>

የኦሮሞ ክልል አመፅ ያስነሳቸው ጥያቄዎችና መፍትሄዎቹ (ያሬድ ጥበቡ)

የኦሮሞ ክልል አመፅ ያስነሳቸው ጥያቄዎችና መፍትሄዎቹ

ያሬድ ጥበቡ 
 
ታላቅ ወንድሜን ለማስታመም ሰሞኑን ቶሮንቶ በመሆኔ ከመረጃ ርቄ ቆይቻለሁ። ዛሬም ከቶሮንቶ ሆስፒታል ክፍል፣ ርዕዮት ሚዲያ ዶክተር መረራ ጉዲና በሰጣቸው አስከፊ አስተያየቶች ላይ ያዘጋጀውን ቅንብር አደመጥኩና፣ ከአራት አመታት በፊት ስለኦሮሞ ወጣቶች ትግል ፅፌው ሳይወጣ ስለቀረው ፅሁፌ አስታወሰኝና ላካፍሳችሁ ወደድኩ። ፅሁፉ ከአራት አመታት በፊት ሳይወጣ የቀረው “አዲስ ቪዥን” ድረገፅ ላይ አብረውኝ ይሠሩ የነበሩ ወጣቶች የኦሮሞ ልሂቃንን ያስከፋል ለትግሉም አይጠቅምም ብለው ስላማከሩኝና የእድሜ ተጋሪዎቼም ተመሳሳይ አመለካከት ስለነበራቸው ነው። አሁን ግን የዱሮ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የክፍል ባልደረባዬ፣ ዶክተር መረራ ጉዲና ከለመድነው “ለዘብተኝነቱ” ርቆ አደገኛ አመለካከቶችን በማራመዱ፣ ላነሳቸው ጉዳዪች ቀጥተኛ መልስ ባይሆንም የኔው ፅሁፍ የተሻሉ አማራጮች የያዘ ስለመሰለኝ ከተቀመጠበት ጨለማ አውጥቼ እንደወረደ ላካፍላችሁ ወድጃለሁ። እስቲ አንብቡት። ጨክነን በመወያየት ይመስለኛል የተሻለ የአስተሳሰብ ማማ ላይ የምንወጣው። ጃዋር በተደጋጋሚ ሰንጋ አርደን ደሙን ግንባራችን ላይ ተቀብተን በአባገዳዎች ፊት ተማምለናል፣ በኦሮሞ ብሄርተኞች መሀል በፊንፊኔ ጉዳይ ላይ የሀሳብ ልዩነት የለንም ይለን የነበረውን ከምር ተቀብለን አናውቅም፣ ሆኖም የመረራን ነገር የመጪው አደጋ አመላካች አድርገን ከልብ ብንቀበል ተገቢ መስሎ ተሰምቶኛል። በመሃላቸው መሠረት የሥራ ክፍፍል አድርገው እንደሚሰሩ መገመት አለብን ብዬ አስባለሁ። ለማንኛውም ፅሁፌን እንካችሁ!
የወያኔ/ኢህአዴግ ቋንቋ ከለል (ዘረኛ) ፖለቲካ የመጨረሻው ጡዘቱ ላይ ደርሶ ባለፉት ሶስት ሳምንታት ያየናቸውን የኦሮሞ ማንነት ጥያቄ አመፅ አስነስቷል ፡፡ አስቸኳይ መነሻ ምክንያቱ በውል የማይታወቀው ይህ አመፅ በክልሉ መንግስትና በፌዴራል ፖሊስ በተተኮሱ ጥይቶች ለብዙ ኢትዮጵያውያኖች ሞት ምክንያት ሆኗል ፡፡ በኦሮሚያ ክልል ብቻ ከሰባ በላይ ዜጎች መሞታቸው በተለያዩ የዜና ምንጮች ተዘግቧል ፡፡ መንግስት ለአመፁ አንዱ ምክንያት ነው የተባለውን የማስተር ፕላን ጉዳይ፣ ያለህዝቡ ፈቃድ ተግባራዊ አይደረግም ሲል ቃሉን ሰጥቷል ፡፡ ኢሳት ቴሌቪዥን ፣ የጨፌ ኦሮሚያ ሸንጎ አባላት በግድያው ማዘናቸውንና የፌዴራል ታጣቂ ሃይሎች ከክልሉ እንዲወጡ መጠየቃቸውን ዘግቧል ፡፡ በአሁኑ ሰአት አመፁ እየረገበ የሄደ ይመስላል ፡፡ ሆኖም በአመፁ ውስጥ የተነሱት ጥያቄዎችና መልስ ያልተገኘለት የመሬቱ ጥያቄ፣ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ባለቤትነት ጋር ተዛማጅ የሆኑት ጉዳዮች፣ የአእምሯችን ጓዳ ውስጥ ልንደብቅ ብንሞክራቸው እንኳ ሳይውል ሳያድር መልሰው የሚኮረኩሩንና የሚኮረኩሙን ጥያቄዎች በመሆናቸው ልንመረምራቸው ይገባል በሚል መንፈስ ነው ብእሬን ማንሳቴ ፡፡
 
የአመጹ መንስኤ ምን ይሆን?
