>

“አብዮታዊ ዴሞክራሲ ሊቀጥል የሚችለው ህብረተሰቡ ከተጋጨ፣ ከተፋጨና  ከተከፋፈለ ነው!!!" (አቶ ንጉሱ ጥላሁን)

አብዮታዊ ዴሞክራሲ ሊቀጥል የሚችለው ህብረተሰቡ ከተጋጨ፣ ከተፋጨና  ከተከፋፈለ ነው!!!”

አቶ ንጉሱ ጥላሁን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ
•  አብዮታዊ ዴሞክራሲ በባህሪው ቤተኛና አልፎ ሂያጅ በሚሉ ልነቶች ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ በመሆኑ ነው። ከፋፋይ ስለሆነ ነው።
•  አብዮታዊ ባህሪ ሲጀመር ከፋፋይ ነው። ጠላትና ወዳጅ ብሎ ይከፍላል፤ ጠላትና ወዳጅ ብሎ ሲከፍል ነበር፤
•  አብዮታዊ ዴሚክራሲ በባህሪው የሚከፋፍል በመሆኑ ዴሞክራሲያዊነትን ሊላበስ አይችልም። ከሥር ነቅሎ ሊተክል፣ አጥፍቶ አፍርሶ ሊገናባ ያሰበ በመሰረታዊነት ዴሞክራሲን እውን ሊያደርግ አይችልም።
•  አሁንም ችግር ውስጥ እንድንገባ ያደረገንና ከችግሩ ለመውጣት እየጣርን ያለነው አብዮታዊ ዴሞክራሲ ባመጣብን ጣጣ ነው።
•  አሁን ያለንበት ፈተና የዛሬ 25 ዓመት የቀበርነው ነገር ነው። ይህንን በሰነድ አስቀምጠናል። እዚህ ላይ በአግባቡ አልሠራንም ብለናል።
•  ይህንን ስንወስድ እንግዲህ ጥያቄ የጠየቀ፤ ሃሳብ ያነሳ፤ የታገለ የሚፈረጅበት፤ ብሎም መስዋዕት የሚሆንበት፤ የኦሮሞና የአማራ ወጣቶች፤ ምሁራንና ለውጥ ፈላጊዎች እስር ቤቱን የሞሉበት ጊዜ እየሆነ መጣ።
•  የአማራን ህዝብ ጥያቄ ማንሳት ትምክህተኝነት፤ የኦሮሞን ህዝብ ጠያቄ ማንሳት ጠባብነት በሚል ያስፈርጇል።
•  አብዮታዊ ዴሞክራሲ ባመጣው ጣጣ ዩኒቨርሲቲዎች ዓለምአቀፋዊ ተልዕኳቸውን ትተው በዘር፤ በጎሳ ተከፋፍለው በዶርም ጭምር መታጠር ጀምረዋል። አብሮ ለመብላት፤ ለመጠጣት፤ ለመኖር የሚቸገር ትውልድ ተፈጥሯል። ወደ መንግሥት መስርያ ቤትም ይሁን ወደ ግሉ ዘርፍ ስንመጣ የጠበበ ጎጠኝነት ነግሷል።
•  ምን ማለት ነው ይሄ! ጭራሹንም የሚወድም የሚጠፋ፤ የማይደመጥ የማይሰማ መወገድ ያለበት አካል አለ ማለት ነው።
•  ዴሞክራሲ ባለበት የማይደመጥ የማይሰማ የሚጨፈለቅ የለም።
•  የኢህአዴግ  ፀረ ዴምክራሲያዊነት  ወደ ውጪም ወደ ውስጥም ነው። ወደ ውስጥ ሲባል ደርጅቱ እርስ በእርሱ የማይደማመጥ፤የሃሳብ ነፃነት የሌለበት ወስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ የኮሰመነበት፤ጥቂት አድራጊዎች፤ ፈጣሪዎች፤አዛዦችና ናዛዦች በደርጅቱ ውስጥ የጎለበቱበት ነው፣
•  ሌላው ግን ወይ አድር ባይ ሆኖ የሚቀመጥበት፤   አይሆንም ብሎ የሚቃወም ደግሞ የሚፈረጅበት ፤ዕጣ ፋንታውም መራር የሚሆንበት ሁኔታ እየጎበለተ የመጣበት ጊዜ ነበር።
•  የኢህአዴግ መገለጫ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰት ጉዳይ ነው። ድርጅቱ ዜጎች በሃሳብ በመለየታቸው፤ ሃሳባቸውን በማራመዳቸው ብቻ ጥፍር የሚነቅል፤ የሚያኮላሽ፤ የሚያሰቃይ፤ የሚገርፍ፤ ድርጅት ሆነናል ብሎ ገምግሟል።
