>

እውነት ክርስቶስ ተወልዶልናል? (ከይኄይስ እውነቱ)

እውነት ክርስቶስ ተወልዶልናል?

 

ከይኄይስ እውነቱ

 

በቅድሚያ ለክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት አደረሳችሁ፡፡ 

 

የጽሑፌ ርእስ የተወለደው ይህንን የበዓል መልካም ምኞት ስናገር በአእምሮዬ ይመላለስ ከነበረው ሃሳብ ነው፡፡ እንደማናቸውም ጊዜ በዓለ ልደቱን ለማክበር ደቡብ መሀል አ.አ. ከሚገኘውና አጥቢያዬ ወደሆነው ቤተክርስቲያን ሳመራ እንደሌላው ጊዜ ምሽቱ አስረሽ ምቺው ነግሦበት ነበር፡፡ ሰዉ በተለይ ወጣቱ በየመሸታና ዳንስ ቤቱ ነው ሌሊቱን የሚያሳልፈው – ‹በዓሉን› ምክንያት በማድረግ (በወገኖቻችን የደረሰውን የትናንትናውን እልቂት ዘንግቶ) ፡፡ ለቅዳሴ ለውዳሴ ያደርኹበት ቤክ በተቃራኒው ከወትሮውም በተለየ መልኩ እንኳን ቅጥረ ግቢው በሕንፃ ቤ/ክርስቲያኑም ውስጥ የነበረው ምእመን ጥቂት ነበር፡፡ 

 የእምነቱ ተከታዮች የሆንን ኢትዮጵያውያን ‹ክርስቲያኖች› (በአስተምሕሮ እና በሥርዓት/ቀኖና ረገድ ያለውን ክፍፍል ለጊዜው ወደ ጎን አድርገን) በውኑ ክርስቶስ ተወልዶልናል? ከ2012 ዘመን በኋላ የክርስቶስ ትምህርቱ/ትምህርተ ክርስትና ገብቶናል? በሕይወታችን፣ በኑሮአችን ተገልጧል? ከመቶ አንድ እጅ እንኳን? ራሳችንን ብንጠይቅ/ብንመረምር መልሳችን አንገት የሚያስደፋ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ምክንያቱም አገራችንና ሕዝቧ ግዙፍ ምስክሮች ነንና፡፡ ከእንስሳት በታች ያለንበት ተዋርዶ በቂ ምስክር ነውና፡፡ በየትኛውም የሕይወት መስክ ዕብደትና ድንቁርና መንገሡ ያሳጣናልና፡፡ ጋሼ መሥፍን ደጋግመው እንዳስተማሩን አለመደማመጡ፣ አለመተባበሩ፣ አለመተማመኑ/መጠራጠሩ፣ ከሃሳብ/ከንግግር ይልቅ በኃይል/በጡንቻ መተማመኑ፣ በትእቢት ተወጥሮ መፎከሩና መሸለሉ፣ መናናቁ፣ ለእውነት ደንታ ቢስ መሆኑ፣ ለእኔ ብቻ የሚለው ቅጥ ያጣ ስግብግብነቱ፣ እስከ የሌለው ክፋትና ጭካኔው፣ ከሁሉም በላይ ለዘመናት ጭቆናን ተቀብሎ ተረኛ ጨቋኝን ብቻ ለማጥፋት መዳከሩ፣ መሪውም ተመሪውም (በቤተመንግሥት ሆነ በቤተ እምነቶች) ተስተካክሎ መበደሉ፣ መንፈሳዊ አባቶችና መካር ሽማግሎች ለወሬ ነጋሪ መጥፋታቸው፣ ወገን ወገኑን ለማጥፋት በየጎጡ በጎሣ አለቆች አስተባባሪነት ጦር እየሰበቀ፣ ቀስቱን እየቀሠረ ‹ሠራዊት› አደራጅቶ በዝግጅት ላይ መሆኑ ወዘተ. የነዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ያስከተለው የመንፈስ ድርቀት ሰውነትን፣ ኢትዮጵያዊነትን፣ የአገርና የሕዝብ አንድነትን አሳጥቶ ኢትዮጵያን በጥፋት ቋፍ ላይ ማድረጉ ድንቄም ክርስትና የሚያስብል ነው፡፡ 

