>

“አቢይን ያመነ ጉም የዘገነ!” - ብለን ነበር ሰሚ ጠፋ እንጂ (ዳግማዊ ጉዱ ካሣ)

“አቢይን ያመነ ጉም የዘገነ!” – ብለን ነበር ሰሚ ጠፋ እንጂ

ዳግማዊ ጉዱ ካሣከመጋላ ፌዴራሊ ኡመታ ኦሮሚያ ፊንፊኔ

ምዕመናን! “የፈሩት መድረሱ የጠሉትም መውረሱ” የነበረና ያለ ነው፡፡ የወደፊቱን ጊዜ በጭላንጭልም ቢሆን የምናይ ጥቂት ሰዎች ብዙ ተናግረናል፤ ለፍልፈናል፡፡ ይሁንና ሰዎች መስማት የሚፈልጉት መቃብር ውስጥ አሊያም ቁስላቸውን እያከኩ መሆኑ የማይወጡት ክፉ ዕጣ ሆነና እስካሁን ሰሚ አልተገኘም፡፡

“ከወደ ጅማ አንድ መልከ መልካም ሰባተኛ ንጉሥ በኢትዮጵያ ይነግሥና የትሮይን ፈረስ እየጎተተ ከህንድ ውቅያኖስ ወደ መሀል ደጋማው የኢትዮጵያ ክፍል ቀጥሎም ወደ ሰሜኑ ነባር አቢሲኒያ ያቀናል፡፡ በፈረሱ ውስጥ የተጫኑት መደዴና ዋልጌ አክራሪዎች ከፈጣሪ በተሰጠቻቸው በጣት የምትቆጠር የጥፋትና ውድመት ጊዜ ሁሉንም ነገር እንደ አንበጣ ይረመርማሉ፡፡ ከዚያም ንጉሣቸው ማር የተለወሰ መርዘኛ ምላሱን ተቆርጦ ወደ ታሪክ ጓዳ ሲወረወር የነሱ ጊዜም ያከትማል፡፡ በተረኝነት ስካር የጀመሩትን ጭፈራ ሳይጨርሱ ከምሥራቅ አቅጣጫ ባለከዘራው ንጉሥ ይመጣና መሀል አዲስ አበባ በምኒልክ ቤተ መንግሥት ይሰየማል፡፡ ያኔም የኢትዮጵያ የዘመናት ፍዳ አብቅቶ የዕዳ ደብዳዋም ተቀዳዶ ይጣልና ስደት ወደ ኢትዮጵያ ይሆናል፡፡” 

የሚል ትንቢት ሰምቼ ቢሆን ኖሮ  በደስታ ተውጬ አሁኑኑ በዚህች አጋጣሚ እናገረው ነበር፡፡ ግን አልዋሽም አልሰማሁም – ቢያንስ በዚህ መልኩ፡፡

አንድ መሠረታዊ እውነት ግን ልናገር፡፡ አንድ ወገን ጠላት እያበዛ በሄደ ቁጥር የራሱን ኃይልና የደጋፊ ብዛት እያመናመነ ይሄዳል፡፡ ትዕቢትና ዕብሪት ደግሞ ጉዳታቸው በአንድ አዳር አይታወቅም፡፡ የደርግንና የወያኔን ድምበር-የለሽ ትምክህት ማሰብ ይገባል፡፡ ማንም አይነካንም ብለው በትዕቢት ታውረው ሳለ ባላሰቡት መንገድና ባልጠበቁት ሁኔታ ድምጥማጣቸው ጠፍቷል፡፡ ቀን ሲጥል እንዲህ ነው፡፡ 

