>

አጼ ምኒልክና የሐረርጌ ጦርነት!!! (ጳውሎስ ኞኞ )

አጼ ምኒልክና የሐረርጌ ጦርነት!!!

ጳውሎስ ኞኞ

ሳሚ ዮሴፍ
የጨለንቆ ጦርነት እውነታው እሄ ነው፤ በተረት ያበዱ ጽንፈኞች ታሪክን ለውጠው ቢያወሩም ታሪክ ታሪክነቱን አይቀይርም!!!
“…እነዚህ ሐበሾች ሰፊ ግዛት አላቸው። ከቀይ ባህር ዳርቻ ከምፅዋ፣ ከሱአኪንና ከአርቂቆ ተነስቶ ግዛታቸው እስከ ሞቃዲሾና ሶፋላ ይደርሳል። በምዕራብ በኩል ግዛታቸው የሚዋሰነው ከኑባውያንና ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ነው።….”
አልፎንሶ አልቡ ከርክ 1503 ዓ.ም 
“…የሐበሾች ግዛት ሰፊ ነው። ቀይ ባህር ዳርቻ ካለው ከትልቁ ወደባቸው ከቢሊ ተነስቶ ወደ ውስጥ ሲጓዝ በአዳል ምድር አልፎ ሐድያ ሁሉ የእነርሱ ሀገር ነው። ወደ ሕንድ ውቅያኖስ አቅጣጫም እስከ መቋዲሾ ይደርሳል።
ሐበሾቹ በጣም ሰፊና ሀብታም ሀገር አላቸው። እነዚህ ሕዝቦች ወሰናቸውን ለማስከበር ወደ ዳር ሀገር ወይም ወደ ወሰናቸው በሚጓዙበት ጊዜ የሚጓዙት ዛፍ እየቆረጡና መንገድ እየሠሩ ነው።….”
ፍራንቼስኮ አልቫሬፅ 1520 ዓ.ም
“…ሐበሾች ዙሪያቸውን በአረመኔዎችና በብዙ ጠላቶቻቸው የተከበቡ ሕዝቦች ቢሆኑም ግዛታቸው ሰፊ ነው። ከነኩዋቸው ተዋጊ ሕዝቦች በመሆናቸው ዙሪያቸውን የከበቡዋቸው ጠላቶች በተነሱባቸው ጊዜ ከጠላቶቻቸው ጋር እየተዋጉና እያሸነፉ ይኖራሉ። የሐበሻ ሰዎች ለማንም ባዕድ አንገዛም እያሉ ራሳቸውን ችለው የሚኖሩና ሀገራቸውን ከማንኛውም ባዕድ ገዥ እየተከላከሉ የሚጠብቁ ሕዝቦች ናቸው። ግዛታቸውም ቀይ ባህርን ተሻግሮ እስከ አረብ ሀገር ድረስ ነው።…”
ካርታ ዳስኖቫስ 1521 ዓ.ም 
“…ቱርኮች በኔ ላይ ክፉ ነገር በመሥራት ወሰኔን እየገፉ አጠገቤ ደርሰዋል። ሐረርን ወሰዱት ከዚያም አልፈው
ኢቱ ኦሮሞንና በረሀውን ሁሉ ሊይዙት ነው። ነገሩ እንዲህ ከሆነ ከእነርሱ ጋር ለመዋጋት መሄዴ ነው። የኤሮፓ ነገሥታት ሁሉ እኔን እንደ ጠላት ስላዩኝ የተገፋው በመሆኔ ግብጾቹን ለመውጋት ለመዝመቴ እርስዎ ምስክር ይሆኑኛል።…”
አጤ ምኒልክ በግንቦት ወር 1876 ዓ.ም ለኢጣልያ ንጉሥ ከፃፉት ደብዳቤ።
“…ሐረር ከአያት ቅድመ አያቶቼ ጀምሮ የሸዋ ግዛት ነው!...”