የማናፍር ጉዶች! በሞግዚት እንደሚተዳደር ሕፃን ኃላፊነታችንን ሁሉ እናመልከዋለን ለምንለው አምላክ አስረክበን  አገር በዓይናችን ሥር ቀስ በቀስ እየፈረሰች አያይ! ለእግዚአብሔር ልዩ የቃል ኪዳኑ አገር ነችና አትፈርስም እያልን ራሳችንንም ሆነ እግዚአብሔርን ለማታለል እንሞክራለን፡፡ ግብዞች! የተባለው ቃል ኪዳን አለ ብለን እናስብ፡፡ በታሪክ እሥራኤላውያን ለቃል ኪዳን ሕዝብነት ከእኛ አይቀርቡም? በሕገ ኦሪት በሙሴና በሌሎቹ አርእሰት አበው አማካይነት፣ በሕገ ወንጌል ደግሞ ክርስቶስ ከነሱ ወገን በመገለጡ፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተመዘገበው ኢየሩሳሌም አልፈረሰችም ወይ? እሥራኤላውያን ለሰባ ዘመን ተማርከው ወደ ባቢሎን አልተሰደዱም ወይ? ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ ወንድማችን ዶ/ር ተድላ እንዳለው እግዚአብሔርን በምናባችን እንደሣልነው ለፖለቲካ ቁማራችን ወይም ለግል ፍላጎታችን አንጠቀምበት፡፡ ሕግና ትእዛዝ ተላላፊዎችን በቁጣው በመዓቱ ይጎበኛል÷ ይቀጣል፡፡ ሕግ አክባሪዎችን ደግሞ በምሕረቱ በይቅርታውና በቸርነቱ ይጎበኛል÷ ይታደጋል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ኰናኔ በጽድቅ፣ ፈታሔ በርትዕ ነውና፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት በእንደዚህ ዓይነቱ የእግዚአብሔር ባሕርያት ታሪኮችና ምሳሌዎች የተሞሉ ናቸው፡፡ ቃል ኪዳኑ እውነት ነው ቢባል እንኳን እርስ በርስ ተለያይተን፣ በድለንና አጥፍተን በቀጣይም ከእስካሁኑ ለባሰ እልቂት በግልጽም በሽምቅም እየተዘጋጀን፣ በፊቱ የምናሳየው በጎ ሥራ/ምግባር ሳይኖረን እንዴት አገራችን አትፈርስም በማለት በባዶ ሜዳ እንመጻደቃለን? ስለ ቃል ኪዳን ማውራትና በተአምር ማመን ለየቅል ናቸው፡፡ ትውልዱ አይጠይቅም፡፡ ማንም በስሜት ነፋስ ይነዳዋል፣ ማንም በስሜት ጎርፍ ይወስደዋል፡፡ ሐሳውያን ባህታውያን፣ ሐሳውያን ፓስተሮች፣ ሐሳውያን ትንቢተኞች (አገዛዙ ወይም አገዛዙን ተገን አድርገው ለሽብር የተሠማሩ ቡድኖች ለዓላማቸው የፈስ ቡክ ሠራዊት እንዳሠማሩ ሁሉ፣ እነዚህንም በየሜዳው ያሠማሩአቸው ይመስላል) እንደ አሸን ፈልተው ይህንን በቀቢፀ ተስፋ ያለ ትውልድ መዓት መጥቷል እያሉ ያስፈራሩታል÷ በተቃራኒው ደግሞ እጁን አጣጥፎ እንዲቀመጥ የተቈረጠ የጊዜ ሰሌዳ አስቀምጠው በባዶ ተስፋ ያነኆልሉታል፣ ከወዲህ ወዲያ ያላጉታል÷ ያንገዋልሉታል፡፡ ዛሬ በዚህ የውሸት ማዕበል የተነሳ ልጆቹን አደብ ማስገዛት የተነሳው ቤተሰብ ቊጥር የለውም፡፡ ‹ሕማሙ› ከልጆች አልፎ ወደ ወላጆች ተጋብቷል፡፡ ችግሩ ከደረሰባቸው አዛውንቶች የሰማሁት ነው፡፡

