>

በጃገማ ኬሎ የሚመራው የአርበኞች ቡድን  የፋሺስት ኢጣሊያ ምሽግ ስለመስበሩ!!!  (ፍቅረማርቆስ ደስታ)

በጃገማ ኬሎ የሚመራው የአርበኞች ቡድን  የፋሺስት ኢጣሊያ ምሽግ ስለመስበሩ!!!

 ፍቅረማርቆስ ደስታ
በውስጥ አርበኛ ሸዋረገድ ገድሌ ጠንሳሽነት ጃገማ አባ ዳማ በጦር አዝማችነት አርበኞችን እየመሩ ወደ አዲስ አለም ገሰገሱ፡፡ ኮ/ል በለው ወ/ጻዲቅ፣ ሌ/ኮሎኔል ተስፋዬ ግዛው፣ ልጅ ኃይለ ማርያም ወ/ጻዲቅ፣ ልጅ አሰፋ ዘርጋው፣ ሻምበል ሹምዬ ደቦጭ፣ ልጅ ተገኝ እሸቴ፣ ልጅ ጽጌ ሚጣ፣ ሻለቃ ኃይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን፣ ዓለሙ መኮንን፣ አድማሱ መኮንን፣ ሻለቃ ከበደ ተሰማ፣ ልጅ አበጋዝ ለማ ከነጓዶቻቸው በጃገማ የቀኝ እንደራሴ በዘውዴ ጥላሁን ትዕዛዝ ስር እንዲንቀሳቀሱ ተደረገ፡፡
በግራ እንደራሴው በሻለቃ ጠንቄሳ ኬሎ በኩል ደግሞ ሻምበል ጊዲ ኬሎ፣ ሻምበል ተጆ ወሰኔ፣ ሌ/ኮሎኔል ሙሊሳ ሶሪ፣ ቀኝ አዝማች ተሰማ ካሳ፣ አቶ ሙሊሳ ቀርጩ፣ አቶ መንግስቱ ወ/አማኑኤል፣ ሻለቃ የሻነህ ወርቅነህ፣ ልጅ አበበ ተሰማ፣ አቶ ብሪ መርጋ፣ አቶ ሚደቅሳ ክልል፣ አቶ በከልቻ ኢጉ፣ አቶ ጉተማ ገመቹ፣ አቶ ታደሰ ጋሻው ከነወንድሞቻቸው፣ አቶ ከበደ ይመር፣ አቶ ወርቅነህ መሸሻና አቶ ያዳ ደራ በምሽግ ሰበራው ላይ እንዲሳተፉ ተወሰነ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ መሳሪያ የሌለው 300 ያልታጠቀ ጀሌ ተዘጋጀ፡፡ የምሽግ ሰበራው ከመፈጸሙ በፊት የተመረጡ አርበኞች አዲስ አለም ገብተው ልጅ አለም ከተባለው ሰው ቤት በመቀመጥ ለ3 ቀን የቅኝትና የስለላ ስራ እንዲሰሩ ወደዛው ተላኩ፡፡ ሰላዮቹ ህዳር 23 ቀን 1933 ዓ.ም መንግስቱና ስዩም ከተባሉት የውስጥ አርበኞች ጋር በርጋ ወንዝ ላይ ተገናኙ፡፡
ከመካከላቸው አንዱ አርበኛ ጎፈሬውን ተላጭቶ የቀን ሰራተኛ በመምሰል በታላቅ ጥንቃቄ ወደ ኢጣሊያ ምሽግ እንዲገባ ተደረገ፡፡ በማግስቱ ጥዋት በጃገማ ኬሎ የሚመሩት አርበኞች በኢጣሊያ ምሽግ አካባቢ  አድፍጠው ካደሩበት ጫካ ውስጥ ተደብቀው እንዲቆዩ ታዘዙ፡፡ የውስጥ አርበኛው አቶ አለማየሁ በጫካ ላደፈጡት አርበኞች 3 ኩንታል የሚሆን ቆሎ አስቆለቶ ሲመግባቸው ዋለ፡፡