የነዚህ “ሰዎች” ጅልነት ደግሞ መለኪያ አጣ፡፡ “ጅል አይሙት እንዲያጫውት” መባሉ ትክክል ነው – የኞቹ ጅሎች ጅልነት ከማሳቅና ከማሳቀቅም አልፎ የስቃያችን ምንጭ ሆነ እንጂ ክፋቱ (እንዴ! የማስተዳደር ችሎታ የላቸው፣ ፍትህ ርትዕ አያውቁ ….ከነዚያኞቹ ምሥጦች እኮ ዕጥፍ ድርብ የበለጡ አጋንንት ሆኑ!)፡፡ ባለፉት 20 ወራት ብቻ የሠሩትንና አሁን ትናንት ደግሞ የሰጡትን ወታደራዊ ሹመት ስናይ በርግጥም እነዚህ ሰዎች አብደዋል ያሰኛል፤ ይህም ብቻ አይደለም – ይሉኝታቢስነትና ሀፍረት የለሽነትም የሚኮረጅ ወይም በተጋቦት የሚተላለፍ መሆኑንም ታዝበናል፡፡ አንድ ሕጻን እንኳን እንደዚህ አያደርግም፡፡ የተሹዋሚዎችን የስም ዝርዝር ስትሰሙ በሀፍረት የምትገቡበትን ታጣላችሁ – እኔ በበኩሌ ስለነሱ በሀፍረት ተሸማቀቅሁ፤ ሰው ነኝ የሚል ፍጡር እስከዚህን የዘቀጠ ደረጃ አይወርድም፤ የሚጠራው ሁሉ ደጃሳና ጉርሜሳ፣ ጫልቱና ዱጋሳ ነው – አንድ ሻል ያለ መካሪ ሰው እንኳን የላቸውም? ስለአቢይ ኢትዮጵያዊነት ያሽቃብጡና ገና ሳያስነጥሰው መሀረብ ያቀርቡ የነበሩ አሽቋላጮች አሁን ምን እንደሚሉ መስማት እፈልጋለሁ፡፡ በመሠረቱ ሁሉም ሰርቤሳም ሆነ ጫልጪሳ ቢሆን ለኔ ችግሬ አይደለም – ችግሩ is the intention behind this modus operandi. በአፄው ወይም በደርግ ዘመን ቢሆን ለምሣሌ አጋጣሚ ነው ብለህ እንዲሁ ታልፈዋለህ – ከናካቴውም ላታስበውም ትችላለህ፡፡ አሁን ግን የዘር ተዋፅዖ በገነነበትና ጠቀመም አልጠቀመም በዜጎች በጉጉት በሚጠበቅበት ሁኔታ እንዲህ ያለ ዕውርነት ውስጥ መግባት የራስን መቀበሪያ ጉድጓድ በይድረስ ይድረስ አርቆ መቆፈር ነው፡፡ መምህሮቻቸው ወያኔዎች ራሳቸው በአሽሙር ፈገግ ሳይሉባቸው አይቀሩም (አንድ ሕጻን ልጅ አባቱ ውሸት እንዲያስተምረው ይጠይቀዋል አሉ፡፡ ትምህርቱ ቀጠለ፡፡ በአባት ቀጭን ትዕዛዝ ሁለቱም ወደ ሰማይ አንጋጠጡ፡፡ አባት ለልጅ ‹ገበሬዎች በነጫጭ በሬዎች እያበራዩ ጤፍ ሲወቁ ይታዩሃል?› ከማለቱ ልጅ ቀበል አድርጎ ‹ውይይይ… አባዬ ጉድ ሆንኩልህ!› ብሎ ማልቀስ ይጀምራል፡፡ አባት ደንግጦ ‹ምን ሆንክ ልጄ?› ብሎ ቢጠይቀው ‹ዕብቁ ዐይኔ ውስጥ ገባ!› ይለዋል፡፡ ያኔ አባትዬው “አሃ! ከኔው በልጠህ የለም እንዴ! ምኑን ውሸት አስተማርኩህ ታዲያ!› በማለት የዕለቱን ክፍለ ጊዜና ጠቅላላ ፕሮግራሙን ዘጋው ይባላል፡፡ አባት ወያኔና ልጅ ኦህዲድ/ኦነግም እንደዚሁ ናቸው)፡፡ ያጠመዱት ፈንጅ ሁሉ በሙሉ ግርማ ሞገሱ ሲገለጥ የገፈቱ የመጀመሪያ ቀማሾች ግን እነሱው ናቸው፡፡ ያኔ እነሱን አያድርገኝ! ለቀንም ቀን አለውና ይህን እንጠብቅ፡፡

