>

የአሕመዲን ጀበል  አይን ያወጣ ቅጥፈት! (አቻምየለህ ታምሩ)

የአሕመዲን ጀበል  አይን ያወጣ ቅጥፈት!

 

አቻምየለህ ታምሩ
የጽሑፌን ርዕስ «የአሕመዲን ጀበል አይን ያወጣ ቅጥፈት» ስል የሰየምሁት አሕመዲን ጀበል ዛሬ በፌስቡክ ገጹ «11ዱ የአፄ ኃይለ ሥላሴ ፀረ-ሙስሊም ስትራቴጂዎች» በሚል ርዕስ ባተመው  ጽሑፉ በ1909 ዓ.ም. የተነገረን  አንድ አዋጅ  በሚፈልገው መልኩ ጎምዶ ካቀረበ በኋላ አዋጁን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እንዳወጁት አድርጎ  እሳቸው ያላወጁትን አዋጅ አውጀዋል ብሎ በመቅጠፉ ነው። ሰው ያልተናገረውን ተናገረ፤ ያላደረገውን አደረገ ብሎ የሚናገርና የሚጽፍ ሰው ቀጣፊ ነው። ለዚህም ነው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ያላወጁትን አዋጅ እሳቸውን ለማጠልሸት ብቻ  ስለሚጠቅመው የሳቸው ያልሆነን  አዋጅ የሳቸው አዋጅ አድርጎ  ጎምዶ በማቅረብ አይን ያወጣ ቅጥፈት የፈጸመው አሕመዲን ጀበልን የደረተውን ውሸት  «የአሕመዲን ጀበል አይን ያወጣ ቅጥፈት» በሚል   አይን ያወጣ  ቅጥፈቱን ለማጋለጥ ለመጻፍ የተነሳሁት።
አሕመዲን ጀበል ቀደም ብዬ የጠቀስሁትን የፌስቡክ ጽሑፉን [«ሦስቱ አጼዎችና ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች» ከሚለው  መጽሐፉ የተቀነጨበ ነው] መጻፍ  የጀመረው  “‹‹… ተምረው ቢሰለጥኑና አንድ ቢሆኑ በአካባቢያቸው ካሉት ዓረብና እስላም ሀገሮች ጋር እየተገናኙ ኢትዮጵያዊ ለሆነው የክርስቲያን ሕዝብ ከባድ የሆነ ችግር ይፈጥራሉና እንዲሁ ዘላን ሆነው እየተጋደሉ ይቆዩ …›› (የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግስት)” በሚል ጥቅስ ነው። ሆኖም ግን ይህንን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቃል አድርጎ የጠቀሰውን ንግግር ንጉሡ የት እንዳደረጉትና እሱም  ከየት እንዳገኘው አይናገርም። ተከታዮቹም እንዲህ ከአእምሮው አንቅቶ ሲነግራቸው «ምንጭህ ከምን?» ብለው ሳይጠይቁ እንደወረደ ሀቅ አድርገው ይቀበሉታል። አሕመዲን ይህን ጥቅስ በመፍሐፉም ውስጥም  ያከተተው  እንዲሁ በበሬ ወለደ  ያለ ምንጭ ነው። ለነገሩ ሳይመረምር የሚያስተጋባ ተቀባይ ስላለው ለምን ይጨነቃል።  እስቲ ማሰብ የጀመራችሁ  ተከታዮቹ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እንደተናገሩት አድርጎ የጠቀሰውን ንግግር ከየት እንዳገኘው ጠይቁት! ምንጭህ ከምን በሉት እስቲ?
