊነት የሚሰማውም  ከሆነ  እናት መዝገብ በሌላቸው ገድላት ላይ ተመስርቶ ለጻፋቸው ጦርነት እንዲሰበቅ ምክንያት ለሆኑት ድርሰቶቹ  ማስተካከያ መስጠትና ገበያ ላይ ወይም በሰው እጅ ላይ ያሉት መጽሐፍቶቹ ደግሞ ተሰብስበው እንዲወገዱ ማድረግ አለበት!
ከታች ያጋራሁት ጽሑፍ ከአምስት ወራት በፊት ዳንኤል ክብረት እናት መዝገብ የሌላቸውንና በታሪክ ምንጭነት ሊቀርቡ የማይችሉ የተሳሳቱ ማስረጃዎችን በመጥቀስ የኢትዮጵያን ታሪክ እያዛባ እንደሚገኝ የተቸሁበት ዘለግ ያለ ጽሑፍ ነው
ይድረስ አገዛዝ በተለዋወጠ ቁጥር የኢትዮጵያን ታሪክ የእጅ መንሻና መተያያ ለምታደርገው ለዳንኤል ክብረት — እባክህን «በሊቃውንት ፊት ጥቅስ አትጥቀስ»!
ዳንኤል ክብረት የሚጽፈውንና በሚናገረውን በሚመለከት ከዚህ በፊት ሁለት ጊዜ አስተያየቴን ጽፌ አውቃለሁ። ለመጀመሪያ ጊዜ የጻፍሁት አስተያየት «የዳንኤል ክብረት ነገር — በአንድ ራስ ሁለት ምላስ » የሚል ጽሑፍ ነበር። በዚህ ጽሑፍ ዳንኤል ክብረት እ.ኤ.አ. በኅዳር 2017 ዓ.ም. ብአዴን ባዘጋጀው መድረክ ከአለምነው መኮንን ጎን ቁጭ ብሎ «እኔ ከአንድ ብሔር መወለዴ እውነታ ነው፤ ማንም ሊክድ የሚችለው ጉዳይ አይደለም» በማለት ያቀረበውን ንግግር የተቸሁበት ነበር።
ዳንኤል ክብረት ከአንድ «ብሔር» መወለዱ እውነታ መሆኑን የተናገረው ይህንን ንግግር ከማድረጉ ከወራት በፊት ከአትላንታ ሆኖ ከሐብታሙ አያሌው ጋር በአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው ክፍል የራዲዮ መጽሔት ፕሮግራም ላይ ተጋብዞ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ በተዘጋጀ ውይይት ተሳትፎ ባደረገበት ወቅት «ብሔር ማለት አገር ማለት ነው፤ ብሔረሰብ ማለት ደግሞ የሰው አገር ማለት ነው» በሚል የሰጠውን የራሱን አስተያየት ተቃርኖ ነው። የኔ ትችትም ዳንኤል ክብረት በአሜሪካን ድምጽ ቀርቦ «ብሔር ማለት አገር ማለት ነው፤ ብሔረሰብ ማለት ደግሞ የሰው አገር ማለት ነው» ብሎ ከተናገረ በኋላ ባሕር ዳር ብአዴን መድረክ ላይ ተገኝቶ ደግሞ «እኔ ከአንድ ብሔር መወለዴ እውነታ ነው፤ ማንም ሊክድ የሚችለው ጉዳይ አይደለም» ማለቱ 180 ዲግሪ መገልበጡንና ከራሱ ጋር መቃረኑን ሚያሳይ ነበር።
ለሁለተኛ ጊዜ በዳንኤል ክብረት ላይ የጻፍሁት በዚህ ዓመት በመጋቢት ወር «የነ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ነገር. . . አካፋውን አካፋ፤ ዶማውን ዶማ ላለማለት ላም ባልዋለችበት ኩበት ለቀማ. ..» በሚል የጻፍሁት ነው። የዚህ ጽሑፍ አላማ ዳንኤል ክብረት የዐቢይ አሕመድ እንደራሴ ከሆነ በኋላ በየመድረኩ እየተገኘ «ኬኛና የኛ አካሄድ ያጠፋናል» እያለ የሚናገረው ያልተገባ ንግግር ነው። በዳንኤል ላይ ያቀረብሁት ሁለተኛ ጽሑፌ መሰረተ ሀሳብ «ኬኛና የኛ አካሄድ ያጠፋናል» እያለ በፖለቲካችን ውስጥ ያልተገባና የሌለ false equivalence  መፍጠሩንና የፖለቲካችን ችግሮች ያልሆኑትን አዲስ አበቤዎች እየሰበሰበ ለማይመለከታቸው ችግር ትምህርት ለመስጠት መድከሙን የሚተች ነው።
ዳንኤል ክብረትና መሰል የአገዛዙ ቤተኞች ሰማዩንም ምድሩንም ኬኛ የሚሉትን የኢትዮጵያ ችግር መስንዔዎች ደፍረው መናገር ስለማይችሉ የሌለ ጽንፍ ወይንም dichotomy በመፍጠር ኢትዮጵያ «የጋራችን» የምንለውን አብዛኛዎቻችን «ኬኛ» የሚሉት ኦነጋውያን ጽንፍ አድርጎ misrepresent ማድረግን እንደ ሞያ ይዘውታል። በዚያ ጽሑፌ ያነሳሁት «ኬኛ» የሚሉትን የኢትዮጵያ ችግር ፈጣሪዎች ንጹህ ለማድረግ «የኛ» የሚል የሌለ ትርክት ፈጥሯችሁ «የጋራ» የሚለውን አቃፊና አካታች የሀሳብ መስመራችንን በአድርባይነት ጥላሸት አትቀቡት የሚል ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ጽሑፌ የነ ዳንኤል ብዕር ድፍረት ካላት በኦሮምኛ «ኬኛ» የሚል እንጂ በአማርኛ «የኛ» የሚል ችግር ፈጣሪ ሌላ ጽንፍ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሌላ ማስተካከያ እንዲሰሩ የሚጠይቅም ነበር።
በአስተያየቴ መጨረሻ ላይም እውነት የማስተማር ድፍረቱ ካላቸው የኢትዮጵያ ችግሮች ምድሩንም ሰማዩንም «ኬኛ» የሚሉ አግላይ ኦነጋውያን ጽንፈኞችና ምድሩም ሰማዩም የጋራ የሚሉ አካታችና አቃፊ እሳቤዎች ብቻ መሆናቸውን፤ በየአካባቢው ችግር የሚፈጥሩት ዐቢይ አሕመድ በሪፑብሊካን ጋርድ የሚያስጠብቃቸው «ፊንፊኔ ኬኛ» የሚሉ ባለሜንጫዎችና ታከለ ኡማ ከክፍለ ሀገር አስመጥቶ መታወቂያ ያደላቸው ባለገጀራና ሚስማር የተጠቀጠቀበት አጣና ይዘው የሚወጡ ባለጊዜዎች እንጂ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ይዘው ወጥተው አዲስ አበባን የጋራችን ናት የሚሉ ሰላማዊ ዜጎች አለመሆናቸውን ለአዲስ አበቤዎች ሳይሆን ኦነጋውያን ከአእምሯቸው ላፈናቀሏቸው የኦሮሞ ወጣቶች እንዲያስተምሩ የሚሞግት  ነበር።
