>

“ከዚህ በኋላ ፍ/ ቤት ላለመቅረብ ወስኛለሁ!...” (ኤርሚያስ አመልጋ - ከቂሊንጦ)

“ከዚህ በኋላ ፍ/ ቤት ላለመቅረብ ወስኛለሁ!…”

 

ኤርሚያስ አመልጋ – ከቂሊንጦ

• ራሳቸውን ከወገንተኝነት ካላጸዱ የፖሊስ፣ የአቃቤ ህግ እና የፍርድ ቤት ተቋማት ጋራ የተጓዝኩበት ረጅም ጎዳና፣ በፍትህ ስርዓቱ ላይ እምነት መጣሌን ትቼ ከመንገዱ ወጣ እንድልና ራሴን በጽሞና እንድጠይቅ አስገድዶኛል፤ አልፎ ተርፎም ከበስተጀርባ በስውር እጆች እየተቀነባበረ የሚሰራብኝ ትልቅ ድራማ እንዳለ ግልጽ አድርጎልኛል!!!

ድፍን አንድ አመት!…

በህግ ሊያስጠይቀኝ የሚችል ምንም አይነት የወንጀል ድርጊት ባልፈጸምኩበት እና ለክስ የሚያበቃ ምንም ተጨባጭ ማስረጃ በሌለበት ሁኔታ ለእስር ከተዳረግኩና ፍትህ አገኝ ብዬ ፍርድ ቤት መመላለስ ከጀመርኩ እነሆ ድፍን አንድ አመት ሞላኝ፡፡
የፌዴራል ፖሊስ፣ አቃቤ ህግ እና ፍርድ ቤት በአንድ ሳምባ በሚተነፍሱበት ስርዓት እና አገር ላይ፣ ገለልተኛ ፍርድ እና ሚዛናዊ ፍትህ ማግኘት እንደማይቻል በአንድ አመት የእስር ቤት ቆይታዬ ያረጋገጥኩት ሃቅ ነው!!!
ከዚህ በኋላ ፍትህ አገኛለሁ ብሎ ማሰብ ራስን ማጃጃል አንደሆነ ተገልጾልኛል፤ አሁን ከስርዓቱ ፍትህ የምጠብቅበት ሳይሆን በእኔ ከደረሰውና ዙሪያዬን ከማየው ተነስቼ የአገራችንን የፍትህ ስርዓት ነውረኛ ባህሪ ለህዝብ የምገልጽበት ወቅት ነው፡፡
“መርምረን እናስራለን እንጂ፣ አስረን አንመረምርም” የተባለለትን የለውጥ ዲስኩርና ፕሮፖጋንዳ ተከትሎ፣ ብዙ ተስፋ የተጣለበት የፍትህ ስርዓት፣ ዛሬም እንደ ትናንቱ ፍጹም የመንግስት ወገንተኝነቱን እና የአምባገነን መንግስት መሣሪያና መጠቀሚያ ሆኖ መቀጠሉን ለመላው ኢትዮጵያውያንና ለዓለም በድፍረት ማሳወቅ አስፈላጊ መሆኑን ከልብ አምኜበታለሁ፡፡
ከዜጎች ጎን ሆኖ ለእውነት፣ ለፍትህና ለህግ ልዕልና የሚቆም ስርዓት መገንባት ቀጣይ የአገራችን ዜጎች ትልቅ የቤት ስራ መሆኑን በአጽንኦት ማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡ራሳቸውን ከወገንተኝነት ካላጸዱ የፖሊስ፣ የአቃቤ ህግ እና የፍርድ ቤት ተቋማት ጋራ የተጓዝኩበት ረጅም ጎዳና፣ በፍትህ ስርዓቱ ላይ እምነት መጣሌን ትቼ ከመንገዱ ወጣ እንድልና ራሴን በጽሞና እንድጠይቅ አስገድዶኛል፤ አልፎ ተርፎም ከበስተጀርባ በስውር እጆች እየተቀነባበረ የሚሰራብኝ ትልቅ ድራማ እንዳለ ግልጽ አድርጎልኛል፡፡
ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንደገለጽኩት፣ ከኢምፔሪያል ሆቴል ሽያጭ ጋር በተያያዘ ፖሊስ ለመጀመሪያ ጊዜ ለቃለ-መጠይቅ እፈልግሃለሁ ብሎ ሲጠራኝ፣ ጥሪውን አክብሬ በመሄድ ስለጉዳዩ በቂ ማብራሪያ ሰጥቼ ነበር፡፡ ሊያስጠይቀኝ የሚችልና ለክስ የሚያበቃ ምንም ጉዳይ እንደሌለ በማስረዳት ተግባብተን ነበር የተለያየነው፡፡
ከዚያ ቀጥሎም፣ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ምንም አይነት የጥያቄም ሆነ የአቋም ለውጥ ሳያደርግ እንደገና በሌላ ሁለተኛ ዙር በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ እንድሰጥ ጠየቀኝ፡፡ እኔም በተጠየቅኩት መሰረት በቂ ማብራሪያ በመስጠት፣ ሊያስከስሰኝ የሚችል ምንም ጉዳይ እንደሌለ በአሳማኝ ማስረጃዎችና በምክንያታዊነት አስረዳሁ፡፡
ያቀረብኩት ማብራሪያ አሳማኝ ሆኖ ሳለ ግን፣ የመንግስት ፍላጎት በሚመስል እና ባልጠበቅኩት መልኩ ወደ እስር ቤት እንድገባ ተደረግኩ፡፡ በዚህ መልኩ በቂ መረጃና ማስረጃ በሌለበት ወህኒ ከተወረወርኩና እስር ቤት ታጉሬ ፍትህ ፍለጋ ቀናትን፣ ሳምንታትንና ወራትን መቁጠር ከጀመርኩ ይሄው ድፍን አንድ አመት ሞላኝ፡፡