ጨለምለም ሲል የጠላት ካምፕ አለቃ ሆነው የሚሰሩት ቀኝ አዝማች አብርሃ ከእነ ዘውዴ ጥላሁን ጋር በመገናኘት የጠላትን ጥበቃ ዘቦች አቋም፣ የመሳሪያና ጥይት ቤቱን አቀማመጥ በማስረዳት የጥቃት ፕላን ተዘጋጀ፡፡ የኢጣሊያ የጦር ሹማምንትና ባለስልጣኖች መኖሪያና ብዛታቸው እንዲሁም ከአዲስ አበባ ወደ አምቦ በሚወስደው መንገድ ላይ ባለው ኬላ ስለሚኖሩት የጠላት ወታሮችም ገለጻ ተደረገ፡፡
የመጨረሻው የማጥቃት እርምጃ ከመወሰዱ በፊት ጃጋማ በትእዛዛቸው ስር ያለውን አርበኛና መሳሪያ እንዲቆጠር አደረጉ፡፡ 2 ድግን መትረየስ፣ 83 ጠመንጃና 20 የእጅ ቦምብ መኖሩ ተረጋገጠ፡፡ መሳሪያ የሚዘርፉ 300 ያህል ያልታጠቁ ጀሌዎችም ተዘጋጅተዋል፡፡ ይህ ሁሉ ዝግጅት ሲደረግ ጠላት ምንም መረጃ አልነበረውም፡፡
መንግስቱ ወ/ማርያም፣ ስዩም ወ/አማኑኤልና ሙሊሳ ቁርጩ ከ15 ጠመንጃ ያዥ ጋር ከአምቦ ወደ አዲስ አበባ በሚወስደው ኬላ ላይ የሰፈረው የፋሺስት ጦር ወደ አዲስ አለም የጦር መሳሪያ ግምጃ ቤት ለእርዳታ የሚመጣ ቢሆን በተኩስ እንዲያቆሙት ተመደቡ፡፡ የምሽጉ መግቢያና መውጫ ላይም የተጠናከረ ጥበቃ ተመደበ፡፡
በሌ/ኮሎኔል ሙሊሳ ሶሪ የሚመሩ 5 ባለጠመንጃዎች ከጽዮን ማርያም ቤ/ክ ፊት ለፊት በስተ ምስራቅ የጠላት ከባድ መሳሪያ ባለበት አቅጣጫ መንገድ እንዲዘጉ ተመደቡ፡፡
ሻምበል ተጆ ኦላኒና አለሙ መኮንን 10 አርበኞችን በመያዝ ከኮ/ል ሙሊሳ ጎን ለጎን ሆነው እንዲጠባበቁ ተመደቡ፡፡ ሻለቃ ኃይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን 15 አርበኞችን በመያዝ ኃ/ጊዮርጊስ የሚባለውን የኢጣሊያ ሹምባሽ ቤት እንዲከብና በጦር ግምጃ ቤቱ ላይ ተኩስ ሲከፈት ጃጋማ ይጠራሃል የሚል መልእክት እንዲነግረው፣ አልታዘዝ ካለ እንዲደመስሱት ተመደቡ፡፡
የመቶ አለቃ ኃይሉ ደግሞ በመኖሪያ ካምፕ ውስጥ የሚገኙትን 3 የኢጣሊያ የጦር አለቆች ተኩስ እንደተጀመረ ወደ ቤት በቀጥታ ገብቶ እንዲገድልና እስረኞችን እንዲለቅ ተመደበ፡፡ የሚፈቱት እስረኞች ከአርበኞች ጋር በጦር መሳሪ ዝርፊያው ላይ እንዲሳተፉ ታዘዘ፡፡
ከ300 በላይ የሆኑት ያልታጠቁ ጀሌዎች 3 ጠመንጃ ተመድቦላቸው በተጠንቀቅ እንዲቆዩና ጡሩንባ ሲነፋላቸው በቀጥታ ወደ ኢጣሊያ ጦር ግምጃ ቤት በመሄድ ዘረፋውን እንዲጀምሩ እቅድ ወጣ፡፡
