>
5:13 pm - Friday April 19, 9850

አገር ትፈረካከሳለች ብዬ እፈራ ነበር!!!" (ጀዋር መሐመድ - ቢቢሲ)

አገር ትፈረካከሳለች ብዬ እፈራ ነበር!!!”

ጀዋር መሐመድ
ቢቢሲ
ጀዋር መሐመድ በይፋ የተቀላቀለው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ብሔራዊ ፓርቲ (አብፓ) ጋር በጥምረት ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሳቸው የተሰማው ባለፈው ሳምንት ነበር። ለመሆኑ ይህ ስምምነት ምን ይዞ ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል? በቀጣዩ ምርጫ እንደሚሳተፍ ያሳወቀው ጀዋርስ ስለ ምርጫው ምን ያስባል? ቢቢሲ በነዚህ ጥያቄዎችና ተያያዥ ጉዳዮች ዙርያ ከጀዋር ጋር ቆይታ አድርጓል።
—–
ኦነግ፣ ኦፌኮና ኦብፓ በጥምረት ለመሥራት መስማማታችሁን በቅርቡ ይፋ አድርጋችኋል። ይህ ጥምረት በምርጫ ወቅት ሕዝቡ ለእናንተ ለሚሰጠው ድምጽ ምን ያህል አስተዋጽኦ ይኖረዋል?
ጀዋር፡ እንግዲህ የዚህ ትብበር ዓላማና ይዘቱን በተመለከተ የፓርቲው አመራሮች በቅርቡ መግለጫ ስለሚሰጡ ከዛ በስፋት መረዳት የሚቻል ይሆናል። የፓርቲዎች ትብብርና አንድ ግንባር መፍጠር በተለይ ለዚህ የሽግግር ወቅት ምርጫ ሁለት ዋና ዋና ጥቅሞች ይኖሩታል የሚል እምነት አለኝ።
አንደኛው የፓርቲዎቹ መተባባር ለፉክክር አዲስ ለሆነች አገርና ለመራጭ እንዲሁም ለፓርቲው አባላት ከምርጫው በፊት በቅድመ ምርጫ ቅስቀሳዎችና ማደራጀቶች ውስጥ ግጭት እንዳይቀሰቀስ ዕድል ይፈጥራል፤ መቀራረብን ይፈጥራል እንዲሁም ሰላማዊ የሆነ የምርጫ ቅስቀሳ እንዲካሄድ ዕድልን ይፈጥራል።
ሁለተኛው ደግሞ በአንድ አይነት አካባቢ የሚወዳደሩ ፓርቲዎች አብረው ለመሥራት መቀናጀትና መስማማታቸው ድምጽ እንዳይባክንና የማሸነፍ ዕድላቸው ከፍ ማድረግ እንዲችሉ ይረዳቸዋል። እናም እነዚህ ሁለቱ ናቸው የትብብሩ ዋና ጥቅሞች።
ከዚህ ቀደም የብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክንፍ ከአንተ ጋር አብሮ የመሥራት ጥያቄ አቅርቦልህ ነበር?
ጀዋር፡ አሁን አይደለም፤ እንግዲህ እንደሚታወቀው ትግሉን በምናካሂድበት ወቅት እኛም ከውጪ ሆነን እነሱ ደግሞ ከውስጥ ትግሉን ያካሂዱ ነበር። አሁን ያሉትም ባይሆኑ ከነባርና አንጋፋዎቹ አመራሮች ጋር ሁለቱን ትግሎች አቀናጅተን ለአስርት ዓመታት የቆየ የትግል አጋርነት ነበረን። ይሄ ለውጥም አነስ ባለ ዋጋ በፍጥነት እንዲመጣ ከእነሱ ሰፊ የሆነ ትብብር ነበረን። ለዚህም ነው መንግሥት ሳይወድቅ ሥርዓት ሳይገረሰስ ወደዚህ ሽግግር ልንገባ የቻልነው። ግን አንድም ቀን አባላቸው ሆኜ አላውቅም፤ አብረንም ስንሠራ ነበር። የነበረንም ግንኙነት በዚህ መሰረት ነበር።
በፓርቲ ደረጃ ግን አንድ ላይ ሆኖ አብሮ ለመሄድ የሚያስችለን ነገር የለም። ሰፊ የሆነ የአመለካካት ልዩነት አለን። ከዛ ባለፈ ግን ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅና ምርጫው የዚህ ትግል ውጤት ስለሆነ እንዲሁም የትግሉ ሌላ ምዕራፍ ስለሆነ እነሱ እንደ ገዢ ፓርቲ፣ እኔ ደግሞ እስከ ቅርብ ጊዜ እንደ አክቲቪስትና በአገሪቱ ፖለቲካ ጫና እንዳለው ሰው ተቀራርበን ስንሠራ ነበር። ወደፊትም እንሠራለን።
የኦሮሞ አመራር ካውንስል አለ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው የሚመሩት። እኔም እንደ አንድ አስተባባሪ ስሠራ ነበረ። ከዚህ አንጻር ምርጫው በተሳካ መልኩ ችግር ሳይፈጠር እንዲካሄድ ወደፊትም አብረን መሥራት እንቀጥላለን። ከዛ ባለፈ ግን አንድ ወገን ሆነን ወደ ምርጫ የምንገባበት ዕድል አይታየኝም።
የቀጣዩ ምርጫውጤት ይፋ ከተደረገ በኋላ አገሪቱ ወደምን አይነት ሁኔታ የምታመራ ይመስልሃል?