በመቀጠል  አሕመዲን ጀበል ወደሰራው  ሁለተኛ ነውርና አይን ያወጣ ቅጥፈቱን ወደ ማቅረብ ልሸጋገር። አሕመዲን ጀበል «11ዱ የአፄ ኃይለ ሥላሴ ፀረ-ሙስሊም ስትራቴጂዎች» በሚል ርዕስ  ዛሬ በፌስቢክ ገጹ ላይ ባተመው  ጽሑፉ አራተኛ አንቀጽ ላይ የሚከተለውን ጽፏል፤
«ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ፀረ-ሙስሊም ዘመቻቸውን ማጧጣፍ የጀመሩት ገና ሥልጣን ሳይቆናጠጡ ነበር። ሥልጣን አያያዛቸው ራሱ ሙስሊሙ ላይ በተሸረበ ሴራ ነበር። ‹‹እስላም አይነግስም!›› በሚል በመኳንንትና በቀሳውስት የጋራ ፀረ-ኢስላም አድማ ነበር ግንባር ፈጥረው ልጅ እያሱን የጣሉት። እንዲህ ሲሉ ነበር ያወጁት፡- ‹‹አዋጅ! የኢትዮጵያ ሕዝብ ስማ! መስሚያ አይንሳህና ልጅ እያሱ ወደ እስላም ሃይማኖት ስለገቡ መንግሥት አይገባቸውም…… ከአዋጁ በላይ የእስላም ወገን ሆኖ ሲረዳ የተገኘ አይቀጡ ቅጣት ይቀጣል›› (መርስኤ ሀዘን ወ/ቂርቆስ፣ የዘመን ታሪክ ትዝታዬ በንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ ዘመነ መንግስት፣ 1938 የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ማዕከል 2062.C፣ ገጽ 24)
አሕመዲን ጀበል የጻፈውን እንዲህ ካቀረብን በኋላ አሁን የአሕመዲን ጀበል ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አዋጁ ብሎ ያቀረበው አዋጅ እውነት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አዋጅ  ስለመሆኑ ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ «የዘመን ታሪክ ትዝታዬ በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመነ መንግስት» በሚል ከጻፉት የዘመን ታሪክ ትውስታቸው ውስጥ ገብተው እንመርምር። አሕመዲን ጀበል ጎምዶ ያቀረበውና ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስን «የዘመን ታሪክ ትዝታዬ በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመነ መንግሥት» በሚል በጻፉት የዘመን ታሪክ ትውስታቸው ውስጥ ያቀረቡት ሙሉው አዋጅ በታተመው  የዘመን ታሪክ ትውስታቸው ገጽ  151 ላይ ይገኛሉ።  ሙሉው አዋጅ ከነ መንደርደሪያው  የሚከተለውን ይመስላል፤  [አንባቢ በራሱ ያገናዝበው ዘንድ  አዋጁን የያዘውን  ገጽ ከታች አትሜዋለሁ]
_______
«. . . [የንግሥተ ነገሥታው ዘውዲቱ ቃል ከተነበበ] በኋላ ጸሐፌ ትዕዛዝ አፈወርቅና ሊጋባ በየነ አደ አዋጅ መንገሪያው ስፍራ ሄደው ዓዋጅ አስነገሩ። የአዋጁ ቃል ከጥቂት ልዩነት በስተቀር መስከረም 17 ቀን ከተነገረው ጋር ተመሳሳይ ነው። እርሱም ቀጥሎ ያለው ነው፤
ዓዋጅ 
የኢትዮጵያ ሕዝብ 
ስማ ስማ መስሚያ አይንሣህ
ልጅ ኢያሱ ወደ እስላም ሃይማኖት ስለገቡ መንግሥት አይገባቸውም  ብለን ሽረን በእርሳቸው ፈንታ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱን አንግሠናል። የንጉሥ ሣህለ ሥላሴን ዘር የራስ መኮንንን ልጅ ራስ ተፈሪን ደግሞ አልጋ ወራሽ አድርገናልና ስለ ሃይማኖትና ስለ አገርህ በያለህበት ጠንክረህ እርዳ። ከዓዋጁ በላይ የእስላም ወገን ሆኖ ሲረዳ የተገኘ አይቀጡ ቅጣት ይቀጣል።»