የዘመቻውን ከባዱን ግንባርና ጠንካራውን የውጊያ ክፍል የአርበኞቹ መሪ ጀግናው ጃጋማና አጋራቸው ዘውዴ ለራሳቸው መደቡ፡፡ በጃጋማና በዘውዴ የሚመሩ 35 አባላት፣ 35 ጠመንጃና 2 ድግን መትረየስ የታጠቀው የአርበኞች ቡድን በጠላት ጦር የፊት በር ጠባቂዎችን እንዲደመስሱ ተመደቡ፡፡
በውስጥ አርበኛ ሸዋ ረገድ ገድሌ ጠንሳሽነት የአዲስ አለምን የኢጣሊያ ምሽግ ለመስበር ወደ አዲስ አለም የገሰገሱት በጃገማ ኬሎ የሚመሩት የኢትዮጵያ አርበኞች በምሽጉ አካባቢ ተጠግተው አሰላለፋቸውን ካደላደሉ በኋላ ግንኙነታቸውን በተላላኪና በይለፍ ቃል እንዲሆን ወሰኑ፡፡
ጃገማና ዘውዴ የሚያዙትን ቡድን በመረጃ አቀባይነት የሚመራው አስቀድሞ ጸጉሩን በመላጨት የቀን ሰራተኛ መስሎ ወደ ፋሺስት ካምፕ በመግባት መግቢያ መውጫውን ሰልሎ የተመለሰው አድምቄ በሻህ ነው፡፡
ዝግጅቱ ከተጠናቀቀ በኋላ አርበኞች በየምድብ አለቃቸው ስር ሆነው ወደ የተመደቡበት ግንባር እንዲንቀሳቀሱ ጀግናው ጃገማ አዘዘ፡፡
ከቀኑ 4 ሰአት ሲሆንም የኢትዮጵያ አርበኞች ወደ በርጋ ወንዝ ተንቀሳቀሱ፡፡ ሚካኤል ቤ/ክ ጋ  ግን የጃገማን የአመራር ብቃት የሚፈታተን መልእክት ደረሰው፡፡ መልእክቱም “ከአዲስ አበባ ወደ አምቦ በሚወስደው መንገድ ላይ 600 ወታደሮችያሉት የኢጣሊያ ጦር መጥቶ ካርቤኒሪ ካምፕ ሰፍሯል፣ በነበረው ጦር ላይ የዚህ መጨመር እቅዳችንን አደጋ ላይ ስለሚጥለው ጦሩ አካባቢውን ለቆ እስከሚሄድ የምሽግ ሰበራውን ለነገ ብናስተላልፈው ምን ይመስለሃል?” የሚል ነበር፡፡
ጃገማ ግን የውስጥ አርበኛውን ሁሉ አሰልፈን ይሄ ሁሉ አርበኛም በቆራጥነት ለመፋለም በተዘጋጀበት ሁኔታ ወደ ኋላ መመለስ በጭራሽ አይታሰብም፡፡ ይሄን ለኔ የነገርከውን ለማንም እንዳትነግር በማለት ጃገማ ተላላኪውን አሰናበተው፡፡
ከምሽቱ 1 ሰአት ተኩል ሲሆን የኢትዮጵያ አርበኞች ወደ ምሽጉ ተጠጉ፡፡ የእለቷ ጀምበር ብትጠልቅም ውጭ ማደር የለመደው አርበኛ ግን ሰማዩ ላይ ሆጨጭ ብሎ የሚብለጨለጩትን ክዋከብት ይመለከታል፡፡ በእቅዱ መሰረት እነ ጃገማ ቀስ እያሉ እየተሳቡ ወደ ጠላት ምሽግ አጥር ተጠጉ፡፡ አድምቄና መሸሻ እየመሩ ዘብ ወደ ቆመው ፈረንጅ አጠገብ ሲደርሱ እነ ጃገማ ተከተሏቸው፡፡ ዘቡ በራሱ የጣሊያንኛ ቋንቋ ማነህ! አለ፡፡ ማንነታቸውን የማያውቃቸው ሰዎች አጠገቡ መቃረባቸውን እንደተረዳ መትረየሱን ጥሎ ፈረጠጠ፡፡ ይሁን እንጂ ነፍሱን ሳያተርፍ ወርቅነህ መሸሻ የመጀመሪያዋን ጥይት በመተኮስ ጣለው፡፡