በዛሬው እለት በዳንኤል ክብረት ላይ የማቀርበው ትችት ዳንኤል ኦሕዴዶቹን  እነ ቀሲስ በላይ መኮንንን ደግፎ « የኦሮምያ ቤተ ክህነት፡- ለትክክለኛ ጥያቄ የተሳሳተ መልስ» በሚል በጻፈው አርቲክል ውስጥ ያቀረበውን የውሸት ታሪክ የሚያጋልጥ ነው።
ዳንኤል ክብረት ኦሮሞዎች ከ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት ሸዋ ነበሩ የሚለውን እነ ቀሲስ በላይን በመደገፍ በጻፈው መተያያ ላይ ያቀረበውን ድርሰቱን ታሪክ አድርጎ በድፍረት እና በግልጽ ስራው አድርጎ በቋሚነት የገፋበት  ኦሕዴድ ከሕወሓት ስልጣን በተረከበ ማግስት ጀምሮ ነው። ዳንኤል ይህንን የጻፈው ከኦሮሞ ታሪክ ጋር የተለየ ፍቅር ይዞት አይደለም። ይህንን አይነት ጽሑፍ በንግግርም ጭምር  እየደጋገመ ማቅረብ የጀመረው ኦሕዴድ ወደስልጣን ከመጣ በኋላ እና ዳንኤል የዐብይ አሕመድ የእልፍኝ አስከልካይ መሆኑን ተከትሎ ነው። ዳንኤል ይህን ማድረጉ  የፖለቲካውን ለውጥ አይቶ አሰላለፉን ማስተካከሉ ነው። ለዚህ ነው የታሪክ ሙህራን “History is a projection of current political interest into the past” የሚሉት። ዳንኤል የሚጽፈው ሀቀኛ ታሪክ ቢሆን ኖሮ ችግርም አልነበረበት። ነገር ግን  ዳንኔል የሚያደርገው የኢትዮጵያን ታሪክ መተያያ እና የእጅ መንሻ አድርጎ ሹመት ሽልማት ለማገኝት ሲል ያልነበረ ታሪክ እየደረሰ ታሪካንን ያለ ተጨማጭ ማስረጃ ማጨማለቁ ነው።
ዳንኤል ኦሮሞዎች ከ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት ሸዋ እንደሚኖሩ ያሳይልኛል የሚለው በቅርብ ዘመን የተቀዱ በመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ ለነበሩ ቅዱሳን የተጻፉ ግድላትን ነው። ዳንኤል እነ ቀሲስ በላይን በደገፈበት ጽሑፉ ያቀረበው መሰረተ ቢስ የፈጠራ ታሪክ ገድል (Hagiography) እንዴት እንደሚመረመር አለማወቁንና ገድል እየጠቀሰ Philology ወይም የጥንታዊ መጽሐፍትና ድርሳናት ጥናት ስለሚባለው የጥናት ዘርፍ አለማወቁን ያስመሰከረበት ነው። ዳንኤል አስደናቂውን እና እድሜ ጠገቡን የኢትዮጵያን የጽሁፍ ባህል ፈጽሞ አያውቀውም። ዳንኤል ባቀረበው በዚህ ጽሑፉ የኢትዮጵያን ታሪክ ለአገዛዙ መተያያ አድርጎ ሲያቀርበው ድፍረቱንና ዲያቆንና ሙዓዘ ጥበባት እየተባለ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የጽሑፍና የሐሰት መዝገቦችን የምታጣራበትን ሥርዓት አለማወቁን የሚያጋልጥ  ሰው ይኖራል ብሎ አላሰበ ይሆናል። ታሪካችንን ያነበብን ግን በታሪካችን ላይ እንደ ዳንኤል አይነት በራዦች ሲነሱ የሚጣላ ኅሊና ስላለን ዝም  አንልም።
ዳንኤል በጽሑፉ ኦሮሞ በመካከለኛው ዘመን ሸዋ ውስጥ ይኖር እንደነበር ለማሳየት በሄደበት ርቀት ያልሞከረው  የፈጠራ ዘዴ የለም። የኔ ትችት ዋና ዓላማ የኦሮሞ ሕዝብ የጥንት አገር የት እንደነበረና በመካከለኛው ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳልነበረ ለማሳየት አይደለም። የጽሑፌ ዓላማ በታሪክ መርመሪዎች ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ተረት ተረት እያመረቱ ሀቀኛ ታሪክ በማስመሰል ለቀጣሪዎቻቸው ለአገዛዙ ሰዎች እንደ መተያያ ይዘው የሚቀርቡት እንደ ዳንኤል ክብረት አይነት ሰዎች የሚያዛቡትን ታሪክ ለማረቅ ነው።
ዳንኤል ክብረት ኦሮሞዎች በመካከለኛው ዘመን ኢትዮጵያ በተለይም በሸዋ አካባቢ ነበሩ ብሎ  የጻፈው ኦሕዴድ ስልጣን በያዘ ማግስት መለትም በጥቅምት ወር 2010 ዓ.ም. «ሸዋ፡- የጥንትና ዛሬ መገናኛ» በሚል ርዕስ በጻፈው መተያያም ተመሳሳይ ድምዳሜ በመድረስ ጥንታዊ መዛግብት እንዴት እንደሚመረመሩ አለማወቁን በአደባባይ ባሳወቀበት ጽሑፉ ጭምር ነው። ኦሮሞዎች ከ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት ሸዋ አካባቢ ባይኖሩም የግድ መኖር አለባቸው ተብሎ ለሚቀርብ መተያያ ካልሆነ በስተቀር ይህንን ተረት ተረት አግባብነት ባለው የታሪክ ማስረጃ ማረጋገጥ አይቻልም።ይህን ትችት ለመጻፍ የተገደድኩበትም ዳንኤል በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የሚሰራውን ሀጢያት ስለደጋገመው እና ብዙ የዋሆች እውነት መስሏቸው እንዳይሳሳቱ በማሰብ ነው።
ዳንኤል ክብረት ቀሲስ በላይ መኮንን ቤተ ክህነት ለመመስረት የጀመሩት እንቅስቃሴ «ተገቢ መነሻ» ብሎ በግል የፌስቡክ አካውንቱ ላይ ጽፎ ባተመው ጽሑፉ ኦሮሞ በመካከለኛው ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚኖር እርግጠኛነት በተሞላበት አኳኋን የሚከተለውን ተረት ተረት አቅርቧል፤