ምኒልክ ግንቦት 1877 ዓ.ም ለኢጣልያ ንጉሥ ከፃፉት ሌላ ደብዳቤ።
ግብጾች ሐረርጌን የያዙት በ1867 ዓ.ም ነው። ኢትዮጵያ በመሳፍንት አገዛዝ ተከፋፍላ ሁሉም የዕለት ጥቅሙን ያሳድድ በነበረበት ጊዜ ክፍት በር ያገኘው በራኡፍ ፓሻ የሚመራው 1200 ወታደሮች ያለበት የግብጽ ጦር በቀላሉ ሐረር ገባ። በዚያን ጊዜ በሐረር ከተማ 5000 ቤቶችና 2000 ጎጆዎች ነበሩባት። #የሕዝቡም #ብዛት 35000 ነበር። ሐረር ከተማ ዙሪያዋን በግንብ ተከባ ወደ ከተማዋ የሚገባውም የሚወጣውም በአምስት በሮች ብቻ ነው።
እነዚህም በሮች የተለያየ ስም ሲኖራቸው ታላቁ መግቢያ #አስበዲን በር ይባላል። ይህ መድፍ ተጠምዶ የተቀመጠበት በር የጨርጨር ሰዎች መግቢያ ነው። ሁለተኛው #ሱቅጣጥ በር ይባላል። ይህ በር ደግሞ የአርሲዎችና የጋራ ሙለታ ሰዎች የሚገቡበት ነው። ሦስተኛው #አርጎባ በር ይባላል። የፈዲሶች የአርጎቦች መግቢይ ነው። አራተኛው #አሱም በር ይባላል። አሱም በር ልክ እንደ አስበዲን በር መድፍ የተጠመደበት ሲሆን የኢሶች መግቢያ ነው። አምስተኛው በር #የረር በር ይባላል። የየረሮች መግቢያ ነው። እነዚህ በሮች ሁልጊዜ በሚገባና በጥንቃቄ ይጠበቃሉ። ማታ ሲሆን በሮቹ ይቆለፉና የቁልፎቹ መፍቻዎች ለአሚሩ ይሰጣሉ። ከዚያ በኋላ ነግቶ በሮቹ እስኪከፈቱ ድረስ የሚወጣም ሆነ የሚገባ የለም።
ኢጣልያኖች ሐረርጌን ከሞቃዲሾ ጋር፣ እንግሊዞችም ከበርበራ ጋር ደባልቀው ለመያዝ ሀሳብ ነበራቸው። እንግሊዞች አንግሎ ኢጂፕቲያን በተባለው ከግብጽ ጋር በነበራቸው ስምምነት መሠረት የግብጽ ጦር ከሐረርጌ ወጥቶ ሐረርጌን ለእንግሊዞች ለማስረከብ ተስማምተዋል።
ይህንን ስምምነት የሰማው የኢጣልያ መንግሥት ደግሞ ሐረርጌን ከእንግሊዝ ቀድሞ በኃይልም ሆነ በፍቅር ለመያዝ አስቦ በሐረርጌ ያለውን የግብጽ ጦር የሚሰልሉ ሰላዮች በየጊዜው ወደ ሐረርጌ ይልክ ነበር።
እንግሊዞች ከግብጾች ጋር በነበራቸው ስምምነት መሠረት ግብጾች ከሐረርጌ እንዲወጡ አደረጉ። ምናልባት የኢጣልያ መንግሥት ገፍቶ የመጣ እንደሆነ በማለት ከግብጾች ቀጥሎ ስልጣን ለያዘው ለሐረርጌው አሚር አብዱላሂ እንግሊዞች የሰለጠኑ ወታደሮች 400 ያህል ጠመንጃና ጥቂት መድፎችን ሰጥተው ጀልዴሳና ሐረር ላይ ምሽጉን እንዲያጠናክር አደረጉት። አሚር አብዱላሂ ስልጣኑን በደንብ ከያዘ በኋላ የግብጽን ገንዘቦች አሽራፊና መሀለቅ የተባሉትን አስገብቶ በሐረርጌ ገበያዎች ላይ እንዲውሉ አደረገ።
