>

"ሆን ብለው ካማሰሉት እንኳን ሀገር ድስት አይረጋም!" (አዳም ረታ ¨መረቅ¨)

“ሆን ብለው ካማሰሉት እንኳን ሀገር ድስት አይረጋም!”

አዳም ረታ (መረቅ) መፅሃፉ ላይ ያስቀመጣት ከባድ እውነት ነች
በሙክታር ኡስማን
 አንድ ከዋናዋ ሶማሊያ በስኮላሺፕ እኛ ዩኒቨርሲቲ የተማረ በጣም አስተዋይ ልጅ ስለኢትዮጵያ ፖለቲካ ስንጨዋወትና ጨወታችን በስሜት ሞቅ ሲል አንዱ “ይህማ ካልሆነ ይህች ሀገር ትፈርሳለች!” ሲል ሌላው በንዴት “ትፍረሳ!” እያለ ሲመልስ፣ ያዳምጠን እና በምፀት ፈገግታ እንዲህ ይላል:— እናንተ የዚህ ዘመን ኢትዮጵያውያን ስለሀገር መጉደል ስለማታውቁ አይፈረድባችሁም። ሀገር ከእጃችሁ ስታመልጥ በቀላሉ የምታገኝዋት መስሏችሁኣል— አለን።
ዝም ብለን ሰማነው።
ሶማሊያ እንዲሁ በእልህና በስሜት፣ በጎጥና በጀብደኛ ልብ የለሽ ተቃዋሚዎች ፈረሰች። ከዚያ የሆነውን ታውቃላችሁ። ሀገር፣ ስርዓትና መንግስት በመፅሃፍ ያነበብኩትን ከሶማሊያ ወደ ኢትዮጵያ ስገባ ነው ትርጉማቸውን የማውቀው። ፖሊስ ያስራል፣ ፀጥታ ያስከብራል። ትራፊክ ማብራት አለ፣ እሱ ካልሰራ ትራፊክ ፖሊስ አለ። በግብር ጉደይ የተዘጋ ሱቅ አለ፣ መታወቂያ ኬላ ላይ ታሳያለህ። ምንም የተሟላ ዴሞክራሲ ባይኖርም፣ ህግ አለ፣ ስርዓት አለ፣ መንግስት አለ። ይህ ለኛ ብርቅ ነው። የሀገርን አስፈላጊነት ንጉሱ ስላወቁ ደርግ ተነሱ ሲላቸው አላመፁም፣ አላሳመፁም። በሉ ሀገርን በተራችሁ ጠብቁ ብለው ታሰሩ። የደርግ ጄኔራሎች ኢህአዴግ አዲሳባን ሲከብ ሀገርን አስረክቦላቸው ወደ እስርቤት ሄዱ። መሳሪያ በጃቸው በመሆኑ በማመፅ ሀገር ሊበትኑ ይችሉ ነበረ። የዚያድባሬ ጄኔራሎች ሀገር ነው የበተኑት። የናንተ ግን መንገድ ላይ ወድቀው ለመኑ፣ ታሰሩ። ሀገርን ስላስቀደሙ ነው። “
እያለ ብዙ ነገር ነገረን። ከዚያ ቀን በኋላ በከረረ ፖለቲካ እንኳ ስለሀገር መፍረስ ሲወራ፣ ይህንም በቴሌቭዥን ስሰማ ዝግንን ይለኛል። ለኢትዮጵያ ሲሉ የታሰሩ፣ የተሰቃዩ፣ የሞቱ ሰዎችን እና ከራሳቸው በላይ ለሀገር ቅድሚያ ሰጥተው ኢትዮጵያን ያቆዩልን መሪዎችን አስታውሳለሁ።  ኢትዮጵያ (እየተጨቃጨቅንባት) ለዘላለም ትኑር!  “ሆን ብለው ካማሰሉት እንኳን ሀገር ድስት አይረጋም!”
Filed in: Amharic