ጀዋር፡ መረጋጋትም አለመረጋጋትም መኖሩን የሚወስነው የአገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን የሚያደርጉት ሥራ ነው። በተለይ የገዢው ፓርቲ የተሰጠው አደራ አለ፤ የአደራ መንግሥት ነው። ይሄ አደራ ለ27 ዓመት ሲጨቁነው፣ ሲበዘብዘው የነበረውን አምባገነናዊ ስርዓት ሕዝቡ ከፍተኛ ትግል አድርጎ አስገድዶ ወደ ለውጥ እንዲመጣ አድርጎታል።
ለእነ ዐብይ [ጠቅላይ ሚንስትር] ደግሞ አደራ ሰጥቷል። አምባገነኑን ስርዓት አዳክመናል፤ ጥለነዋል፤ ስለዚህ ወደ ዴሞክራሲ አሸጋግረን የሚል ኃላፊነት ተሰጥቶታል። ከእነዚህ ኃላፊነቶች አንዱ ፍትሃዊ፣ ነጻ እንዲሁም ፉክክር የሚታይበት የምርጫ ስነ ስርዓት ማካሄድ ነው። ይህ ማለት የመንግሥት አካላት ከአላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት፣ ለገዢው ፓርቲ አለማዳላት፣ ግጭት እንዲቀሰቀሱ የሚያደርጉ ነገሮችን አለማድረግ ኃላፊነት አለባቸው። ኃላፊነታቸውንም መወጣት አለባቸው።
የተቃዋሚ ፓርቲዎችም ቢሆኑ ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው። ምክንያቱም ይህ ምርጫ ሕዝባችን፣ ምናልባት ለመጀመሪያ ጊዜ ወይም ለሁለተኛ ጊዜ ሊሆን ይችላል ከ97ቱ ምርጫ ወዲህ የሚፈልገውን ፓርቲ፣ እጩ ወይም የሚፈልገውን መሪ የሚመርጥበት ስለሆነ ተቃዋሚዎችም ለግጭት በማይጋብዝና በተረጋጋ መልኩ ሕዝብ ሲቀሰቅሱና ሲያደራጁ፤ ውጥረት በማይፈጥር፣ ለዘብ ባለ መልኩ መሄድ ይጠበቅባቸዋል።
ይሄን ደግሞ ለማድረግ መተማማን ይጠይቃል። የተቃዋሚውም አመራር በመሀከሉ ሰብሰብ ማለት አለበት። እንዲሁም ደግሞ ከገዢው ፓርቲ አመራሮች ጋር በመቀራረብ የግድ በሁሉ ነገር ባንስማማ እንኳን፣ ሌላው ቢቀር ሰላማዊ የምርጫ ቅስቀሳ፣ ሰላማዊ የድምጽ አሰጣጥ፣ ተዓማኒነት ያለው የድምጽ አሰጣጥና ቆጠራ እንዲካሄድ፤ ከዚያ በኋላ አሸናፊውም ተሸናፊውም ውጤቱን በጸጋ እንዲቀበል የሚያስችል ስምምነት ያስፈልጋል።
ይሄን መገንባት ላይ ከሠራን ለሃምሳ፣ ስልሳ ዓመታት ብዙ ወጣቶች የተዋደቁለት ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፌደራላዊ ስርዓት ለመገንባት የሚያስችለንን ጅማሮ ላይ መድረስ እንችላለን። ያ ካልሆነ ግን ገዢው ፓርቲም እንደለመደውና 27 ዓመት ሲያደርገው እንደነበረው ወደ ማፈን፣ የመንግሥትን ሀብትና ተቋማት ለራሱ መጠቀምና ሌሎችን ለማግለል የሚሄድ ከሆነ፣ የተቃዋሚውም ኃይልም በቁጭትና በንዴት ብቻ እየተመራ የሚሄድ ከሆነ፣ ከምርጫ በኋላ ከፍተኛ አደጋ ሊመጣ ይችላል።
ደጋግሜ እንደምለው ይሄ ምርጫ በአግባቡ ከተጠቀምንበት የአገራችን ትንሳኤ ሊሆን ይችላል፤ ያለአግባብ የምንሄድበት ከሆነ ግን የአገር መውደቅ፣ ወደ አገር መፈረካከስና እርስ በርስ ጦርነት ሊወስደን ይችላል።
እውነቱን ለመናገር ሁሉም ነገር ምናልባት ከመቶ በሚያንሱ ሰዎች እጅ ነው ያለው ካልን ብዙም ማጋነን አይሆንም። ያሉት የፖለቲካ አመራሮች በተቃዋሚውም ደረጃ ያሉት፣ በገዢውም ፓርቲ ያሉት ከፍተኛ ኃላፊነት በሚሰማው መልኩ መንቀሳቀስ አለባቸው። አንዱም ወደዚህ የገባሁት ባለኝ እውቀትና ልምድ በዚን ያህል ለመርዳት ነው።
እንግዲህ ፈጣሪ ብልሀቱን ከሰጠንና ትዕግስቱን ከሰጠን ጥሩ ነገር እንሰራለን የሚል ተስፋ አለኝ።
ከምርጫው በኋላ አለመረጋጋቶች ሊኖሩ ይችላሉ የሚል የግል ስጋት አለህ?