የእነዚህን ገንዘቦች መግባት ያየው የሐረርጌ ኦሮሞና የሱማሌ ብሔረሰቦች ገንዘቡን አንቀበልም በማለት በአሚሩ ላይ ጥላቻ አሳድረው ገበያ ጠፋ። በገበያው መጥፋት ምክንያት የአሚር ወታደሮች ችግር ላይ ወደቁ።
አብዱላሂ በዚህ ብቻ ሳይሆን በሚያወጣው አዋጅ ሁሉ በሕዝብ ዘንድ እየተጠላ ሄደ።
በሐረርጌ የውጭ ሸቀጥ አስመጪና የሀገር ውስጥ ሸቀጥ ላኪ የነበረው ኢጣሊያዊው ጋይታኖ ሲኮኒ በስለላ ተግባር ይጠረጠር ስለነበር አብዱላሂ ጋይታኖን ጠርቶ “…በእስልምና ኃይማኖት እመን የማታምን ከሆነ ሀገሬን ለቀህ ውጣ።…” አለው። ጋይታኖም አላምንም ብሎ ከሐረር ተባሮ ወጣ።
ጋይታኖ ከሐረር ተባሮ እንደወጣ ኢጣልያ ገብቶ ሚላን ላለው የአፍሪካ የንግድ ማህበር የደረሰበትን በደል አመለከተ።
ማህበሩም ለስም የተቋቋመ እንጂ ዋንኛ ሥራው የኢጣልያ መንግሥት ሰላዮች ማስተባበርና መላክ ስለነበር ስምንት የታወቁ የኢጣልያ ሰላዮችን በኢጣልያ መንግሥት ስም ስጦታ አሲዞ ወደ ሐረር ወደ አሚር አብዱላሂ ላከ።
እነዚያ የኢጣልያ መላክተኞች ሚያዚያ1 ቀን 1878 ዓ.ም የሐረርጌ ግዛት ከሆነው ጀልዴሳ ደረሱ። ከዚያም ሆነው “የተከበሩ ታላላቅ ስጦታዎች ይዘን መጥተናልና እንዲቀበሉን ፍቃድ እንጠይቃለን” ብለው ለአሚር አብዱላሂ ላኩ። አሚር አብዱላሂም ክርስቲያን ኢጣልያኖች ወደ ግዛቱ በመግባታቸው ተናዶ እንዲገድሏቸው ወታደሮቹን ላከ። የተላኩትም ወታደሮች ሰባቱን ኢጣልያኖች አርደው ገደሏቸው። አንደኛው ግን በፈረስ አምልጦ ዘይላ ገባ።
ኢጣልያኖቹን የገደሏቸው ወታደሮች የመጣውን ስጦታ ይዘው ለአሚር አብዱላሂ አቀረቡ። አብዱላሂ ከኢጣልያ ንጉሥ መጥቶለት የነበረውን ስጦታ ተቀብሎ ኢጣክያኖቹን የገደሉትን ወታደሮች አሰራቸው። አብዱላሂ ይህንን ማድረጉ ኢጣልያኖቹ የተገደሉት በስህተት ስለሆነ ወንጀለኞቹን አስሬአለሁ ለማለት ነበር። ይህ ከሆነ በኋላ ኢጣልያኖች ሐረርጌን በጦር ኃይል ለመያዝ ጥሩ ሰበብ አገኙ።
“በሐረርጌ የተገደሉብን ወገኖቻችን ደም እንበቀላለን” የሚል መግለጫ ማውጣታቸውንና ሐረርን ለመያዝ ማሰባቸውን የሸዋው ንጉሥ ምኒልክ ሰሙ ወዲያው ለአሚር አብዱላሂ ደብዳቤ ፃፉለት።
