>
5:13 pm - Sunday April 18, 0162

ዕለታዊ የኑሮ ውጣ ውረድና ትምህርት በብርግነትና አካባቢዋ (ጋዜጠኛ ፍስሃ ተገኝ)

ዕለታዊ የኑሮ ውጣ ውረድና ትምህርት በብርግነትና አካባቢዋ

 

ጋዜጠኛ ፍስሃ ተገኝ

 

 

ባለፈው አንድ አመት ከግማሽ ግዜ ውስጥ በግል ህይወቴ የተፈጠረው ክስተት በአመለካከቴ ላይ የፈጠረብኝ ተጽኖ እጅግ በጣም የገዘፈና ተወዳዳሪ የሌለው ነው። በጋዜጠኛነት ሞያ በተሰማራሁበት ወቅት እንደአቅሚቲ ዝናን በማግኘቴ ብዙዎች ስለኔ የማወቅ ፍላጎታቸው በመጨመሩ ምክንያት በተለያዩ አጋጣሚዎች በህትመትም ሆነ ሌሎች የመገናኛ ብዙሃን በኩል ቃለ-መጠይቆች ሲደረጉልኝ ባወራኋቸው መረጃዎች ‘’ፍስሃ ማነው፧’’ የሚለው ጥያቄያቸው ከሞላ ጎደል ስለተመለሰላቸው ሰዎች ስለኔ ያውቃሉ የሚል እምነት አለኝ።

ከ1975-1977 ዓ.ም ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ተከስቶ በነበረው አስከፊ ርሃብና ድርቅ ምክንያት ያንን አስከፊ ግዜ ለማምለጥ ከእናቴ ጋር የትውልድ ቀዬዬን ትቼ ከተሰደድኩ በኋላ እናቴ ሰፈራ ጣቢያ ውስጥ ህይወቷ በማለፉና አባቴም ይሙት ወይም በህይወት ይኑር ባለመታወቁ እንደሞተ ተቆጥሮ ወላጅ አልባ የሆኑኩት ልጅ በሰፈራ ጣቢያው ጥቆማ ወደ ህጻናት ማሳደጊያ ተልኬ የአምስት አመት ህጻን ልጅ ከሚያክለው እድሜዬ ጀምሮ ያደኩት ሐረር በሚገኘው የኤስ. ኦ. ኤስ የህጻናት ማሳደጊያ ውስጥ ነው።

ትምህርቴን ጨርሼ ወደስራው አለም ከተሰማራሁበት ግዜ አንስቶ ቤተሰቤንና የትውልድ ቦታዬን ለመፈለግ አልፎ አልፎ አስብ የነበረ ቢሆንም “የተወለድኩት ላስታ አውራጃ ውስጥ ነው” ከሚለው እውቀቴ በስተቀር “ላስታ የት አካባቢ” የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ ተጨባጭ መረጃ ስላልነበረኝ የፍለጋ ህልሜ ህልም ብቻ ሆኖ ለረጅም ግዜ ቆይቷል።

ምንም እንኳ በአንዳንድ ጥሩ ወዳጆች ርዳታ በህጻንነቴ በትውልድ ቦታዬ አካባቢ የማስታውሳቸው ምልክት የሚሆኑ ነገሮች ካሉ ጠይቀውኝ አዚህ ግባ የሚባል ጠንካራ መረጃ ሳልሰጣቸው ያገኙትን ፍንጭ መነሻ አድርገው የቀድሞው ላስታ አውራጃ ውስጥ ፍለጋቸውን ቢያጠናክሩም የነገርኳቸው ምልክቶችና መረጃ ፍለጋቸውን የትም ሊያደርሰው አልቻለም ነበር። በዚህ መሀል ነበር ካደኩበት የሐረር ኤስ. ኦ. ኤስ የህጻናት መንደር ሰፈራ ጣቢያ በነበርኩበት ወቅት ልክ ወደሰፈራ ጣቢያው እንደሄደው ሰው በሙሉ የተመዘገብኩበት ቅጽ መገኘቱን የሚጠቁም መረጃ ያገኘሁት። ቅጹ ስካን ተደርጎ በኢሜሌ በኩል ተልኮልኝ መልክቱን ከፍቼ የሰፈረው መረጃን ሳይ ማመን ነበር ያቃተኝ። የእናቴና የአባቴ ሙሉ ስም፣ የትውልድ ቦታዬ (ወሎ ክፍለሀገር፣ ላስታ አውራጃ፣ ልዩ ስሙ ሙጃ) ቁልጭ ብሎ ሰፍሮ ያገኘሁት።