ጀዋር፡ አዎ አለኝ፤ ምክንያቱም እኔ የፖለቲካ ተመራማሪ ነኝ፤ ብዙ ለውጦችን አጥንቻለሁ። ብዙ ሽግግሮችን በአካል ሄጄ፤ የተሳኩትንም የተጨናገፉትንም አይቻቸዋለሁ። ሲከናወኑም ከተከናወኑም በኋላ በአረብ ሀገራት፣ በእስያ፣ በምሥራቅ አውሮፓ፣ በደቡብ አሜሪካ እንደ ታዛቢም እንደ ባለሙያም በቅርበት ሳያቸው ስለነበረ ስህተቶች እንዴት ችግር ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ስለምገነዘብ ስጋቶች አሉኝ፤ ፍርሀቶችም አሉኝ።
ሁሌም ስናገር የነበረው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን እንደያዙ በማግስቱ ማድረግ የነበረባቸው ከተቃዋሚው ጋር ቁጭ ብለው የሰፋውን የፖለቲካ ምህዳር እንዴት በአግባቡ እንጠቀምበት፤ እንዴት በኃላፊነት እንጠቀምበት፤ በተለይ ደግሞ ከዛሬ አንድ ዓመት ከስድስት ወር በፊት ምርጫው ሩቅ በሚመስልበት ወቅት በምርጫ ቀነ ገድብ ላይ፣ በምርጫ አካሄድ ላይ፣ በምርጫ ሕግጋቶች ላይ ጠለቅ ያለ ውይይትና ስምምነት ያስፈልግ ነበር።
ያ ባለመሠራቱና በቂ ዝግጅት ስላልተደረገ ስጋት አለኝ፤ ትልቅ ስጋት አለኝ። የተስፋ ጭላንጭሎችም ይታዩኛል። በተለይ ሕዝቡ ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ያሳየው አይነት ትጋት፣ የመንግሥት ንህዝላልነትና ድክመት፣ የፖለቲካ አመራሩ ስህተት የታየበት ሆኖ ሳለ በአገራችን ውስጥ የምንፈራው ግጭትና ቀውስ ባለመፈጠሩ ወደፊትም ሕዝቡ ከዚህ የበለጠ ሥራ ይሠራል፣ ከዚህ የበለጠ ትዕግስትና ብስለት ያሳያል የሚል እምነቱ አለኝ። አመራሩም ምርጫ በቀረበ ቁጥር እየተቀራረበ ይሄዳል የሚል ግምትና ተስፋ አለኝ።
ወደ ምርጫው የገባህበት ዋነኛ ምክንያትህ ይኼ ስጋትህ ነው?
ጀዋር፡ አዎ ይኼ ስጋት ነው። ለረዥም ጊዜ ስለውም ሳስበውም የነበረው እንደኔ ዓይነት ተጽዕኖ ፈጣሪዎች፣ በወጣቱ ላይ ተጽዕኖ ያለን፣ ዕውቀቱም ታዋቂነቱም ያለን ሰዎች ወደ ምርጫ ከምንገባ ይልቅ ባለን ተጽዕኖ በተቃዋሚውም፣ በገዢውም ፓርቲ ላይ ጫና እየፈጠርን ሽግግሩን ማካሄድ ነው የተሻለው የሚል ግምት ነበረኝ።
ባለፈው አንድ ዓመትም ይህንን ነበር ስሞክር የነበረው። በተለይ ደግሞ የትጥቅ ትግል ባሉባቸው አካባቢዎች፣ በኦነግና በመንግሥት መካከል እርቅ እንዲፈጠር፣ ወታደሮች በሰላም ወደ ቀያቸው እንዲገቡ፣ ብዙ ሙከራ አድርገናል። የሕብረተሰብ ግጭቶች በነበሩባቸው በኦሮሞና ሶማሌ፣ በቤንሻንጉልና ኦሮሞ እንዲሁም በአማራና ኦሮሞ መካከልም ያሉ ግጭቶች እንዳይባባሱ ብዙ ጥረት ሳደርግ ነበር።
በሂደት ግን ያየሁት፣ በተለይ ደግሞ በገዢው ፓርቲ አመራር ላይ ብዙ፣ የሽግግር ፖለቲካን ባለመረዳት፣ በአምባገነናዊ ሥርዓት ውስጥ ያደጉ ግለሰቦች ስለሆኑ፣ ሁሉንም ነገር በዚያ በተካኑበትና በለመዱት አምባገነናዊ አካሄድ፤ ማለትም ለፖለቲካ ችግር ፖለቲካዊ መፍትኼ ከመስጠት ይልቅ የሴኪዩሪቲ [ኃይል የመጠቀም] መፍትሄ ወደ መሻት ማዘንበሉ እያየለ ከመምጣቱ የተነሳ ምናልባት እንደኔ ተጽዕኖ ያለን፣ ልምዱም ያለን ሰዎች ወደ ተቃዋሚ ጎራ ከገባን ለመገሰፅም ጫና ለመፍጠርም የኃይል ሚዛኑንም ለማስጠበቅ፣ ይረዳል ወደሚለው እያዘነበልኩ መጣሁ።
በሂደትም ካሉ አመራሮች፣ ምሁራን፣ ከተለያዩ ሽግግሮችን ከመሩ አመራሮች [ከኛ አገር ውጪ ካሉትም] ጋር ስንወያይ የኔ ወደተቃዋሞው መግባቱ የተሻለ አማራጭ ይሆናል ወደሚለው እያዘነበልኩ መጣሁ።
ይህንንም ላሉት አመራሮች፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩም፣ ለተቃዋሚውም፣ ለሁሉም አብራርቼ ነው ወደዚህ የገባሁት። ያለንን ዕውቀትና ተሰሚነት በመጠቀም ይህ ምርጫ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ሕዝባችን የሚፈልገውን ዓይነት በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እንዲያቋቁም እንዲረዳ ያለንን እውቀት ለመጠቀም፣ ያለኝን ጫና ለመጠቀም ነው ወደዚህ ለመግባት የወሰንኩት።
በምርጫው ላይ ለመሳተፍ የአሜሪካ ፓስፖርትህን የመመለስ ሂደት ላይ እንዳለህ ተናግረህ ነበር እርሱ ሂደት ምን ደረሰ?
ጀዋር፡ ፓስፖርቴን መልሼያለሁ። በኔ በኩል የሚጠበቀውን ጨርሼያለሁ። ምንም የሚያግደን ነገር የለም።
ሌላ በምርጫ ላይ ለመሳተፍ እንቅፋት ይሆኑብኛል ብለህ የምትጠብቃቸው ነገሮች አሉ?