“…ቀድሞም ቢሆን ሐረርጌ ከኢትዮጵያ ውጪ ተገዝቶ አያውቅም። ከኢትዮጵያ አውራጃዎች አንዱ መሆኑን አንተም በታሪክ ሰምተኸው ይሆናል። ለአራት መቶ ዓመት ግብሩን ሳያቋርጥ ለአያቶቹ ሲገብር ኖሯል። አሁንም ነገሩን በሰላምና በወዳጅነት  ለመጨረስ ገብር እና እንደ አባቶቻችን ወዳጅ እንሁን።…” የሚል ደብዳቤ ለአሚር አብዱላሂ ላኩበት።
አሚር አብዱላሂ ደብዳቤውን ከተቀበለ በኋላ “…በውኑ በዚህ ዓለም ላይ ከቱርክ የሚበልጥ መንግሥት አለን?…” ብሎ ለመኳንንቱ ተናገረ።
ምኒልክም ለመጀመሪያው ደብዳቤ መልስ አለመምጣቱን እንዳዩ ዳግመኛ “ብትገብር ይሻልሃል” ብለው ላኩለት።
የምኒልክ ሁለተኛ ደብዳቤ ሲደርሰው አሚር አብዱላሂ ሳቀ።
ለምኒልክም ደብዳቤ መልስ ሲመልስ “…በእስልምና ኃይማኖት ገብተህ የሰለምክ እንደሆን ጌትነትህን እቀበላለሁ” ብሎ ሙስሊሞች የሚያሸርጡትን ሽርጥ፣  በራሳቸው ላይ የሚጠመጥሙትን ጥምጣምና የጸሎት ጊዜ መስገጃ ምንጣፍ ላከላቸው።
ይህንን መልስ ያገኙት ምኒልክ “…ወደ ሐረር እመጣለሁ፣ በዚያ ያለውንም መስጊድ ወደ ቤተክርስቲያን እለውጠዋለሁ፣ ጠብቀኝ…” የሚል ደብዳቤ ልከውለት ይዘጋጁ ጀመር። ወዲያውኑም በአስቸኳይ ተዘጋጅተው በአጤ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት ኅዳር 4 ቀን 1879 ዓ.ም ከእንጦጦ ከተማ ተነሱ። የምኒልክን ከእንጦጦ መነሳት የሰማው አሚር አብዱላሂ ክርስቲያኖች በሙሉ የሐረርጌን ከተማ ለቀው እንዲወጡ አዋጅ አስነገረ። በኃይማኖት ሰበብ ይረዳሉ ብሎ ኤሮፓውያኖችንም ጠርጥሮ ስለነበረ ከሀገር አልወጣም ያለ ማንኛውም ክርስቲያን የሆነ ፈረንጅ ሁሉ ከቤቱ እንዳይወጣ አዘዘ። ጠባቂም በየበራቸው ላይ አደረገ።
 በዚያን ጊዜ በሐረር የነበረው #እንግሊዛዊው #ፔተን በፃፈው ማስታወሻ “…በከተማው ውስጥ እንደ እስረኞች ነን ደብዳቤ የመላክምና የመቀበልም ነፃነት የለንም። ከሐረር ከግንቡ ውጭ እንኳ እንዳንወጣ ክልክል ነን…” ብሏል።
የገና በዓል ደርሶ ነበርና ምኒልክ ጨለንቆ ላይ ሰፍረው የገናን በዓል ለማክበር ወሰኑ። በዚያም ሰፈር አድርገው ሳለ ምኒልክ መኳንንቶቻቸውን ሰብስበው “…ይህ አሚር አብዱላሂ እኛ ክርስቶስ ተወልዷል ስንል እርሱ አልተወለደም የሚልበት ቀን ነውና የልደት ዕለት ጦርነት መግጠሙ አይቀርም…” ብለው ተናገሩ። ከዚህም በኋላ “…ግባ፤ እኔ ለአንተው ነው እንጂ የመጣሁት ሀገር ለማጥፋት አልመጣሁም ከገባህ ከተገዛህ ሀገር አልነሳህም፤ ኋላ ይቆጭሃል…” ብለው ላኩበት። አሚር አብዱላሂ ግን የፈሩት ስለመሰለው ጭራሽ መልክተኞቹን አሰራቸው።