ለአመጹ መነሳሳት ግፊት አድርገዋል ተብሎ የሚታመንባቸውን ምክንያቶች ለማጣራት፣ የሰውም የሚዲያ ምንጮቼን ሳጠያይቅ ያገኘኋቸው ምክንያቶች የተለያዩ ናቸው ፡፡ ከነዚህም መሃል፣
ጊንጪ አካባቢ ያለ ጭልሞ የተሰኘ ጫካ ለልማታዊ ባለሃብት ተሰጥቶ ሥራ ለመጀመር ሲል የጊንጪ ከተማ ወጣቶች በማመፃቸው
የማስተር ፕላኑን ተግባራዊ ለማድረግ ጨፌ ኦሮሚያ እንዲቀበለው እነ አባይ ፀሃዬ ግፊት ስላደረጉ፣ የሸንጎው አባላት የኦ.ኤም.ኤን ቴሌቪዥን ላይ ወጥተው ለህዝቡ ጥሪ በማድረጋቸው
ማስተር ፕላኑን ተግባራዊ ለማድረግ የተቋቋመው ቢሮ ሠራተኞች ለመቅጠር ማስታወቂያ ማውጣቱ
ኦሮሞ ፈርስት (ቀዳማይ ማንነቴ – ኦሮሞነቴ) የተሰኘው በወጣት ጃዋር መሃመድ የሚመራው ንቅናቄ ዝግጅቱን ጨርሶ ለአመፅ ጊዜው አሁን ነው ብሎ ስላመነ፣ የሚሉና ሌሎችም ምክንያቶች ሲቀርቡ ሰንብቷል ፡፡
እሳት በሌለበት ጭስ የለምና፣ ወደፊት የተጣራውን ምክንያት እስክናውቅ ድረስ፣ ከላይ የተጠቀሱት ምክንያቶች ሁሉ በተለያየ ደረጃ ለአመጹ አስተዋፅኦ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ገምተን ውይይታችንን እንቀጥል ፡፡ አንድ በግልጽ የሚታየው ሃቅ፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ተብለው የሚታወቁት ነባርና አዲስ ድርጅቶችም ሆኑ ሃገር ቤት በህጋዊነት የሚንቀሳቀሱት የኦሮሞ ድርጅቶች፣ ስለአመፁ ዝግጅትም ሆነ እውቀት እንዳልነበራቸው ነው ፡፡ እንደ ሁላችንም ድንገቴ ነው የሆነባቸው ፡፡
 
የማንነት ጥያቄው አመጣጥ፤
ወያኔ/ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ ባለፉት 25 አመታት ዋነኛ ጠላቴ ነው ብሎ የፈረጀውን የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ለመደቆስ ከተጠቀመባቸው ስልቶች አንዱ የኦሮሞ ብሄርተኝነትን ተገዳዳሪ ሃይል ሆኖ እንዲጠናከር በማድረግና፣ የኢትዮጵያን ብሄርተኝነት የነፍጠኛ ግፍና የአማራ ትምክህት መሳሪያ አድርጎ በመሳል በመንግስት ሚዲያም ሆነ በትምህርት ሥርአቱ ይህ አመለካከት እንዲተባና እንዲጠናከር ማድረጉ ነው ፡፡ በውጤቱም፣ 65 በመቶ የሆነው የሃገሪቱ ህዝብ ወጣት በመሆኑ፣ በአሁን ሰአት በኦሮሚያም ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ክልሎች ከፍተኛ የሆነ የዘረኝነት መንፈስ እንዲሰርፅ ተደርጓል ፡፡ በደቡብ ክልልም ቢሆን የአካባቢውን ሰው የማይመስል ኢትዮጵያዊ ዜጋ በየጊዜው ይዘረፋል፣ ይፈናቀላል፣ ይገደላል ፡፡ መንግስት ተብዬውም “ጎሽ፣ ይበሏቸው!” በሚል ስሜት የአፈናቃዮቹና ብሄርኞቹ ወገን በመሆን በግዴለሽነት እጁን አጣጥፎ ይመለከታል ፡፡
ወያኔ/ኢህአዴግ በተለይ በምርጫ 97 በዝረራ በተሸነፈ ማግስት፣ በአማሮች፣ ጉራጌዎችና ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ላይ በጀመረው ዘመቻ አንዲተባበሩት በኦነግነት ተጠርጥረው በእስር ታጉረው የነበሩ ኦሮሞዎችን ነጻ በመልቀቅና፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችና የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ኦህዴድን ተቀላቅለው ክልሉን እንዲረከቡ በማደረጉ፣ ዛሬ ጦዞ ለሚገኘው የኦሮሞ የማንነት ጥያቄ የድርሻውን አስተዋፅኦ አድርጓል ፡፡ በተጨማሪም፣ በህገመንግስቱ ውስጥ የወሸቀውን የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም የተባለ መርዝ ብልቃጥ በመክፈት፣ ኦህዴድ ከአዳማ ፅህፈት ቤቶቹን ወደ አዲስ አበባ እንዲለውጥ በመጠየቅ ፣ የኦሮሞ ብሄርተኝነት በአዲስ አበባና አካባቢው ላይ ያለው የባለቤትነት ጥያቄ እንዲጠናከር አድርጓል ፡፡
ሆኖም አገዛዙ ከምርጫ 97 ውድቀቱ አንዱ የተማረው ትምህርት፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ልሂቃን መክተሚያ የሆኑትን ከተሞች እድገት ንቆ መተው ለስልጣኑ አለመረጋጋት አስተዋፅኦ ማድረጉን በመገምገም፣ ፊቱን ወደ ከተሞች ልማት መመለሱና፣ ይህም ልማት እርሱን በሚደግፉ ልማታዊ ባለሃብቶች ብቻ እንዲደረግ በመወሰኑና፣ ይህም ለትግራይ ኤሊት ሃብት የማካበት እድል መፍጠሩ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ያሉትን መሬቶች ወደመቀራመት በመሸጋገሩ፣ ለአመታት አይዞህ ሲለው ከከረመው የኦሮሞ ብሄርተኝነት ጋር እንዲላተም ሊያደርገው ችሏል ፡፡ ዘረኝነትና ሙስና ተባብረው የጥያቄውን ባህርይ ባያስቱት ኖሮ፣ ይህ የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ተይዞ መፍትሄ ማግኘት በቻለ፣  ለብዙ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችም ሞት ምክንያት ባልሆነ ነበር ፡፡ ሆኖም አገዛዙም ሆነ በአሁን ሰአት ተቃርኖ የቆመው የኦሮሞ ብሄርተኝነት፣ ችግሩን የመሬት ባለቤትነት ችግር አድርገው ለመቀበል ፈቃደኛ አይደሉም ፡፡
የወጣቶቹ ጥያቄዎች ምን ይሆኑ?
