>

መገፋት መልካም ነዉ !!! (ዳንኤል ክብረት)

መገፋት መልካም ነዉ !!!

 

ዳንኤል ክብረት

• ዮሴፍ ባይገፋ ኖሮ ጎበዝ እረኛ ሆኖ ይቀር ነበር። በመገፋቱ የግብፅ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነ!!!

ቅቤና ማር ተከራከሩ ይባላል። 
ማርም ተናገረች፡- “የምጣፍጠው እኔ አናት ላይ የምትወጪው ግን አንቺ ነሽ ለምንድነው?” አለቻት። ቅቤም፡- “እኔም ወድጄ አይደለም ገፍተው፣ ገፍተው ነው አናት ላይ ያወጡኝ” አለች ይባላል። ቅቤ፣ ቅቤ የሚኮነው ተንጦ፣ ተንጦ ነው።
 እግዚአብሔር ሁሉም ሎሌው ነው። በክፉዎች ሳይቀር ይሠራል። ወዳሰበልን የሚያደርሰን እየገፋን ነው። ካልተገፋን ያለንበትን ትንሽ ቦታ ተላምደን እንኖራለን። እርሱ በደጎች አይገፋንም፣ ደጎች መግፋት ባሕርያቸው አይደለምና። ክፉዎች ግን ቅድስናም ይሉኝታም የላቸውምና በእነርሱ ይገፋናል። እነርሱ የሚያውቁት ወደ ገደል እንደሚገፉን ነው፣ ሳያውቁት ግን ወደ ተራራ ይገፉናል።
ጠላቶች የነጻ ሠረገላ ናቸው። ለኛ ከ ማይገባን ቦታ እየገፉን ወደ ሚገባን ቦታ … ከ ዝቅታ ወደ ከፍታ ቦታ ያደርሱናል። በእውነት ጌታ ሆይ ጠላቶቻችንን ባርክልን። እነርሱ ባይኖሩ ሥራው አይበዛልንም ነበር። ይህን ጥንቁቅ ሕይወት፣ ይህን ዝግጅት፣ ይህን ቶሎ ቶሎ መሥራት ያገኘነው ከጠላቶቻችን ነው። እያንዳንዱን ቀን በትክክል እንድንኖር ያተጉንን ጠላቶች እባክህ ባርክልን።
 የሰዓት ደወል ብንሞላ ጠዋት 12 ሰዓት ሞልተነው፣ ማታ 12 ሰዓት ሊጮህ ይችላል። ቀስቅሱን ብንላቸው ወዳጆቻችን ከሥራችን ለእንቅልፋችን አዝነው ይተውናል። ክፉዎች ግን በሰዓቱ ያነቁናል። እንደዚህ ያሉ ነጻ ደወሎችን ያስቀመጠልን አምላክ ስሙ ይባረክ። እነርሱ እንዳይነቅፉን ስንጠነቀቅ የቅድስናን ሕይወት ያለማምዱናልና እነዚህ ጠባቂዎቻችን ናቸው።
 የተገፉ ሁሉ ከፍ እንጂ ዝቅ ሲሉ አይተን አናውቅም። ገፊዎች ሲገፉን ከእኛ የክፋት ሰፈር ምን ትሠራላችሁ? እልፍ በሉ እያሉን ነው። ጠላቶች ሐሰተኛ ወዳጆችን ወስደው እውነተኛ ወዳጆችን ያስቀሩልናል። ክፉዎች ጥሩ ማጣሪያ ናቸው። ተረስተን የምንኖረውን እነርሱ ያሳውቁናል። በነጻ ማስታወቂያ ይሠሩልናል። ሰዎች ስማችንን የሚያነሡት በሁለት ነገር ነው። ስለሚወዱንና ስላስደሰትናቸው ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ ስለሚጠሉንና ስላስጨነቅናቸው ነው። እንዲሁ ርእስ መሆን አይገኝም። የአትርሱኝ ሳንከፍል ላስታወሱን በረከት ይሁን።
 ዮሴፍ ባይገፋ ኖሮ ጎበዝ እረኛ ሆኖ ይቀር ነበር። በመገፋቱ የግብፅ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነ። ጠላት ያውቃል እንላለን፣ እንደ ጠላት ግን አላዋቂ የለም። ኢየሱስን ከኢየሩሳሌም ሊያጠፋ ገደለው፣ በሞቱ ግን በዓለም ሁሉ አበራ። ጠላት ሰፈር እየቀማ ዓለም ያወርሳል። ሰው ማፍረስ ይችል ይሆናል፣ እግዚአብሔር ደግሞ ማስነሣት ይችላል /ዮሐ. 2፡19/። “መገፋት ጥሩ ነው እጅግም ሳይወድቁ፣ የተገፉት ቆመው የገፉት ወደቁ።
Filed in: Amharic