ኮንቲ ሮስኒ ሲጽፉ “…ገብር የሚለው የምኒልክ ደብዳቤ ለአሚር አብዱላሂ እንደደረሰው የሕዝቡን አስተያየት ለማወቅ ሕዝቡንና ወታደሮቹን አሰባስቦ የምኒልክን ጥያቄ አሰማቸው።
ሕዝቡም በኃይማኖታችን ላልገባና  በእስልምና ኃይማኖት ለማያምን አንገብርም፤ እንዋጋለን፤ ቢያሸንፉን ሐረርን ይውሰዱ፤ ያንጊዜም የሚፈልጉትን ግብር እንገብርላቸዋለን ብለው መለሱለት…” ይላሉ።
የሐረርጌ ሽማግሌዎች ግን አሚር አብዱላሂ ዘንድ ሄደው ጦርነቱ እንዲቀርና እንዲገብር መከሩት።
አብዱላሂም “…ስለ ምኒልክ ሠራዊት እንድትነግሩኝ አልፈልግም እንድትነግሩኝ የምፈልገው መጽሐፋችን ለካፊር እጃቹህን ስጡ ይላልን?…” ብሎ አማካሪዎቹን አሰራቸው።
ካፊር ማለት በእስልምና ኃይማኖት የማያምን ነው።
ከዚያም በኋላ የጅሃድ ጦርነት አወጀ። ሊያስገብሩት ሄደው የነበረውን የደጃች ወልደ ገብርኤልን ሠራዊት በጥቂት መሣሪያ በማባረሩ የምኒልክም ሠራዊት እንደዛው በቀላሉ ይሸሻል ብሎ አሰበ። ከዚህ በኋላ ሠራዊቱን አስከትሎ የምኒልክን ጉዞ ለማስቀረት ወደ #ጨለንቆ ተጓዘ።
ቀኑ የክርስቶስ ልደት በዓል ስለነበረ የምኒልክ ሠራዊት እየበላ፣ እየጠጣ ይጫወታል። ንጉሥ ምኒልክ ከድንኳናቸው ደጃፍ ተቀምጠው አሸጋጋሪውን ኮረብታ በመነጥር ሲመለከቱ የአብዱላሂ ሠራዊት ሲመጣ አዩ። ምኒልክ ሠራዊቱ እንዲሰበሰብ አድርገው “ሂድ በለው” ብለው አዘዙ።
ከቀኑ 5 ሰዓት ሲሆን የአሚር አብዱላሂ መድፎች በሸዋ ሠራዊት ላይ ይተኩሱ ጀመር። የሸዋ ሠራዊትም በአስደናቂ ፍጥነት የአሚር አብዱላሂን ሠራዊት ወርሮ መድፎቹን ማረከ። በተማረኩት የአብዱላሂ መድፎችም የአብዱላሂ ሠራዊት ይመታበት ጀመር። ጦርነቱ ብልጭ ብሎ ጠፋ።
የአብዱላሂ ሠራዊት ሩብ ሰዓት ከተዋጋ በኋላ ሸሸ።
አብዱላሂም በፈረስ ሆኖ ወደ ሐረር ሸሽቶ አመለጠ።
ከአሚር አብደላሂ ሠራዊትም አንድ ሺህ ያህል ወታደሮች ተገደሉ። ታህሳስ 29 ቀን 1879 ዓ.ም የሐረርጌው  የአብዱላሂ ጦር ድል ሆነ። ይህን የአብዱላሂ ጦር ድል መሆን የሰሙት እቴጌ ጣይቱ አዲስ በመሠረቱት አዲስ አበባ ሆነው