የሱሉልታ፣ የአምቦ፣ የአመያ ወዘተ ወጣቶች ልማትና የኢንዱስትሪ እድገት የሚገፉትን ዘመናዊነት አምቢ ይላሉ ብሎ መገመት የዋህነት ይመስለኛል ፡፡ የአዲስ አበባንም መስፋፋትና በዙሪያው ያሉትን ትናንሽ ከተሞች እያቀፈና አስፈላጊም ሲሆን እየዋጠ መሄድ የሚቃወሙበት ምክንያት አይታየኝም ፡፡ ጥያቄያቸው ሊሆን የሚችለው የልማቱና ኢንደስትሪ ግንባታው ተጠቃሚ እንሁን ነው ፡፡ ባለሃብቱ መሬታችንን ከፈለገ፣ ገበያው በሚፈቅደው ዋጋ፣ ራሳችንም በገበያው ዋጋ ለመሸጥ ባለን ፍላጎት ይወሰን ነው ፡፡ ለምሳሌ ሱሉልታ ላይ ያለን ሩብ ጋሻ መሬት አንድ አበባ አምራች የደች ተወላጅ ሊከራይ ከፈለገና፣ የገበያው ዋጋ አምስት ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ከሆነ፣ ያ አምስት ሚሊዮን ብር የመንግስት ባለስልጣናትና ደላሎቻቸው ኪስ የሚገባ ሳይሆን፣ መንግስት የሚገባውን ታክስ ቀርጦ (20ም ይሁን 25 በመቶ) የቀረው ያ የኦሮሞ ቤተሰብ ኑሮውን በፈለገበት መስክ ለማቋቋም የሚጠቀምበት ሃብት ይሁን ነው ፡፡ አዲስ አበባ ገብቶ ለመኖርም ሆነ፣ መሬት ርካሽ የሆነበት ገጠር ባገኘው ገንዘብ ዘመናዊ እርሻ ለማቆም፣ የመሬት ባለሃብት የሆነው ገበሬ ውሳኔ ይሁን የሚል ነው ፡፡ የወጣቶቹ ጥያቄ እዚህ ብስለት ላይ ዛሬ ያልደረሰ ቢሆን እንኳ፣ በጣም በቅርቡ የመሬት ባለቤትነትን ጥያቄ በማያወላዳ መንገድ ማቅረቡ የማይቀር ነው ፡፡ ዛሬ የተጣለበትን የብሄርተኝነት ማነቆና እገዳ እምቢ ማለት እንደሚችል ከወዲሁ ማየት ይቻላል ብዬ መሟገት እወዳለሁ ፡፡ ዋናው ጥያቄ፣ ይህ የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ ሲነሳ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ምላሽ ይኖረዋል ወይ ነው ፡፡
የመሬት ባለቤትነት ጥያቄና የኦሮሞ ብሄርተኝነት!!!