«እኔ ባለኝ መረጃ በኦሮምኛ ቋንቋ በማስተማር ቀደምቶቹ አቡነ ቀውስጦስ ዘመሐግልና አቡነ አኖሬዎስ ናቸው፡፡ በአቡነ ቀውስጦስ ገድል ውስጥ አቡነ ቀውስጦስ ያስተማሯቸው የተለያዩ የኦሮሞ ጎሳዎች ተጠቅሰዋል፤ ያስተማሩባቸው ቦታዎች ሲጠቀስ አንዳንዶቹ የኦሮምኛ ስም ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህን ሕዝቦች ያስተማሯቸው በቋንቋቸው ነው።» ይህ ያልነበረው ነበረ፥ያልተፈጸመውን ተፈጽሟል ብሎ ዳንኔል በድፍረት የጻፈው ተረት ተረት የቁዳሳኑን መንፈሳዊ ተጋድሎ ዝቅ የሚያደርግ ነው። ይህ ተረት አቡነ ቀውስጦስን እና አቡነ አኖሬዎስን ከመቃብራቸው ውስጥ ሆነው እንዲገለባበጡ የሚያደርግ ነው።
ገድለ አቡነ ቀውስጦስ በአንድ ቦታ ላይ ‹ዘሀለወት ደብር ወበል ስማ ሰገሌ – ሰገሌ የምትባል ደብር ነበረች› ይላል፡፡ በሌላም ቦታ ‹ደብረ ሰገሌ› ይላታል (Gli Atta di Qawsetos, 240) ሰገሌ ኦሮምኛ ነው፡፡ ‹ድምጽ› ማለት ነው፡፡ ‹ግበር ሎቱ(ለገላውዴዎስ) መልዕልተ የይ፤ ወለቴዎድሮስ ላዕለ ደብረ መንዲዳ – ለገላውዴዎስ በየይ ተራራ ላይ (ቤተ መቅደስ) ሥራ፤ ለቴዎድሮስ ደግሞ በመንዲዳ ተራራ ላይ› ይላል(ገጽ 119፤139)፤ መንዲዳ ኦሮምኛ ነው፡፡ ‹የዱር ቤት› እንደማለት ነው፡፡ ዛሬ ከደብረ ብርሃን ከተማ ወደ ጅሩ በሚወስደው መንገድ መንዲዳ የምትባል ከተማ አለች፡፡ ‹ወለፊቅጦርኒ በሀገረ ለሚ ዘትሰመይ ደብረ ዲባናው – ፊቅጦርንም ደብረ ዲባናው በምትባል በለሚ ሀገር› ‹ለሚ›፣ በኦሮምኛ ‹ዜጋ› ማለት ነው፡፡ ‹ወይብሉ ርእዩ ሰብአ ገላን ወየይ – የገላንና የየይ ሰዎችን ተመልከቱ አሉ›(ገጽ 121)፤ ገላን የኦሮሞ ጎሳ ስም ነው፡፡ ‹ወአጥመቆሙ በህየ ሰብአ የይ፣ ወመሐግል ወገላን፣ ወሰብአ ጋሞ ወወላሶ ወቀጨማ – የየይን፣ የመሐግልንና የገላንን፣ የጋሞን፣ የወላሶ(ወሊሶ)ና የቀጨማን ሰዎች አጠመቃቸው›(ገጽ 137)፡፡ ወላሶ(ወሊሶ) ዛሬ በስሙ ከተማ የተሠራለት የኦሮሞ ማኅበረሰብ ስም ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በሸዋ ከወግዳ አጠገብ የነበሩ ናቸው፡፡ እነዚህን ሁሉ አቡነ ቀውስጦስ አስተምረዋል፡፡ በግራኝ ጊዜ ነው ብዙ ነገር የጠፋው፡፡ አቡነ አኖሬዎስም በባሌ አካባቢ ሲያስተምሩ ኦሮምኛን ይጠቀሙ እንደነበር መዛግብቱ ይነግሩናል፡፡»
ዳንኤል ክብረት «የኦሮምያ ቤተ ክህነት፡- ለትክክለኛ ጥያቄ የተሳሳተ መልስ» በሚል በግል የፌስቡክ ግድግዳው እ.ኤ.አ. በMONDAY, SEPTEMBER 2, 2019 ካተመው የተወሰደ  የመተያያ ክታብ «ኦሮምያ» የሚባለው ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ‹‹የኦሮሞ ታሪክ እስከ አስራ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን›› በሚል ርዕስ ባሳተመው የፖለቲካ መጽሐፍና የኦሮሞ ብሔርተኛው ፕሮፌሰር መሐመድ ሐሰን «The Oromo and the Christian Kingdom of Ethiopia: 1300-1700» በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ. በ2015 ዓ.ም. ባሳተሙት መጽሐፍ ውስጥ የተደረተው እቶፈንቶ «ቅጂ» ነው።
ዳንኤል ክብረት እንዲህ የውሸት ታሪክ በማቀናበር መተያያ ሲያቀርብ አገዛዙ የሚሰፈርለትን  ቀለብ እንጂ ዲያቆንና ሙዓዘ ጥበባት የሚባሉ ማዕረጎችን ሰጥታ እዚህ ያደረሰችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አሰራርና የጽሑፍ ባህል፣ እያንዳንዱ አድባር ሀሰተኛ መዝገብ እንዳይራባ የሚከተለው የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት አላስጨነቀውም።
ዳንኤል ክብረት «በአቡነ ቀውስጦስ ገድል ውስጥ አቡነ ቀውስጦስ ያስተማሯቸው የተለያዩ የኦሮሞ ጎሳዎች ተጠቅሰዋል፤ ያስተማሩባቸው ቦታዎች ሲጠቀስ አንዳንዶቹ የኦሮምኛ ስም ያላቸው ናቸው፡፡ «እነዚህን ሕዝቦች ያስተማሯቸው በቋንቋቸው ነው» እያለ ሲናገርም እጅግ  በድፍረት ነው። ሆኖም ግን በአቡነ ቀውስጦስ ገድል እናት መዝገብ ውስጥ ይህንን የዳንኤል ክብረት የውሸት ክታብ በመብራት ብንፈልግ አናገኘው። የዳንኤል ክብረት ሌላው ድፍረት ደግሞ  ይህ የውሸት ክታቡ በግራኝ ዘመን እንደተቋረጠ ያለጥርጥር መናገሩ ነው።