ጀዋር፡ ምንም የሉም። ምንም አልጠብቅም። በዚህ ምርጫ ውስጥ እንደማንኛውም የአገራችን ዜጋ፣ እንደ ማንኛውም የፖለቲካ አመራር፣ ኃላፊነቴን እወጣለሁ። መብቴንም እጠቀማለሁ የሚል ግምት ነው ያለኝ። ምንም የምጠብቀው ነገር የለም።
ምርጫው የቀረው ጥቂት ወራት ነው። ከምርጫው በፊት የፖለቲካ ፓርቲዎች አጀንዳቸውንና ፖሊሲያቸውንለሕዝቡ ሲያስተዋውቁ አይታይም።ይህንን እንደ ችግር ታየዋለህ?
ጀዋር፡ በጣም፤ በጣም እንደ ትልቅ ችግር ነው የማየው። የሽግግር ጊዜ ምርጫ የምንለው ከፍተኛ ዝግጅት፣ ከፍተኛ ጥንቃቄ፣ ከፍተኛ ብልሃትና ብስለትን የሚጠይቅ ነው። የምርጫ ሕጉን ከማርቀቅ፣ የምርጫ ጊዜን ከመወሰን ጀምሮ ገዢው ፓርቲ ነው ብቻውን እየወሰነ የመጣው። በቂ ውይይት አልተካሄደም። በርግጥ ገዢው ፓርቲን ብቻ መኮነን አንችልም።
የተቃዋሚ ፓርቲዎችም በጣም ኮስተር ብለው፣ ተባብረው፣ ተስማምተው ጫና አልፈጠሩምና በቁም ነገር አልተወሰደም። ምናልባት እዚህ አገር [የሽግግሩ] የመጀመሪያው ዘጠኝ ስምንት ወር የባከነ ጊዜ ነው የምለው።
እና አሁን የፖለቲካ አመራሮቻችን በምርጫ ሕግጋትና አካሄድ ላይ ጥያቄ የሚያነሱበትን ሁኔታ ነው የምናየው። ይኼ ያሳዝናል። ከዚህ በፊት የዛሬ አንድ ዓመት፣ የዛሬ ሁለት ዓመት መነሳት፣ መፈፀም የነበረበት ነው። አሁን ደግሞ ምርጫው እንደታሰበው በሕጉ መሰረት ግንቦት ላይ የሚካሄድ ከሆነ የመራጮች ምዝገባ የሚጠናቀቅበትና ቅስቀሳ የሚጦፍበት ጊዜ ነበር። ያ አልተካሄደም።
በተለያየ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ የተለያዩ የፖለቲካ አመራሮች ባሉበት፣ በተለይ አቶ ሌንጮ ለታ ደጋግመው ጥያቄ አቅርበው ነበር። የዚህ ምርጫ መካሄድ አለመካሄድን በደንብ እንገምግመው፤ እንስማማበት የሚሉ የተለያዩ ሀሳቦች ሲነሱ ነበር። አድማጭ አልተገኘም። አቶ ሌንጮ ብቻ አይደሉም፤ አቶ ልደቱም የተለያዩ ሰዎችም ሲያነሱ እሰማለሁ። ግን በትኩረት አልተወሰደም። ስለዚህ ይህ ያሳስበኛል።
ያም ሆነ ይህ ግን በኛ በኩል፣ እንደኔም ግምት ዝግጅት ቢኖር ጥሩ ነበር። ዝግጅት አለመኖሩ እንደሚታየን ገዢው ፓርቲ ዝግጅት ከተካሄደ የተቃዋሚው ፓርቲ አድቫንቴጅ [እድል] ይኖረዋል። ሊያሸንፍ ይችላል። ስለዚህ እኛ የመንግሥት አቅምና ቢሮክራሲ ስላለን መጨረሻ ላይም ብንገባ የተሻለ እድል አለን ወደሚለው መደምደሚያ የገቡ ነው የሚመስለኝ። ያ ስለሆነ ተቃዋሚው ጊዜ ማባከን የለበትም። ራሱን ማደራጀት፣ ማዘጋጀት ሕዝቡም ይህንን እድል ለመጠቀም ዝግጁ መሆን መቻል አለበት። በቂ ዝግጅት የለም፤ ግን ዝግጅት የለም ብለን ይህን ምርጫ፣ ይህንን በደም፣ በከፍተኛ መስዋዕትነት የመጣ ዕድል እንዲባክን መጠበቅ የለብንም።
ሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ ቢባል ይሻላል፤ ያለበርበሬ ወጡን ከመብላት ሠርገኛ እየመጣም ቢሆን መቀንጠሱ ይሻላል። ስለዚህ አሁን መቀንጠሱን ማጣደፍ ነው።
እዚህ ውስጥ እንግዲህ ሌላው ተዋናይ ምርጫ ቦርድ ነው። ምርጫ ቦርድ የሚጠበቅበትን እያደረገ ነው?