እንግዲክ ልበልና ነገሬን ልቀጥል እንደኃይሌ ገ/ሥላሤ – እንግዲክ ኦነግ ማለት ማሰብ የማይችሉ የነፈዞች ስብስብ ነው ማለት ነው፡፡ ሁሉንም ነገረ ሥራቸውን ስታዩ የሰው መዓዛና ሽታ የለባቸውም፡፡ የወለጋውን የተማሪዎች እገታ ድራማ፣ የወለጋ ባለሥልጣናትን ግድያ፣ ኦርቶዶክስን የማጥፋት ዘመቻ፣ ከነባሩ የሀገራችን ባንዲራና ከአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለማቱም ጭምር ያላቸውን ጠብ ያለሽ በዳቦ፣ ጴንጤንና ሙስሊም አክራሪዎችን እየመረጡ ትላልቅ ሥልጣኖችን የማደል የቂል ተግባር፣ አማራ ጓዳ ድረስ በመግባት ያከናወኑትን ምርጥ አመራሮችን የመግደልና ምናልባትም የማገዳደል ሥራ፣ ኢንጂኔር ስመኘውን የማጥፋትና ራሱን በራሱ ነው ያጠፋው የማለት ሚዛን የማይደፋ ከንቱ ሙከራ፣ በጠ/ሚኒስትራቸው በኩል በየጊዜው የሚሰራጨው የውሸት መድብልና ጉንጭ አልፋ የተስፋ ዳቦ ቱሪናፋ (ለአብነት ነዳጅ ወጣ፣ ባመጠቅነው ሣተላይት “በቀን አሥር ጊዜ ልንመገብ” ተቃርበናል ዓይነት የቁጭ በሉ ቱሪናፋ፣…) … ሁሉ ሲቃኝ እነዚህ ሰዎች “ይች ሰው ቸኮለች ልታድር ነው መሰል” ያስብላሉ፡፡

ይህን የጨለማ ዘመን አጥብቀው የሚተጋሉ ሰዎች ያስቀኑኛል፡፡ በተለይ የዘሃበሻው ሄኖክ ዓለማየሁና የዩቲዩቡ ዮሴፍ ይጥና የተለዩ ናቸው፡፡ ሌሎችም አሉ፡፡ በጨለማ ዘመን ፋኖስ ሆኖ ሀገርንና ሕዝብን ማገልገል በመሬት ባይሆን በወዲያኛው ዓለም ትልቅ ዋጋ አለውና በርቱልኝ ልጆቼ፡፡ልጅም ይውጣላችሁ፡፡

ዛሬ ጧት የዮሴፍ ይጥናን የሰሞኑን የኦነግ ሹመት የሚመለከት ትንታኔ ስሰማ ደነቀኝ – (ለዚህ መሆን አለበት የላይኛዋን አንቀጽ በድንገት የጨመርኩት)፡፡ ሰዎቹ በርግጥም ዮሴፍ እንዳለው ለይቶላቸው አብደዋል፤ በሥነ ልቦናዊ ትራኮማም ታውረዋል፡፡ መታወራቸውን ግን በበኩለይ በበጎ ጎኑ ነው የምወስደው፡፡ ኦነግ እንደወያኔ ብልጥ ቢሆን ኖሮ መከራችን ይረዝም ነበር፡፡ ወያኔዎች 27 ዓመታትን የቆዩት መሠሪዎች ስለሆኑ እንጂ እንደኦነግ ጀዝባ ቢሆኑ ኖሮ ሦስት ዓመትም ባልቆዩ፡፡ ቢሆንም ግን በተለይ አማራው ላይ  የሠሩት ግፍና በደል መቼም አይረሳም – ሒሣቡን ማወራረዳቸው የማይቀር መሆኑ እንዳለ ሆኖ ነው ታዲያ፡፡ አማራው ዝም ስላለ ማንም እንደፈለገው ተጫውቶበት ዋጋ ሳይከፈለው የሚቀር ከመሰለው ተሳስቷል፡፡ ወያኔን ጠይቁ፡፡ ወያኔ አሁን ለደረሰበት “የዕድገት ደረጃ” ሊደርስ የቻለው በቄሮ ጫጫታና በጃዋር ላፕቶፕ (ብቻ) ነው ካላችሁኝ እስቃለሁ – ላፕቶፕ ፈተናን ከማሰረቅ የበለጠ ወንጀል አልሠራም፤ ያም ገና በሀገር ሀብት ብክነት የሚያስጠይቅ ወንጀል መሆኑን ልብ ይሏል -ህጋዊና ሕዝባዊ መንግሥት ሲኖር/ረን የሚነሳ ጉዳይ ነው፡፡