የመጀመሪያው ተኩስ እንደ ተከፈተ የበጋው መብረቆች በየተመደቡበት ኃላፊነታቸውን ለመፈጸም መራወጥ ጀመሩ፡፡ እነ ጃገማም በቀጥታ የኢጣሊያ ጦር መኮንኖች መብራት አብርተው እራት ወደ ሚበሉበት ክፍል በመግባት ረፈረፏቸው፡፡ ሩጠው ለማምለጥ ከሞከሩት 20 የኢጣሊያ ወታደሮች  መካከል ለመትረፍ የቻሉት 3 ብቻ ናቸው፡፡ እነዚህ 3ቱ ወደ ፎቅ ወጥተው ቦምብ ለመወርወር ቢሞክሩም ጃገማና ዘውዴ እንደ ጉሬዛ ፈጥነው ወደ ፎቆ በመውጣት አፋቸውን ዘጉት፡፡
እነዚህ ከተደመሰሱ በኋላ እነ ጃገማ 50 የኢጣሊያ ወታደሮች አሉበት ወደ ተባለው ክፍል ከመሄዳቸው በፊት በስህተት ጡሩንባ ተነፋ፡፡ የጥሩንባ ድምጽ የድል ምልክት ነው ተብሎ የተነገረው ግንቡ ስር ተኮልኩሎ ይጠብቅ የነበረው ጀሌ ሆ ብሎ እየዘለለ መሳሪያ ለመዝረፍ ወደ ኢጣሊያ መሳሪያ ግምጃ ቤት መሮጥ ጀመረ፡፡ ጀሌው ከ50ዎቹ የኢጣሊያ ወታደሮች ጋር በስህተት ቢቀላቀልም በዛ ድቅድቅ ጨለማ በቋንቋና ማየት ሲቻልም በአለባበስ እየለየ አብዛኞቹን በዱላ ደብድቦ ገደላቸው፡፡
ሁሉም ከፊት ለፊቱ የተጋረጠውን የጠላት ጦር ሃይል እየበታተነ ወደ ጦር መሳሪያ ማከማቻ መጋዘኑ በመንደርደር በእቅዱ መሰረት ዘረፋውን ጀመረ፡፡ በግምት ሁለት ሰአት ተኩል ያህል ዘረፋው ከተካሄደ በኋላ ጃገማ የኢትዮጵያ አርበኞች ከኢጣሊያ ካምፕ እንዲወጡ ትእዛዝ አስተላለፈ፡፡
ከኢጣሊያ ምሽግ ውጭ ሆነው በኬላው አካባቢ የማያባራ የማደናገሪያ ተኩስ እንዲተኩሶ የተመደቡት 15 አርበኞች በፈጸሙት ጀብዱ በኬላው የነበሩት የኢጣሊያ ጦር አዛዦች ከምሽጋቸው ሳይንቀሳቀሱ ጥርስ የሌለው አንበሳ እንዲሆኑ ተደረገ፡፡ በከፍተኛ ወኔና በብልጠት የታገዙት ኢትዮጵያ አርበኞችም ድላቸውን ካለ ችግር አጣጣሙ፡፡
እስረኞችን እንዲያስፈታ በመሪነት የተመደበው መቶ አለቃ ኃይሉ በበኩሉ ተኩስ እንደተከፈተ የኢጣሊያ አዛዦችን ገድሎ መሳሪያቸውን ከገፈፈ በኋላ ወደ 80 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን እስረኞች ያሉበትን ክፍል አስከፈተው፡፡ ወደ እስረኞቹ በመጠጋትም፣
በጃገማ ኬሎ የሚመራው ኢትዮጵያ አርበኞች ቡድን የኢጣሊያን ጦር አነካክቶ የመሳሪያ ማከማቻ መጋዘኑን በመዝረፍ የዘመናዊ ትጥቅ ባለቤት ሆኗል፡፡ እናንት የጠላት ግፍ ቀማሾች የዘረፍነውን መሳሪያ እንደየአቅማችሁ በመሸከም አርበኞችን በፍጥነት በመቀላቀል ለእናት አገራችሁ ከኛ ጋር እንድትዋደቁ ጥሪ ቀርቦላችኋል አላቸው።