ጀዋር፡ ምርጫ ቦርድ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ብዙ ነገር እየሞከሩ ነው። እንግዲህ እስካሁን የፈተናቸው ወሳኙ የሲዳማ ሪፍረንደም ነው። መጀመሪያ ላይ በጣም ከፍተኛ ስህተት በመስራት የብዙ ሰዎች ሕይወት እንዲቀጠፍ ከፍተኛውን ሚና የተጫወተው ምርጫ ቦርድ ነው። ከዚያ በኋላ ግን ሪፍረንደሙን [ሕዝበ ውሳኔውን] በተሳካ ሁኔታ በማካሄዳቸው ሊመሰገኑ ይገባል።
ከዚያ ወዲህ አንዳንድ የምናስተውላቸው ግድፈቶች አሉ። ለምሳሌ የገዢው ፓርቲን ውህደት ሙሉ በሙሉ ስርዓትን በጠበቀ መልኩ አይደለም ያካሄዱት። ለምሳሌ ጉባኤዎችን በሙሉ ሄደው ማየት ነበረባቸው፤ በተቃዋሚው ላይ የሚያደርጉትን አይነት ጠለቅ ያለ ምርመራ ሳያከናውኑ ነው ያደረጉት [ውህደቱን ያጸደቁት]። ትንሽ መድልዎ የሚመስል ነገር እየታየኝ ነው። አሁንም ግልጽነት የለም። የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ መቼ እንደሚወጣ የታወቀ ነገር የለም። ሕጉ ግን ውህደቶችና የትብብር ስምምነቶች ሁለቱ አስቀድመው መግባት አለባቸው ይላል። ግን መቼ እንደሚያስታውቁ የምናውቀው የለም። ግልፅነት ይቀረዋል።
ከዚህ አንጻር አንዳንድ የሚያጠራጥሩ ነገሮች እየተፈጠሩ ነው። ሆኖም ግን አመራሮቹን አውቃቸዋለሁ። በተለይ ወ/ት ብርቱካን እዚህ አገር ዲሞክራሲ እንዲመጣ፣ ፍትህ እንዲመጣ በግንባር ቀደምትነት የታገሉ መስዋዕትነት ጭምር የከፈሉ ናቸው። በቅርብም የማውቃቸው ሰው ናቸው።
እዚህ አገር ዲሞክራሲ እንዲሰፍን ከሁላችን የበለጠ እንጂ ባነሰ መልኩ ቁርጠኝነት ያላቸው ሰው ናቸው ብዬ አላስብም። ይህንን ታሪካዊ ኃላፊነት መወጣት አለባቸው። ይህንን ታሪካዊ ኃላፊነት እንዳይወጡ ሊያግዷቸው የሚችሉ አንዳንድ ነገሮች እንዳሉ እናያለን። ለምሳሌ የምርጫ ወረቀቶች የሚታተሙት ዱባይ አገር ባለ ኩባንያ ነው ተብሏል።
ይህ ኩባንያ ከዚህ በፊት በኡጋንዳ፣ በኬኒያና በተለያዩ አካባቢዎች የፈጸማቸው ግድፈቶች የምርጫ መዛባትን በመፍጠር፣ በፍርድ ቤትም የተከሰሰ፣ ሕዝብን ያጫረሰ ድርጅት ነው። እንዲህ አይነት ፊርማ ወስጥ ከመግባታቸው በፊት ወ/ት ብርቱካንም ሆኑ ሌሎቹ መመርመር ነበረባቸው። እንዲህ ዓይነት ነገ ለቁጭት፣ ለግጭት፣ ምርጫ ቦርድንም ለተጠያቂነት ሊያጋልጥ የሚችሉ ነገሮችን በጣም በጥንቃቄ መሄድ አለባቸው።
ተስፋ አለኝ፤ ሕዝቡም በፀሎትም በሁሉም አብሯቸው እንደሚቆም። እኔም እንደ አንድ የፖለቲካ አመራር በተቻለ መጠን ላምናቸው እወዳለሁ። ስህተት ቢሰሩም አውቀው ሳይሆን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ነው የሚል ግምት ውስጥ ነው የምገባው። ግን የሚቀጥሉት ወራት በጣም በጣም ወሳኝ ናቸው። በተለይ ደግሞ የገዢው ፓርቲና ተቃዋሚውን እኩል ሚዛናዊ በሆነ መልኩ የማገልገል ሥራ በጣም በጣም ወሳኝ ነው።
ውስብስብ የሆነው የአገራችን ፖለቲካ በእነዚህ ሰዎች እጅ ነው ያለው። አንዳንዴ ሳያውቁም ሊያዳሉ ይችላሉ። ከእንደዚህ ዓይነት ነገሮች ራሳቸውን እየቆጠቡ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ እንዲሄዱ እማፀናለሁ።
የተለያዩ ፓርቲዎች አብረው ለመሥራት የሚያስችሏቸው እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው። አሁን አንተ ኦፌኮን ተቀላቅለሀል። ሕወሓት ከእናንተ ጋር አብሮ የመሥራት ጥያቄ ቢያቀረብ ትቀበላላችሁ?