ኦነግ በዚህ ጅልነቱ ይቀጥል፡፡ መልካም ነው፡፡ አሁን የማን ምንነት ቁልጭ ብሎ የሚታይበት ወቅት ላይ ነን፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የኅልውና አደጋ እንደተደቀነበት ይበልጥ እየተረዳ ነው፡፡ እስካሁን አብሮነቱና አንድነቱ እንደሚጠቅመው አውቆ ኢትዮጵያዊነትን ሳይለቅ የቆዬው በአብዛኛው አማራው ነው፡፡ ይህን ጎራ የለቀቁ የሚጎዱበት፣ ይጠቅመኛል ብለው የያዙት ደግሞ የሚካሱበት ዘመን በፍጥነት እየመጣ ስለመሆኑ ዕድሜ ለወያኔና ለኦነግ አሁን ላይ ፍንትው ብሎ እየታዬ ነው፡፡   

ለማንኛውም ድኙና ቀበርቾው እየተጨሰ ነው፡፡ ጠበሉም እየተረጨ ነው፡፡ ዱኣና ጸሎቱ፣ ፆምና ሶላቱም በየአምልኮት ቤቶች እየተካሄደ ነው፡፡ እናም ቡዳውና ረጋው በቅርቡ ይለይና ጥጉን ይይዛል፡፡ አንፍራ፤ ብዙም አንጨነቅ፡፡ ሞትንም ኖርንም በአንድዬ የምናምን ከሆነ ምን ጊዜም የርሱው ነንና ከልክ በላይ አንጠበብ፡፡

አየህ – ግም ለግም አብሮ እየተደናበረ ይህችን ሀገር ለማጥፋት ሲያሴር ደግ ደጉ በአንድ ማዕድ ይሰባሰባል፡፡ ከዚያም አማራው ሶማሌ ይሆናል፤ አፋሩ አማራ ይሆናል፤ ጋሞው ሶማሌ፣ አፋሩም ኮንሶ ይሆናሉ፤ አማራው ጉራጌ ጉራጌውም ደራሳ ይሆናሉ፤ የመኖር ፍላጎት ሲያስገድዳቸው – የቀትረ ቀላሎች ግፍና በደል ሲጠንባቸው – የባለጊዜዎች ዱላ ሲጠናባቸው … ወደ አንድነቱ ጎራ ይመሰጋሉ … ሥሌቱ በዚህ ይቀጥልና የመኖር እስትንፋሱ ኢትዮጵያዊነት ብቻ የሆነው የተናቀው ሰፊ ሕዝብ ክንዱን ያስተባብራል፡፡ ሲያጎርሱት የማያላምጥ፣ ሲመቱትም የማይመክት የለምና ምንም እንደማያመጣ ታስቦ በነዚህ ነፈዞች የተናቀው ሕዝብ ላለመጥፋት ሲል በአንድነት ይቆምና የማይቀረውን የመጨረሻ የሞት ሽረት ትግል ያካሂዳል፤ ያኔም እነዚህን የታሪክ አዛባዎች ዋጋቸውን ይሰጣቸዋል፡፡ ለተኩሱ አትጨነቁ፡፡ ለማነጣጠሩ አታስቡ፡፡ ለጀግነንቱም አትስጉ፡፡ ለወሬውም እኛም አለንና አትሰቡ፡፡ ከላይ እስኪታዘዝና ልቦናችን ወደርሱ እስኪመለስ እንጂ እነዚህ ጥቅምና ሥልጣን ከየተሸሸጉበት ሰብስቦ አራት ኪሎ ያከማቻቸው ጉዶች በአንድ ጀምበር እንደጉም ይበናሉ፡፡ ተስፋ ብቻ አይደለም – የማይቀር እውነት እንጂ፡፡ ላምም እኮ በሬን ያሸነፈች’ለት ምድር አትበቃትም፡፡ እነዚህም የላም አሸናፊዎች ናቸው፡፡