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የጽሑፍ ሥርዓት መሰረት አንድ መዝገብ ትክክለኛ ቅጂ [original and authentic] ነው የሚባለው እናት መዝገብ ሲኖረው ብቻ ነው። ይህ የቤተክርስቲያን የጽሑፍ ሥርዓት ባይኖር ኖሮ መጻፍ የሚችል ሁሉ እየሞነጨረ ዛሬ ላይ በየገዳማቱና አድባራቱ ብዙ አይነት መጽሐፍ ቅዱስ ይኖረን ነበር። ቀደም ብዬ ያነሳሁት ስለ የጥንታዊ መጽሐፍትና ድርሳናት ጥናት የሚጠበበው Philology የሚባለው የጥናት ዘርፍ የሚያጣራው ይህንን ነው። እናት መዝገብ የሌለው ማንኛውም ገድል ሆነ ተዓምር እንደ ታሪክ ምንጭ ሊጠቀስ አይገባውም። ዳንኤል ክብረት ገድል እየጠየቀ ያላወቀው Philology የሚባለውን የጥናት መስክ ብቻ ሳይሆን የወጣባትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የጽሑፍ ስርዓት ጭምር ነው። አባቶች «በሊቃውንት ፊት ጥቅስ አትጥቀስ» ይላሉ። ዳንኤል ክብረት ግን እናት መዝገብ የሌለውን ገድል በታሪክ ምንጭነት በመጥቀስ አለማወቁን በሊቃውንት ፊት ራሱን አጋልጧል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ዳንኤል ክብረት የጠቀሰውን አይነት ታሪክ የሚያፋልስ እናት መዝገብ የሌለው ገድል ስታስወግድ ኖራለች። ዳንኤል የጠቀሰው እናት መዝገብ የሌለው ገድል ቤተክርስቲያን ስታስወግዳቸው ከኖረቻቸው ጽሑፎች መካከል አንዱ ነው።
በPhilology ስነ ዘዴ የአቡነ ቀውስጦስን ገድል የመረመረው ዶክተር ሀብታሙ ተገኝ ዳንኤል ክብረትና መሰል የኦሮሞ ብሔርተኞች የውሸት ትርክታቸውን ለማንበር ከእናት መዝገቡ ያልተቀዳውን፣ ኦሮሞ ሸዋን ከወረረና የቦታ ስሞችን ከለወጠ በኋላ በ19ኛውና በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ስለተገለበጠው የነዳንኤል ክብረት የተሳሳተ የታሪክ ምንጭ የሚከተለውን ጥፏል፤
«ገድለ ቀውስጦስን የጻፈው መባ ጽዮን የተባለው የጻድቁ የመጨረሻ ተከታይ ሲሆን ጊዜውም በዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ነው። ነገር ግን እስካሁን በተደረገው ጥናት በዳዊት ዘመን የተጻፈው የመጀመሪያው ገድል አልተገኘም። ገድለ ቀውስጦስን ኦስቫልዶ ሬነሪ እስካሁን የተገኙትን የገድሉን ቅጅዎች ሁሉንም አመሳክሮ ወደ ጣሊያነኛ ተርጉሞ ከግዕዙ ጎን ለጎን በ2004 ዓመተ ምህረት አሳትሞታል። በሬነሪ ጥናት መሰረት እስካሁን በአጠቃላይ 8 የገድለ ቀውስጦስ ቅጅዎች እንዳሉ ይታወቃል። አንደኛው ጣሊያናዊው እንሪኮ ቸሩሊ ያጻፈው ቫቲካን ቤተ መጻሕፍት የሚገኘው መለያ ቁጥሩ 194 የሆነው ነው። ሁለተኛው መለያ ቁጥሩ 420 የሆነ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የሚገኘው ቅጅ ነው። ሶስተኛው በቫቲካን ቤተ መጻሕፍት በፎቶግራፍ የሚገኘው መለያ ቁጥሩ 207 የሆነ ነው። አራተኛው በብሄራዊ ቤተ መጻሕፍት የሚገኘው የመለያ ቁጥሩ 207 የሆነው ነው። ከላይ ከተዘረዘሩት በተጨማሪ ክንፈ ርግብ ዘለቀ ባሳተመው ጥናት መሰረት ገድለ ቀውስጦስ ንብጌ ማርያም፥ ደብረ ጽላልሽ እቲሳ ተክለ ኃይማኖትና ደብረ ሊባኖስ ገዳም ይገኛል። ኦስቫልዶ ሬነሪ ያሳተመው በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቸሩሊ ያስቀዳውንና ከቫቲካን ቤተ መጻሕፍት የሚገኘውን ነው።»
[ ምንጭ፡ ሀብታሙ ተገኝ (2012)፥ በራራ (ቀዳሚት አዲስ አበባ)፡ ከአመሰራረት እስከ ዳግም ልደት፥ በራራና የኦሮሞ ወረራ ከሚለው ምዕራፍ ገጽ 28፣ ያልታተመ]
እንግዲህ! ዳንኤል መተያያውን ያቀረበው ይህንን ሁሉ በተለያዩ ዘመናት የተገለበጡ የገድሉ ቅጂዎች ሳይመረምር ነው። እሱ ብቻ ሳይሆን ኦሮሞ ከግራኝ በፊት ሸዋ እንደነበር የውሸት ታሪክ የሚጽፉ ሰዎች ቢያንስ ሬነሪ ወደ ጣሊያንኛ የተረጎመውን ገድለ ቀውስጦስን ማንበብ ነበረባቸው። ይህንን ትርክት በግንባር ቀደምትነት የሚመሩት ፕሮፌሰር መሀመድ ሐሰንም ሆነ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ዳንኤል ክብረት በገድሉ ውስጥ እንደተጠቀሱ አድርጎ ስላቀረባቸው ያያና ገላን ስለተባሉ የኦሮምኛ ስሞች የጻፉት ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት በChurch and State ጥናታቸው  ወደ እንግሊዘኛ የተረጎሙትን መሰረት አድርገው ነው። ነገር ግን ፕሮፌሰር ታደሰ የተጠቀሙበት ገድለ ቀውስጦስ በቅርብ ዘመን የተቀዳና ብዙ እርማትና ለውጥ የተደረገበት መሆኑን ራሳቸው አውቅና ሰጥተው ጽፈዋል። እ ንደ ዳንኤል ክብረት አይነት ታሪክ የመፍጠር ሕልም ይዘው የተነሱት የኦሮሞ ብሔርተኞቹ ፕሮፌሰር መሀመድ ሐሰንና ዶክተር ነጋሶ ግን ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት የተጠቀሙት በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተገለበጠውን ቅጅውን ሳይሆን በዐፄ ዳዊት የተጻፈውን የመጀመሪያውን አስመስለው ያቀርቡታል።
የገድለ ቀውስጦስን ቅጂዎች የመረመረው ዶክተር ሀብታሙ ተገኝ እንዲህ ሲል ይቀጥላል. . .
