>

የአባቱ ልጅ….መድረክ አድማቂው ሽመልስ አበራ ጆሮ!!! (ዳዊት ንጉሡ ረታ)

የአባቱ ልጅ….መድረክ አድማቂው ሽመልስ አበራ ጆሮ!!!

ዳዊት ንጉሡ ረታ
አበራ ደስታን (አበራ ጆሮ) ተጋንኖ ስለሚወራለት የመድረክ ላይ ትወናው ወቅቱ ላይ ደርሼ በዓይን ዕይታ ላጣጥመው ባልችልም ሲደነግጥና ሲናደድ ጆሮውን ቀጥ አድርጎ የማቆም ችሎታው፣ ገፀ-ባህሪን ከውስጡ የመላበስ ብቃቱ፣ ኩምክናውና ሁሉም ስለእርሱ የሚነገሩ ነገሮች ልክ ያኔ በመድረክ ላይ ያየሁትን ያህል መስሎ እንዲሰማኝ አድርጎአል፡፡
በ1980ዎቹ አጋማሽ የአባቱ ልጅ ብዬ የሰየምኩት ሽመልስ አበራ ጆሮ፤ በ “ህሊና ዕዳ” ተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማ ወደ ኪነ-ጥበቡ ዓለም በስፋት ከህዝቡ ጋር ሲቀላቀል ሁላችንም የጥበቡ አድናቂዎች ከዓይን ያውጣህ፣ ለትልቅ ደረጃ ያድርስህ ብለን መርቀነው ነበር፡፡
ዛሬ ምርቃትና መልካም ምኞታችን ረብ አግኝቶ፣ ሽሜም ከዕለት ወደ ዕለት፣ ከመድረክ መድረክ ችሎታው እየጨመረ እነሆ በአንድ ከሰዓት ሁለት የተለያዩ ቴአትሮችን፣ የተለያዩ ገፀ-ባህሪያትን በመወከል እስከሚጫወትባት ዘውትር እሁድ ላይ ደርሰናል፡፡
የአርቲስት አበራ ደስታ (አበራ ጆሮ) የቴአትር ክበብ የአባቱን ስም ለማስታወስ በ1980ዎቹ መጨረሻ አካባቢ በራሱ ፍላጎት የመሰረተው ክበብ ነበር፡፡ በወቅቱ ዛሬ ትላልቅ መድረኮች ላይ የምንመለከታቸው የመድረክ ዕንቁ ተዋንያን ከሽሜ ጋር አብረው በክበቡ የመድረክ ድራማ ይሰሩ ነበር፡፡
የሰው ልጅ የህይወት መንገዱ መታጠፊያ አንድ የሆነች ጊዜ በህይወት ውስጥ መፈጠሩዋ አትቀርምና በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ለረጅም ሳምንታት በወቅቱ ተወዳጅ በነበረው የ120 ፕሮግራም ላይ የቀረበው “የህሊና ዕዳ” ድራማ የሽሜን ህይወት ወደ አንድ የተሻለ የህይወት መንገድ ሊመራው ችሎአል፡፡
“ህልም -ዕልም ትዝ በሚለኝ የያን ጊዜው “የህሊና ዕዳ” የቲቪ ድራማ፤ ሽመልስ አበራ ጆሮ፤ የፍቅረኛውን የብሩክን ገፀ-ባህሪ ተላብሶ በመጫወትና በሚለቀስበት የፊልሙ ክፍል፣ የዕውነቱን በማንባቱ በተመልካች አንጀት ውስጥ ዘፍ ብሎ በመደላደል ሊቀመጥ የሚችልበትን ነጥብ አስቆጠረ፡፡
ከወዳጅ ዘመዱ ርቆ….አንጀቱን በአንጀቱ ታጥቆ
 ተሸሽጎ፣ ተገልሎ፣ ተሸማቆ…ተሸማቆ
 ከቤተ-ሰው ተደብቆ
 መሽቶ የማታ ማታ ነው ሌት ነው የወንድ ልጅ
 ዕንባው
 ብቻውን ነው የሚፈታው…..ብቻውን ነው
 የሚረታው!
(ከሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን “ወንድ ብቻውን ነው የሚያለቅስ” ከሚለው ግጥማቸው የተቀነጨበ)
 