ጀዋር፡ በሕወሓትና በእነ ዐብይ መካከል የተፈጠረው በአንድ ቤተሰብ ውስጥ፣ በአንድ ፓርቲ ውስጥ የተከሰተ ግጭት ነው። ይህ ግጭት እንግዲህ ሕወሓት በበላይነት ኢሕአዴግን ሲመራ የነበረ ነው። አብረው አገር ሲዘርፉ ሲጎዱና ሕዝብን ሲያሰቃዩ ነበር። አሁን ይኼ ለውጥ ምስቅልቅላቸውን አውጥቷቸዋል። በመካከላቸው ያለው ግጭት ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን የደህንነትም ጭምር ነው።
ከሁለቱ አንዱን በማቅረብ የዚህ ውስብስብ፣ ብዙ ቆሻሻ ያለበት ግጭት አካል መሆን አንፈልግም። ሕወሓትም ሕገ መንግስቱንና ሕጉን በጠበቀ መልኩ ክልሉን እንደሚያስተዳድር ፓርቲ መብትና ግዴታውን እንደሚወጣ እንጠብቃለን። የፌደራል መንግሥቱም ሆነ የፌደራል መንግሥቱን እየመሩ ያሉት የቀድሞ ኢሕአዴጎችም ግጭትን ባረገበ መልኩ ከሕወሓት ጋር አላስፈላጊ እሰጥ አገባ ውስጥ ገብተው ትግራይንና የፌደራል መንግሥቱን አላስፈላጊ ግጭት ውስጥ ከማስገባት እንዲቆጠቡ በተደጋጋሚ ስንመክር ነበር። አሁንም የምንመክረው እርሱኑ ነው።
ግን እንደኔ ግምትም ሆነ ምክር ሕወሓትን አሁን ወደ ተቃዋሚው በማምጣት በኢሕአዴግ መካከል የተፈጠረውን ግጭት ወደ ራሳችን መጋበዝ የለብንም።
ሕወሓትም ራሱን ችሎ ከኢሕአዴግ ጋር የጀመረውን፣ ከቀድሞ ባልደረቦቻቸው ጋር የጀመሩትን፣ በሰላማዊና ሕጋዊ መልኩ እንዲጨርሱ [ነው የምንመክረው]። [ቀሪው ነገር] ወደፊት በሂደት ምናልባት ከምርጫው በኋላ አሸንፈው የሚመጡ ከሆነ የሚታይ ይሆናል።
ከዚያ ወዲህ ግን የኢህአዴግን የበሰበሰና የተበለሻሸ፣ ብዙ ግለሰባዊ ሽኩቻዎች ያሉበት፣ የአገር ደህንነትን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ሽኩቻዎችና ግጭቶችን፣ ወደ ተቃዋሚው በማምጣት ተቃዋሚውን የዚያ ሰለባ ማድረግ ትክክል ነው ብዬ አላምንም። እኔ ያለሁበትም ሆነ ሌሎቹ ፓርቲዎች እዚህ ውስጥ አይሳተፉም።
የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ለማ መገርሳ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የመደመር ፍልስፍና እንደማያምኑ፣ የተቻኮለ መሆኑንም መግለጻቸውን ይታወሳል። በኋላ ደግሞ ተመልሰው አብረው ለመሥራት ተስማምተዋል። እንደዚህ አይነት ልዩነቶች ሲፈጠሩ ይህ የመጀመሪያው አይደለምና እነዚህ መንገራገጮች ያሰጉሀል?
ጀዋር፡ ለማ መገርሳ የዚህ አገር ታላቅ ባለውለታ ነው። ይህ ትግል እየጦፈ በመጣ ወቅት፣ ሥርዓት ሳይፈርስ አገር ለአደጋ ሳይጋለጥ፣ በድርድር የሚካሄድ ሽግግር እንዲካሄድ፣ የእርሱ ቁርጠኛ አቋም፣ አመራር በጣም በጣም ወሳኝ ነበር። የአገራችን ከፍተኛ ባለውለታ ነው።
ያም ብቻ ሳይሆን ዐብይ አሕመድን ወደ ሥልጣን ያመጣው ራሱ ለማ ነው። ከዚያ በኋላ ዐብይንም አገርንም በከፍተኛ ትዕግሥት አገልግሏል። ልዩነቶች መፈጠር ከጀመሩ ቆይተዋል። ግለሰባዊ አይደሉም። ሽግግሩ የተመራበት አካሄድ ትክክል አይደለም የሚል አቋም ወስዷል። ይህንን በውስጥ የምናውቀው ነው። ሆኖም ግን ሁለቱ ካላቸው ከፍተኛ ሚና አንጻር ሽግግሩ ላይ የሚኖረውን አደጋ ለማ በደንብ አድርጎ የሚረዳ ሰው በመሆኑ የተነሳ ረዥም ጊዜ በውስጥ ብቻ በተወሰኑ ሰዎች መካከል ይዞት ነው የቆየው። መጨረሻ ላይም ተቃውሞ ውህደቱን በአቋም ማክሸፍ ይችል ነበር። ያን ማድረግ ሊያመጣ የሚችለውን ግጭትና አለመረጋጋት በመገንዘብ ውህደቱ ከተፈፀመ በኋላ አቋሙን ለሕዝብ ግልጽ አድርጓል።
ከዚያ በኋላም ነገሮች እየተባባሱ እንዳይሄዱ፣ በኦሮሚያ ውስጥ ሰፊ የሆነ በቢሮክራሲው ችግር መፈጠር ስለጀመረ ነገሮችን በውይይት እንፈታለን በሚል ነገሮችን ወደ መረጋጋት መመለስ ችሏል።
ከዚህ አንጻር ለማ አገርን ለአደጋ የሚያደርስ፣ ክልሉንም ፌዴሬሹኑንም ለአደጋ የሚጥል እርምጃ ይሠራል ብዬ አላምንም። ዐብይም ቢሆን ይህንን የሚረዳ ይመስለኛል። ወደፊትም እንግዲህ እየተወያየን፣ እየተረዳዳን ወደፊት የምንሄድ ነው የሚሆነው። ለማ ቀላል ሰው አይደለም።
አሁን ብቻ ሳይሆን፣ ወደፊትም አገሪቱ ለምትወስደው እርምጃ ከፍተኛ ሚና የሚኖረው ሰው ነው። ከፍተኛ እውቀት፣ ተሰሚነት፣ ያለው ግለሰብ ነው። ወደፊትም ከተስማሙና ፓርቲውን ማሻሻል ሊያቀራርባቸው የሚችል ከሆነ በዚያ፣ ካልሆነ ግን ከተቃዋሚው ጋር በመሆን በግለሰብ ደረጃም ቢሆን ለአገር የሚጠቅም፣ ይህንን ሽግግር የሚያሳካ ሥራዎችን ይሠራል ብዬ ነው የማስበው።
ለማ እንግዲህ የፖለቲካ መሪ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ አዋቂና እንደአገር ሽማግሌም የሚያረጋጋ ሰው ነው። ወደፊትም ለማ ብዙ ነገር ይሠራል የሚል እምነት አለኝ።
አሜሪካ ሳለህ በአሜሪካ የደህንንት ወይም የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያለና ከአንተ ጋር በቅርብ በመነጋገር ወይም በሌላ መንገድ ታደርግ የነበረውን ትግል የሚደግፍ አካል ነበር?