«በመካከለኛው ዘመን በሸዋ ስለነበሩ ገዳማትና ቅዱሳን ታሪክ በ19ኛውና በ20ኛ መቶ ክፍለ ዘመን የተጻፉ ገድላትና ድርሳናት ብዙዎቹ እርማትና ለውጥ እንደተደረገባቸው ማወቅ ያስፈልጋል። ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ ግልጽ ነው። በግራኝ አህመድ ወረራ ጊዜ ብዙ የሸዋ አድባራትና ገዳማት ከመጥፋታቸውም በላይ የኦሮሞ ጎሳዎች ብዙ ስፍራዎችን ስማቸውን እንደቀየሯቸው የሚታወቅ ነው። ብዙ ገዳማትና አድባራት ከሶስት መቶ ዓመታት በላይ ጠፍ ሆነው ቆይተዋል። የሸዋ ኃይል ባንሰራራበት በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ደብረ ሊባኖስን ጨምሮ ብዙ ጠፍ የነበሩ አድባራት እንደገና ተመስርተዋል። የጥንቱ ገድሎችም ድርሳናትም እየተፈለጉ እንደገና ተቀድተዋል።
በ19ኛውና በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ገድላቱና ድርሳናቱ እንደገና ሲቀዱ የጥንቱን የቦታ ስምና የህዝብ ስርጭት በአዲስ ስያሜ ይቀይሩታል። በዚህ ምክንያት የብዙ አድባራት ታሪክና የቦታ ስሞች ይፋለሳሉ። በዐፄ ዮሐንስና በዐፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ብዙ አድባራትና ገዳማት ሀሰተኛ ገድል በመጻፍና የጥንት ድርሳናትን ይዘታቸውን በመቀየር ታሪካችን ተቀየረ በማለት በትግራይ፥ በሸዋና በጎጃም የነበሩ አድባራት እስከ ክስ ደርሰው ነበር። ለምሳሌ ሱዛኔ ሁመል በቅርቡ ባሳተመችው ጥናት በዐፄ ልብነ ድንግል ዘመን ተጽፎ የነበረው ድርሳነ ዑራዔል በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ይዘቱን ቀይረው የጎጃምና የሸዋ ጸሐፊዎች እንደገና ገልብጠውት ነበር። በዚህ ምክንያት የዲማ ጊዮርጊስ ካህናት ወደ ዐፄ ምኒልክ ክስ አቅርበው ታርሞ የተጻፈው ድርሳነ ዑርዔል ከየአድባራቱ ተለቅሞ እንዲቃጠል በንጉሡና በአቡነ ማቴዎስ ተወስኖ ነበር። ሀውዜን የሚገኘው የጽረ አብረሀ ወአጽብሀና ጎጃም የሚገኘው የመርጡለ ማርያም ገዳማት በአንድነት የጻፉት ገድለ አብርሀ ወአጽብሀ በተመሳሳይ ወደዮሀንስና ወደምኒልክ ክስ ቀርቦበት ነበር።
ታሪኩ በሰፊው የሚታወቀው ክብረ ነገስት ሳይቀር በየዘመኑ ሲገለበጥ ጸሐፊዎች እርማትና ለውጥ ያድርጉበታል። በማይክል ክላይነርና በዌንዲ ቢልቸር መሰረት በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተጻፈውን ጨምሮ ቀዳሚ የክብረ ነገስት ቅጂዎች 39ኛው ምዕራፍ ላይ የሰለሞን ልጅ በይነ ለኪምን “የደቡብ ንጉሥ” ይለዋል። በኋላ ዘመን የተጻፉት የመጽሐፉ ቅጂዎች ቀይረው “የደቡብ የሸዋ ንጉሥ” ብለው ቀይረውታል። በተመሳሳይ ገድለ ቀውስጦስ ብዙ እርማትና ለውጥ እንደሚደረግበት መገመት አይከብድም።»
[ ምንጭ፡ ሀብታሙ ተገኝ (2012)፥ በራራ (ቀዳሚት አዲስ አበባ)፡ ከአመሰራረት እስከ ዳግም ልደት፥ በራራና የኦሮሞ ወረራ ከሚለው ምዕራፍ ገጽ 29-30፣ ያልታተመ]
ዳንኤል ክብረት የጥንት መጻሕፍትን ታማኝነት መርምረው፣ የአርትኦት ስራ ሰርተው የሚያሰናዱ የታርካዊ እና ንጽጽራዊ ስነ ልሳን ሙሑራን [Philologists] የጻፉትን ቢያነብ ኑሮ በዚህ ሳምንት በደረሰው መተያያ ያስተጋባውን የውሸት ታሪክ አይጽፍም ነበር። የታሪካዊ እና የንጽጽራዊ ስነልሳን ሙሑራን የጻፉትን ማንበብ እንኳ ቢሳነው የወጣባት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ስለ ጽሑፍ ያላትን ባሕልና ስርዓት በወጉ ማወቅ የጠበቅበታል። ፊሎጅስቶች የድላትን ጨምሮ የአንድን መጽሀፍ የመጀመሪያውን መዝገብ “Vorlage” ይሉታል። ይህ በኢትዮጵያውያን የስነጽሑፍ ባሕል አገላለጽ “እናት መዝገብ” እንደ ማለት ነው።
በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የጽሑፍ ሥርዓት  አከራካሪ ነገር ከመጽሑፍ ላይ ተጽፎ ሲገኝ ስለ ጽሑፉ እውነተኛነት ብይን የሚሰጥ እናት መዝገብ ታይቶ፥ ተመርምሮ ነው። ይህ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የጽሑፍ ሥርዓት መሰረታዊ እውቀት ነው። ዳንኤል ክብረት ሊጠቅሰው የሄደው እናት መዝገብ የሌለው ገድል ግን በተለያየ ጊዜ ጸሐፊዎች ሲቀዱ ከመጀመሪያው ወይም ከእናቱ መዝገቡ [Vorlage] ላይ የሌለውን አዳዲስ ነገር እየጨመሩ ያጨማለቁትን ነው። አዋቂ ነኝ የሚለው ዳንኤል ክብረት ራሱ የጠቀሰውን የአቡነ ቀውስጦስ ገድል እናት መዝገብ አቅርብ ቢባል መልስ የለውም፤ በጽሑፉም የጠቀሰው ገድል ትክክለኛ ቅጂና ከእናት መዝገቡ የተቀዳ ስለመሆኑ የሰጠው ማረጋገጫ የለም። ይህን ትንሹን ነገር ማድረግ ያልቻለውን ዳንኤል ክብረትን ገድሉ ላይ አገኘሁት ያለው ታሪክ በዘመኑ ታሪከ ነገሥት ስለመደገፉ፣ በታሪከ ነገሥቱ ላይ ስለመኖርና አለመኖሩ አጣርተሀል ወይ ብዬ ልጠይቀው ከቶ አይቻለኝም።
እንግዲህ! ዳንኤል ክብረት አቡነ ቀውስጦስ በሸዋ፣ አቡነ አኖሬዎስ ደግሞ በባሌ ኦሮሞዎችን በኦሮምኛ አስተማሩ የሚለው ኦሮሞ በአካባቢው ሳይኖር ነው። በእውነቱ  ቅዱሳን ያላስተማሩትን ማኅበረሰብ እንዳስተማሩ አድርጎ ማቅረብ፣ ባላስተማሩበት ቋንቋ እንዳስተማሩበት አድርጎ ማቅረብ የቅዱሳኑን ሥራና ታሪ  ማራከስ ነው። «አቡነ አኖሬዎስም በባሌ አካባቢ ሲያስተምሩ ኦሮምኛን ይጠቀሙ እንደነበር መዛግብቱ ይነግሩናል» ብሎ ታማኝነት በሌላቸው እቶፈንቶዎች ላይ በመመስረት የሚደርተው ዳንኤል ክብረትም በጻፈው መተያያ ያደረገው ይህንን ነው። አቡነ «አኖሬዎስም በባሌ አካባቢ ሲያስተምሩ ኦሮምኛን ይጠቀሙ እንደነበር መዛግብቱ ያሳያሉ» ሲል ዳንኤል ክብረት በድፍረት ስለተናገረው ጉዳይ  እስቲ ይህንን ታሪክ ያሳያል ያለውን አንድ የጥንት ቅጂ ወይም እናት መዝገብ አቅርብ በሉት?
