>

መድደመርና መደምመር (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም)

መድደመርና መደምመር

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም

“መደመር” ማለት፡

የመደመር ዋነኛ ዓላማ ሀገራችን ባለፉት ዓመታት ያስመዘገበቻቸውን የፖሊቲካና የኢኮኖሚ ድሎች ጠብቆ ማስፋት፣ የተሠሩ ስሕተቶችን ማረም እንዲሁም የመጻኢውን ትውልድ ጥቅምና ፍላጎት ማሳካት ነው፡፡ በመሆኑም መደመር ከችግር ትንተና አንጻር ሀገር በቀል ነው፡፡ ከመፍትሔ ፍለጋ አንጻር ደግሞ ከሀገር ውስጥም ከውጭም ትምህርት በመውሰድ የተቀመረ ነው፡፡›› (ዓቢይ አህመድ 36)

የበጎ ለውጥ ሁሉ ዋና ዓላማ ማናቸውንም ዓይነት ጉድለት በመሙላት ጉድለቱን ማስወገድ ነው፤ ከአለመኖር ወደመኖር፣ ከአለመሆን ወደመሆን ለመሸጋገር መጣር ነው፤ በዚህ ጥረት ውስጥ መደመርና መደመር ዋናዎቹ ግብዓቶች ናቸው፤ መደመር ራስን ለድምር አቅርቦ መሳካት ነው፤ መደመር የራስ የሆነውን ሁሉ ለድምር አቅርቦ ማሳካት ነው፤ በግልም ይሁን በቡድን ከድምር ውጭ የሆነ ጎደሎ ሆኖ ይቀራል፤ ያልተደመረ ብቻውን ይቀራል፤ ለብቻም ሆነ በቡድን ብቻ መቅረት አለ፤ ብቻውን የቀረ ጎደሎ ነው፤ ጎደሎነቱን ካወቀ፣ ወይም ጎደሎነቱን ያወቀለት ካገኘ ወደድምር ያመራል፣ አለዚያ ቆሞ ይቀራል! ግንጥል ሆኖ ይኖራል፣ ኑሮ ከተባለ፡፡
መርዘምም ይሁን መወፈር፣ ማወቅም ይሁን መሠልጠን፣ መሥራትም ይሁን መበልጸግ፣ ማግባትም ይሁን መውለድ የመደመር ውጤቶች ናቸው፤ ደሀነት ከድምር ውጭ ያለ ብቸኛነት ነው፤
ማናቸውም እድገት የሚገኘው ከድምር ነው፤ ማባዛትና ማካፈል ከድምር በኋላ የሚመጡ ናቸው፤ ያልተደመረውን ማባዛትም ሆነ ማካፈል አይቻልም! የሚሰነጠቅ እስኪጠፋ ይሰነጠቃል! እድገት የበጎ ነገሮች ድምር ከሆነ ኑሮ የስኬት ጎዳና ይሆናል፤ ሙሉ ሰላም፣ ሙሉ ጤንነት፣ ሙሉ እውቀት፣ ሙሉ ኃይል፣ ሙሉ ስምምነት፣ ሙሉ ደስታ፣– በማያቋርጥ ምቹ ጉዞ ሕዋውን እየሰነጠቁ መክነፍ! መሬትን እየቦረቦሩ መግለጥ! ውቅያኖስን እየጋለቡ ማቆራረጥ ነው፤ በየትኛውም በኩል የማያቋርጥ ጉዞ፡፡

ለማንም ሰው መደመር ከአለበት ሁኔታ የሚያወጣ አንድ ወሳኝ እርምጃ መራመድ የሚያስችል ቆራጥነትና መንፈሳዊ ወኔን ይጠይቃል፤ ያ የመጀመሪያ ወሳኝ እርምጃ የማይቆምና የማይታገድ ነው፤ በመንገዱ ላይ ያገኘውን ሁሉ እያቀፈና እየደመረ ያድጋል፤ ጉልበት ይጨምራል፡፡

የተደመረና የተደመረ ተገናኝተው ሲፋጠጡ ምን ይሆናል? አይጋጩም! ለመደማመር ይተሻሻሉ! አንዱ በአንዱ ውስጥ ይገባና አንድ ይሆናሉ፡፡ ድንቅ ሀሳብና ድንቅ አስተሳሰብ ነው፤ እዚህ ላይ ቢያልቅ ጥሩ ነበር! ተከለሰና ተበላሸ! ከዚህ በኋላ ያለው እኔን ድንግርግርግር አድርጎኛል፤

የብልሽቱ ዋና ምክንያት ‹‹ሊቃውንት›› እየተባለ የሚተረከው ነው፤ ‹‹ብሔር በማኅበራ ሂደት የሚገነባ ነገር እንደሆነ (በርካታ ሊቃውንት) ይስማማሉ፤
የሚከተሉት ጥቅሶች የዚሁ ዓይነት ናቸውና የቅሬታዬን መሠረት ይገልጻሉ፡—-
የኢንዱሰትሪ መስፋፋትና የዘመናዊ ሀገረ የዘመናዊ ሀገረ መንግሥት መመሥረት ለብሔሮች መፈጠር መክንያት ሆኗል፤(112)
ሀገረ ብሔር የብሔርና የዘመናዊ ሀገረ መንግሥት ጋብቻ ውጤት ነው፤ ስለዚህም ብሔርተኝነት የሀገረ መንግሥታት መፈጠርን ተከትሎ የመጣ … ነው፤››(112)
የሀገረ መንግሥቱ ምሥረታ የምስለት ፖሊሲን ያስከተለ ሂደት መሆኑን ውጤቱ ግን አንድ ሀገረ ብሔር ከመፍጠር ይልቅ ተገንጥሎ የቀረ ወይም በከፊል የተገነባ ሀገረ ብሔር መሆኑ … (115)
ፌዴራላዊ ሥርዓታችን የሀገራችንን ብሔረሰቦች መሠረታዊ የሆነውን የራስን ቋንቋና ባህል መጠቀምና የማሳደግ ብሎም ራስን በራስ የማስተዳደር መብታቸውን ለማስከበር ችሏል፤(116)
ከገጽ 110 ግድም በኋላ ያለውን ለማንበብ አማርኛና ግእዝ ረስቶ እንግሊዝኛ ደኅና አድርጎ ማወቅ ያስፈልጋል፤ ይዘቱም አጻጻፉም በጣም ግራ የሚያጋባ ነው በያለበት የተንፈራጠጠ አስተሳሰብ ነው፡፡

Filed in: Amharic