>

የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች አነጋጋሪ ንግግሮች!!! (ዶቼ ቬለ - ታምራት ዲንሳ) 

የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች አነጋጋሪ ንግግሮች!!!
ዶቼ ቬለ – ታምራት ዲንሳ 
* ከስድስት ወራት በኋላ መንግሥት እንመሰርታለን!!!
* «በቀለ ገርባ ያታገልልናል ካላችሁ ፣ ጀዋር መሓመድ ታግሎ ያታግለናል ካላችሁ ፣ ድምጻችሁን ሰጥታችሁን እንደፍላጎታችሁ እንደ ህልማችሁ እንመራችኋለን!!!»
—-
በቅርቡ ጥምረት የፈጠሩት ሦስቱ የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ ፣ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረንስ ኦፌኮ እና የኦሮሞ ብሄራዊ ፓርቲ ኦብፓ በጋራ እና በተናጥል የምርጫ ዘመቻ ማድረግ ጀመሩ።
ፓርቲዎቹ ከባለፉት ሶስት ቀናት ጀምሮ አዲስ አበባን ጨምሮ በምስራቅ ኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች አጀንዳዎቻቸውን ሲያስተዋውቁ እና ደጋፊዎቻቸውን ሲቀሰቅሱ ቆይተዋል።
የኦሮሞሞ ፖለቲካን በቅርበት የሚከታተሉ አንድ ምሁር ደግሞ ዘመቻው ጊዜውን ሳይጠብቅ መጀመር አልነበረበትም ፤ እንዲያውም ፓርቲዎቹ አጀንዳ ብለው ይዘዋቸው የቀረቡት ሃሳቦች ጊዜ ያለፈባቸው ነው ሲሉ ተችተዋል።
ኦነግ ኦፌኮ እና ኦብፓ ጥምረት ከመሠረቱ ወዲህ የአዲስ አበባውን የሚሊኒየም አዳራሽ ጨምሮ በምስራቅ ኦሮሚያ ከደጋፊዎቻቸው ጋር ተገናኝተዋል ፤ ስሜታዊ ሊባሉ የሚችሉ ንግግሮችን አድርገዋል። ለቀጣዩ ምርጫ መወዳደሪያ አጀንዳችን ይሆናል ያሉትን ሃሳባቸውን በየመድረኩ አንጸባርቀዋል።
ፖለቲከኞቹ በንግግራቸው ገና ከጅምሩ አነጋጋሪ የሆኑ ሃሳቦችንም እንዳንጸባረቁበት ተነግሮላቸዋል።
አቶ በቀለ ገርባ በሚሊኒየም አዳራሽ ባደረጉት ንግግራቸው ከስድስት ወራት በኋላ መንግስት ማቋቋም ስለመቻላቸው እርግጠኛ የሆኑበትን ንግግራቸውን ኣድርገዋል።
«ይህ ህዝብ ከተሰበረ ወዲህ የራሱ መንግስት ኖሮት አዛውቅም ። ዘርፎት የሚሄድ እንጂ ፣ ረግጦት የሚሄድ እንጂ ፣ የሚጨቁን እንጂ፣ ማንነቱን ረግጦ ቋንቋውን የሚያጠፋ እንጂ የራሴ መንግስት የሚለው አቋቁሞ አያውቅም ። ነገር ግን እውነት እውነት እላችኋለሁ ከ6ወራት በኋላ የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተጣምረን የኦሮሚያን ድንበር የሚስከብር ራሱን ቀና አድርጎ እንዲሄድ የሚያደርግ የራሳችንን መንግስት እናቋቁማለን።»
ኣቶ ጀዋር መሐመድ ሐረር ላይ ለተሰባሰበው ደጋፊያቸው የምርጫ ቅስቀሳ መሰል ንግግር አድርገዋል።
«በቀለ ገርባ ያታገልልናል ካላችሁ ፣ ጀዋር መሓመድ ታግሎ ያታግለናል ካላችሁ ፣ ይሄ ቡድን የምንፈልገውን አመራር ይሰጠናል ብላችሁ እምነት ከሰጣችሁን ድምጻችሁን ሰጥታችሁን እንደፍላጎታችሁ እንደ ህልማችሁ እንመራችኋለን።»
