>

ፅንፈኛ የኦሮሞ ብሔርተኝነት እና ኢስላማዊ አክራሪነት የተምታታበት አህመዲን ጀበል!! (ብሩክ አበጋዝ)

ፅንፈኛ የኦሮሞ ብሔርተኝነት እና ኢስላማዊ አክራሪነት የተምታታበት አህመዲን ጀበል!!

ብሩክ አበጋዝ
«…ኑር ኢብኑ ሙጃሂድም የሙስሊሞች ማዕከልና የሱልጣኑ መቀመጫ (ቤተ መንግስት) የነበረችውን የሐረር ከተማን ከክርስትያኑ ጦር ጥቃት ለመከላከል የጁገል (በተለመዶ ጀጎል) ግንብን ማስገንባት ጀመረ። «#ጁገል»ም ተገነባ።…» (አህመዲን ጀበል: ¨3ቱ አፄዎች እና የኢትዮጲያ ሙስሊሞች¨)
«…ከድሉ በሁዋላ ( የሃዘሎ ድል ማለታቸው ነው) የምችሌ ባለ ገዳዎች ለተሸነፈው ጠላት ፋታ አልሰጡትም። ከፍጅቱ ተርፎ ከጦር ሜዳ የሽሸወን የኑር ሰራዊት ተከታትለው እየፈጁ ሃረር ከተማ በር ድረስ ሄዱ። በምስራቅ ፈጠጋር፣ ሰፍሮ የቆየው የከረዩ ነገድ የጦሩን ዱካ ተከትሎ በደጋው ሃረር ላይ እየጎረፈ ሰፈረበት ። በሃረር ከተማ ዙሪያ በእስላሞች እጅ የቀሩትንም ወረዳዎች አከታትለው እየወረሩ፣ መንደሮቹን ለቃጠሎ ከመስጠት አላቋረጡም። ሲም፣ ሾሃ፣ ነጃቭ፣ ጂዳያና ደካር በሚባሉት ወረዳዎች ላይ ታላቅ ጥፋት ደረሰባቸው። ከወረራው ለመከላከል አሊ ኑር በክተማው ዙሪያ እሰከ ዛሬ የሚታየውን የሃረርን ግንብ ሰራ። ጦርነቱን ተከትሎ የደረሰው የሶስት አመት ረሃብና ወረርሽኝ የሃረርን ህዝብ ለብርቱ ጉዳት ሰጠ። በደረሰበት መከራና ሀዘን ተጎሳቅሎ ኑርም ራሱ……በወረርሺኝ በሽታ ተለክፎ ሞተ። ታላቁ የኦሮሞዎች ወረራ ባሌ ውስጥ በተጀመረ በአምስተኛው ገዳ ቀድሞ ጦርነቱን ያስነሳው የከረዩ ነገድ በስተምስራቅ የሚገኘውን ደጋና ወይና ደጋ አጠቃሎ ያዘ።» (ይልማ ዴሬሳ: የኢትዮጲያ ታሪክ በ16ኛው ክፍለ ዘመን)
.
ሀረሬዎች ለዘመናት ከክርስትያኖች ጋር እየተዋጉ ሲገብሩም ሲያምጹም ሲኖሩ ከጦርነት ለመከላከል ለከተማቸው መከዳ የሚሆን ግንብ ሳይገነቡ ኖረዋል። ይሁንና የኦሮሞወች መስፋፋትን ተከትሎ በተለይ በምቸሌ ባለገዳ ጊዜ የደረሰባቸው ታላቅ ሽንፈት ከተማቸው ላይ ብቻ እንዲወሰኑና ከተማቸውን መከላከል ብቻ ላይ ተወስኑ በዚህም ምክንያት ዓሊ ኑር የሀረር ከተማ ዙሪያውን አቅፎ የያዘውን የጀጎል ግንብን ለመስራት ተገደደ። እንግዲህ ለዘመናት ከክርስትያኖች ጋር በነበራቸው ግጭት ሳይሰሩት የቆየውን ግንብ የምቸሌ ባለገዳወችን ጥቃትና ጦርነት ተከትሎ መስረታቸው የግንቡ ዓላማ ግልጽ ሆኖ እያለ ግንቡ የተሰራው ክርስትያኖቹን ለመከላከል ነው በማለት ትክክለኛውን ታሪክ በመዝለልና ምንም አንድ ዐረፍተ ነገር ሳያወሩ የማይሆን ምክንያት ማስቀመጥ ለትዝብትም ለትችትም የሚዳርግ ነው።
Filed in: Amharic