>
5:13 pm - Tuesday April 18, 7741

ግጭት በማባባስ እና እውነታን በመደበቅ፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ባዳ የሆኑት መገናኛ ብዙሃን!  (ያሬድ ሀይለማርያም)

ግጭት በማባባስ እና እውነታን በመደበቅ፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ባዳ የሆኑት መገናኛ ብዙሃን! 

 

ያሬድ ሀይለማርያም
ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን የመገናኛ ብዙሃን በብዙ ዘርፍ ልንመድባቸው እንችላለን። ለአሁኑ ትኩረቴ የሳቡት ግን ሁሉቱ ብቻ ናቸው። በመንግስት ሥር ሆነው ለሕዝብ ጉዳይ ባዳ የሆኑት እና በግል ተይዘው ግጭቶችን እያራገቡ ያሉ ሚዲያዎች። ወደ ምርጫ ፖለቲካ እየገባን ስለሆነ የእነዚህን ሚዲያዎች ባህሪ ከወዲሁ መግራት እና ማነጽ ተቀዳሚ ሥራ ካልተደረገ መዘዙ ብዙ እንደሆነ ይሰማኛል።

በመንግስት ሥር ያሉት፤

የመንግስት ባለሥልጣናትን ጭራ እየተከተሉ እና በሌሎች ትርኪቡርኪ ዘገባዎቻቸው ሕዝብን የሚያደናቁሩት የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ዛሬም ለሕዝብ ችግር ባዳ ሆነው ቀጥለዋል። የሥራ ነጻነታቸው በመንግስት ሹማምንት ተለክቶ የሚሰጣቸው ጋዜጠኞች በሕዝቡ መሃል እየኖሩ ለሕዝብ ችግርና ድምጽ አይናቸውን እንዲጨፍኑ፣ ጆሯቸውን እንዲደፍኑ እና አፋቸውን እንዲለጉሙ ተደርገው ለአመታት የአገዛዙ መሰራሪያ ሆነው ቆይተዋል። ዛሬም ልማድ ሆኖባቸው ይሁን ጥርነፋው ቀጥሎ በአንዳንድ የሕዝብ ጉዳዩች ምንም እንዳልሰሙ እና እንዳላዩ ሆነው ሲያልፉ ደጋግመን እያየን ነው። ይህ በቅርቡ በአማራ ክልል የተከሰተው የሕጻናት ጠለፋ እና አሁን ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ከደንቢዶሎ ዩንቨርሲቲ በኦነግ ሺኔ ታጣቂዎች ታፍነው የተወሰዱት ሴት ተማሪዎች ጉዳይ ጥሩ ማሳያዎች ናቸው። ከዚያ ቀደም ብሎም እንዲሁ 86 ሰዎች በጠራራ ጸሀይ የተገደሉበትን ክስተት እንዲሁ በገደምዳሜ እየቀባቡ አልፈውታል። አሁንም በምዕራብ ወለጋ በመንግስት ጦር እና በኦነግ ሽኔ መካከል ጦርነት ተከፍቷል የሚሉ ዘገባዎች ከየአቅጣጫው ቢወጡም መንግስት እና የሚያስተዳድራቸው ሚዲያዎች ዝምታን መርጠአል። ሕዝብ በአገሩ ውስጥ ያለውን ሁኔታ የማወቅ መብት እንዳለው የተረዱ አልመሰለኝም።
አሁን ያሉትን እና በመንግስት በጀት የሚተዳደሩትን ሚዲያዎች በጠቅላላ በቅጡ የታዘባችሁ እንደሆነ ከዘገባዎቻቸው መካከል አብዛኛዎቹ በየሆቴሉ እና በየአዳራሹ የተካሄዱ ስብሰባዎችን፤ በተለይም የመንግስት ባላሥልጣናት የተገኙባቸውን ድግሶች ሁሉ ሙሉ ቀን ሲዘበዝቡ ነው የሚውሉት። እንደ እነሱ ዘገባ ከሆነ ኢትዮጵያ አንድም ችግር ኮሽ የማይልባት ደሴት ትመስላለች። ስለችግርም ከዘገቡ ጉዳዩ የመንግስት ሹማምንትን፣ የክልል ባለስልጣናትን ወይም አንዳን ተጽዕኖ ፈጣሪ ኃይሎችን በማይጎረብጥ መልኩ መሆን አለበት።
ለነገሩ በዚህ ለውጥ ውስጥ ክስተቶችን ተከትሎ አንድ የተለመደ ቃል ደጋግመን በየዘገባው እና በመንግስት ባለሥልጣናት መግለጫዎች ላይ እንሰማለን። እሱም ጥፋት ፈጻሚዎች ሁሉ “አንዳንድ ኃይሎች” የሚል የወል ስም ተሰጥቷቸዋል። በአንዳንዱ ጉዳይ የአድራጊዎቹ ማንነት በግልጽም እየታወቀ አንዳንድ ኃይሎች በሚል አጥፊዎችን የመሸፋፈን እርምጃ ተደጋግሞ ተስተውሏል። መንግስት በአጥፊዎቹ ላይ በቂ መረጃ ስለሌለው እና ጥፋተኝነታቸው በፍርድ ሂደት እስኪረጋገጥ ድረስ በመንግስት በኩል የተወሰደ ጥንቃቄ አድርገን እንዳንወስደው የመንግስት ባህሪ ያንን አያሳይም። ይህ አይነቱ የሽፍንፍን አካሄድ ግን አገሪቱን ዋጋ እያስከፈላት፣ ለአጥፊዎችን ከለላ እየሆነ እና ህብረተሰቡም ግራ እንዲጋባ እያደረገ ነው።

