>

የወለደ አይጥልም!!! (መስከረም አበራ)

የወለደ አይጥልም!!!

 

 

መስከረም አበራ
አንድ ስሙን በማላስተውሰው መፅሃፍ ውስጥ (ሌኒን አለው ተብሎ የተቀመጠ መሰለኝ) ያነበብኩት ጥቅስ “Some weeks are longer than a year; some decade are shorter than a week” ይላል(ቃል በቃል ካላልኩት ይቅርታ ይደረግልኝ ሃሳቡን ግን አልሳትኩም)፡፡ በእኛ ሃገርም ወያኔ ከአድራጊ ፈጣነቷ “ወረድ በይ” ከተባለች በሁለት አመት ውስጥ የተከናወነው ፖለቲካዊ ሁነት ብዛቱ፣አስገራሚነቱ፣ፍጥነቱ ለውጥ ከመጣ በአስራ ሁለት አመት ያስቆጠረ የሚመስልበት አጋጣሚም አለ፡፡
 ከነዚህ ገራሚ ነገሮች አንዱ “መሃል መንገድ ፈላጊ ነኝ” የሚሉትን ዶ/ር መረራን ፅንፈኝነቱን አድማስ እንኳን የሚመልሰው ከማይመስለው  ጃ-war ጋር ያወዳጀው፤በኤርትራ በረሃ ሊጋደሉ ሲፈላለጉ የነበሩትን ኦቦ ዳኦድ ኢብሳን እና ጀነራል ከማል ገልቹን ያጣመረው የኦሮሞ ፓርቲዎች ጥምረት ነው፡፡ዶ/ር መረራ የእነ ዳኦድ/ከማል/ዲማ/ሌንጮን/ገላሳን ኦነግ (እናትየውን ኦነግ) በክፍል ውስጥ ሌክቸር ሲያደርጉ “least likely to succeed” በሚል የሚያጣጥሉት እንደነበረ ተማሪያቸው የነበረ ጓደኛየ እንዳጫወተኝ አስታውሳለሁ፡፡ ጃዋር ደግሞ ኦነግጎችን በከፋፋይነት፣አውራጃዊነት፣አሳፋሪነት እና  “Retarded” ታጋይነት ሲሞልጫቸው ነበር፡፡ አሁን እነዚህ ሰዎች አንድ ላይ ለመታገል ተሰልፈዋል፡፡ይህን ከመሰለ መራራቅ ወደ መቀራረብ ብሎም አብሮ ወደመስራት መሄዳቸው ጥሩ ነው፡፡ (የአቶ ጃዋር  የኢትዮጵያ ዜግነት እና የበአፉ በመለፍለፉ ያመጣቸው ወንጀሎች ተጠያቂነቱ ነገር እንዳለ ሆኖ)
እነዚህ ሲራከሱ የኖሩ ፓርቲዎች በአንድ የመጡት ለምንድን ነው ብሎ ሲጠየቅ የሚመጣው መልስ ነው ዋናው ነገር፡፡ ፓርቲዎቹ የተጣመሩት በየተወለዱበት አካባቢ ብልፅግና ፓርቲ ድምፅ እንዳይተርፈው ለማድረግ ነው፡፡ወለጋን በኦቦ ዳኦድ፣አርሲን፣ባሌን፣ሃረርጌ አካባቢን የጀነራል ከማል እና የጃዋር ውልደት ሳቢያ በማድረግ፤ምዕራብ ሸዋን (አምቦን) በዶ/ር መረራ በአካባቢው መወለድ ምክንያት  ድምፅ ለማግኘት ነው ጥምረቱ የተፈለገው፡፡
የሚሸጥ ሃሳብ የሌለው ወደ ተወለደበት ቀየ ሄዶ “ወልደህ ያሳደግከኝ ህዝብ እንደሚሆን አድርገኝ” ማለቱ የተለመደ ነው፡፡ይህ ነገር በልጅነታችን የማናሸንፈው ልጅ ወደ ሰፈራችን ሲመጣ ጠብቀን ሃይለኝነት እንደሚሰማን፤ ለመሳደብ ድንጋይ ለመወርወር እንደምንሯሯጠው ይመስለኛል፡፡
የሚገርመኝ ግን ከዚህ ሁሉ ትምህርት፣ከዚህ ሁሉ የህይወት ልምድ በኋላም ከተወለዱበት ቀየ በቀር “እህ!” ብሎ የሚሰማ ማጣት፣ምርጫ በመጣ ቁጥር እትብት ወደ ተቀበረበት መንደር ማዝገሙ የሚያኮራ ድል ነው ሽንፈት? የትውልድ ቀየ ሰውማ ይመርጥ ዘንድ ከምረጡኝ ባዮቹ እናት አባት ጋር በእድር እቁብ መተሳሰሩ እንኳን ለመምረጡ በቂ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡
Filed in: Amharic