>
5:13 pm - Monday April 20, 6268

እጅግ አደገኛና አሳሳቢ እየሆነ የመጣው የጋምቤላ ክልል ጉዳይ!!!  (ብሩክ አበጋዝ)

እጅግ አደገኛና አሳሳቢ እየሆነ የመጣው የጋምቤላ ክልል ጉዳይ!!!

 ብሩክ አበጋዝ
ኑዌር በጋምቤላ አካባቢ ጅካዎ ከሚባል ወረዳ ያለፈ እንዳሁኑ ጋምቤላን በብዛት የተቆጣጠረ ህዝብ አልነበረም። ኑዌሮች በጋምቤላ ብቻ ሳይሆን በደቡብ ሱዳንም የሚገኝ ጎሳ ነው። ጋምቤላ ከፍተኛ የለም የመሬት እና የማዕድን ሀብት ያለበት አካባቢ በመሆኑ ድንበር ተሻጋሪ ጎሳወች በተለይም ኑዌሮች በአካባቢው ላይ በተደጋጋሚ ወረራ ስለሚያደርጉ ከንጉሡ ጌዜ አንስቶ አካባቢው ከፍተኛ ጥበቃ ይደረግለት ነበር። በዚያ ዘመን አካባቢውን ለመጠበቅ ተመድበው የነበሩ አሁንም በህይወት ያሉ የንጉሱ ዘመን ወታደሮች  ይመሰክራሉ።
ነገሮች ተቀይረው ባለፉት በህወሓት/ኢህአዴግ መሪነት ዘመናት በነባር የጋምቤላ ሕዝቦች ላይ ክህደት ተፈጸመ። በተለይ የአኙዋኮችን ጭፍጨፋ ተከትሎ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የኑዌር ብሔር ተወላጁ ጋትሉዋክ በህወሓት መራጭነት ከተቀመጠ በኋላ የመጠቃቀም ፖለቲካና ከፍተኛ ሙስና ተንሰራፋ። በዚህ ወቅት በደቡብ ሱዳን ሕዝቦች በመሪወች ልዩነት ምክንያት ጦርነት ተጀመረ።
የህወሓት የጦር አዛዦች፣ ጡረተኛ ወታደሮች እና ባለሀብቶች ለጥቅም ያላቸውን ስግብግብነት የተረዳው ጋትሉዋክ የእነሱን እምነት ለማግኘት የክልሉን መሬት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መሬት አደላቸው። የህወሃት ሰወች መሬቱን በማስያዝ ከልማት ባንክ ብር ተበድሩበት፤ ከዚያም ብራቸውን ይዘው ለባንኩ ባዶ የጋምቤላ መሬት አሳቅፈው ጠፉ።
የክልሉ ፕሬዝዳንት ይኼ ሁሉ እየሆነ መሬቱን አስይዘው ከባንክ ብር የወሰዱት ሰወች ሲጠፉ በህግ ከመጠየቅ ይልቅ ይባሱን ወደ ክልሉ የሚመጣ አመራር ሁሉ ዳጎስ ያለ ብር ከመንግስት በጀት እያወጣ ሲሰጥ ቆየ (ለአብነት በካሳ ተ/ብርሃን ትዕዛዝ ለዋግ ልማት ማህበር የተሰጠውን የገንዘብ ስጦታ ማስታወስ ይቻላል)።
በደቡብ ሱዳኖች ጦርነት ምክነያት ከደቡብ ሱዳን የሚፈልሱት ኑዌሮች ያለምንም ስጋት ወደ ክልሉ በነጻነት በሁሉም አቅጣጫ እንዲገቡ እና እንዲሰፍሩ የጋምቤላ ክልል ኑዌሩ ፕሬዝዳንት ከህወሓት ጋር ባለው የጥቅም ትስስር አመቻቸላቸው።
በዚህ አላበቃም በኑሯቸው እንዳይቸገሩ የመኖሪያ መታወቂያ እንዲታደሉ ካደረገ በኋላ በክልሉ የመንግስት መዋቅር ኢትዮጵያዊ ተብለው እንዲቀጠሩ በማድረግ የክልሉ መንግስት በጀት ለእነርሱ የኑሮ መደጎሚያ መዋል ከጀመረ ሰንብቷል። የጋምቤላ ክልል ሕዝብ ቁጥር 310 ሺህ ሆኖ እያለ በክልሉ የሚገኙት የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ቁጥር 470 ሺህ ሆኗል።