ትውልዱን እንዴት እንታደገው÷ ምን ይሻላል? ትምህርት ቤቶች የግጭት ዓውድማዎች በሆኑበት፣ አገዛዞች ዕውቀትና ጥበብን ያለ ባሕርያቸው የውሸት አገልጋይ ባደረጉበት፣ መንፈሳዊ አባቶችና በጎ መካር ሽማግሎች በሌሉበት መፍትሄውን ከየት እናምጣው? የመንፈሳዊ ሕይወት ድርቀቱን በኢኦተቤክ ምሳሌነት ብናየው አንድ የቤክ አባት ሲመነኩስ ዓለምን መተዉ፣ መናቁ፣ ከዓለም ፍትወት መለየቱ ነው፡፡ ከዚህ አልፎ እንደ ሞተ ሰው ኾነ ነው የሚለው የመዝገበ ቃላት ፍቺው (ከሣቴ ብርሃን ተሰማ)፡፡ ንዋይ/ከብት፣ የጎሣ ተዛምዶ፣ ሌላው ዓለማዊ ነገር ሳያሸንፈው ከእውነት÷ ከነፃነት÷ ከሰብአዊነት÷ ከፍትሕና ርትዕ÷ከእኩልነት ወዘተ ጋር በመቆም የሰማያዊው መንግሥት እንደራሴ በመሆን ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ተጋብቷል፡፡ በአደራ የተሰጠውን ‹መንጋ› በእረኝነት ለመጠበቅ፡፡ እነዚህን መንፈሳዊ ዕሤቶች በሰማዕትነት ጭምር ለመጠበቅ፡፡ እንደ ኢትዮጵያዊው ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስ፡፡ ዛሬ እነዚህ ሰዎች ተልእኮአቸውን ዘንግተው ዓለማዊ ጥቅም አሸንፎአቸው ለምድራዊ አገዛዞች ባርነት አድረዋል፡፡ በጎላው ለመናገር መነኰሳትን አነሳሁ እንጂ ባጠቃላይ ሥልጣነ ክህነት የያዙትን ሁሉ ይመለከታል፡፡ ዛሬ የኢኦተቤክ በአመዛኙ የወንበዶች ዋሻ ሆናለች፡፡ (የሊቃውንት ማፍሪያ የነበረችው ቤት ካድሬዎች ተሠግሥገውባት ‹መጋቤ ምሥጢር›፣ ‹መጋቤ ሐዲስ›፣ ‹መልአከ ምንትሴ› ወዘተ. የሚሉ ማዕርጋት ተሸክመው ከአብነት ትምሀርቱ የማይተዋወቁ በርካታ ሐሳውያንን ታቅፋ ተቀምጣለች፡፡ (አንድ የቅ/ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ኮሌጅ መምህር በቅርብ ለማውቃቸው የመጻሕፍትና ቅኔ መምህር ጓደኛቸው ሲያጫውቱ ቊጥራቸው ቀላል የማይባል የተጠቀሰውን ማዕርጋት የያዙ ተማሪዎች በት/ቤቱ በየጊዜው የሚሰጠውን መመዘኛ ፈተናዎች  መመለስ እንደተሳናቸው ተናግረዋል)፡፡ ቤተክርስቲያኗ እንኳን ትውልዱን ልትታደግ ራሷ ታዳጊ ትፈልጋለች፡፡ ታዲያ የምእመናንና ካህናት መገደል፣ የ‹መንጎች› መባዘን፣ የአብያተክርስቲያናት መቃጠል ያስደንቀን ይሆን? እንዳትሳሳቱ ነውረኛ ድርጊቱን እያፀደቅኩ አይደለም፡፡ ከመወገዝም አልፎ፣ አገዛዙ ዋና ተልእኮውን እንደ ቤተክህነቱ ባይዘነጋ ኖሮ ሕግና ሥርዓትን በማስከበር እልቂቱንና ውድመቱን ቢያንስ መቀነስ ይችል ነበር፡፡ ላገር ለወገን ባለመጨነቁ ደዌ ያልተመታ የለም፡፡ ለኢኦተቤክ የተነገረው ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ ለሌሎችም ቤተ እምነቶች የሚሠራ ይመስለኛል፡፡ ስለሆነም ቤተ እምነቶች ዓላማና ተልእኮአቸውን በመረዳት በቅድሚያ ራሳቸውንና ቤታቸውን ያፅዱ፡፡ ይህን ካደረጉ ከአገዛዞች በተሻለ ለአገርና ለወገን የሚጠቅም ተግባር ማከናወን ይችላሉ፡፡

ዛሬ እግዚአብሔር በጊዜው ጊዜ ወደዚህ ዓለም መጥቶ ሰው ሆኖ የተወለደበት ምሥጢር ቢገባን ኖሮ፣ የምሥራቹን ቃል (ወንጌልን) ብንረዳው ኖሮ፣ የፍቅርና የነፃነት ትርጕም በገባን ነበር፡፡ በይስሙላና በቃል ሳይሆኑ በተግባር የሚገለጡት ፍቅርና ነፃነት ከገቡን አሁን ከምንገኝበት ዐዘቅት አንገባም ነበር፡፡ ከዐዘቅቱም ለመውጣት አያዳግተንም ነበር፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍ እንደሚያስተምሩን ሕግጋተ እግዚአብሔር በሁለት ፍጹማን ሕጎች ሊጠበቁ ይችላሉ፡፡ በፍቅረ እግዚአብሔር (እግዚአብሔርን ከወደዱ ሕግና ትእዛዛቱን ማክበር ይኖራልና) እና በፍቅረ ቢፅ (ባልንጀራን/በተፈጥሮ ሰው የሆነውን ሁሉ/ እንደራስ አድርጎ በመውደድ)፡፡ ይቅርታውና ዕርቁ፣ አንድነትና ሰላሙ፣ መተማመኑና መተባበሩ ከእነዚህ ሕግጋት ይመነጫሉ፡፡ ይሁን እንጂ በምድር ላይ ከሚታየው ጽድቅ (እውነት) ተነስተን መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ‹ያልተወለደለት› ‹ክርስቲያን› በቊጥር የሚያመዝን ይመስለኛል፡፡

Filed in: Amharic