>
5:14 pm - Monday April 20, 5953

የቴዲ አፍሮ 40 እውነታዎች!!! (ግሩም ሰይፉ)

የቴዲ አፍሮ 40 እውነታዎች!!!

ግሩም ሰይፉ 
1.  40ኛ ዓመቱን ደፍኗል!
2. የተወለደው ሐምሌ 7 ቀን በአዲስ አበባ ፤ኳስ ሜዳ በተባለው ሰፈር ነው፡፡
3. ወላጆቹ ለኪነጥበብ ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች ናቸው፡፡ አባቱ አቶ ካሳሁን ገርማሞ ፤ እናቱ ደግሞ ወይዘሮ ጥላዬ አራጌ ይባላሉ፡፡
4. አቶ ካሳሁን ገርማሞ ታዋቂ ጋዜጠኛ ፤ የዘፈን ግጥም ደራሲ እና የመድረክ መሪ የነበሩ ናቸው፡፡ ሙዚቃ ህይወቴ የተሰኘው ዘፈኑን መታሰቢያ አድርጎ ሰርቶላቸዋል፡፡
5. እናቱ ወይዘሮ ጥላዬ ደግሞ ፕሮፌሽናል ዳንሰኛ ናቸው፡፡
6. በሙሉ ስሙ ቴዎድሮስ ካሳሁን ገርማሞ ተብሎ ቢጠራም የሚታወቀው ቴዲ አፍሮ በተሰኘው የመድረክ ስሙ ነው፡፡ ይህን ስያሜ ከአፍሮ ሳውንድ የሙዚቃ ባንድ ጋር በነበረው ተመክሮ አግኝቶታል፡፡
7. በሙዚቃ ሙያው ከ15 ዓመታት በላይ ልምድ አለው፡፡
8. ከድምፃዊነቱ በተጨማሪ የዘፈን ግጥምና የዜማ ደራሲ ፣ ገጣሚ፣ ታሪክ አዋቂ፤ በጎ አድራጊና የሰብዓዊ ተሟጋችም ነው፡፡
9. ወደ ሙዚቃው የገባው የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ሲሆን በልጅነቱ የህክምና ዶክተር የመሆን ፍላጎት ነበረው፡፡
10. ከሙዚቃ መሳርያዎች ኪቦርድን ከመጫወቱም በላይ የተለያዩ አኩስቲክ የሙዚቃ መሳርያዎችን በመጫወት በመድረክ ላይ ባንዶቹን አጅቦ የመስራት ልዩ ተሰጥኦ አለው፡፡
11. በአልበሞቹ ከፍተኛ ሽያጭ በማስመዝገብ ፤ በመላው ዓለም በርካታ ኮንሰርቶች በመስራት፤ በአገር ውስጥ በሚሰራቸው ኮንሰርቶች ከፍተኛ ታዳሚ በማግኘት እንዲሁም በሙዚቃ ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ተከፋይ በመሆን ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው፡፡
12. ትልልቅ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የአፍሪካ ሬጌ ሙዚቃ ንጉስ እያሉ ያሞካሹታል፡፡ በእንግሊዙ ቢቢሲ ፤ በቻይናው ሲሲቲቪ፤ በአሜሪካው ዋሽንግተን ፖስት በሙዚቃ ስኬቱ ላይ ሰፋ ያሉ ዘገባዎች ተሰርተውለታል፡፡ በአፍሪካ በተለይ በምስራቅ አፍሪካ ተፅእኖ ፈጣሪነቱና በሬጌ ሙዚቃ ስልት ምርጥ ስራዎች ካሏቸው ሙዚቀኞች ተርታ ይሰለፋል፡፡
13. ከፊልም ባለሙያ ፤ ፀሃፊና ተዋናይት አምለሰት ሙጬ ጋር ትዳር ከመሰረተ 6 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ከዚህ ትዳራቸውም ሁለት ልጆች አፍርተዋል፡፡
14. ከትዳር አጋሩ አምለሰት ሙጬ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቁት የሜክአፕ አርቲስቱ ሆና በሰራችበት አጋጣሚ ሲሆን ከጋብቻቸው በፊት ያሰረላት የቃልኪዳን ቀለበት 750ሺ ብር እንደሚያወጣ ተወስቷል፡፡