በዓለም አቀፉ ስደተኞች ማህበር አሰራር ስደተኞች በሚኖሩበት አካባቢና ክልል በቋሚነት ከሚኖረው ሕዝብ መብለጥ የለበትም የሚል ህግና አሰራር  ያለው ሲሆን ይህን የአሰራር በመጣስ በክልሉ ዋና ከተማ በሰባት እና ሃያ ሰባት ርቀት እንዲሰፍሩ በፕሬዝዳንቱ ጋትልዋክ ትዛዝ እንዲሰፍሩ ተደርጓል።
እያንዳንዱ ነባር ኢትዮጵያዊ ኑዌር በታቀደ መልኩ ካምፕ ውስጥ ከሚኖሩት ከተሰደዱት ኑዌሮች ከሁለት ሶስት በላይ ሚስት አግብቶ እየወለደ ነው። መውለድ ብቻ ሳይሆን ቤት እየሰራ በአካባቢው በማስፈር የስደተኞች ሬሽን እደላ ሲደርስ ብቻ ወደ ካምፕ ሔደው ተቀብለው ወደ ማህበረሰቡ የመመለስ ነጻነት አላቸው።
እስካሁን ባለው ሁኔታ በጋምቤላ ክልል ኑዌር የሆኑ አመራሮች ብልጽግና ፓርቲን የተቀበሉ አይመስሉም፤ ጠሚ ዓቢይንም ሲሳደቡ ይስተዋላሉ። በብዙ የሚቆጠሩ የትህነግ ሰዎች ጋር ዛሬም በጀርባ በተለይ በጋምቤላ ከተማ ኒው ላንድ ቀበሌ ዘወትር እየዶለቱ ከሴራ ተግባር ባለተለየ እንቅስቃሴ ውስጥ ከመሆናቸውም በላይ አካባቢው ላይ የሚሰሩት ኦፕሬሽን ያለ ይመስል አጋጣሚወችን ጠብቀው የሚፈልጉት ቡድን ላይ ጥቃት ለመውሰድ እየተዘጋጁ ይመስላሉ።
በተለይም የጠሚ ዓቢይን ስልጣን ላይ መምጣት ተከትሎ ኑዌሮች ከፕሬዚዳንትነት ቦታ ተነስተው አኙዋክ ስለተተኩና የበላይነታቸውን ስላሳጣቸው የጠሚ ዓቢይን አመራር በጠላትነት ነው የሚመለከቱት። ሌላው ቀርቶ ትህነግ መቐለ ላይ ባደረገው የፌዝራሊዝም ስብሰባ ከሃያ አምስት ያላነሱ የኑዌር ተወካዮች ተገኝተዋል። ይህን በማመቻቼት በኩል ደግሞ የትህነግ ጉዳይ አስፈጻሚ የሆነው የክልሉ ሰራተኛ ማህበራዊ ጉዳይ ምክትል ሃላፊ አቶ አለምሰገድ ቀዳሚው ሰው ነው።
በጋምቤላ አሁንም አለመረጋጋት እንዲፈጠር የትህነግ ሰዎች ትልቅ ስራ አየሰሩ ይገኛሉ። ምክንያቱም ይህ አካባቢ የደቡብ ሱዳን አማጺወች፣ የሸኔ ኦነግ እና መሰል መገናኛ አጎራባች ቦታ መሆኑ ለእነሱ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል። ከምንም በላይ አሁንም በኢንቨስትመንት ስም ተሰማርተው የሚገኙ የቀድሞ የትህነግ ወታደሮች በክልል ስለሚገኙ እጃቸው ረጃጅም ሆኗል።
የUNHCR ፊልድ ኦፊስ ኃላፊ የነገረችውን እና ከህዝብና ቤት ቆጠራ መቃረብ መነገሩን ሲሰሙ ከሱዳን እየተሻገሩ ኢትዮጵያ መሬት ላይ መስፈራቸው አሳዝኗት የነገረችውን ወዳጄ እንደሚከተለው ነግሮኛል።
——–
በመጀመሪያ ስራ ከመጀመራቸን በፊት ወደ UNHCR ፊልድ ኦፊስ ሃላፊ ጋር ተገናኙ ስለተባልን ለማናገር አመራን። ሃላፊዋ አፍሪካዊት እንጅ የየትኛውም ሃገር ዜጋ መሆኗን ማወቅ አይቻልም። በፈገግታ ተቀብላ ለውይይት መቀመጫ ጋበዘችን። ተዋወቅን ጌዜ ሳናጠፋ «አብረዋችሁ ያሉ ሰራተኞች ውጪ ላይ እንዳሉ አውቃለሁ እና ብሔራቸውን ንገሩኝ» አለችን። ለምን እንደጠየቀች ገባኝ ስራው የሚሰራው ለኗሪው ማህብረሰብ (Host commmunity) በመሆኑ ጋምቤላ በተፈጠረው የኑዌር እና አኝዋ ብሔርሰቦች ግጭት አንዱ ብሔር ወደ ሌላኛው ብሔር አካባቢ ለማንኛውም ስራ አይሔድም ከሔደም አደጋ ይጠብቀዋል።