 “የሚጓዘው ሰንጋ የሚነዳው ሽህር ለልደት ባይደርስ
  እሱ ላም አርዶ ዋለ የሸዋው ንጉሥ”
ብለው ተቀኙ። አንዳንድ የሀገራችን ታሪክ ፀሐፊዎች
 “እሱ እስላም አርዶ ዋለ” ብለው ቅኔውን በመተርጎም ጽፈዋል። እንዲያ ከሆነ ቅኔነቱ ይቀራል።
ምኒልክ ድል ካደረጉ በኋላ የኢጣልያ መንግሥት ሐረርጌን ለመያዝ እጅግ የተነሳሳ ጉጉት ስለነበረው እዚያው ጨለንቆ እንደሆኑ ለኢጣልያው ንጉሥ ለኢምቤርቶ “…ኢጣልያኖችን የገደለው አሚር አብዱላሂ በፈረስ አመለጠኝ ግን እግዚአብሔር ይመስገን ሰዎቹን ፈጀሁበት። ሰንደቅ ዓላማዬንም በሀገሬ ላይ አቆምኩ። ወታደሮቼንም አገባሁ። ኢጣልያኖችን ለመርዳት ስል ተደርጎ የነበረውን አደጋ በብዙ ሬሳዎች ተበቀልኩ ከዚህ ደብዳቤ በኋላ ሁኔታውን የሚያስረዳ በሰፊው እሰዳለሁ…” የሚል ታህሳስ 30 ቀን ማለት በጦርነቱ ማግስት የተፃፈ ደብዳቤ ላኩ።
ምኒልክ ይሄንን ደብዳቤ የፃፉት ሐረርጌ የኢትዮጵያ ግዛት መሆኑን ለኤሮፓ ነገሥታት ለማሳወቅና ኤሮፓውያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ ባላቸው ሀሳብ መሠረት ወደ ሐረርጌ ጦር ቢልኩ ውጊያው ከምኒልክ ጋር መሆኑን ለማሳወቅ ጭምር ነበር።
ምኒልክ አብዱላሂን ለመያዝ ወደ ሐረር ከተማ ገሰገሱ
ጥር 1 ቀን አማሬሳ ሲደርሱ አብዱላሂ የሸዋ ጦር እንደደረሰበት ስላወቀ “ልግባና ልገዛ፤ ሀገርዎን አያጥፉት” ብሎ ላከ። ምኒልክም “እሺ ግባ፤ ምሬሃለሁ” ብለው ላኩበት። አብዱላሂ ግን ፈርቶ ለሊቱን ሚስቱንና ልጆቹን ይዞ ወደ ጅጅጋ ሸሸ። የአብዱላሂን መጥፋት ያወቁት ሐረርጌዎች
ማለት የአብዱላሂ አጎት አሊ አቡበከር፣ የሱፍ በርከሌ፣
ቃዲ አብደላና ሌሎች ሽማግሌዎች ሆነው ወደ ምኒልክ ዘንድ መጥተው “…አሚር አብዱላሂ ለሊት ጠፋብን ግብርዎን ይቀበሉን ሕዝቡንም አያጥፉት ንጉሥ ሆይ…” ብለው አመለከቱ። ከመልክተኞቹም ጋር እስረኞች የነበሩ ሁለት ግሪካውያንና ሌሎችንም ፈትተው ወደ ምኒልክ ላኩ።