•  በዚህ ላይ ህብረተሰቡ ብቻ የሚያነሳው ሳይሆን በተጨባጭ ግፍ በተሠራባቸው ሰዎች ጭምር ማስረጃ እየቀረበ ግምገማ ተደርጎበታል።
•  ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ያለመኖር ነው። ይህ በግምገማ ውቅት ጎልቶ የወጣ ቢሆንም ወደ ኋላ ተድበስብሶ ታልፏል።
•  የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጉዳይ የፌዴራል ስርዓቱን ጥያቄ ውስጥ አስገብቷል። በመሰረተ ልማት፤በመንገድ፤በመብራት የፍትሐዊነት መጓደል በጉልሁ ታይቷል። እልፍ ሲልም ካሳ የሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች አሉ ተብሎ በተጨባጭ ማስረጃዎች ቀርበዋል። ሆኖም ተድበስብሰው ቀርተዋል።
•  የተደራጀ ሌብነትና ዘረፋም በድርጅቱ ውስጥ በስፋት ታይቷል። ይህም ግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ እንደ ስርዓት የተመራ ነበር። ለአብነትም የልማት ባንክ ብድር፤በጋምቤላ፤ በቤኒሻንጉል፤ በአፋር ፤በሶማሌ ክልሎች የተቀነባበሩ ዘረፋዎች እየተነሱ ግምገማዎች ተካሂደዋል።
•  ሀቁ ወጥቶ ህዝቡ እንዲያውቀው የሚፈልጉ አመራሮች ፤በሌላ በኩል ይህ የለም ብለው የሚሸመጥጡ ወገኖች በአንድ በኩል ሰፊ ክርክሮች አድርገዋል።
•  ድርጅቱ እነዚህን ችግሮች አራግፎ በአዲስ መልክ እንዲጓዝ በጥልቅ ተሃድሶ አቅጣጫ ተይዟል። በእዚህ ሁኔታ ውስጥም እያለ የ2010 ለውጥ ተወለደ።
•  የህዝቡ እንቢተኝነትና የድርጅቱ የውስጥ ትግል ተመጋግበው ድርጅቱ ራሱን እስካልቀየረ ድረስ የኢትዮጵያን ህዝብ የመምራት ቁመና ላይ እንዳልሆነ ግልጽ ብሎ ወጣ።
•  ጥያቄው የድርጅቱ ብቻ ሳይሆን የህዝብ ጥያቄ ነው፤ ሀገር የማስቀጠል ጥያቄ ነው፤የህልውና ጥያቄ ነው የሚል በእንድ ወገን፣ የለም ይህ የትምክህተኞችና የጠባቦች ሃሳብ ነው የሚል በሌላ ወገን ትግል የተደረገበትና በመጨረሻም በሚያስደንቅና በሚያስገርም ሁኔታ ያለምንም የጥይት ጩሀት፤ በአዳራሽ ትግል ለውጡ ዕውን የሆነበት ሁኔታ ተከሰተ።
•  የኢትዮጵያ ህዝብ በየትኛውም አካባቢ፤ የትኛውም ህዝብ በነበረን የረጅም ጊዜ ታሪክ አብረን ተሰናስለን ኖረናል። በድንገትም የተገኘ፤ በድንገትም የሚለያይ አይደለም።  በዚህ ሂደት የታሪክ ጠባሳዎች አሉ፤ መልካም ጎኖችም አሉ።
•  የኦሮሞና የአማራ ህዝብ ግንኙነት ወይም ደግሞ በተለምዶ አጠራር ‹‹ኦሮማራ›› የተባለው አንዳንድ ሰዎች ሁለትና ሦስት ሰዎች በአንድ ሰሞን ግንኙነት ያስተሳሰሩት ያገናኙት አድርገው ይገልፃሉ።
•  የኦሮሞና የአማራ ህዝቦች ትናንትና ዛሬ የተገናኙ አይደሉም። ጥንት ነው ግንኙነታቸው። አብረው ኖረዋል፣ ተዋልደዋል ፣ ተጋምደዋል። እኛ ፖለቲከኞች ግን አበላሸነው።
•  በተሃድሶ ወቅትም ከተለዩት ዋነኛ ችግሮች ውስጥ ብሄራዊ ማንነትንና ኢትዮጵያዊነትን አጣጥሞ ያለመሄድ ችግር አንዱ ነው፤ ወደ ብሄር ማንነት የማድላትና ኢትዮጵያዊነትን የማኮስመን ችግር እንዳለ ተማምነን ወጥተናል።
ምንጭ አዲስ ዘመን ጥር 5 ቀን 2012 ዓ.ም
Filed in: Amharic