ለአካባቢው አዲስ የነበረው ጓደኛዬ የሁለቱን ብሔር ቀለም ለመለያየት የነበረውን ሁኔታም ስለማያውቅ ቶሎ ብሎ «አንደኛው ነዌር ነው ሌሎቹ ግን ደገኞች ናቸው» አለ በድንጋጤ ደርቀው ራሳቸውን ይዘው ለመጮህ ምንም አልቀራቸውም። እኔ ቶሎ ብየ «ኑዌር ሳይሆን አኝዋክ ነው፤ ሁለቱን መለየት ስላልቻለ ነው አልኩ»። ነፍሳቸው ተመለሰች ከደንጋጤያቸው ግን ቶሎ አልወጡም።
«አንተ እንኳን አዲስ ስለሆንክ ለምን እንደደነገጥን አታውቅም። እዚህ አካባቢ ዙሪያውን የአኙዋክ ብሔሮች መኗሪያ ነው። በቅርብ የኑዌር ስደተኞች ካምፕ አለ። የብሔር ቁርሾውን ታውቃላቹህ። እኛ ስደተኞችን ስንቀበል እንደማንኛውም ስደተኛ ቢሆንም አሁን ላይ እጅግ አደገኛ የሆነ ችገር ነው የተፈጠረው። በአካባቢው ኑዌሮች አሉ፤ ከአኙዋኮች ጋርም ግጭት አለ። ነገር ግን እኛን ፈተና የሆነብን ሰድተኞች ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር አለመግባባት ሲፈጠር የኢትዮጲያ ኑዌሮች ለስደተኞች አግዘው ረብሻውን በማባባስ ላይ መሆናቸው ነው።»
ለምሳሌ አለች ከጎኗ የተቀመጠውን ኑዌር እየጠቆመች «ይህ ሰው ኢትዮጵያዊ ኑዌር ነኝ በሎ ነው እኛ ጋር ተቀጥሮ የሚሰራው በስደተኞች እና በአካባቢው ሰዎች መካከል ግጭት ሲፈጠር ገለልተኛ ሆኖ ማረጋጋት ሲገባው በተቃራኒው ደንጋጊ ለስደተኞች አግዞ አብሮ ይወረወራል። ይህ በጣም አሳፋሪ አስቸጋሪም ነው። እዚህ አካባቢ በዚህ ምክንያት ሁሌ ግጭት ሁሌ ውጥረት ነው። እኛ እዚህ ስደተኞችን ስናሰፍር ይህ ነገር ይከሰታል ብለን አስበነው አናውቅም። አሁን ላይ አስቸጋሪ ነው። ለዚህ ነው የጥናቱ መረጃ የሚሰበሰበው አኝዋክ ኗሪዎች ጋር በአብዛኛው ስለሆነ ኑዌር ከመጣ አዳጋ ይፈጠራል ብለን ነው የደነገጥነው፤ ብሔር የጠየቅናቹህም» በማለት እያዘነች እየተከዘች የነገረችን።
እንደ አጠቃላይ የጋምቤላ የስደተኞች ጉዳይ ስጋት እንደሆነ በነጻነት ከማህብረሰቡጋ የመቀላቀል እቅስቃሴ፣ የመሬት ወረራ ተጨማሪ ከፍተኛ የሆነ በዕለት ተለት ኑሮ ላይ ጫና መፍጠሩ፣ የህወሓት፣ ኦነግ ሸኔ እና የደቡብ ሱዳን አማጽያን በአካባቢው ላይ ያላቸው እንቅስቃሴ ከጸጥታ ስጋት እና በግጭት ሞት በተጨማሪ በጤና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች እና በክልሉ ብቸኛ ሆስፒታል ለመታከም በወረፋ መጨናነቅ ኗሪው እየተማረረ ከመሆኑ ጋር አካባቢው ለቀውስ የተመቻቸ እንዲሆን አስችሎታል።
Filed in: Amharic