15. አምለሰት በወይዘሪት ኢትዮጵያ የቁንጅና ውድድር አሸናፊ የነበረች ሲሆን በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ የኮሌጅ ወጎችን በመፃፍም ታውቃለች፡፡ “ይፈለጋል” እና በሌሎች የአማርኛ ፊልሞች ላይ በመተወን ልምድ ያላትም ስትሆን “ስለ ፍቅር” የተባለ አስቂኝ የፍቅር ፊልም በመድረስ እና ፕሮዲውስ ያደረገችም ናት፡፡ በኒውዮርክ የፊልም አካዳሚ የተማረችው አምለሰት በአካባቢ ጥበቃ ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ፊልም የሰራች ሲሆን በቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ህይወት ላይ ያጠነጠነ ዶክመንተሪ ፊልም እየሰራች መሆኑም በአንድ ወቅት ሲገለፅ ነበር፡፡
16. በሙዚቃ ስራዎቹ በተለይ በሰብዓዊነት ፤ በአንድነት እና በፍቅር ዙርያ አተኩሮ በመስራትም ልዩ ከበሬታ ያተረፈ ሲሆን፤ ለሚሰራቸው ዘፈኖች በሚፅፋቸው ድርሰቶች ከፍተኛ ምርምርና ጥናት እንደሚያደርግ ተወስቶለታል፡፡ በእያንዳንዱ የሙዚቃ አልበሙ ታሪክ ቀመስና ለታላላቅ ሰዎች መታሰቢያ በሆኑ የሙዚቃ ስራዎችም የሰራ ነው፡፡ ለአፄ ኃይለስላሴ፤ ለጃማይካዊው ሬጌ ኮከብ ቦብ ማርሌይ ፤ ለታዋቂዎቹ አትሌቶች ኃይሌ ገብረ ሥላሴና ቀነኒሳ በቀለ ለአፄ ምኒልክ ይጠቀሳሉ፡፡
17. ‹‹ፍቅር ያሸንፋል›› በሚለው መርሁ ይታወቃል፡፡
18. ከሙዚቃው ባሻገር የግጥም መፅሃፍ ለህትመት ማብቃትም ችሏል፡፡ የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህንን የልብ አድናቂ ሲሆን፤ የስነ ጽሁፍ ችሎታውን አስተሳሰቤን የቀየሩ ናቸው በማለት በአንድ ወቅት ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ ‹‹ጥቁር ሰው›› በሚለው አልበሙ ይህን አድናቆቱን በሚያረጋግጥ መንገድ በባለቅኔው የግጥም ንባብ በመታጀብ ምርጥ ሙዚቃም እንደሰራ ይታወቃል፡፡
19. በአጠቃላይ 7 አልበሞችን በካሴት፤ በሲዲ፤ በዲቪዲና በቪሲዲ በመስራት ለገበያ አቅርቧል፡፡
20. በአልበሞቹ አሳታሚነት አብረውት ከሰሩ አሳታሚዎች ናሆም ሪከርድስ ዋናው ተጠቃሽ ቢሆንም፤ ከኢቫንጋዲ ፕሮዳክሽን እና ከአዲካ ሪከርድስ ጋርም ያሳተማቸው አልበሞችም አሉት፡፡
21. የመጀመርያ አልበሙ ‹‹አቦጊዳ›› በሚል ርእስ በ1993 ዓ. ም በናሆም ሪከርድስ የታተመው ነበር ፡፡
22. ሁለተኛ የአልበም ስራው ደግሞ በ1996 ዓ. ም ላይ በኢቫንጋዲ ፕሮዳክሽን ለገበያ የበቃው ‹‹ታሪክ ተሰራ›› ነው፡፡ ‹‹ታሪክ ተሰራ›› በኢትዮጵያ የ10ሺ ሜትር አትሌቶች የቡድን ስራ በመማረክ በአንድ ሌሊት ተሰርቶ በማግስቱ በኤፍኤም ሬድዮ በመለቀቅ ከፍተኛ አድናቆት ያተረፈ ነጠላ ዜማ መሆኑ ይታወቃል፡፡
23. በ1997 ዓም ላይ 3ኛው አልበም ‹‹ያስተሰርያል›› በሚል ርዕስ በናሆም ሬከርድስ ለመታተም በቅቷል፡፡ ይህ አልበም በጥቂት ወራት ሁለቴ ለመታተም የበቃ ሲሆን፤ ከሚሊዮን ቅጂዎች በላይ ተሰራጭቶ ክብረወሰን እንዳስመዘገበም ይገለፃል፡፡