ሁሉም አይነት የኦሮሞ ብሄርተኞች፣ ከመረራ ጉዲና እስከ ጃዋር መሃመድ፣ ከቡልቻ ደመቅሳ እስከ ዮሐንስ ለታ የሚስማሙበትና ከወያኔ ጋርም አንድ የሚያደርጋቸው ጉዳይ ቢኖር የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ ነው ፡፡ ሁሉም እጅግ አሳፋሪ በሆነ የህዝብ ንቀት፣ ገበሬው የመሬቱ ባለቤት ከሆነ መሬቱን ለአማሮች ቸብችቦ አረቄ/ቁንዱፍቱ ይጠጣበትና ደህይቶ ዘበኝነተ ወይም ቀን ሰራተኝነት ይወርዳል ይላሉ ፡፡ መፍትሄውም እነርሱ በሚመሩት መንግስት የበላይ ጠባቂነት፣ ገበሬውን እንደ ህፃን ልጅ እሹሩሩ እያሉ ማቆየት ነው ፡፡ የዚህ ፖሊሲ ውጤት ግን ባለፉት 25 አመታት በተግባር ሲውል ምን እንደሚመስል እንደምናየው፣ ገበሬውን በሃገሩ ላይ የበይ ተመልካች አድርጎ ደላሎችና ሸሪኮቻቸው የሆኑት የመንግስት ባለስልጣናት እንደልባቸው የሚቀራመቱት ከገባርነት ያልተላቀቀ ድሃ ማህበረሰብ መገንባት ነው ፡፡ ገበሬው የመሬቱ ባለቤት አለመሆን በሚየሽቆጠቁጡት ካድሬዎች ሥር በአሽከርነት የሚገዛና ፈሪ፣ ለዜግነት ልቦናና ድፍረት የሌለው ከሚያርሳቸው በሬዎች ያልተሻለ ከብት የሚያደርገው መንገድ ነው ፡፡ “እኛ ቋንቋውን ስለምንነጋገር ከወያኔ የተሻለ እናስተዳድረዋለን” የሚለውን ቡፋ፣ ሩቅ ሳንሄድ የትግራይን ገባሮች በመጠየቅ መልሱን ማግኘት እንችል ይመስለኛል፤ ወይም ከአስመራ ወጣ ብሎ ገባሩን ማነጋገር ነው ፡፡ ስለሆነም በቅንነት የሚነሳ ስጋት ፈፅሞ ሊሆን አይችልም ፡፡ የኦሮሞ ገበሬ የመንግስት ገባርነት እንዲያከትምና፣ የመሬቱ ባለቤት ሆኖ፣ ዛሬ ፎቅ በሚደረድሩ መንግስታዊ ነቀዞችና ደላሎቻቸው ኪስ የሚገባው ገንዘብ ተጠቃሚ እንዲሆን መወሰን፣ ከኦሮሞ ብሄርተኞች የምንጠብቀው ውሳኔ ነው ፡፡ ይህም ሲሆን፣ ከብሄርተኛ አጥሮች በዘለለ ትግሉን ለማስተባበርና ውጤታማ ለማድረግ ይቻላል ፡፡
በኦሮሚያ ክልል አነስተኛ ከተሞች ሁሉ ተቃውሞው የተስፋፋ እንደነበር ግልጽ ቢሆንም፣ የሰሞኑ የደቡብና ደቡብ ምእራብ ሸዋ አመፆች ስለ ሸዋ፣ አዲሰ አበባና የማንነት ጥያቄዎችን እንድናሰላስል ግን ያስገድዱን ይመስለኛል ፡፡
ሸዋ በእኔ እይታ
የዘመናዊት ኢትዮጵያ መሠረት ሸዋ ነው ፡፡ ምንሊክ ከቴዎድሮስ እስር አምልጦ ሲመጣ ወሎ ላይ በመንገድ የሸኙትም ሆኑ ሸዋ ላይ ተቀብለው ታላቁን የሸዋ ጦር የገነቡት ኦሮሞዎች ናቸው ፡፡ የኦሮሞ ብሄርተኝነት በጠላትነት የፈረጃቸው ራስ ጎበና ዳጬ፣ ፊታውራሪ ሐብተጊዮርጊስ ዲነግዴ፣ ራስ ባልቻ ሳፎና የሌሎችም ቁጥራቸው ተቆጥሮ የማያልቅ ኩሩ ኢትዮጵያውያን ጦር ነው ምንሊክን ተንከባክቦ፣ የዘመናዊት ኢትዮጵያን ምሶሶና ማገር ያቆመው ፡፡ እነዚህ ኩሩ ኢትዮጵያውያን ኦሮሞዎች አድዋ የሚገኘው እንዳ ማርያም ሸዊቶ ተሬ ድረስ ጋልበው በጀግንነት ተሰውተዋል ፡፡ ለኢትዮጵያ ሲሉ!