ባለፈው ታህሳስ 17 ቀን 2012 ዓ.ም…

ማልጄ ወደ ልደታ ፍርድ ቤት ስሄድ፣ በእለቱ የሚሰየመው ችሎት የመጨረሻ ብይን እንደሚሰጠኝ በመተማመንና በሙሉ ተስፋ ነበር፡፡ ችሎቱ ሌላ ቀጠሮ ሲሰጥ ግን፣ በውስጤ የተዘራው ተስፋ ድንገት መከነ፡፡ ቀጣይ ያልታወቁ ወራትን በእስር ስማቅቅ እንድገፋ የሚያደርገኝ ቀጠሮ የተሰጠኝ፣ ከፍርድ ቤቶች በስተጀርባ ባሉት ስውር እጆች ግፊት እንደሆነ ቁልጭ አድርጎ ታየኝ፡፡
ይህን እውነታ እየተረዳሁ፣ ፍትህ አገኛለሁ ብዬ መተማመን ከንቱ ጅልነት ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ከዚህ በኋላ የሚሰጠው ፍትህ ቢኖር እንኳን፣ “የዘገየ ፍትህ እንደተነፈገ ይቆጠራል” የሚለው ብሒል እንኳን የሚገልጸው አይመስለኝም፡፡ በአገራችን ነጻና ገለልተኛ ተቋማትን ለመገንባት በተደረገው ረጅም ትግል የተከፈለው መስዋዕትነት፣ በጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ በፖሊስና በፍርድ ቤቶች ነውረኛ እና ወጋኝ አካሄድ ከንቱ መቅረቱን ባሰብኩ ጊዜ ጥልቅ ሃዘን ይሰማኛል፡፡
በየዘመናቱ ለመጣው አምባገነን ስርዓት ሁሉ ትልቅ መገልገያ ሆነው የዘለቁት ከላይ የጠቀስኳቸው ተቋማት ነጻና ገለልተኛ መሆን እስካልቻሉ ድረስ፣ የዜጎች መብት ይረጋገጣል ብሎ ማሰብ ፍጹም የማይታሰብ ነው፡፡የታመመውን የአገራችን ኢኮኖሚ ለማከም እንዲሁም በስርዓቱ ተስፋ ቢስ የሆኑ የአገራችን ወጣቶችን ወደ ዘላቂ መሻሻልና ዕድገት ሊወስዱ የሚያስችሉ ትልልቅ ዕቅዶችን ለመተግበር በተነሳሁበት ወቅት፣ ከበስተጀርባ ባሉ ስውር እጆች የሚጎነጎንብኝ ሴራ እና የሚፈጸምብኝ ደባ፣ ፖለቲካዊ ባህሪ እንዳለው ለመገንዘብ ችያለሁ፤ መላው ኢትዮጵያዊም ይህንን እውነታ እንዲረዳልኝ እፈልጋለሁ፡፡
ከአሁን በኋላ ከወገንተኝነት ካልጸዳ ፍርድ ቤት ችሎት መታደም፣ “ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” እንደሚሉት ራስን ማታለል ሆኖ አግኝቼዋለሁ፤ ስለሆነም የራሴን አቋም መያዜን እና ከዚህ በኋላ ፍትህ ፍለጋ ወደ ፍርድ ቤት ላለመሄድና ችሎት ፊት ላለመቅረብ ቁርጥ ውሳኔ ላይ መድረሴን ለህዝቡ በይፋ ለማሳወቅ እፈልጋለሁ፡፡
በመጨረሻም በኖቤል የሰላም ተሸላሚው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ እንዲሁም በጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ በጠቅላይ አቃቤ ህግ እና በሌሎች ተቋማትና ሃላፊዎቻቸው ላይ የተሰማኝን ጥልቅ ሃዘንና በእነሱ ተስፋ መቁረጤን ሳልናገር ማለፍ አልፈልግም፡፡
ኢትዮጵያውያን ሁሉ ለመሰረታዊና ለሁለንተናዊ ለውጥ ዝግጁ የሚሆኑበት፤ ዘላቂ ትግል በማድረግ ነጻና ገለልተኛ ተቋማትን መገንባት የሚያስፈልግበት ጊዜው አሁን ነው!!!
(የማይነበብ ፊርማ)
ኤርሚያስ አመልጋ
ታህሳስ 20 ቀን 2012 ዓ.ም
ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት
አዲስ አበባ
Filed in: Amharic