ባጭሩ ዳንኤል ክብረት ኦሮሞ በሸዋ ከመስፋፋታቸው በፊት ከሌሎች ማኅበረሰቦች ጋር በሸዋ ምድር ይኖሩ እንደነበር ለማሳየት የጠቀሰው ገድል የተሳሳተ ቅጂና እናት መዝገብ የሌለውን የውሸት ገድል ነው። እናት መዝገብ የሌላቸው የውሸት ገድሎች ደግሞ በተለያየ ጊዜ ሲቀዱ ጸሐፊዎች ከመጀመሪያው ወይም ከእናቱ መዝገብ [Vorlage] ላይ የሌለ አዳዲስ ነገር ይጨምሩበታል። ዳንኤል በጠቀሰው ገድል ውስጥ የታየውም ይህ ነው።
በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ጥልቅ ምርምር ያደረገው ፕሮፌሰር ዶናልድ ክራሚ በኢትዮጵያ የጽሑፍ ባሕል የመሬት ስሪት የሕግ ሰነዶች ሳይቀር በየጊዜው ሲቀዱ ከእናቱ መዝገብ ላይ የሌለ አዳዲስ ነገር እንደሚጨመርባቸው እ.ኤ.አ. በ2011 ዓ.ም. «Gondär Land Documents: Multiple Copies, Multiple Recensions» በሚል ባሳተሙት ጥናት ጽፈዋል። ፕሮፌሰር ክራሚ ያጠኑት  በጎንደር ዘመን የተጻፉትን እቴጌ ምንትዋብ (1730-1769) ያሰሩት የደብረ ፀሀይ ቁስቋም ቤተ ክርስቲያን የስሪት መዝገብ ነው። እንደ ፕሮፌሰር ክራሚ ጥናት ከሆነ የደብረ ፀሀይ ቁስቋም የስሪት መዝገብ ቢያንስ ሶስት የተለያየ ቅጅ አለው። ምንም እንኳ ክራሚ ያጠኑት በጎንደር ዘመን የነበረው የኢትዮጵያን የጽሑፍ እና የሰንድ ባሕል ቢሆንም እናት መዝገቦችን መከለስ፥ ማስፋፋት እና አርትኦት ማድረግ በመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክም የነበረ፥ ስር የሰደደ እና ጥልቅ ታሪካዊ መሰረት ያለው አሰራር እንደሆነ ይገልጻሉ። ፕሮፌሰሩ ለዚህ አብነት ዳንኤል ክብረት በተደጋጋሚ የጠቀሰውን ገድለ ተክለ ሃይማኖትን  በማውሳት የተጨመረውን በዘመናት ውስጥ በገድሉ ስለተጨመሩ ጉዳዮች አቅርበዋል።
[ምንጭ፡ Crummey, D. (2011). Gondär Land Documents: Multiple Copies, Multiple Recensions. Northeast African Studies, ገጽ 36]
ገድለ ተክለ ሃይምኖትን በ1895 ዓመተ ምሕረት ጣሊያናዊ የታሪካዊ ስነልሳን ሙሑር ካርሎ ኮንቲ ሮሲኒ ወደጣሊያንኛ ተርጉመውታል። በመቀጠልም በ1906 ዓመተ ምሕረት እንግሊዛዊው ዋሊስ በጅ ገድሉን ወደ እንግሊዘኛ ተርጉሞታል። በኮንቲ ሮሲኒ ጥናት መሰረት እስካሁን የሚታወቀው ቀዳሚው የተክለ ሃይማኖት ገድል በፓሪስ ብሔራዊ ቤተ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው የመለያ ቁጥሩ MS. Et. 136 ተብሎ የተመዘገበው ሲሆን የተጻፈበትም ዘመን በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው። በጅ ወደ እንግሊዘኛ የተረጎመው በዋናነት በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተቀዳውን ለንደን እንግሊዝ ሙዚየም የሚገኘውን የመለያ ቁጥሩ Orient 723 ተብሎ የተመዘገበውን የገድለ ተክለ ሃይማኖት ቅጅ ነው።
ኮንቲ ሮሲኒ የተረጎመው ቀዳሚ የሆነውን በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዋልድባ ገዳም ከሚገኘው የተቀዳውን እና አሁን በፓሪስ ብሔራዊ ቤተ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን ገድለ ተክለ ሃይማኖት ነው። ዳንኤል ክብረት ግን ትልቅ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የሚጠቅሰው ይህንን የገድሉን ቅጂ አይደለም። ይህ ቀዳሚው የጻዲቁ ገድል የተወለዱበትን ቦታ ጽላልሽ ይለዋል። ዳንኤል ግን ታሪኩን ወደ ኦሮሞ ለማስጠጋት ሲል ጻዲቁ የተወለዱበት ኢቲሳ በማለት በእናት መዝገቡ የሌለ ታሪክን በእርግጠኛነትና በድፍረት ሊነግረን ይሞክራል። ጽላልሽ ወደ ኢቲሳ የተቀየረው ከኦሮሞ ወረራ በኋላ ነው።
በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተጻፈው የአቡኑ ገድል በኋላ በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከተቀዳው ጋር ከፍተኛ የሆነ ልዩነት አለው። ለምሳሌ የዋልድባው እና ቀዳሚው ገድል የሚጀምረው በተክለ ሃይማኖት የዘር ሀረግ እና የትውልድ ቦታ ነው። ገድሉ እንዲህ ይላል፦
«ናሁ ዜና ሕይወቱ ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት። ሙላዱሰ ምድረ አምሓራ እንተ ትሰመይ ባህረ ቀጋ። ወዘመዱ ሐርብ ጋሴ። ወእምህየ ፈለሰ ብእሲ ዘስሙ ይድላ ብሔረ ሴዋ ወበጽሐ ጽላልስ ወነበረ ምድረ ዛራሬ»