ከአድዋም በሁዋላ በማይጨው ዘመቻ ወቅትም ሆነ የጣሊያን ፋሺዝም አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ፣ ትልቁን የሽምቅ ውጊያ ያቀናጁትና የመሩት ታላላቅ ኢትዮጵያውያን ኦሮሞዎች ነበሩ ፡፡ በአዲስ አበባ ዙሪያ በሆለታ፣ በአድአ በርጋ፣ በእንጪኒ፣ በጉደር፣ በአመያ፣ በወሊሶ፣ በሞጆና አቃቂ ወዘተ የሰሞኑ አመፅ በተዛመተባቸው የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ዙሪያ ባሉ ገጠሮች ሁሉ፣ ኢትዮጵያውያን ኦሮሞዎች በታላቅ ወኔ ታግለዋል፡፡ አበበ አረጋይ፣ ገረሱ ዱኪ፣ ከበደ ብዙነሽ፣ ጃጋማ ኬሎ ወዘተ ስማቸው ተቆጥሮ የማያልቅ ጅግኖች ኢትዮጵያ ወይም ሞት! ፈክረው ለነፃነቷ ተዋድቀዋል ፡፡ ይህን የጀግኖች ታሪክ ነው የኦሮሞ ብሄርተኞች የነፍጠኛ ታሪክ ብለው ሲያንቋሽሹት የኖሩት ፡፡ ዛሬ ለኢትዮጵያውያን ኦሮሞዎች መታሰቢያ ይቁምላቸው ሲሉ፣ እኛም አዎን ይቁምላቸው እንላለን ፡፡ ምኒሊክ ሀውልት  ፊትለፊት ለጎበና ዳጨ ሃውልት ይቁምለት፣ እንጦጦ አናት ላይ ለአቢቹ (ትንሹ ልጅ) በነጭ ክብር ድንጋይ የተሰራና፣ ከምንሊክ አደባባይ የሚታይ ግዙፍ ሃውልት ይቁምለት፣ በደስታ ፡፡ የአቢቹን ውለታ ለማስታወስ፣ የፓርለሳክን የሃበሻ ጀብዱን ማንበብ ነው ፡፡ አዲስ አበባ ላይም ብቻ ሳይሆን፣ ታሪክ ፀሃፊዎች እንደዘገቡት “መሣሪያህን ጥለህ ካልሮጥክ፣ መስለብ የሚቀናው የኦሮሞ ፈረሰኛ አሳዶ ይጎምድልሃል“ ተብሎ ለተነገረላቸው ታላቅ የኦሮሞ ፈረሰኞች ከብዘትና እንትጮ የሚታይ ሽምጥ የሚጋልቡ የኦሮሞ ፈረሰኞች ምስል የአድዋ ሶሎዳ ተራራ ላይ ቢጠረብ ለጀግንነታቸው አያንሳቸውም ባይ ነን ፡፡ በሽሽት ላይ በነበሩ ሰአሊ የጣሊያን ወታደሮች በወቅቱ የተሳሉ ስእሎች በአውሮፓ ቤተመዘክራት ውስጥ ስለሚገኙ፣ የሃውልቱ ንድፍ በእጃችን ያለ ነው ፡፡
ያለ ኦሮሞ ፈረሰኛ የአድዋ ድል
 የማይታሰብ ነው!!!
በወቅቱ የዮሃንስ ዘውድ ሸዋ በመውረዱ፣ የአክሱም፣ ሽሬ፣  አድዋ ኤሊት ኩርፊያ ላይ ነበር ፡፡ በዚህ ላይ ጄኔራል ዲቦኖ በአውሮፕላን በትግርኛ የሚረጨው ፕሮፓጋንዳ ይህንኑ ቅሬታ የሚያባብስ ነበር ፡፡ በፓርለሳክ “የሃበሻ ጀብዱ” ላይ ከአውሮፕላን ስለሚረጨው የፋሺስት ፕሮፓጋንዳ ያነበብኩትንና፣ በፀረ ደርግ የሽምቅ ውጊያ አመታት፣ ትግራይ ውስጥ በጆሮዬ የሰማሁት በህወሐት ይተላለፍ የነበረውን ጠባብ ብሄርተኛ ቅስቀሳ ሳመዛዝን፣ ምን ያህል የጣሊያን ፋሺስት ፕሮፓጋንዳ የትግራይ ብሄርተኝነትን አስተሳሰብ መርዞት እንደነበር ፍንጭ ይሰጥ ይመስለኛል ፡፡ ስለሆነም፣ አንፀባራቂውንና በታላቁ ታሪክ ፀሃፊ እምነት “የአፍሪካን ቀለም ጥቁር ሆኖ መቆየት የወሰነው ታላቁ ታሪካዊ ክንዋኔ (world historical event)“ ብሎ የመሰከረለት የአድዋ ጦርነት፣ ያለ ኦሮሞ ፈረሰኞች ጀግንነት የማይታሰብ ነበር ፡፡ የኦሮሞ ብሄርተኞች ይህንን አኩሪ ታሪክ ሳይቀበሉ በፊንፊኔ ለኦሮሞዎች መታሰቢያ ይሠራላቸው ማለታቸው ትርጉም አይኖረውም ፡፡ ከታሪካቸው ጋር መታረቅ ይኖርባቸዋል ፡፡ ባለፉት አርባ አመታት ምናልባት አዲሱን የኦሮሞ ብሄርተኝነት ለመከትኮት ከታሪካዊት ኢትዮጵያ የሚያስተሳስረውን እትብት ሁሉ መቆራረጥ አስፈላጊ ሆኖ አግኝተውት ሊሆን ይችላል ፡፡ ሆኖም፣ በኦሮሞ ብሄርተኞች ውትወታም ሆነ፣ በመላ ኢትዮጵያ ተራማጆች መስዋእትነት ዛሬ የኦሮሞ ህዝብ ቁመና በኢትዮጵያ ውስጥም ብቻ ሳይሆን፣ በአለም የፖለቲካ ተዋስያን ዘንድ ከሩቅ የሚታይ ሆኗል ፡፡ ብሄርተኝነቱን ለመኮትኮት የታመነባቸው የፈጠራ፣ የሃሰትና የጥላቻ ታሪኮች መቀየር ይኖርባቸዋል ፡፡ ዛሬ ከሩቅ ለሚታየው ለታላቁ ኦሮሞ ህዝብ ቁመና የሚመጥኑ አይደሉም ፡፡ ድንክዬ ነው ፡፡ በውሸትና ጥላቻም ላይ ስለተመሠረተ ውሎ አድሮ ይፈርሳል ፡፡ በህብረትም የጨለማውን ቀን ለማሳጠር እንዳይቻል፣ የመተማመኛ መሠረቱን የሚንድ ነው ፡፡
