>
5:13 pm - Tuesday April 18, 3786

ምኒልክና ጫማ!!! (ተስፋዬ ሀይለማርያም)

ምኒልክና ጫማ!!!

 

ተስፋዬ ሀይለማርያም

 

እንግዲህ ዛሬ የምኒልክን ስም የሚያጠፋው ሁሉ ጎንበስ ብሎ እግሩን ማየት የማይችል መደዴ ትውልድ ነው!!!
 
 ስለምኒልክ ሺህ ጊዜ ቢወራ አይሰለችም። ምኒልክ ህዝባቸው ጫማ ማድረግ እንዲለምድ አዋጅ እስከማውጣት የደረሱ ታላቅ ሰው ናቸው።
እንዲያው እምዬ ምኒልክን የሚተካ መሪ ድጋሚ እናገኝ ይሆን? ምኒልክ ከሚስታቸው እቴጌ ጣይቱ ጋር ሆነው ለህዝባቸው ከመጨነቃቸው የተነሳ፣ ህዝቡ የሚበላውና የሚለብሰው ሁሉ የሚያሳስባቸው የሚሊኒየሙ ምርጥ መሪ ነበሩ።
እቴጌ ጣይቱ መሃን በመሆናቸው ልጅ አልወለዱም። አንድ ቀን ምኒልክ የልጅ ነገር አንስተው ከጣይቱ ጋር ሲጫወቱ “እግዚአብሔር ለምን ልጅ አልሰጠንም ጣይቱ?” ብለው ቢሏቸው ጣይቱ ሲመልሱ “ለምን በዚህ ያዝናሉ? ሁልጊዜ የምንሳሳላቸው 14 ሚሊዮን ልጆች አሉን አይደለምን?” አሏቸው። በዚያን ጊዜ የኢትዮጵያ ህዝብ 14 ሚሊዮን ነበረ።
በምኒልክ ዘመን ሽፍን ጫማ ማድረግ ህዝቡ አይወድም ነበር።ህዝቡ ነጠላ ጫማ  ያደርግ ነበር ። የምኒልክ ዘመን ፎቶዎችን ስመለከት ታላላቅ ሰዎች ሁሉ ከላይ ሽክ ብለው ለብሰው ከታች ግን ባዶ እግራቸውን ናቸው።
እምዬ ምኒልክ የሽፍን ጫማን ጠቃሚነት ከፈረንጆች ከተረዱ በኋላ ሽፍን ጫማ ማድረግ ጀመሩ። መኳንንቱ ሁሉ ሽፍን ጫማ እንዲያደርግ ቢመክሩም ሰሚ አጡ። ሽፍን ጫማ የሚያደርግ እንደ ቆማጣ ተቆጠረ።
ምኒልክም ቆማጣ አለመሆናቸውን በአደባባይ ባዶ እግራቸውን እያሳዩ ሽፍን ጫማ ቢያደርጉም ተከታይ ጠፋ። ምኒልክ በውዴታ እንጂ በግዴታ የማያምኑ ስለነበሩ፣ የልጅ ልጃቸን ኢያሱን እንኳን ሽፍን ጫማ ማስደረግ አቃታቸው።
ምኒልክ ከአማካሪዎቻቸው ፈረንጆች ጋር ከተማከሩ በኋላ ፣ ከፊት ጣትን ከኋላ ደግሞ ተረከዝን የሚሸፍን ግማሽ ሽፍን ጫማ አሰርተው “ቆማጣ ላለመሆንህ ግማሽ እግርህ ይታያልና እኔን የወደድህ እኔን ምሰል። ሽፍን ጫማ ከእሾህ፣ ከብርድና ከእንቅፋት ይከላከልልሀል ብዬ ነውና ለጤናህ ስትል ሽፍን ጫማ አድርግ” ብለው ችሎት ላይ ከተናገሩ በኋላ ጥቂቱ ሠራዊት እየቀፈፈው ያን ጫማ ማድረግ ጀመረ።
እንግዲህ ዛሬ የምኒልክን ስም የሚያጠፋው ሁሉ ጎንበስ ብሎ እግሩን ማየት የማይችል መደዴ ትውልድ ነው። እምዬ ምኒልክ! እኔ ደግሞ ለእርስዎ ክብር እነሆ ጫማዬን አወልቃለሁ።
Filed in: Amharic