ይህ ጽሑፍ አሕመዲን ጀበል የጠቀሳቸው ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስን «የዘመን ታሪክ ትዝታዬ በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመነ መንግሥት» ከጻፉት እንደወረደ የቀረበ ነው።
እንግዲህ ይታያችሁ! እንዲህ የሚለውን አዋጅ ነው አሕመዲን ጀበል ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ያስነገሩት አዋጅ አድርጎ የሚያቀርበውና  አንባቢን የሚያሳስተው።  አሕመዲን ጀበል አላማው ታሪክን መመርመር ሳይሆን ንጉሡን ማውገዝ ስለሆነ ተነገረ ያለውን  አዋጅ እንኳ  ሲጠቅስ  የአዋጁን ሙሉ  አረፍተ ነገር አማልቶ አልጠቀሰውም።   የአዋጁን ሙሉ አረፍተ ነገር ቢጠቅሰው  እሱ  ለሚፈልገው ፖለቲካ ስለማይጠቅመው  «ልጅ ኢያሱ ወደ እስላም ሃይማኖት ስለገቡ መንግሥት አይገባቸውም  ብለን ሽረን በእርሳቸው ፈንታ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱን አንግሠናል።» የሚለውን የአዋጁ ሙሉ አረፍተ ነገር  ከወገቡ ላይ ጎምዶ «ልጅ እያሱ ወደ እስላም ሃይማኖት ስለገቡ መንግሥት አይገባቸውም……» ብሎ ሌላ ትርጉም  አሰጥቶ አቀረበው።  በሃይማኖት ስሙ የሚሰራው እንዲህ  አይነቱ ኅሊና ቢስነት “Academic Offence” ነው።
ምይ ይሄ ብቻ! አዋጁን ሲጠቅስ «የንጉሥ ሣህለ ሥላሴን ዘር የራስ መኮንንን ልጅ ራስ ተፈሪን ደግሞ አልጋ ወራሽ አድርገናልና ስለ ሃይማኖትና ስለ አገርህ በያለህበት ጠንክረህ እርዳ።» የምትለዋን  የአዋጁን ሌላኛውን አረፍተ ነገር  በመዝለል «የንጉሥ ሣህለ ሥላሴን ዘር የራስ መኮንንን ልጅ ራስ ተፈሪን ደግሞ አልጋ ወራሽ አድርገናልና. . . » ከሚለው አረፍተ ነገር ውስጥ  አንባቢ አዋጁን ያወጁት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሳይሆኑ እሳቸው ያነገሡ አካላት መሆናቸውን እንዳያውቅ ሆን ብሎ አንባቢን አጭበርብሯል።
እንግዲህ! አሕመዲን ጀበል  በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ላይ የሚዘምተውና ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነታቸው ላይ እንዲያምጹ የሚያደርገው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ያላወጁትን አዋጅ እንዳወጁ አድርጎ በማቅረብ፤  የሚጠቅሰውንም  ጽሑፍ  አረፍተ ነገር ነገር በመጉመድና በመዝለል  በቅጥፈት ነው። እንግዲህ ስለተያያዝን  ወደፊት በሌሎች ቅጥፈቶቹ  ዙሪያ እውነቱን ከምንጭ እየጠቀስሁ በሰፊው እመለስበታለሁ!
 የታተመው ማስረጃ  አሕመዲን ጀበል ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጸረ ሙስሊም አድርጎ ለመወንጀል  ሲል እንዳወጁ አድርጎ  ጎምዶና ዘልሎ ያቀረበው አዋጅ ሙሉውን ምን እንደሚመስልና  አዋጁን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሳይሆኑ እነ ማን እንዳስነገሩት የሚያሳይ ነው። አሕመዲን ጀበል በቅጥፈት የጻፈውንና በጠቀሰው ምንጭ ላይ የተጻፈውን አገናዝቡና ፍረዱ!
Filed in: Amharic