አቶ ዳውድ ኢብሳም በአዲስ አበባ እና በመሬት ጉዳይ ላይ ስለሚከተሏቸው ፖሊሲዎች ለደጋፊዎቻቸው ንግግር አድርገዋል።
«የፊንፊኔ ከተማ በኦሮሚያ ክልል መንግስት ስር መሆኑ ለኦሮሞ እና ለኦሮሚያ ከሚሰጠው ጥቅም በላይ በፊንፊኔ ከተማ ውስጥ ለሚኖሩት ነው። መሬት የህዝብ ነው፤ ለህዝብ መመለስ አለበት ። ለህዝብ ሲመለስ በህዝብ በተመረጠ መንግስት የሚተዳደር እና በክልል መንግስታት የሚተዳደር ነው እንጂ የፌዴራል መንግስት አይደለም የፌዴራል መንግስት መሬት የለውም።»
የኦሮሞን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉት እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪኣቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙት ረዳት ፕሮፌሰር ብዙአየሁ ገደፋ ፓርቲዎቹ ያለጊዜው የጀመሩት ዘመቻ በሃገሪቱ ሰላማዊ ምርጫ ለማካሄድ በሚደረገው ሂደት ላይ አሉታዊ ጫና አለው ይላሉ።
«የምርጫ ዘመቻ ነው የጀመሩት ። የብሄራዊ የምርጫ ቦርድ በግልጽ ማስጀመር የነበረበትን እነርሱ ከወዲሁ የጀመሩ ይመስለኛል። ምን አስቸኮላቸው ብለን ስናይ በእርግጥ እነዚህ ሰዎች ከህዝብ ተራርቀው ስለነበር ተጠምተዋል ልትል ትችላለህ ፤ ነገር ግን ለእኔ ትክክል አይደለም። ሁሉም በጊዜው ይደርሳል። ገና አምስት እና ስድስት ወራት ናቸው የቀሩት ። ቀድመው ስለሮጡ አያሸንፉም ፤ ስለዘገዩም አይሸነፉም ። ትልቁ ነገር የህዝብ ልብ ውስጥ ያለው ጉዳይ ነው።»
ረዳት ፕሮፌሰር ብዙአየሁ እንደሚሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሻቸውን አጀንዳ ይዘው መቅረብ መብታቸው ቢሆንም በተለያዩ ጊዜያት ለተለያዩ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች ተጋልጦ ለኖረው የኦሮሞ ህዝብ የተለመደ አጀንዳ ይዞ በመምጣት ህዝቡን ከነበረበት ችግር ለማላቀቅ መፍትሄ እንደማይሆን ይናገራሉ።
«ሰሞኑን ቅስቀሳ እያደረጉ ያሉ ፓርቲዎች የዘዋቸው የመጡት አጀንዳዎች ቀደም ሲል ብዙ የተባለላቸው ናቸው። አሁን እንደ አዲስ መምጣቱ ገርሞኛል። ስለ አፋን ኦሮሞ ፣ ስለ ፊንፊኔ ጉዳይ ፣ ራስን በራስ ስለ ማስተዳደር እነዚህን ነገሮች ኣጀንዳ አድርጎ ይዞ የሚወጣ ፓርቲ ምነው ሌላ አጀንዳ የለውም ወይ የሚል ጥያቄ ያስነሳል።»
የሆኖ ሆኖ ቀን ያልተቆረጠለት የኢትዮጵያ ምርጫ 2012 ቅስቀሳ ፣ፍልሚያው ጠንከር እንደሚል ከሚጠበቅበት ከኦሮሚያ ክልል እንዲህ ተጀመረ። የኢትዮጵያ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ ምርጫ የሚካሄድበትን ቀን ገና አላሳወቀም ። ዘመቻውን የሚቀላቀሉ ተከታዮችስ እነማን ይሆኑ?
Filed in: Amharic