በግል የተቋቋሙ መገናኛ ብዙሃን

በተቃራኒው ደግሞ ወገን ለይተው እና የዘር መስመር አድምቀው የእኔ በሚሉት ሕዝብ ላይ የሆነውንም፣ ያልሆነውንም፣ እንዲሆን የተመኙትንም ነገር እጅግ በከረረ እና ፍጹም ከጋዜጠኝነት ስነ-ምግባር በራቀ እና ሕዝብንም ለበለጠ የእርስ በርስ ግጭት በሚዳርግ መልኩ ዘገባ ሲሰሩ የሚውሉ ሚዲያዎችም ተፈጥረዋል። ለአንዳንዶቹ የብሮድ ካስቲንግ ኤጀንሲው የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ የሰጠ ቢሆንም ማንም ከቁብ እንዳልቆጠረው ለማወቅ ዘገባዎቻቸውን ማየት በቂ ነው። እነዚህ ሚዲያዎች በዩንቨርሲቲዎች ውስጥ የተፈጠሩትን ግጭቶች እጅግ እንዲባባዙ የሃሰት መረጃ ከመፈብረክ አንስቶ አንዱን ወገን ተጠቂ ሌላውን ወገን አጥቂ አድርገው በማቅረብ ግጭቶቹ እንዲባባሱ እና የትምህርት ሂደቱም እንዲስተጓጎል ትልቁን ሚና ተጫውተዋል። በተመሳሳይ ሁኔታም የኃይማኖት ግጭቶችን እንዲስፋፉ፣ በክልል ጥያቄ ስም የፖለቲካ ጡዘቱ እንዲከር እና በሕዝብ መካከል እርስ በርስ መጠራጠር እና መፈራራት እንዲፈጠር ዛሬም ተግተው እየሰሩ ነው።
ባለንበት ብዙና ውስብስብ ችግር ላይ ኃላፊነት የጎደላቸው የመገናኛ ብዙሃን እየፈጸሙ ያሉት ኃላፊነት የጎደለው ተግባር አገሪቱን ለበለጠ ቀውስ ሊዳርጋት ይችላል። የሕዝብ ብሶትና ድምጽ እያፈኑ የመንግስት ባለሥልጣናት ልሳን በሆኑት መገናኛ ብዙሃን እና ሕዝብ ያላከከውን እያከኩ በአክራሪነት ስሜት ግጭትን በሚያራቡት የግል ወይም ብሔር ተኮር ሚዲያዎች መካከል ብዙም ልዩነት የለም። ሁለቱም ከእውነት የራቁ፣ የሕዝብን ድምጽ ያፈኑ፣ በሕዝብ ብሶት የሚነግዱ እና ከካድሬነት እሳቤ ገና ያልተላቀቁ ናቸው።
ለመሆኑ የብሮድካስቲንግ ኤጀንሲውስ አለ ወይ? ምን እየሰራ ይሆን? ያንን ዝነኛ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤውን ተከትሎ ማስጠንቀቂያ የሰጣቸው ሚዲያዎች ከክፉ አድራጎቶቻቸው አልታቀብ ሲሉ ምን አደረገ? ነው ወይስ ፉከራም ዝም አላልኩም ለማለት ያህል? ሚዲያዎች ኃላፊነት በመሞላው መልኩ እውነትን እንዲዘግቡ፣ ሕዝብን እንዲያነቁ እና ሃሳቦችን እንዲያንሸራሽሩ መፍቀድ የሚደገፍ አና ሃሳብን የመግለጽን ነጻነት የማክበር ውጤት ነው። ይህን አደገኛ እና ጥንቃቄ የሚያስፈልገውን መድረግ ለሕገ ወጥ እና በማህበረሰቦች መካከል ቅራኔ ለመፍጠር ወይም የሕዝብን ድምጽ ለማፈኛ ማዋል ግን ሊወገዝ የሚገባው ተግባር ነው።
ጎበዝ ሩዋንዳን ያየ በእሳት አይጫወትም!
Filed in: Amharic