ጀዋር፡ትግሉን ስናካሂድ በነበርኩበትም አገርም ሆነ በተለያዩ አገራት ውስጥ ካሉ ምሁራን፣ የፖለቲካ አመራሮች ጋር ግንኙነት ነበረን። የሀሳብ ልውውጥም ሆነ ትችትም ምክርም ስወስድ ነበር። ከብዙዎች ጋር የተቀራረበ ሥራ ነበረኝ። ምክንያቱም እዚህ አገር ስናደርግ የነበረው እንቅስቃሴ አገራችንን ብቻ ሳይሆን በአገራችን ላይ ብሔራዊ ጥቅም አለን ብለው የሚያስቡ የተለያዩ አካላቶች ተጽዕኖ መፍጠር ይፈልጉ ነበር። ሊረዱ ይፈልጉ ነበር።
እንግዲህ ከ [ትግሉ] ፀባይ አንጻር ከሁሉም ድርጅቶች፣ ከሁሉም ግለሰቦች፣ ከሁሉም አገር መንግሥታት ጋር የቀረበ ውይይት አደርግ ነበር። የሚጠቅም ሃሳብ ሲያመጡ የመውሰድ፤ የማይጠቅም ሃሳብ ሲያቀርቡና አገር ሊጎዳ ይችላል ብዬ ሳስብ ሃሳባቸውን ውድቅ ሳደርግ ነበር። ይኼ ነው ብዬ የምለው ግለሰብ የለም፤ ግን ከብዙ አገሮች፣ ከብዙ አመራሮች፣ ድርጅቶች፣ ተቋማት፣ ምሁራን ጋር የቀረበ ግንኙነት እንደነበረን አስታውሳለሁ።
እነዚህ ግለሰቦች ቁልፍ የሚባል ሚና ያላቸው ግለሰቦች ናቸው?
ጀዋር፡እንግዲህ የተለያዩ ምሁራኖች፣ የተለያዩ የመንግሥት አካላት የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ የ’ቲንክ ታንክ’ አመራሮች ጋር ስሠራ ነበር። ቁልፍ ይሁኑ አይሁኑ ብዙ ስለሆኑ አላስብም። ግን ብዙ ወሳኝ የሆኑ ምሁራኖች በተለይ ደግሞ በዲሞክራታይዜሽን ላይ በሽግግር ላይ የሚሠሩ ምሁራንና ተቋማት ጋር አብሬ ስሠራ ነበር። በግለሰብ ደረጃ ግን እከሌ የምለው አሁን የማስታውሰው የለም።
ከወራት በፊት መንግሥት የመደበልህ ጥበቃዎች ሊነሱ መሆናቸውን በፌስቡክ ላይ ከጻፍክና በሌላ የጸጥታ አካላት የምትኖርበት አካባቢ መከበቡን በፌስቡክ ገጽህ ላይ ካሰፈርክ በኋላ በማግሥቱ ግጭት ተቀስቅሶ የበርካታ ሰዎች ሕይወት አልፏል። እነዚህ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎችን ስታስብ ምንድን ነው የሚሰማህ?
ጀዋር፡ይህንን የፈፀመው የመንግሥት አካል ነው። ሕግን፣ ሥርዓትን፣ ባህልን ባልተከተለ መልኩ ያንን እርምጃ ወስደዋል። በኋላ ላይ እንደተረዳሁት እኔን ብቻ ሳይሆን አገርንና ሽግግሩን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል እርምጃ ነው የወሰዱት። በጣም የሚያሳዝን የሚያሳፍር ክስተት ነበር። ይህ ስህተት፣ ይህ ወንጀል ለፈጠረው አደጋ ተጠያቂው የመንግሥት አካላት ናቸው። ይህንን ደግሞ የመንግሥት አካላት አምኖ የተቀበለው ሁኔታ ነው።
በውስጥ አሠራራቸው አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ከጠቅላይ ሚኒስትሩም ከሁሉም ጋር የተነጋገርንበት ሁኔታ ነው ያለው። በጣም ነው የማዝነው። ፈጽሞ ሊሆን አይገባም። ትናንትና አምባገነናዊ ሥርዓቱን ስንታገል ለመስዋዕትነት ዝግጁ ነበርን። ሕዝባችን ለመስዋዕትነት እንዲዘጋጅ ስንመክር ስንንቀሳቀስ ነበር። ዛሬ ግን ያ አስከፊ ስርዓት ሄዶ ወደ ዲሞክራሲ ለመሸጋገር ተስፋ ባለን ወቅት በማንኛውም ሁኔታ ሕዝባችን አይደለም ሕይወቱ ፍላጎቱ ራሱ እንዲጓደልበት አንፈልግም። በጣም ነው የማዝነው። ከዚህ ስህተት አገራችን አመራሮቻችን፣ ተምረው እንዲህ አይነት አደጋ ፈጽሞ እንዳይፈጸም እንዳንደግመው ቁርጠኛ ሆነን መቀጠል እንዳለብን ነው የምገልጸው።
ከመነጋገር ባለፈ ጥፋቱን ፈጽመዋል የተባሉ ሰዎች ላይ የተወሰደ እርምጃ ስለመኖሩ የምታውቀው ነገር አለ?