በዚህ መሃል መቶ አለቃ ኃይሉና ቀሪዎቹ አርበኞች በአስቸኳይ አዲስ አለምን ለቀው እንዲወጡ የሚጠይቅ ትእዛዝ መጣ፡፡ መቶ አለቃ ኃይሉ ሀሳባቸውን በነጻነት እንዲገልጹ እድል ከሰጣቸው እስረኞች አንዱ እንደ በግ ታጉረን ከመሞት ይልቅ እንደ አንበሳ እያጓራን ከወንድሞቻችን ጋር ጠላታችንን እንዋጋለን የሚል አስተያየት ሰጡ፡፡
ሌላ አዛውንት ግን አገሪቱን የያዘው ጣሊያን ስለሆነ ከዚ ብናመልጥም መያዛችን ስለማይቀር ዳግመኛ ተይዘን መንገላታት አይገባንም በማለት ተቃወሙ፡፡ መቶ አለቃ ኃይሉ ለመፈታት ፈቃደኛ የሆኑትን 40 እስረኞች ብቻ አርነት በማውጣት ጊቢውን ለቀቀ፡፡ ጃገማ አባ ዳማና አርበኞቹም በጥቂት ጊዜ ውስጥ ጥርግርግ ብለው ከአዲስ አለም ወጡ፡፡
በዚህ ዘመቻ ከኢትዮጵያ አርበኞች የሞተው ልጅ ኃ/ማርያም ወ/ጻድቅ ብቻ ነው፡፡ ልጅ ኃ/ማርያም እነ ጃገማን እስከ ኤጀርሳ ለፎ ድረስ ከሸኘ በኋላ የኢጣሊያ ምሽግ ሽቦ ይዞ ያስቀረውን ጓደኛውን ለማስለቀቅ ሲመለስ በጣሊያኖች ተገደለ፡፡ ከጠላት ወገን ግን 72 የአዲስ አለም ምሽግ አዛዦችና ጠባቂዎቻቸው እንዲሁም በእንግድነት ወደ ምሽጉ የመጡ አንድ ኮሎኔልና 6 ጠባቂዎቻቸው ተደምስሰዋል፡፡ ከኢትዮጵያ አርበኞች ጥቃት መትረፍና ማምለጥ የቻሉት 7 ብቻ ናቸው፡፡
በውድቅት ሌሊት ከአዲስ አለም በመነሳት ሜጫ ወደሚገኘው ጀምጀም ለመድረስ ሌሊቱን ሲኳትን ያደረው አርበኛ ሊነጋጋ ሲል ጀምጀም ደረሰ፡፡ የተዘረፈው መሳሪያ ዋርካ ስር እንዲከመር ተደርጎ እረፍት ሆነ፡፡ እያንዳንዱ ጀሌ ከተዘረፈው ጠመንጃ 3 ለራሱ በመውሰድ አንዱን በመሸጥ ጥይት እንዲገዛና ለወደፊቱ ለግዳጅ ሲጠራ አንድ ሌላ ሰው ጨምሮ እንዲመጣ በማዘዝ ጀግናው ጃገማ ኬሎ የወደፊቱን ደጀን ጭምር ከወዲሁ አዘጋጀ፡፡
* በምስሉ የሚታዩት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ጀግናው ጃገማ ኬሎና ወንድማቸው ቂንጤሳ ኬሌ እንደሆኑና ምስሉም ከነጻነት 1 አመት በኋላ በ1934 ዓ.ም እንደተነሳ ይገመታል።
ጃገማ ኬሎ፣ የበጋው መብረቅ፣ ፍቅረማርቆስ ደስታ እንደጻፈው፣ 2ኛ እትም 2002 ዓ.ም፣ ገጽ 74-77
Filed in: Amharic