ይሄ መረጃ ለኔ ለከርታታው የገነት ቁልፍ ያህል ነበር የሆነልኝ። ይሄን መረጃ ይዤ ከቤተሰቦቼ እንኳን ማንንም በህይወት ባላገኝ የትውልድ ቦታዬንና አካባቢውን አይቼ እመለሳለሁ በሚል ተስፋ ወደ ላልይበላ አቅንቼ ከዛ በኋላ የፍለጋ ዘመቻዬን የተያያዝኩት። ከቤተሰቤ ማንንም አላገኝም የሚል እምነት የነበረኝ ሰው አባቴን፣ የእናቴን ወንድምና እህቶች፣ እንዲሁም ልጆቻቸውንና የልጅ-ልጆቻቸውን ከማግኘቴ በተጨማሪ የተወለድኩት በቀድሞው ላስታ አውራጃ፣ ላስታ ተከፋፍሎ ከተመሰረቱት ወረዳዎች መካከል አንዱ በሆነው ግዳን ወረዳ ውስጥ ብርግነት ተብላ በምትጠራ የገጠር አካባቢ ሰማይ ቀበሌ በምትባለዋ ቦታ መሆኑን አረጋገጥኩ።

ቤተሰቦቼንና የትውልድ ቦታዬን ካወኩ በኋላ ወደ ስፍራው በተደጋጋሚ በመመላለስ በገጠር ከሚኖሩት ቤተሰቦቼ ጋር ለረጅም ግዜያት ተቀምጬ ኑሯቸውን በመኖር ምን አይነት አስቸጋሩኢና ፈታኝ ህይወትን እንደሚኖሩ በአካል ተገኝቼ በተለያዩ መንገዶች ታዝቤያለሁ። ይሄንን የታዘብኩትን የገጠር ህይወት በተለያዩ መንገዶች (በተለይ እኔ አዘውትሬ በምጠቀመው ትዊተር በሚባለው ማህበራዊ ሚዲያ በኩል) ያጋራሁ ሲሆን የተለያዩ ምላሾችን ከተመልካቾችም ሆነ ከተከታዮቼ አግኝቼበታለሁ። የአካባቢውን ሙሉ የኑሮ ፈተና እዚህ ገልጾ መጨረስ እጅግ በጣም ከባድና የልምዣት መጽሃፍን የሚያህ ገጽ እንኳን በቂ ባለመሆኑ የአካባቢው ህጻናትና ታዳጊ ወጣቶች በተለይ በትምህርት በኩል የሚያጋጥማቸውን ፈተና በመጠኑ ልግለጽ።

ግዳን ወረዳ ኢትዮጵያ ውስጥ በድህነታቸው በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት ወረዳዎች መካክል አንዱ ሲሆን በወረዳው ውስጥ ከሚገኙት የገጠር ቀበሌዎች መካከል የእኔ የትውልድ ቦታ ብርግነት የምትገኝበትና በብርግነት አካባቢ ያሉት በርካታ የገጠረ ቀበሌዎች የሚኖሩ ህጻናትና ወጣቶች የትምህርት እድል ካገኙ ትምህርታቸውን የሚከታተሉት በአንጻሩ በአቅራቢያቸው ያሉት ሁለት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ነው። አንደኛው ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ክፍል ትምህርት የሚሰጥበትና በተለምዶ ቡቾ መጫወቻ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ የሚገኘው ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ወንዳች ተብላ በምትጠረዋ አነስተኛ የገጠር ከተማ የሚገኘው ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ትምህርት የሚሰጥበት ነው።