24. በ1998 ዓም ‹‹ቤስት ኮሌክሽን ናሆም ቮሊውም 14›› ተብሎ በናሆም ሪከርድስ አሳታሚነት በተለያዩ ጊዜያት የሰራቸው ነጠላ ዜማዎች ተሰባስበውበት 4ኛው አልበም ለገበያ ቀርቧል፡፡
25. ‹‹ጥቁር ሰው›› በሚል በአዲካ ሬከርድስ አሳታሚነት ለገበያ የቀረበው የመጨረሻ አልበሙ ነው፡፡
26. ጥቁር ሰው የሚለው አልበሙን ለአሳታሚው አዲካ ሪከርድስ በ4.6 ሚሊዮን ብር መሸጡ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ሪከርድ ሲሆን ይህ አልበም በመጀመርያው እትም በቴፕ ካሴት 300ሺ እንዲሁም በሲዲ 500000 ቅጂዎች መሸጡና ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማስገኘቱ በሙዚቃኢንዱስትሪው ክብረወሰኖች ሆነው የሚመዘገቡ ናቸው፡፡
27. ጥቁር ሰው ለተባለው ዘፈኑ የሙዚቃ ቪድዮው ከ500ሺ በላይ ወጭ በማድረግ ባለ ሪከርድ ነው፡፡
28. ጥቁር ሰው ያለውን የመጨረሻ አልበም ካወጣ አራት አመት ሲሆነው ይህን አልበም ለማስመረቅ በጊዮን ሆቴል ቀርቦ የነበረው ኮንሰርት በቅርቡ በአምባሳል አሳታሚነት ለገበያ እንደቀረበ ይታወቃል፡፡
29. አዲስ ሙሉ አልበሙንም እየሰራ ነው፡፡ ይህ አልበሙ በኒውዮርክ ከተማ በሚገኝ ታዋቂ ስቱዲዮ መዘጋጀቱ ልዩ ያደርገዋል፡፡ ከቦብ ማርሌ ልጅ ዳይመን ማርሊ ጋር በጋራ የሚጫወቱት የሬጌ ስራ እንዳለውም ለማወቅ ተችሏል። በዚህ አልበም ውስጥ ከሚገኙ አዳዲስ ስራዎች አምስት ዘፈኖቹን የሚያቀናብርለት ታዋቂውና የሶስት ግራሚ ተሸላሚ የሆነው ዝነኛው አሜሪካዊ አቀናባሪ ጎርደን ዊሊያምስ ነው፡፡ ጎርደን፤ ለአሊሺያ ኪስ፣ ሎሬን ሂል፣ ካርሎስ ሳንታና፣ ኤሚ ዋይን ሀውስ እና ለፊፍቲ ሴንት የሰራና ሶስት የግራሚ ሽልማቶችን ያገኘ ትልቅ የሙዚቃ ባለሙያ ነው፡፡
30. በተለያዩ ጊዜያት በሚወጡ ነጠላ ዜማዎች ስኬቱም ይታወቃል፡፡ ነጠላ ዜማ ሲያወጣ አገር ይንቀጠቀጣል አገር ይቅበጠበጣል አቧራ ይነሳል፡፡ ይህ ደግሞ በኢንዱስትሪው ምርጥ ብቃት እንዳለው የሚያረጋግጥ ነው፡፡ እንደማስረጃ በተለያዩ ጊዜያት የተለቀቁ ነጠላ ዜማዎችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡ አቦጊዳ ከሚለው አልበም አቦጊዳ፣ ልጅነት አላት፣ ለማን ልማሽ እና ሞናሊዛ ፤ ያስተሰርያል ከሚባለው አልበም ያስተሰርያል፣ በል ስጠኝ፣ ላምባዲና አላምን የሚታወሱ ናቸው፡፡ መንታ ወድጄ፣ያረጋል፣ ላሜ ቦራ እና ስደት የተባሉት ሌሎች አራት ነጠላ ዜማዎችም ከፍተኛ ተደማጭነት በማግኘት የተሳካላቸው ሲሆኑ፤ የመጨረሻው አልበሙ ጥቁር ሰው ከመውጣቱ በፊት ደግሞ ሰላም ፣ ፊዮሪና ፣ ልረሳሽ አልቻልኩም ፣አባይ፤ ውዴ፤ አይደነግጥም ልቤ እና ትዝታ ይጠቀሳሉ፡፡ ከ5 በላይ ነጠላ ዜማዎች በአንድ ዘፋኝ እንዲህ በዝተው በአንድ ሰሞን ሲሰራጩ የተለመደ ስላልነበር እነዚህ ነጠላ ዜማዎች ለመጀመርያ ጊዜ በተሰሙበት ወቅት በከፍተኛ ደረጃ ያነጋገሩ ነበሩ፡፡ ሰባ ደረጃ እና ኮርኩማ አፍሪካ ደግሞ እጅግ በጣም የተሳካላቸው ነጠላ ዜማዎቹ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡
31. በመኪና ሰው ገጭቶ በመግደል ክስ ፍርድ ቤት ቀርቦ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የ6 ዓመት እስራት እና የ18ሺ ብር ቅጣት ተላልፎበት ነበር፡፡ ይግባኝ ተጠይቆ እስሩ ወደ ሁለት ዓመት ወርዶለታል፡፡ በወንጀሉ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ከዋለበት ጊዜ አንስቶ በፍርድ ውሳኔ እስር ቤት እስገባበት ድረስ 482 ቀናትን ካሳለፈ በኋላ በአመክሮ ሊፈታ ችሏል፡፡
32. በማህበራዊ ሚዲያዎች ከኢትዮጵያ ዝነኛ ሙዚቀኞች የሚስተካከለው የለም፡፡ በፌስቡክ ከ1 ሚሊዮን በላይ ወዳጆች አሉት፡፡ በትዊተር ገፁ ከ3ሺ በላይ ተከታታዮችን አፍርቷል፡፡ በዩቲውብ የተጫኑ ከ145ሺ በላይ የሙዚቃ ቪድዮች እና ተያያዥ መረጃዎች አሉት፡፡ አንዳንድ የዩቲውብ ቪዲዮቹ ከሚሊዮን በላይ ተመልካች ያገኙ ሲሆኑ ብዙዎቹን የሙዚቃ ቪድዮች፤ የኮንሰርት ትእይንቶች ፤ቃለምልልሶች እና ሌሎች ጉዳዮች በዩ ቲውብ በአማካይ ከ10 እስከ 100ሺ ተመልካቾች ይጎበኟቸዋል፡፡ በአድናቂዎቹ አማካኝነት በስሙ፤ በስራዎቹ እና ሌሎች በሚሰጡት ልዩ ልዩ ማዕረጎች የተከፈቱ በርካታ የፌስቡክ ገፆችም ይገኛሉ፡፡ http://www.teddyafromuzika.com በአሁኑ ጊዜ ጥሩ እየተንቀሳቀሰያለ ድረገፁ ነው፡፡
33. በ1991 ዓም ከያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ከወጡ ሙዚቀኞች ጋር ላስታስ ባንድን አብሮ መስርቷል፡፡ ባንዱንም በበላይነት በመቆጣጠር እና በመምራትም ትልቅ ድርሻና ሃላፊነትም ነበረው:: ከላስታስ በኋላ አቦጊዳ ባንድን ማናጀሩ ከነበረው ታዋቂው አዲስ ገሠሠ ፤ በታዋቂው ዳሎል ባንድ ከሰሩ ሙዚቀኞች በመቀናጀት ሊመሰርት ችሏል፡፡ በዋናነት ተቀማጭነታቸው በአሜሪካ የሆኑ ከ5 እስከ 7 ሙዚቀኞችን በአባልነት ያሰባስበው አቦጊዳ ጋር በኢትዮጵያ ፣ በሰሜን አሜሪካ ፣ በአውሮፓ እና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በርካታ ኮንሰርቶች በመሥራት ከፍተኛ ልምድ አለው ፡፡ በባንዱ የሚሰሩት ሙዚቀኞች ዓለም አቀፍ ደረጃ ባላቸው የሬጌ ሙዚቃ ባንዶች፣ ከአንጋፋ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ጋር በመስራት ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡
34. የመጀመርያው ኮንሰርትን የሰራው በ2003 እኤአ ላይ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ገቢ ማሰባሰቢያ በመስቀል አደባባይ በተዘጋጀበት ወቅት ነበር፡፡ በ2005 እኤአ ላይ የቦብ ማርሌይ 60ኛ ዓመት የልደት መታሰቢያ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ኮንሰርት በተዘጋጀበት ወቅት ላይ የተሳተፈው የዝግጅቱን መክፈቻ ሙዚቃዎች በማቅረብ ነበር፡፡