ስለሰሞኑ የምእራብና ደቡብ ምእራብ ሸዋ አመጾች ሊካድ የማይችለው ሃቅ፣ ትናንት የምንሊክን ሃውልት ለማፍረስ ኦህዴድና ሌሎች ጠባብ ብሄርተኞች ሲያሴሩ፣ “በሬሳችን ላይ ተረማምዳችሁ ካልሆነ በቀር አትነኩትም” ያሉት በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ የኦሮሞ ፈረሰኞች ናቸው ፡፡
በታሪክ ፀሃፊዎቻችን ድክመትም ሆነ፣ በመንግስት አትድረሱብኝ ባይነት የተጠና አሃዝ ባይኖረንም፣ በኢትዮጵያ  ሠራዊት ውስጥ የኦሮሞዎች ቁጥር ያመዝን እንደነበርና፣ ከነዚህም የሠራዊት አባላት ለአዲስ አበባ ባለውም ቅርበት ሆነ፣ የፀረ ፋሽስት ትግሉ በውስጣቸው ባሳደረው የኢትዮጵያዊነት ወኔ የተነሳ፣ የሸዋ ኦሮሞዎች ቁጥር ከፍተኛ ድርሻ እንደነበረው ልቦናችን ያውቀዋል ፡፡ ቀጥ ብለው በተተኮሱ የክብር ዘበኛ ዩኒፎርም የኮሩ ወታደሮች ወደጦር ሠፈራቸው በእግራቸው ሲጓዙ፣ ከ50 አመታት በፊት፣ የተፈሪ መኮንን ተማሪዎች የነበርን ወጣቶች እርምጃችንን ከነርሱ ጋር ለመመጠን ኋላኋላቸው ኩስኩስ እያልን ስንሮጥ፣ ሰንቶቹ ኦሮሞዎች እንደነበሩ ልቦናችን ያውቀዋል ፡፡ በደርጉ ዘመንማ የመካከለኛውንና የከፍተኛውን መኮንነት ማእረግ የያዙት ኦሮሞዎች ብዛት፣ ሁሌም የሚገርመን ጉዳይ ነበር ፡፡ የነዚህም ወታደሮች ቤተሰቦች ናቸው፣ ወያኔ አሸንፎ ከገባ በኋላ እንኳ፣ እንደ አምቦና ጀልዱ በመሳሰሉት ከተሞችና ገጠሮች በድንገተኛ የሽምቅ አደጋ፣ ተጋዳላዩን ያስጨንቁት የነበረው ፡፡ ስለሆነም፣ ስለ አድዋና ማይጨው በይበልጥም ስለ አምስቱ አመት የአርበኝነት ተጋድሎ ሲወሳ፣ የሸዋ ኦሮሞዎች ዋነኛውን ቦታ ይዘው ይገኛሉ ፡፡ ለዚህም ነው የዚህ ህዝብ ቀዳሚ ማንነት ኢትዮጵያዊነቱ ነው ብዬ መከራከር የምፈልገው ፡፡
ይህን ክርክር ሳነሳ ግን፣ በመንግስት የትምህርት ፖሊሲም ሆነ፣ በኦህዴድ ሚዲያ ናዳ፣ ብሎም እንደ ኦሮሚያ ፈርስት በመሰሉ አክራሪ ንቅናቄዎች በሚደረጉ ሰርጎ ገብ ሥራዎች ይህ በታሪክ የቆየ የሸዋ ኦሮሞዎች ቀዳሚ ኢትዮጵያዊ ማንነት በወጣቱ ዘንድ አልተሸራረፈም አልልም ፡፡ ከአቅሙ በላይ በሆኑ ሐይሎች ነው የጥላቻ ናዳ የሚወርድበት ፡፡ ከኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ጋር የሚያቆራኘው አንዱ ጠንካራ ሐረግ፣ የተዋህዶ ኦርቶዶክስ እምነት በመሆኑ፣ ይህን ሐረግ ለመበጣጠስ “ወደ አባቶችህ ሐይማኖት ተመለስ፣ ተዋህዶ የነፍጠኛ ሐይማኖት ነው፣ ያንተ ፈጣሪ ዋቃ ነው“ በሚል፣ የአባቶቹን እምነት እንዲተው ከፍተኛ ውዥንብር ተነዝቶበታል ፡፡ ከጥምቀት በአልና ቁልቢ ገብርኤል ይልቅ የኢሬቻን በአል በናፍቆት እንዲጠብቅ ተደርጓል ፡፡ ይህ ሁሉ ሲደረግ፣ በወያኔ የተያዘው ቤተክህነትና ሲኖዶሱ በተባባሪነት ቆመዋል ፡፡ በውጤቱም በተለይ በሆሮ ጉድሩ የተዋህዶ አብያተ ክርስትያናት መዘጋትን አስከትሏል ፡፡ ይህ ተግባር ከጠባብ ብሄርተኝነት ጋር መቆላለፉን የምናውቀው፣ የ”ሐይማኖትህን ቀይር” ዘመቻ ያነጣጠረው ሙስሊሙ ላይ ሳይሆን፣ ተዋህዶው፣ በተለይም የሸዋው ላይ በመሆኑ ነው ፡፡ ምክንያቱም በጠባብ ብሄርተኞች እምነት ሙስሊምነትና ኦሮሞነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅ ነው ብለው ስለሚያምኑ ነው ፡፡
የሰሞኑ አመፅ የት ይደርሳል?