ቡቾ መጫወቻ የሚባለው ቦታ የሚገኘው ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ክፍል ትምህርት የሚሰጥበት ትምህርት ቤት ለአካባቢው ህጻናት በትምህርቱ በኩል የልብ ምት ቢሆንም ትምህርት ቤቱ ያለበት ደረጃ ግን እንኳን እለታዊ የኑሮ ፈተና የሚያታግላቸው ህጻናትና ቤተሰቦቻቸውን ይቅርና ምንም ችግር ሳይኖርበት መማርን ብቻ አላማው ያደረገ ልጅና ቤተሰብ የሚስብና ለትምህርት የሚያነሳሳ አቅም የለውም። ከፍተኛ የሆነ የመቀመጫ ወንበሮች እጥረት በመኖሩ መሬት ላይ ቁጭ ብለው ለመማር ከመገደዳቸው በተጨማሪ መሰረታዊ የሆኑ የመማሪያ ቁሳቁሶች አለመሟላት፣ የመማሪያ ክፍሎቹ ወለሎች ያልተለሰኑ በመሆናቸውና ግርግዳዎቻቸውም በአግባቡ ያልተመረጉ በመሆናቸው ተማሪዎችን ለክፉ የጤና ችግር የሚያጋልጡ መሆናችው፣ እንዲሁም ትምህርት ቤቱ እልም ያለ ገጠር ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ ህጻናቱ ቢያንስ በመጠኑም ቢሆን ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት እንዲማሩ የሚያስችል ብቁ አስተማሪ ከአካባቢው የኑሮ ሁኔታ ጋር የተመጣጠነ ደሞዝ እየከፈሉ ማምጣት የሚያስችል አቅም አለመኖር ትምህርት ቤቱን አደጋ ላይ ጥለውታል። ይሄ አንጻራዊ ቅርበት ያለው ትምህርት ቤት በአካባቢው መኖሩ ትምህርትን ከመስጠት በተጨማሪ ሌላኛውና ከአካባቢው አኗኗር ዘይቤ አንጻር ያለው በምንም ነገር የማይለካ ግዙፍ ጥቅም ልጆች ጠዋት የሚማሩ ከሆነ ከሰአት ላይ ወደቤታቸው ተመልሰው ቤተሰባቸውን በእረኝነቱ፣ ዉሃ በመቅዳቱና በአጨዳው እንዲሁም በተለያዩ የቤት ውስጥ ስራዎች እንዲያግዙ የሚያስችል ግዜ እንዲኖራቸው ማድረጉ ነው።

