>

ሲነርጂ (Synergy) የመደመር በሻሻ!!! (ግዛው ለገሰ)

ሲነርጂ (Synergy) የመደመር በሻሻ!!!

ግዛው ለገሰ
የዛሬ 13 ዓመት፣ እንዲያውም ከዚያ በላይ አይሆንም ብላችሁ ነው፣ ከፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ ነው ስለ ሲነርጂ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት፡፡ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ አዳራሽ ሌክቸር ሲሰጡ ከኋላ ቁጭ ብለን እየሰማን ነው፡፡ «A whole that is greater than the sum of its parts» እያሉ በአማርኛም እየተኮላተፉ ፕሮፌሰሩ ሲነርጂን ሲያብራሩ በሰዓቱ «ሾጥ ናቸው እንዴ?» በማለት በዓይን ተጠያይቀናል፡፡ ሆ! ምን ማለት ነው ከድምራቸው የላቀ? ከአዳራሽ ከወጣን በኋላ ግን ሀሳቡን ተረዳነው፡፡ ደስ የሚል ነገር አለው፤ ግን ደግሞ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ሁላችንም እንደየመጠኑ ስንኖረው የነበረ ጽንሰ-ሀሳብ ነው(ነበር)፡፡
ዛሬ በሻሻ ላይ እንደፀበል የፈለቀ የሚመስለን «መደመር» መነሻውም፣ ሁሉ ነገሩም ሲነርጂ ነው፡፡ «συνεργός» (synergos) የተሰኘ ግሪካዊ ስረ-ቃል ሁሉ አለው፤ ትርጉሙም «አብሮ መስራት» ማለት ነው፡፡ (እንደማስታወሻ፣ ፕሮፌሰሩ በ97 እንደፔንዱለም አንዴ ቤተመንግስት አንዴ ቃሊት ሲወዛወዙ መቆየታቸው አይዘነጋም፡፡)
«መደመር» ቀሽም ቃል ነው፡፡ የሲነርጂ ጽንሰ-ሀሳብ እኮ ከነገሮች ተራ ድምር የላቀ «ምሉዕነት» ስለመፈጠር የሚተነትን ነው፡፡ ከመደመር በላይ ነው፤ በቅንጅት የሚመጣ ውጤት ነው፤ በመስተጋብር የሚፈጠር ምንነት ነው፡፡ ምክንያትም፣ ውጤትም ነው፡፡ በጣም ደስ የሚል ነገር አለው፤ ግን «ባምር ጠላሁ!» ብላልች ሴትየዋ፡፡
በነገራችን ላይ ይህን ስፅፍ ሲነርጂን ወይም መደመርን ለማርከስ አይደለም፤ ይልቁንም ለማግዘፍ ነው፡፡ ሲነርጂን ከተለያየ አውድ እና ዲሲፕሊን አንፃር ስንት ፀሐፍት እያዳበሩት ዘመናትን እንዳስቆጠሩ፣ ይህን ሊንክ ብቻ ፈትሹ፡፡ (https://en.m.wikipedia.org/wiki/Synergy)
ታዲያ ምን ለማለት ነው፣ ሲነርጂ የመደመር በሻሻ ነው፤ ማለትም መፍለቂያ ነው፡፡ ግን የትም ይፍለቅ መልካም ነገር አለው፡፡
ሰይፉ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ቀርቦ ሲጨዋወቱ ስለ ራዕዩ ሲጠይቀውና እርሱም ስለመደመር ሲያብራራ «የጠሉኝ ገብቷቸዋል» ሲል ስቅጥጥ ያላለው ካለ መደመር አልገባውም፣ ማለትም የአብይ (ጭፍን) ወዳጅ ነውና (እንደማለት ይቆጠራል)፡፡ አብይ እግዜር ይስጠውና ወዲያው በግማሽ አስተካከለውና «የሚቃወሙኝ» ሲል አስተካከለው፡፡ አብይን አልጠላውም፣ እንዲያውም አደንቀዋለሁ፡፡ አንዳንዴ የሚሰራው ሾው ምናምን እና አጉል እንደሕፃን ሊቆጥረኝ(ን) ሲፈልግ ያናድደኝና ለተወሰነ ቀን «ወለ በል!» ብለውም ስር-ሰደድ ተቃውሞ እስካሁን የለኝም፡፡ እየገባቸው የሚቃወሙት፣ ሳይገባቸው ከሚደግፉት አይሻሉትምን?
«መደመር» በተለያየ ቋንቋ ይተረጎማል ሲባል ነበር፡፡ ከሁሉም የምፈራው ለሲነርጂ አቻ ቃል በማጣት «መደመር» የሚል ርዕስ ከሰጠ በኋላ፣ በእንግሊዝኛ ሲተረጎም «Medemer» ብሎ እንዳያወጣው ነው፡፡
አንድ የመጨረሻ ነገር ላንሳ፣ አብይ በሚቀጥለው ምርጫ የማሸነፍ (የበለጠ) ዕድል የሚኖረው የት ቢወዳደር ነው? በሻሻ ወይስ አዲሳባ? የትስ የሚወዳደር ይመስላችኋል፡፡ እንደኔ እንደኔ አዲሳባ ቢወዳደር ይሻለዋል፤ ነገር ግን እርሱ የሚወዳደረው በሻሻ ይመስለኛል – ያለ ነገር ከፍ ከፍ አላደረጋትም፡፡
Filed in: Amharic