እንደ ሁሉም ግብታዊ የህዝብ አመጾች፣ የዚህ ሰሞኑም የኦሮሚያ ክልል ህዝብ ትግል በመንግስት ሃይሎች አሸናፊነት መጠናቀቁ አይቀሬ ነው ፡፡ ለሽንፈቱም ምክንያት ከሚሆኑት ጉዳዮች መሃል፣ በቂ አመራርና ድርጅት የሌለው መሆኑ ዋነኛው ይመስለኛል ፡፡ ሌላው ወሳኝ ጉዳይ ግን ሌሎች ኢትዮጵያውያን ሊተጋገዙበት የሚያስችል የጋራ አላማ የሌለው መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል ፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት ዋነኛው ጥያቄ የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ ሆኖ ሳለ፣ ጠባብ የሆነው የኦሮሞ ብሄርተኞች ፍላጎት ግን፣ የጥያቄው ድንበር ዘለል ባህርይ እንዲሰለብ አስገድዶታል ፡፡ ተራ የማንነት ጥያቄ ሆኖ ወያኔ እንዲያጨማልቀው ተትቶለታል ፡፡ ይሄ ስህተት ይመስለኛል ፡፡ እንዲህ አምርሬ መናገሬ ያለምክንያት አይደለም ፡፡ አመፁ ከመሬት ባለቤትነት ጋር በግልፅ ተቆላልፎ ቀርቦ ቢሆን ኖሮ፣ በየዕለቱ በወያኔ መሬቱን የሚነቀለውና ወደከተማው ዳርቻ የሚወረወረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ነዋሪ በቀላሉ ትግሉን ለመቀላቀል በቻለ ነበር ፡፡ ከአዲስ አበባም አልፎ ተመሳሳይ ብካይ በሚካሄድባቸው የመሬት ቅርምት በገነነባቸው የኢትዮጵያችን ክፍሎች ሁሉ ጥያቄው እንደ ቋያ እሳት በተቀጣጠለ ነበር ፡፡ ይህ እንዳይሆን ትልቁ ጋሬጣ ሆኖ የተገኘው ኢትዮጵያን ተቀብሎ ከኦሮሞ ህዝብ ቁመና ጋር የሚመጥን ሚና መጫወት ያልቻለው የሁሉም አይነት የኦሮሞ ብሄርተኝነት አስተሳሰብ ነው ፡፡
ከእንግዲህ ወዴት?
ምኞቴ ባይሆንም የሰሞኑ አመፅ በወያኔ አሸናፊነት እንደሚጠናቀቅ ተንብያለሁ ወይም አሟርቻለሁ ፡፡ ሆኖም ለአመፁ መዳከም ምክንያት የሆኑትን ጉዳዮች ከመቀበል ይልቅ፣ በሶስተኛው ሳምንት ላይ የኦሮሞ ድርጅቶች ሌላውን ኢትዮጵያዊ ወደማስጠንቀቅ ሲሸጋገሩ ይታያል ፡፡ የህዝቡን ግብታዊ እንቅስቃሴ ከማንነት ጋር አቆላለፈው እንዳሽመደመዱት ሁሉ፣ ውድቀቱንም ለጠባብ ብሄርተኛ አላማቸው ብካይ ሊያደርጉት ይከጅላሉ ፡፡ በአንድም ሆነ በሌላ ቋንቋ ይሄ አመፅ ቢከሽፍ ሌሎቻችሁ ልትተባበሩን ፈቃደኛ ስላልነበራችሁ ነው ወደሚል ክስ ሲወርዱ ይስተዋላል ፡፡ ሆኖም ወሳኙ ድክመት ትግሉ ሁሉን አቀፍ ባህርይ እንዲያዝ በመፈክር አቀራረፅና በአመራር ፣ ክልል ዘለል አስተሳሰብ ይዞ ለመገኘት ካለመቻል የሚመነጭ መሆኑን ተቀብለው ለማይቀሩት ቀጣይ ፍልሚያዎች ራሳቸውን ወደማዘጋጀቱ ቢሸጋገሩ ተመራጭ ይመስለኛል ፡፡ የኦሮሞ ብሄርተኞች ምንድን ነው ወደኋላ የሚያሰኛቸው? ለምንድን ነው ደፍረው ኢትዮጵያዊነታቸውን ማቀፍ የማይችሉት? በሃይማኖቱ ከጴንጤዎችም ይበልጥ አክራሪ የሆነውን ዘርፍ የሚከተል፣ በብሄረሰቡም ወላይታ የሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ማንነቱ ፈፅሞ ለጥያቄ በማይቀርብበት ሃገር፤ ከደጉ ኦሮሞ ህዝብ የወጡ  ምሁራን የሚያሳዩት ኢትዮጵያን እንደ እንጀራ እናት የማየት አስተሳሰብ ከአእምሯቸው ሊፍቁት ይገባል ፡፡
ምን ይሻላል?
