>
5:13 pm - Sunday April 20, 5062

የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት መግለጫ አንድምታው ምንድነው? (ቴዎድሮስ ሀይለማርያም)     

የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት መግለጫ አንድምታው ምንድነው? 

ቴዎድሮስ ሀይለማርያም 
  * የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚመስል መግለጫ ማውጣትስ ዓላማው ምን ይሆን? የተፈጠረው ክስተት  ከአማራ ክልል መንግሥት አቅም በላይ ነው? የራሱን  የውስጥ ጉዳይ  አፈታት ላይ የታየ ዳተኝነት ወይም ሌላ  ቅሬታ አለ? አዎ  ቢባል እንኳን ችግሩን በዘለቄታው  መቅረፍ የሚቻለው በሰላማዊ ውይይትና መተባበር ነው ወይስ በማውገዝና እጅ በመጠምዘዝ????
በእውነት የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ፍላጎት ያንፀባርቃል? ከእስካሁን ሰልፎች  መፈክሮች እንደሚታየው አላማው ኢትዮጵያን ማፍረስ ፣ ኦርቶዶክስ ኃይማኖትን ማውገዝ ፣ አማራን ማንኳሰስ ነው? በዚህ አጋጣሚ “ታሪካዊ በደሎችን” በመበቀል የበላይነታችንን እናረጋግጥ የሚል ጀብደኝነት አጥልቶበታል?
    * “ኦሮሞ እስላም ነው ፣ አማራ ክርስቲያን ነው”  ከሚለው የከፋፋዮችና ዘር አጥፊዎች መርህና ተልእኮ ጋር ልዩነቱ ምንድነው? ወይስ ከአመፅ አበጋዞቹና ኡስታዞቹ አሰላለፍ እንደምናየው  የኦሮሞ ጂሃዲስቶችና ፅንፈኛ ሃይሎች በእስልምና ሽፋን የሚያራምዱት ሴራ ነው?
    * የእምነት አባቶች ከፖለቲከኞች የተሻለ ፍትህ የላቸውም? ከዚህ ቀደም በተለያዩ ክልሎች የሚደረገው የመስጊድ ማቃጠል ድርጊት የኢትዮጵያን ሙስሊሞች አይመለከትም ነበር? በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች ያ ሁሉ መዓት ሲወርድ ይህ ምክር ቤት የት ነበር? ዛሬስ ምን የተለየ ወይም አዲስ ነገር ተገኘ?
   * ለመሆኑስ ፍትህ ነው በቀል የተፈለገው ?  በኦሮሚያ ያሉ ክርስቲያኖችስ ማነው ጠበቃቸው? ዛሬም በእስልምና ስም  ማተብ የሚበጥሱ ፣ “ከኒሳ” የሚያቃጥሉ ፣ ክርስትናን የ”ሚያረክሱ ድርጊቶች በአደባባይ ሲፈፀሙ እንደ ተገቢ በቀል እየተቆጠረ ነው?
   * በኢትዮጵያ ሙስሊሞችና በክርስቲያኖች መካከል ሰላም ያወርዳል? አብሮነትና መተሳሰብ ከአንድ ወገን ብቻ ነው?  በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል ቤተክርስቲያን ከነቀሳውስቱ ሲያቃጥሉ ፣ ክርስቲያኖችን ሲጨፈጭፉ የነበሩ ፅንፈኞች ጉዳይ መች ተፈታ? ነው ወይስ ያ ባለቤት የሌለው የውሻ ደም ነው?
    * “በመላው ሀገሪቱ ያላችሁ ሙስሊሞች ድርጊቱን ስላወገዛችሁ እናመሰግናለን” የሚለውስ ጤናማ ግድፈት ነው? የሞጣውን ድርጊት መላው ኢትዮጵያዊ አላወገዘም?  ወይስ ህዝበ ክርስቲያኑ አያገባውም ወይም ተጠያቂ ነው  ለማለት ይሆን ?
    * በዋነኝነትስ ሀገር አቀፍ ዘመቻው በማን ላይ ነው ያነጣጠረው? በአማራ ክልልና ህዝብ ላይ ነው?  በአማራ  ክልል ያሉ ሙስሊሞች ከሌላው የተለየ ችግር አለባቸው?  ይህ እንዲታይላቸው አቤቱታ አቅርበዋል?   ም/ቤቱ እንዲህ ያለ ክልሉንና ህዝቡን ከማይገልፅ ፣ የአማራ ሙስሊሞችን ከሚንቅ እኩይ  ድምዳሜ ላይ የደረሰው እንዴት ነው?
    * የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚመስል መግለጫ ማውጣትስ ዓላማው ምን ይሆን? የተፈጠረው ክስተት  ከአማራ ክልል መንግሥት አቅም በላይ ነው? የራሱን  የውስጥ ጉዳይ  አፈታት ላይ የታየ ዳተኝነት ወይም ሌላ  ቅሬታ አለ? አዎ  ቢባል እንኳን ችግሩን በዘለቄታው  መቅረፍ የሚቻለው በሰላማዊ ውይይትና መተባበር ነው ወይስ በማውገዝና እጅ በመጠምዘዝ?
    * በቀጥታ ወደ አመፅና ግርግር እርምጃ መግባት የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ያገናዘበ ነው? በቀንደኛ ሙስሊም አክራሪዎች ፣  ዘር ማጥፋት በሚሰብኩ  ግለሰቦችና ቡድኖች የተጠለፈ አካሄድ ሰላም ፈላጊ ነው ወይስ እንደሚታየው የማናለብኝነት መግለጫ ነው? “ከሰልፍ ወደ ሰይፍ” የሚለው መርህ ምን ሊያስከትል ይችላል?
    * ፌዴራል መንግሥቱስ ሚናው ምንድነው? በጠ/ሚ አብይና በኦዲፒ ቁንጮ ባለሥልጣናት ግንባር ቀደምትነት የተጀመረው የውግዘት ድርጊት ለአክራሪ ኦሮሞ  ጂሃዲስቶች ምን አይነት መልእክት አስተላልፏል? እንደ ጥቅምት 12ና 13 ሁሉ ነገስ በተያዘው ደምፍላት ለሚከሰተው አደጋ አብይና ወገኖቻቸው ዳር ቆመው ሊስቁ ነውን?  ከዚህ  ግርግር ማን ሊያተርፍ እንደሚችል ተሰልቷል?
————————
     እነዚህ ጉዳዮች መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በጥሞና የሚመለከታቸው እንደሆኑ አምናለሁ።
      በተለይ የአማራ ህዝብ ጠላት ያጠመደለትን የመከፋፈል ወጥመድ በተለመደ ጥበብና በተፈጥሯዊው የአንድነት መንፈስ  እንደሚወጣው አልጠራጠርም።
መግለጫው ይህን ይመስላል
*****
የአማራ ክልል መስተዳድር የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት በሰጠው መግለጫ ያቀረባቸውን ጥያቄዎች እየመለሰ አይደለም!
 