35. ከአገር ውጭ በመላው አለም በአፍሪካ፤ በአውሮፓ፤ በሰሜን አሜሪካ፤ በአውስትራልያ እና በመካከለኛው ምስራቅ በመዘዋወር በ40 ትልልቅ ከተሞች ኮንሰርቶችን አቅርቧል፡፡ በተለይ በ2006 እኤአ ላይ ለአስር ወራት በቆየ እና ወደ አገር ቤት በሚል ስያሜ የኮንሰርት ዝግጅቱ
 የዓለም ከተሞችን ማካለሉ ይገለፃል፡፡ በ2009 እኤአ ላይ ከእስር ከተፈታ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በአዲስ አበባ ስታድዬም በተዘጋጀ ኮንሰርት ሙዚቃዎቹን ሲያቀርብ ከ60ሺ በላይ ታዳሚዎችን አግኝቷል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚያቀርባቸው የሙዚቃ ዝግጅቶች በአማካይ እስከ 15ሺ ዶላር እንደሚከፈለውም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
36. የኔዘርላንድ ኩባንያ ሄኒከን ከሚያስተዳድረው በደሌ ቢራ ጋር በመሆን በመላ አገሪቱ በመዘዋወር የፍቅር ጉዞ በሚል ርእስ ለሚያቀርባቸው ኮንሰርቶቹ 25 ሚ.ብር ተመድቦ ሊሰራ ነበር፡፡ በኢንተርኔት በተካሄደ የተቃውሞ ዘመቻ ከ20ሺ በላይ ሰዎች በሰበሰቡት ድምጽ ኮንሰርቶቹ ቢሰረዙም በውሉ መሰረት 4.5 ሚ. ብር ተከፍሎታል፡፡
37. ጥላሁን ገሰሰ እና ቦብ ማርሌይ ትምሳሌቶቹ ናቸው፡፡
38. በበጎ አድራጎት ስራዎቹም ይታወቃል፡፡ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የገቢ ማሰባሰቢያ ኮንሰርት በመስራት፤ ለአበበች ጎበና የህፃናት ማሳደጊያ እና ለአካል ጉዳተኞች ማህበር የገንዘብ ድጋፍ በመስጠት እንዲሁም በሱዳን ታስሮ ለነበር ኤርትራዊ ዋስትና 700ሺ ብር ለዋስትና በመክፈል የሰራቸው ተግባራት ይጠቀሳሉ፡፡
39. በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ በህይወት እያለ መፅሃፍ የተዘጋጀለት ብቸኛው ድምፃዊም ነው፡፡ ‹‹የቴዲ አፍሮ ታላቅነት ሚስጥር›› በሚል ርእስ የህይወት ታሪኩን የሚዳስስ መፅሃፍ ያዘጋጀው አቤል ዘነበ የተባለ ፀሃፊ ሲሆን አብዮታዊ ሙዚቀኛ ብሎታል፡፡
40. በካናዳ አገር በዊንፔግ ከተማ ” የትውልዱ ተፅዕኖ ፈጣሪ እና አርአያ ለሆኑ ሰዎች ” የሚሰጠውን ሽልማት የወሰደው 40ኛ ዓመት ልደቱን ባከበረበት እለት ነው፡፡ በ2016 የኮራ አዋርድ ላይ በምርጥ ዝነኛ ድምጻዊ (LEGENDARY AWARD) ዘርፍ ታጭቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በ2014 እ.ኤ.አ ላይ ብራዚል ላስተናገደችው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ዘፈን እንዲሰሩ በውድድሩ ዋና ስፖንሰር በኮካኮላ ኩባንያ ከተመረጡ ሙዚቀኞች አንዱ ነበር፡፡ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አፍሪካንም በወከለ የሙዚቃ ስራው ተደንቋል፡፡
☞ማስታወሻ; 
ተጨማሪ መረጃዎችን መስጠት እና ማስተካከያዎችን መጠቆም ይቻላል
☞ ምንጮች; አዲስ አድማስ ጋዜጣ፤ ፎርቹን ጋዜጣ፤ ዊኪፒዲያ፤ ቴዲ አፍሮ ሙዚቃ የተባለ ድረገፅ ፤ሰዋሰው…ሌሎች
Filed in: Amharic