ጀዋር፡እኔ እስከማውቀው ድረስ በአንድም ሰው ላይ እርምጃ አልተወሰደም። ይህንን ያደረጉ ሰዎች በግልጽ ይታወቃሉ። የተካደ አይደለም። በዚያን ጊዜ ነገሮች እንዲረግቡ ነው የፈለግነው። ጉዳዩ በሕዝቡ ውስጥ ቁጣ ስለፈጠረ፣ ቁጣ እንዲረግብ ስለፈለግን አጀንዳ መሆን አልፈለግንም፤ ግን ከጠቅላይ ሚኒስትሩም ጋር በግልም በቡድንም ስንወያይ አጥብቀን ተናግረናል። በወቅቱ የመንግሥት አመራሮችም ደጋግመው እንደተናገሩት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በሐረርጌ በአምቦ ባደረጉት ንግግር ጠንካራ የእርምት እርምጃ በአጥፊዎቹ ላይ ይወሰዳል ብለው ቃል ገብተው ነበር። እኔ እስከማውቀው ድረስ ግን እስካሁን ድረስ አንድም የተወሰደ እርምጃ የለም።
ይህ ደግሞ በጣም ያሳዝነኛል። እዚህ አገር እንዲህ አይነት ክስተቶች ብዙ እየተፈፀሙ፣ ሰዎች እየተገደሉ፣ እርምጃ እንወስዳለን ለሕግ ይቀርባሉ ይባላል። ለሕግ ሳይቀርቡ የቀጠሉበት ሁኔታ ነው ያለው። እና ያሳስባል። ምናልባት ምርመራቸውን ሲጨርሱ እርምጃ ይወስዳሉ የሚል እምነት አለኝ።
የዛሬ አራት፣ አምስት ዓመት ወደኋላ ልውሰድህና ትግሉ በተጋጋለበት ወቅት ኢትዮጵያ የነበረችበትን ሁኔታ አይተህ ዛሬ ኢትዮጵያ ያለችበትሁኔታ እንደሚመጣ፣ አንተም ምርጫ እንደምትወዳደር አስበኸው፣ አልመኸው ታውቃለህ?
ጀዋር፡በጣም ነው የፈጠነው። ትዝ ይለኛል እኤአ በ2005 ወደ አሜሪካ እንደሄድኩ በዚያ ላለው የኦሮሞ አመራር፣ በ2020 የኢህአዴግን ሥርዓት በመጣል ወደ ዲሞክራሲ መሸጋገር አለብን ብዬ ሳቀርብ [ፈገግታ] በጣም ነው የተቆጡኝ።
15 ዓመት ይህ አምባገነናዊ ሥርዓት እንዲቆይ ትፈልጋለህ እንዴ በሚል፤ እንደውም እነርሱ ናቸው የላኩት የሚል ማጣጣል ነበር የደረሰብኝ። ከዚያ በኋላ በስፋት አጠናሁ። በተለይ ሰላማዊ ትግልን በሕንድ አገር፣ በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ፣ በተለያዩ አገራት በመሄድ በስፋት ካጠናሁ በኋላ ይመስለኛል ከ2007 በኋላ ዕቅድ ነደፍን።
በ2020 እኤአ ይህንን ሥርዓት መጣል አለብን የሚል አቅደን ነው ወደ እንቅስቃሴ የገባነው። ነገሮች በጣም በጣም ፈጠኑ። ሁለት ዓመት ቀድሞ ያ ያሰብነው በመሳካቱ ፍጥነቱ ስኬት ብቻ ሳይሆን ጉዳትም አምጥቷል።
አንዳንድ ያሰብናቸው ነገሮች ነበሩ። ለምሳሌ ፓርቲዎችን የማደራጀት፣ አቅም የመገንባት ሥራዎች ወደኋላ ቀሩብን። አንዳንዴ ቁጭ ብዬ ሳሰላስል ምናልባት አሁን የምናያቸው ችግሮች፣ ስህተቶች፣ በአግባቡ ያልተመራ ለውጥ ሽግግር ሳይ በአግባቡ ልንመራው እንችል ነበር የሚል ግምት አለኝ። አንዳንድ የፈራኋቸው ነገሮች አሉ።
ስለሽግግር መናገር መጻፍ የጀመርኩት 2016 አካባቢ ነው። ከእሬቻው ክስተት በኋላ። ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ሊገባ ይችላል በሚል በጣም ሰግቼ ነበር፤ አንዱ ኢሕአዴግ እንዳይወድቅና በውስጡ ለውጥ እንዲመጣ በጣም የገፋሁበት ምክንያት ኢሕአዴግና መንግሥት፣ መንግሥትና አገር አንድ ስለሆኑ መፈረካከስ ይመጣል ብዬ እፈራ ነበር። ያ በፈራሁት ደረጃ ባለመምጣቱ ደስተኛ ነኝ።
ሆኖም ግን የነበረኝ ተስፋ እነ ዐብይ መጀመሪያ እንደመጡ አካባቢ፣ ገዱና ለማ ሊሰጡ ይችሉ የነበረው አመራር፣ ሁለቱ ከቦታቸው በመነሳታቸውና በመገፋታቸው የተፈጠረው ክፍተት አደጋ ጋርጦብናል።
ዛሬ ለምርጫ አምስት ወር ቀርቶን የምናያቸው መልፈስፈሶች፣ የምናያቸው ብልሃት የጎደላቸው ንግግሮችና እርምጃዎችን ሳይ ደግሞ ያሳዝነናል። ሆኖም ግን አምስት ዓመት ወደኋላ ሄጄ ሳስብ ፍጥነቱ በጣም ይገርመኛል። የደረስንበት ሁኔታ ደግሞ ተስፋ ይሰጠናል።
ቅድም እንዳልኩት በተስፋ፣ በስጋት፣ በቁጭት መካከል ነው ያለሁት። ግን ለምርጫ እወዳደራለሁ የሚል ግምትም እቅድም አልነበረኝም። እኔ አላማዬ አምባገነን የነበረውን ሥርዓት አምበርክከን፣ ሽግግር ጀምረን ከዚያ ኮምፒውተሬን ሰቅዬ ወደ ዩኒቨርሰቲ መመለስ ነበር። ያ አልሆነም።
አሁንም ተገድጄ በትግል ውስጥ እንድቆይ የሆንኩበት ሁኔታ ደግሞ ትንሽ ይቆጨኛል።
Filed in: Amharic