>
5:13 pm - Sunday April 20, 3423

ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማ/ወርቅ የጠየቀው ይግባኝ በፍርድ ቤቱ ውድቅ ተደረገ!!!

ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማ/ወርቅ የጠየቀው ይግባኝ በፍርድ ቤቱ ውድቅ ተደረገ!!!

የግዮን መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማ/ወርቅ፤ ዛሬ ታህሳስ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ልደታ ከፍተኛ ፍ/ቤት 8ኛ ወንጀል ችሎት ቀርቦ ያቀረበው ይግባኝ ውድቅ ተደረገ፡፡ ህወሓት መራሹ መንግሥት በ2006 ዓ.ም በዕንቁ መጽሔት በከፈተው የክስ መዝገብ ከሁለት ወራት በፊት የ7 ዓመት እስርና የ15 ሺህ ብር ቅጣት እንደተላለፈበት የሚታወሰው የአሁኗ የግዮን መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ፍቃዱ ማኅተመወርቅ፣ ክሱ ፖለቲካዊ በመሆኑ እንዲቋረጥለት ከመጋት 2010 ዓ.ም ጀምሮ ሲጠይቅ ቢቆይም ሰሚ አጥቶ ቆይቷል፡፡
በዚህም ምክንያት በውርስ ክስ የተላለፈበትን የእስር ውሳኔ አስመልክቶ ከሀያ ቀን በፊት ለልደታው ከፍተኛው ፍ/ቤት ይግባኝ ቢጠይቅም “በውስጥ አሠራር ችግር” ተብሎ በተጠቀሰ ምክንያት በሰዓቱ በችሎት ሳይገኝ ቀርቷል፡፡
ይሁን እንጂ ባሳለፍነው ሳምንት ማክሰኞ ታህሳስ 14 ቀን 2012 ዓ.ም በልደታ ከፍተኛ ፍ/ቤት 8ኛ ወንጀል ችሎት ቀርቦ ለከፍተኛው ፍ/ቤት አላግባብ የተከሰሰበትንም ሆነ የተወሰነበትን ፍርድ በይግባኝ እንዲታይለት ያቀረበ ሲሆን ፍ/ቤቱ የቀረበውን የይግባኝ ዝርዝር አጢኖ “ተብራርቶ ሊቀርብልኝ ይገባል” በማለት ለዛሬ ታህሳስ 23/2012 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በዛሬው ችሎትም ጋዜጠኛው ያቀረበውን ይግባኝ ፍ/ቤቱ “ከዓመት በፊት በተሰጡ የተለያዩ የጊዜ ቀነ ቀጠሮዎች ሊቀርብ ይገባ ነበር” በማለት ውድቅ አድርጎ ውሳኔውን አጽንቶበታል፡፡
Filed in: Amharic