[ምንጭ፡ Rossini, C. C. (Ed.). (1896). Il” Gadla Takla Hāymānot” secondo la redazione waldebbana፥ ገጽ 102]
[ትርጉም፡ “የአባታችን የአቡነ ተክለ ኃይማኖንት የሕይዎት ታሪክ ተመልከቱ። የተወለደበት ሀገር ባህር ቀጋ ከተባለ ከአማራ ምድር ሲሆን ቤተሰቡም ሀርብ ጋሴ ይባላል። ከዚህ ቦታ አንድ ይድላ የሚባል ሰው ተነስቶ ከሴዋ [ሸዋ] አገር ወደ ጽላልሽ መጣ፣በዘራሬ መሬትም ተቀመጠ”]። ከአማራ አገር ባህረ ቀጋ ከተባለ ልዩ ስፍራ ተነስቶ ሸዋ ጽላሊሽ ውስጥ ዛራሬ ከተባለ ስፍራ የተቀመጠው ይድላ የተክለ ሃይማኖት 7ኛ አያት ነው።
በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተቀዳው በጅ ያሳተመው ኮንቲ ሮሲኒ ካሳተመው በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከተጻፈው ጋር የማይገኝ እጅግ በጣም ብዙ ነገረ የተጨመረ አለው። ለምሳሌ የተክለ ሃይማኖትን የዘር ሀረግ የሚጀምር ከአዳም ነው። ገድሉ መዕራፍ ፩። “ንቀድም በረድኤተ እግዚአብሔር መጽሐፈ ልደቱ ለአቡነ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ወልደ እግዚአብሔር በጸጋ ወወልደ አዳም በሥጋ። አዳም ወለዶ ለሴት […]” እያለ ከአዳም ጀምሮ እስከ ጻድቁ ተክለ ኃያማኖት ድረስ ትውልዱን ይዘረዝራል።
ይህ ሀተታ በጂ  ባሳተመው መጽሐፍ ውስጥ የተክለ የተክለ ሃይማኖት 7ኛ አያት ስለሆነው ስለ ይድላ የተገለጸበትም አውድ የኮንቲ ሮሲኒ ያሳተመው ከተገለጸበት ጋር በጣም ይለያል። [ ምንጭ Budge, E. A. W. (1906). The Life of Takla Haymanot in the Version of Dabra Libanos and the Miracles of Takla Haymanot in the Version of Dabra Libanos፥ ገጽ 1]
በገድሉ በምዕራፍ 5 ላይ በተጻፈው መሰረት አባ ይድላን ከ150 ሌዋውያን ካህናት ጋር ወንጌልን ይሰብኩ ዘንድ፥ ሰዎችን ያጠምቁ ዘንድ ወደ ሸዋ የላካቸው ድግናዛ የተባለው የአክሱም ንጉሥ ነው። ይድላም በትዛዙ መሰረት ሸዋ ውስጥ ጽላልሽ ተቀመጠ ይላል ገድሉ (ወዘተናገሩ ነገር ይከውን በጊዜሁ ወለአባ ይድላ ፈነወ ድግናዛን ንጉሥ ብሄረ ሸዋ ምስለ ፻ወ፶ ካህናት ክቡራን ሌዋውያን እለ ይነብሩ በመናብርት ከመ ያጥምቁ ኵሎ ሰብአ እለ ይነብሩ ውስቴታ ሊቆሙሰ አባ ይድላ ውእቱ። ወበጺሖሙ ሸዋ ነበረ አባ ይድላ ብሔረ ጽላልሽ”)። [ምንጭ፡ Budge, E. A. W. (1906). ገጽ 4]።  ከዋልድባ ቅጅ ላይ ግን የድግናዛ ስምም ሆነ ከይዳላ ጋር ወደ ሸዋ የተላኩ ካህናት ስለመኖራቸውም ምንም ነገር አልተጻፈም።
በቀዳሚው በዋልድባው ገድለ ተክለ ሃያማኖት ጻድቁ የፈፀማቸው ታምራት ሶስት ብቻ ናቸው። በጅ ባሳተመው በ18ኛው ቅጅ ግን በጠቅላላው 44 ታምራት ተጽፈው እናገኛቸዋልን። ስለዚህ ገድላት በየጊዜው በሚቀዱበት ጊዜ ከእናቱ መዝገብ ላይ የማይገኝ ብዙ ነገር ይጨመርባቸዋል። ለዳንኤል ክብረት ግን ይህ ጉዳዩ የሆነ አይመስልም። በመጽሐፉም ሆነ በማኅበራዊ ሜዲያ በሚለቃቸው አርቲክሎቹ የሚጽፈው ታሪክ ምንጩ በእናት መዝገቡ ላይ የማይገኝ ሳይሆን  ኋላ ላይ የተጨመረውን ያልነበረ ታሪክ እያጣቀሰ ነው።
ዛሬ ላይ ወለጋ የምትገኝን አንድ የማርያም ቤተክርስቲያን መገኛ አንድ ሰው ሲገልጽ «በኦሮምያ ክልል በምስራቅ ወለጋ ዞን የምትገኘዋ የማርያም ቤተክርስቲያን» ብሎ ሊጽፍ ይችላል። ከዛሬ መቶ ዓመት በኋላ የዚቺን ቤተክርስቲያን ታሪክ የሚያጠና ሰው የቤተ ክርስቲያኗ መገኛ ከጥንት ጀምሮ «በኦሮምያ ክልል በምስራቅ ወለጋ ዞን» የነበረው ቢመስለው እንደ ዳንኤል ክብረት አይነት የታሪክ ስህተት ይሰራል። ኦሮምያ ክልል የሚባለው መዋቅር የተፈጠረው ገና 28 ዓመቱ ነው። በወለጋም ኦሮሞ ከመስፈሩ በፊት ሌሎች ነገዶች ይኖሩበት ነበር። የግዛቱ ስምም ወለጋ አልነበረም። ወለጋ ወለጋ  የሆነው ኦሮሞ ወርሮ ስሙን ከለወጠው በኋላ ነው። ኦሮምያ ክልልም የተፈጠረው በወያኔና ኦነግ ዘመን ነው። ዳንኤል ክብረት የሚጠቅሳቸው የገድል ቅጂዎች እንዲህ አይነት ለውጥ ከተከሰተ በኋላ ተጨምሮባቸው የተጻፉት ያልነበሩ የቦታና የነገድ ስሞች የተካተቱባቸውን ቅጂዎች ነው።
አባቶቻችን ለታሪክና ለትውልድ የሚጨነቁ ጠንቃቆች ነበሩ። እናት መዝገብ የሌላቸው ማናቸውም ድርሳናት ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፉ ታሪክ እንዳያዛቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጉባቸው ነበር። እነዚህ ታላላቅ ኢትዮጵያውያ በዘመናዊው ዓለም የአርትኦት ስራ ሰርተው የሚያሰናዱ የታርካዊ እና ንጽጽራዊ ስነ ልሳን ሙሑራን የሚሰሩትን የሚሰሩ ነበሩ። የማይከጅሉ እጆች የነበሯቸው ታላላቆቹ አባቶቻችን የምዕራብ አገራት ዲግሪ ባይኖራቸውም ገና ጥንት የተዋጣላቸው Philologists ነበሩ።