ሌላኛው ወንዳች ተብላ በምትጠራው አነስተኛ የገጠር ከተማ የሚገኘው ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል የትምህርት አገልግሎት የሚሰጥበት ትምህርት ቤት ሲሆን ይህ ትምህርት ቤት በአካባቢው ላሉ በርካታ የገጠር ቀበሌዎች የትምህርት እስትንፋስ ነው። በእኔ የትውልድ ቦታ ብርግነት የሚኖሩ ልጆች በተለይ ወንዳች ድረስ ሄደው ትምህርታቸውን ለመማር ቢያንስ የአንድ ሰአት ተኩል ያህል የእግር ጉዞ የሚያደርጉ ሲሆን ከብርግነት ራቅ ያሉ የገጠር ቀበሌዎችም ከሁለት ሰአት በላይ የሆነ የእግር ጉዞ እያደረጉ የሚማሩበት ለአካባቢው በቅርበት ያለ ትምህርት ቤት ነው። የዚህን ትምህርት ቤት ጥቅም በቅርበት በአጎቴ ልጅ በኩል በጥሞና የተከታተልኩት ሲሆን እኔ ቤተሰቤንና የትውልድ ቦታዬን ሳውቅ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ የነበረችው የአጎቴ ልጅ ምንም እንኳን ከአንድ ሰአት በላይ (ደርሶ መልስ ከሁለት ሰአት ተኩል በላይ) ለሆነ ግዜ በእግሯ በየቀኑ እየተጓዘች የምትማር ብትሆንም የጠዋት ፈረቃ ስትሆን ጠዋቱን ተምራ ከሰአቱን በቶሎ ወደቤት በመመለስ በእረኛነት እናትና አባቷን ታግዝ ነበር። እረኛነት በተለይ በደጋው አካባቢ ለሚኖሩ እናትና አባት እጅግ በጣም ከባድ የሆነ የጉልበት ፈተና በመሆኑ ከዚህ ፈተና የሚታደጓቸው እንደ አጎቴ ልጅ ያሉ ልጆች በልጅነት ጉልበታቸው እየረዷቸው ነው። የአጎቴን ልጅ በምሳሌነት አነሳሁ እንጂ በርካታ የአካባቢው ልጆች ቤተሰቦቻቸውን የሚያግዙት በእንዲህ አይነት ሁኔታ ነው።

ይህ ወንዳች ውስጥ የሚገኘው ትምህርት ቤት የመቀመጫ ወንበሮችን ጨምሮ መሰረታዊ የመማሪያ ቁሳቁሶች እጥረት ያለበት ሲሆን ሌላው በጣም አሳሳቢው ነገር ተማሪዎች የመጠጥ ውሃ የሚያገኙበት እድል አለመኖሩ ነው። ተማሪዎች የመጠጥም ሆነ እጆቻቸውንና ፊታቸውን እንዲታጠቡ የሚያስችል የውሃ አገልግሎት የሌለው ትምህርት ቤት ነው።

ምንም እንኳን በአካባቢው በርካታ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው አንገብጋቢ ጉዳዮች ቢኖሩም የገንዘብ ማሰባሰብ ዘመቻዬን ከአንገብጋቢ ጉዳዮች መካከል አንዱ ከሆነውና ለልጆች እውቀት መቅሰሚያ ከሆነው ትምህርት ቤትና የትምህርት አገልግሎት ለመጀመር የመረጥኩት ከላይ በጠቀስኳቸው ምክንያቶች ነው። እድሚያቸው ሰባት፣ ስምንት፣ አስርና ከዛም በላይ ሆኖ ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ብዙ ልጆችን አይቻለሁ፤ አግንቻለሁም። ላለመማር ፈልገው፣ ወይም ቤተሰቦቻቸው ልጆቻቸውን እንዳይማሩ ከልክለው ሳይሆን እለታዊ የሆነው የኑሮ ውጣ ውረድና ብቁ የሆነ የትምህርት አገልግሎት መስጫ አለመኖራቸው ተደማምረው ነው።

እነዚህን ሁለት ትምህርት ቤቶች ለመደገፍ የጀመርኩት የ GoFundMe ዘመቻ ግቡን እንዲመታ እንተባበር። የትምህርት አገልግሎትን በብቃት ላለመስጠት የገንዘብ እጥረትን እንደምክንያት የሚጠቀሙ ባለስልጣናትና ወኪሎች ምክንያት እንዳይኖራቸው ቢያንስ ገንዘቡን በማቅረብ አስፈላጊው ነገር እንዲሟላ ለማድረግ እንንቀሳቀስ ብዬ ይሄንን ዘመቻ ጀምሬያለሁ። ይሄንን ማስፈንጠሪያ ይንኩና በድጋፍዎ ይተባበሩ https://www.gofundme.com/f/maintenance-of-two-schools-in-gidan-wereda?utm_medium=email&utm_source=product&utm_campaign=p_email%2B4803-donation-alert-v5

Filed in: Amharic