ረቡዕ ታህሳስ 15/2012 || አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ
 
ድምፃችን ይሰማ
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በሞጣ ከተማ የተፈጸመውን አስነዋሪ የሃይማኖት ጥቃት አስመልክቶ የሰጠው መግለጫ የጉዳዩን አንገብጋቢነት የሚያሳይ እና የክልላዊ መስተዳድሩን አስቸኳይ ትብብር የሚጠይቅ ቢሆንም በክልሉ በኩል ግን ጋዜጠኞች እንዳይገቡ ከመከልከል ያለፈ ተግባር አልተፈጸመም። መጅሊሱ ያቀረባቸው ጥያዌዎች የሚከተሉት ናቸው፦
1) በሞጣ የደረሰውን ችግር ለማጣራት በፌዴራል እስልምና ም/ቤቱ ለተሰየመው አጣሪ ኮሚቴ ክልሉ አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርግ፤
2) ይህን ወንጀል ከመፈጸም በተጨማሪ ከባሕልና ልማዳችን ውጪ በሆነ መንገድ የእምነት ተቋማትን አቃጥለው ፉከራ እና ጭፈራ ሲያሰሙ የነበሩ ግለሰቦችና አካላትን በአስቸኳይ በመያዝ ተገቢውን ፍርድ አንዲያገኙ እንዲያደርግ፤
3) የንብረትም ሆነ ሌላ ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦች እና ድርጅቶች ተገቢው ካሳ እንዲሰጣቸውና በክልሉ መንግሥት ይቅርታ እንዲጠየቁ፤
4) የተቃጠሉ መስጊዶችን በአፋጣኝ በማስገንባት የዘወተር አገልግሎታቸውን እንዲሰጡ እንዲደረግ፤
5) በአጠቃላይ በክልሉ የሚገኙ ሙስሊሞች ያለባቸውን ችግር የሚያጣራ እና የሚፈታ ኮሚቴ በአጭር ጊዜ ተቋቁሞ ወደ ተግባር እንዲገባ፤
ምንም እንኳን ምክር ቤቱ ይህንን ቢጠይቅም የክልኩ መንግስት ግን ጋዜጠኞች ሞጣ ከመድረሳቸው በፊት መታገዳቸው እንዲነገራቸው አድርጓል። ይህም ጥቃቱ የተቀናበረ እና ምናልባትም የመንግስት ኃላፊዎች እጃቸውን ያስገቡበት መሆኑን የሚጠቁም ነው። ክልሉ አሳፋሪው ነውር ተሸፋፍኖ እንዲቀር ለማድረግ የሚያደርገው ጥረት በምንም መልኩ ተቀባይነት የለውም። ከዜጎች ሰብዓዊ መብት ጋርም በብርቱ የሚጣረስ ተግባር ነው። ፍትህ የሚያሳስባቸው ኢትዮጵያውያን ሁሉ ይህንን መስተዳድራዊ ሊቃወሙ ይገባል።
ለእውነት የሚወግንና ለፍትህ የሚተጋ ዜጋን በመፍጠር አገራችንን ወደ ስልጣኔ እናሻግራለን!
አላሁ አክበር!
ጎበዝ ጉድጓዱን አርቀን ባንቆፍረው ይበጃል። የሚገባበት አይታወቅም!!
Filed in: Amharic