ከእናት መዝገብ ላይ የማይገኝ ከፍተኛ የሆነ የታሪክ መፋለስ ያለባቸው ድርሳናት ሲገኙ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዳይተላለፉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጉ የነበሩ የኢትዮጵያ ነገሥታትም ነበሩ። ከነዚህ መካከል ቀዳሚው ተጠቃሽ ዳግማዊ ምኒልክ ነበሩ። ዶክተር ሱሳኔ ሁመል «The Disputed Life of the Saintly Ethiopian Kings ʾAbrǝhā and ʾAṣbǝḥa” በሚል ባቀረበችው ጥናት ዳግማዊ ምኒልክ የድርሳነ ኡራኤል ቅጂዎች ተመርምረው ሐሰተኛ ቅጂዎች እንዲወገዱ ስላደረጉት ታሪክ ታወሳለች።
ድርሳነ ኡራኤል የተጻፈው በዐፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግሥት ነበር። በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድርሳነ ኡራኤልን የሸዋ ሰዎች እንደገና ሲጽፉ ከእናቱ መዝገብ የማይገኝ ብዙ የተፋለሰ ታሪክ ሰለተገኘበት የዲማ ጊዮርጊስ ካህናት ለዐፄ   ምኒልክ ክስ አቅርበው ነበር። የድርሳነ ኡራኤሉ ቀዳሚው እናቱ መዝገብ እና በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተጻፉት ቅጅዎች በዘመኑ በነበሩት በአቡነ ማቴዎስ፥ በአጼ ሚኒልክ፥ በሊቅውንቱ እና በመኳንንቱ ፊት ጉባኤ ተጠርቶ ከተመረመረ በኋላ የተጻፉት ብዙ መሰረተ ቢስ ትርክት ተጽፎባቸው ተገኙ። በዚህ ምክንያት በኋላ የተጻፈው ድርሳነ ኡራኤል ከየአድባራቱ እየተለቀመ እንዲፋቅ እና እንዲቃጠል በጉባኤ ተወሰነ። ንጉሡም በውሳኔው መሰረት አዲሱ ድርሳነ ኡራኤል እንዲቃጠል ለየአድባራቱ ደብዳቤ ላኩ። ጋይንት ውስጥ ለሚገኘው ለቤተልሄም ቤተ ክርስቲያን ምኒልክ የጻፉትን ደብዳቤ ቀጥሎ አቅርቤዋለሁ፤
____
ሞዓ፡ አንበሳ፡ ዘእምነነገደ፡ ይሁዳ፡ ዳግማዊ፡ ምኒልክ፡ ሥዩመ፡ እግዚአብሔር፡ ንጉሠ፡ ነገሥት፡ ዘኢትዮጵያ፡ አሁን፡ እየተጻፈ፡ የሄደው፡ ድርሳነ፡ ኡሩኤል፡ ሁሉ፡ በሐሰት፡ በምቀኝነት፡ ያለውነት፡ ያለ [እናት] መዝገብ፡ በቃል፡ የተጻፈ፡ ነው፡ ብለው፡ ዲሞች፡ ቢጮሁልኝ፡ብሉይ፡ ድርሳነ፡ ኡርኤል፡ ሌሎችም፡ መጻሕፍት፡ አስመጥቼ፡ ባባታችን፡ በአቡነ፡ ማቴዎስ፡ ፊት፡ ደግሞም፡ እንጦጦ፡ ባሉት፡ ሊቃውንት፡ ፊት፡ በጉባኤ፡ ባስነብበው፡ [እናት] መዝገብ፡ የሌለው፡ ሐሰተኛ፡ ሆኖ፡ ተገኘ። ስለዚህ፡ ግን፡ በባቶቼ፡ ያልተገኘ፡ በኔ፡ ጊዜ፡ ሐሰተኛ፡ መጽሐፍ፡ ተጽፎ፡ ቢገኝ፡ ሀገሬንም፡ ያስነቅፈዋል፡ ደብሬንም፡ ያቀለዋል፡ ብዬ፡ ይፋቅ፡ ብዬ፡ አለሁ። የኡሩኤል፡ ድርሳን፡ የማይጠረጠር፡ የማይነቀፍ፡ የአመት፡ ድርሳን፡ አለውና፡ በዚያ፡ እንዲጻፍ፡ አዝዢአለሁ። ይሕነን፡ ሐሰተኛውን፡ ያልፋቀ፡ እንዳይፍቅም፡ ደብቆ፡ የተገኘ፡ ይቀጣ።
በጳጕሜን፡ በ፩ቀን፡ በእንጦጦ፡ ከተማ፡ በ፲ወ፰፻፹ወ፩፡ አመተ፡ ምሕረት፡ ተጻፈ።
[ምንጭ፡  Hummel, S. (2016). The Disputed Life of the Saintly Ethiopian Kings ʾAbrǝhā and ʾAṣbǝḥa. Scrinium, 12(1), ገጽ 69]
______
በዚያ ዘመን የኖሩ አባቶቻችን እናት መዝገብ የሌላቸው ሐሰተኛ ድርሳናት በሊቃውንት ጉባኤ  እንዲመረመሩና ሐሰተኞቹ እንዲወገዱ ይህን ያህል ጥንቃቄ ያደርጉ ነበር። በዚህ ዘመን የሚኖረው ዳንኤል ክብረት ግን እናት መዝገብ የሌላቸውን ገድላት እየጠቀሰ ፣ ጻድቃን ያልሰሩትን ታሪክ እየፈጠረ መጽሐፍት ያሳትማል፣ የውሸት ትርክት ያሰራጫል። «በኦሮምያ ቤተክህነት» እንመስርት ብለው ከተነሱት አንዱ «በመካከለኛው ዘመን በሸዋ በኦሮምኛ ክርስትና እንዳልተሰበከች ሁሉ እንዴት ዛሬ በኦሮምኛ አትሰበክም?» ሲል ያቀረበውን መከራከሪያ ያጣቀሰው ዳንኤል ክብረት «አራቱ ኃያላን» በሚል ያለ እናት መዝገብ የጻፈውን መጽሐፍ ነው። በዚህ ዘመን እንደ ዳግማዊ ምኒልክ ለአገርና ለትውልድ የሚቆረቆር አባት ቢኖር ኖሮ እናት መዝገብ የሌለው ሐሰተኛ ገድል ላይ የተመሰረተው የዳንኤል ክብረት ሐሰተኛ መጽሐፍ ይፋቅ ይል ነበር።
ባጭሩ የዳንኤል ክብረት ጽሑፍ የታሪክን የሙያ ስነ ምግባር ተከትሎ በኃላፊነት የተጻፈ የታሪክ ጥናት ሳይሆን በድፍረት እናት መዝገብ ከሌለው በኋላ ዘመን እየተጨመረበት ከተገለበጠ የሐሰት መዝገብ የተጻፈ እጅ መንሻ፣ መተያያና የፖለቲካ ጽሑፍ ነው።
Filed in: Amharic