የሸዋ አማርኛና አፋን ኦሮሞ ተናጋሪዎች ቀዳሚ ማንነታችን ኢትዮጵያዊነት ነው ። ተጋብተናል፣ ተዋልደናል፣ በአመዛኙ የአንድ ታሪካዊት ተዋህዶ ክርስትና እምነት ተከታዮች  ነን ። ታሪካዊት ኢትዮጵያን በዘመናዊ መልኩ ለማቆየት ወደር የሌለው መስዋእትነት ከፍለናል ። በሺህ የሚቆጠሩ ወላጆቻችን ከራስ ካሳር እስከ ሞያሌ ከጋምቤላ እስከ ቆራሄ በየጦር ሜዳው ወድቀዋል ። ይህን የመስዋአትነት ታሪክ በአዲስ ብሄርተኞች እምነትና አዲስ ማንነት ተገዢ እንድናደርግ ልንጠየቅ አይገባም ። በታሪክ የቆየ ውስጣዊ የብሄረሰቦች ወሰን (internally differentiated historical borders) በሌለበት ሀገር በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ክልል ለዘላቂ ሰላምና አብሮ መኖር አይመችም ። አሁን ሸዋ ላይ አማራ የት ጋ አልቆ ኦሮሞ የተ ጋ ይጀምራል? ቀዳሚ ማንነታችን ኢትዮጵያዊ የሆንነው የሁለቱ ቋንቋ ተናጋሪ ህዝቦች፣ ሊያስማማን የሚችለው ሰፋ ባለ የመካከለኛ ኢትዮጵያ አስተዳደር መጠቃለል ነው ። የአስተዳደር ዩኒቱም ክልል ይሁን ከተባለ፣ ከቁመናችን ጋር የሚመጥነው፣ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ነው ።
ሁሌም የኦሮሞ ጥያቄ ዋና ችግር የሸዋ ችግር ነው ። ሸዋ ላይ መተላለቅ ሳይፈጠር ነፃ የሚወጣ ኦሮሚያ ከቶ ሊኖር አይችልም ። ጎጃሙ ጎጃሜ፣ ጎንደሩ ጎንደሬ መሆን ሲችል ሸዌው ግን አማራም ሆነ ኦሮሞ መሆን ከቶ አይቻለውም ። ሸዌ ኦሮሞኛም ተናገረ አማርኛ ቀዳሚ ማንነቱ ኢትዮጵያዊ ነው ። አንዱን ወይም ሌላውን መምረጥ መገደድ የለበትም ። ለአማርኛ ተናጋሪው ሸዌ ከወሎዬው ይልቅ የጀልዱ ኦሮሞው ቅርቡ ነው ። ለአዳማ ኦሮሞውም ከባሌ ኦሮሞው ይልቅ የሸንኮራ አማራው የአክስቱ ልጅ ነው ። ይህን ሃቅ የወያኔ ብልጠትና መርዝም ሆነ፣  የኦሮሞ ብሄርተኞች አዲስ ህልም አይገድለውም ።
ወያኔ ካደረገው እኩይ ተግባሮች መሃል እጅግ አደገኛው፣ የኦሮሞ ብሄርተኝነትን ከኢትዮጵያዊነት ጋር የሚገዳደር ሃይል እንዲሆን ያደረገው ራስወዳድነት ነው ። ሥልጣኑን ለማቆየት የዘራው ክፉ መርዝ ። በአቦይ ስብሃት ቀማሚነት መለስ የኢትዮጵያ ህገመንግስት ውስጥ የሰነቀረው ” ኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለው ልዩ ጥቅም” የሚል ሃረግ፣ ከሃገራዊ ርእይ የመነጨ ሳይሆን ከተመሠረተtበት ቤዝ ብዙ መቶ ኪሎሜትሮች ርቆ ለመጣው የወያኔ ጉጅሌ፣ በውስጡ የሚበርደውን የፀጉረ ልውጥነትና ባእድነት ቆፈን ለማስታገስና፣ የሥልጣን መጨበጫና ማቆያ እኩይ ስልት ነው ። የታላቁን ኦሮሞ ህዝብ ፍላጎት እናውቃለን የሚሉትም ብሄርተኞች ይህን በክፋት የተጠቀለለ መርዝ መድሃኒት ነው ብለው መዋጥ የለባቸውም ። መፍትሄ ከቶ ሊሆን አይችልም ። እውነተኛው መፍትሄ፣ በመሬት ላይ ያለውን እውነታ ያገናዘበ ብቻ ሲሆን ነው ።  አንድ ቋንቋ የሚናገር ህዝብ ሁሉ በአንድ ወሰን ይከለል የሚል የታሪክም፣ የህግም፣ የፖለቲካ ሳይንስም ፍልስፍና የለም ። ኦርቶዶክሱም፣ ሙስሊሙም፣ አድቬንቲስቱም በአንድ ክልል እንዲጠቃለሉ የሚያሰገድደው፣ በተማሪ አንደበት የተቀረፀ አይዲዮሎጂካል ሆምላንድና፣ በማይሆን መፍትሄ የኦሮሞ ብሄርተኞችን ልብ በማማለል፣ በጠላትነት የፈረጀውን የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ለመደቆስና አናቱን ለመተርተር ወያኔ የተጠቀመበት ሽብልቅ ነው ፡፡ መልሳችንም ሊሆን የሚገባው፣ በመሬቴ ላይ የመንግስት ነቀዞች ጭሰኛ አልሆንም ፣ ቀዳሚ ማንነቴ ኢትዮጵያዊነቴ ብለን መዘመር ነው ።
Filed in: Amharic