ግዴለም፡፡ በክፍለ ሀገራት ቀርቶ በአዲስ አበባም ጭምር የዘንድሮን ጥምቀት – 2012 – በተለመደው መልክ ላናከብር እንችላለን፡፡ ማዕከላዊ ሥልጣኑ የተያዘው በጉግማንጉጎች በመሆኑ ብዙ ያፈነገጡ አሠራሮችን ልንታዘብ እንችላለን፡፡ ፖሊሱም ፌዴራሉም መከላከያውም በአብዛኛው ኦነግ/ኦህዲድ በመሆኑ ኢትዮጵያዊነትን መሬት ረግጠው ሲረመርሙ ልናይ እችላለን – ከሰሞኑ ሹመት የምንረዳውም ይህንኑ ነውና፡፡ በየእሥር ቤቱ ብዙ ጉድ ልንሰማ እችላለን – እየሰማንም ነው፡፡ ተረኝነት ያሳበዳቸውና ኅሊናቸውን ያስጣላቸው ዕብዶች እጅግ ብዙ ማስጠሎ ተግባራትን ሲያደርጉና ሲያስደርጉ ልንሰማ እንችላለን፡፡ ቢሆንም ኢትዮጵያ ሞታ መነሳት ብርቋ አይደለምና በጣም በቅርቡ – በኔና ባንተ/ባንቺ ሕይወት – ትንሣኤዋን እናያለን፡፡ ይብላኝ ለካዷት፡፡ ይብላኝ በስንት መከራ የሚገኝን የአሜሪካ ዜግነት ሣይቀር ወርውረው ሕዝብን በማፋጀት ለሚገኝ ፔትሮዶላር ለተንበረከኩ ጉዲፊቻዎች! ወዮ ለነዚያ እየቀዘቀዝ ለሚሞቅ ሀብትና ገንዘብ ብለው ኢትዮጵያን ለካዱ አማሮችና ሌሎች ዘውጎች! ወዮ ለሆዳሞች! ይህችን ጠባብ ድልድይ አይሻገሯትም!!

መጥምቁ ዮሐንስ “መንግሥተ ሰማይ ቀርባለችና ንስሃ ግቡ!” እያለ ብቻውን በበረሃ ይዞር ነበር – አንበጣ እየተመገበ፡፡ አዎ፣ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን – አልሃምዱሊላ – የኢትዮጵያ የከፍታ ዘመንም እየመጣ ነው፡፡ ይህን በኩራት እንመሰክራለን፡፡ እነዶ/ር አቢይ ሊያንኮታኩቷትና ለጠላት ሊሸጧት የሚፈልጓት ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከነሙሉ ክብሯ ትነሳለች፡፡ ያኔ ለክፋትና ለተንኮል ተልእኳቸው ሲሉ የተውትን የውጭ ዜግነት ቢፈልጉት አይገኝም፡፡ አሁን ግን ይፏልሉ! “ጊዜ ገቢር ለእግዚአብሔር፡፡” ሁሉም በጊዜው ይሆናል፡፡ ይደረግልናል ብለንም እናምናለን፡፡ መልካም የጥምቀት በዓል፡፡

Filed in: Amharic