ንጉሥ ምኒልክም መልክተኞቹን ተቀብለው “…ከዚህም በፊት ብያለሁ እኔ እስልምናን ኃይማኖት ለማጥፋት አልመጣሁም። ሁሉም ሰው እንደየእምነቱ ያድራል። እናንተም ለሰላምና ለእርቅ ስለመጣችሁ በሰላም ወደ ሐረር እስክመጣ ይህንኑ ለሰው ነግራችሁ ከዚያው ቆዩኝ…” ብለው መልክተኞቹን መለሱ። ከመልክተኞቹም ጋር በጅሮንድ አጥናፌ ከተማዋን ለመረከብ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ይዘው እንዲሄዱ አደረጉ። የሻቃ ተክሌን፣ ባላምባራስ ዳምጠውን፣ የሻቃ አድነውን፣ የሻቃ ገበየሁን የከተማውን በሮች እንዲጠብቁ አዘዙ። እነኚህም ታዛዦች እንደታዘዙ ሐረር ከተማ በሰላም ገብተው ፈረስ መጋላ በሚባለው አደባባይና በአምስቱም በር ላይ #የኢትዮጵያን #ሰንደቅ #ዓላማ ሰቀሉ። ሰንደቅ ዓላማውን መስቀል ብቻ ሳይሆን የሐረር ከተማ ሕዝብ እንዳይዘረፍም በየቤቱ በራፍ ዘብ አስቁመው ያስጠብቁ ጀመር።
በዛሬው በጅቡቲ ውስጥ አቦክ ከተማ የነበረው #ታውሪን እ.ኤ.አ. ፌብሩዋሪ 3 ቀን 1887 ወደ ሀገሩ በፃፈው ደብዳቤ
“…ከተማዋ የተያዘችው ሐበሾች ድል ሲያደርጉ እንደሚይዙት ዓይነት አይደለም። ያለምንም ደም መፋሰስና ዝርፊያ ድል አድራጊው የሸዋ ጦር ከከተማዋ ገባ…” ብሏል።
ንጉሥ ምኒልክ አንድ ወር ያህል በሐረር ከቆዩ በኋላ ባላምባራስ መኮንንን ደጃዝማች ብለው ጥር 18 ቀን 1879 ዓ.ም የሐረርጌ የበላይ ገዢና የወታደር ሹም ብለው ሾሟቸው። 3000 ወታደሮችም ሰጧቸው። ለሕዝቡ ግን እንደ ባህሉና እንደ ኃይማኖቱ እንዲያስተዳድሩ የአሚር አብዱላሂን አጎት አሊ አቡበከርን ሾሙ። የካቲት 1 ቀን ወደ ሸዋ ለመመለስ ከሐረር ተነሱ።
ከሐረርጌ ጦርነትም 3000 ጠመንጃ 600,000 ጥይትና 4 መድፎች ማርከው ይዘው መጡ።
ንጉሥ ምኒልክ የካቲት 28 ቀን እንጦጦ ከተማቸው ሲገቡ ከዚያ በፊት ያልታየ አቀባበልና ሰልፍ ታየ። የዚያን ጊዜ የምኒልክን ሰልፍ ድንቅ ያደረገው በሐረር የነበሩ የአሚር አብዱላሂ ግብጻውያን ሙዚቀኞች ስለተማረኩ ከሰልፉ ፊት ቀድመው ሙዚቃ (ማርሽ) በማሰማት ይጓዙ ስለነበር ነው።
ከዚህም ሌላ ከግብጽ የመጡ የኤሮፓ ውሾችንና በየዓይነቱ ቀለም ያላቸውን የርግብ ለማዳዎችን ሌላም አውሬ ሀሉ ይዘው ገቡ። የዚያን ጊዜ ዘፋኞችም…..
“የምኒልክ ነገር ይመስለኛል ተረት
አሞራው በቀፎ ውሻው በሰንሰለት” ብለው ዘፈኑ።

ክብር ለእምዬ ምኒልክ!!!

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!
ሳሚ ዘብሔረ ኢትዮጵያ
Filed in: Amharic