 ይህን የባለቅኔውን የግጥም ዕውነታ ሽሮ “የህሊና ዕዳው” ገፀ-ባህሪ ብሩክ በሽመልስ አበራ ጆሮ ድንቅ ትወና በአደባባይ በማልቀሱ የዚህ ተዋናይ ረጅሙ የጥበብ ጉዞን በአስተማማኝ መንገድ ላይ መጀመሩን አበሰረልን፡፡ ሽሜ ያኔ በሴት በወንዱ በተለይ ግን በወጣት ሴቶች ዓይን ውስጥ ገባ፡፡ ሽሜ…ብሩክ….ብሩክ..ሽሜ ሆነ የወቅቱ ጨዋታ……
እሁድን በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የቴአትርና ባህል አዳራሽ፡- ያሳለፍነው እሁድ ተስፋ ኢንተርፕራይዝ ያቀረበውን “የጠለቀች ጀንበር” ቴአትር ለማየት ወደ አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የቴአትርና ባህል አዳራሽ ከባለቤቴ ጋር ብገኝ መቆሚያ መቀመጫ እስኪጠፋ ድረስ ምድረ ጥበብ አድናቂ መግቢያውን በሰልፍ አጥለቅልቆታል፡፡
 ቦታ እንደማላገኝ ተስፋ በቆረጥኩበት ወቅት የቴአትርና የጥበቡ የረጅም ጊዜ ባለውለታ ነው ብዬ የማስበውና የተስፋ ኢንተር ፕራይዝ ባለቤት (በርካታ የቆዩ ቴአትሮችን እንደገና ለተመልካች በማቅረብ የሚያስደስተን) አርቲስት ተፈራ ወርቁን አግኝቼው በክብር ወደ አዳራሹ እንድገባ ከነባለቤቴ ተጋበዝኩ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ተፈራ ወርቁን ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
የጠለቀች ጀምበር ቴአትር ማስታወቂያ በልጅነት ትዝታ፡- በልጅነት አዕምሮዬ አንድ የሬዲዮ ማስታወቂያ ተደጋግሞ ሲነገር አስታውሳለሁ፡፡ ቃል በቃል እንዲህ ይል ነበር:- “የጠለቀች ጀምበር…በሃገር ፍቅር ቴአትር!….ድርሰት ሄነሪ ኢብሰን አዛማች ትርጉም አጥናፉ መኩሪያ፡፡ አዘጋጅ ሃይለማርያም ሰይፉ…ረዳት አዘጋጅ ግርማ ብስራት”….ፓ ፓ ፓ ፓ ምንም አልተረሳኝም፡፡
 ያን ጊዜ የተዋናይ ስም ዝርዝር ሲጠቀስ ግን ዛሬ ሽመልስ አበራ ጆሮ ይጫወተው የነበረውን ባህሪ የሚጫወተው ነፍሱን ይማረውና አርቲስት ጌታቸው የሻው ነበር፡፡
ድንቅ ጊዜ!ይህ ማስታወቂያ በሚነገርበት ጊዜ ዕድሜዬ ለአቅመ ቴአትር ቤት ባለመድረሱ ቴአትርን ጌታቸው ሲሰራው አልተመለከትኩትም፡፡
ሆኖም ቴአትሩ ከሃገር ፍቅር ቴአትር መድረክ ከወረደ ከብዙ ዓመታት በሁዋላ ይኸው ቴአትር ተመልሶ፣ በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ የጌታቸው ቦታ በሽሜ ተተክቶ ዳግም ለመድረክ በቃ፡፡ “የጠለቀች ጀንበር” እንደገና ለሶስተኛ ጊዜ መሆኑ ነው ከሽመልስ ውጪ አዳዲስ ተዋንያንን ይዞ አሁንም በተስፋ ኢንተርፕራይዝ አማካኝነት ዳግም ወደ መድረክ የተመለሰው፡፡…ድንቅ ነው!
ያኛውና ይሄኛው “የጠለቀች ጀምበር” ቴአትር በእኔ ንፅፅር፤ ሽሜ በአካልም በችሎታም ገዝፎ የሚታይበት ይሄኛው “የጠለቀች ጀምበር” ቴአትር በዘመኑ የቴአትር እሳቤ እንመዝነው ብንል ለእኔ የያኔው ሚዛን ይደፋብኛል፡፡ ምክኒያቱም ዛሬ እኔም ሽሜም በአካልም፣ ቴአትርን በመመዘን ችሎታም፣ በልምድና በትምህርትም አንድ ደረጃ ከፍ ብለናል፡፡
በመሆኑም ቴአትሩ ለዚህ ዘመን ምጣኔ ብዙ ጥያቄዎች ቢነሱበትም የሽመልስ አስገራሚ የመድረክ ትወናና አብረውት የሚጫወቱት ወጣትና አንጋፋ ተዋንያን ብቃት ዛሬም ያንን ዘመን በትዝታ የኋልዮሽ መለስ ብለን እንድንመለከተው ግድ ያስብለናል፡፡ በቴአትሩ ማጠቃለያም የሽሜን አንጀት የሚበላ ድምፅ በመስማት የዕምባ ዘለላዎች ከአይናችን ዱብ እስኪሉ ድረስ እንመሰጣለን!
በዚሁ ዕለት ሽሜ “የጠለቀች ጀምበር”ን ቴአትር እንደጨረሰ ለሌላ የመድረክ ቴአትር ዝግጅት ከመድረክ ጀርባ ገብቶ ራሱን ያዘጋጃል፡፡ “ዕንግዳ” የተሰኘው የተወዳጁ ማንያዘዋል እንደሻው ቴአትርን ለመጫወት!….ለሌላ የሁለት ሰዓት ድራማ በአዲስ ሃይልና ጉልበት እንደገና ተሞልቶ በሌላ ገፀ-ባህሪ ተመልሶ ወደ መድረኩ ብቅ ይላል፡፡ ዕፁብ ድንቅ ነው ይሄም!
 ደሞ ወደሬዲዮ ድራማ፡- የተወዳጁ ፀሃፊ ተውኔት ሀይሉ ፀጋዬ ድርሰት የሆነው “የማዕበል ዋናተኞች” የሬዲዮ ድራማ ሽመልስ አበራ ዳግም በጥበቡ ዓለም የነገሰበትን አጋጣሚ ይዞ የመጣ ነው፡፡
በድራማው የጌትን የልብ ወዳጅ ሆኖ ከራሱ ከሀይሉ ፀጋዬ ጋር አብሮ የሚጫወተው ሽሜ ድራማው የዕውነት እስኪመስለን ድረስ በጥበብ ባቡር ይዞን ጭልጥ ብሎአል፡፡ የእነ እፁብ ድንቅ ድራማ ተብሎ በተለምዶ ይነገር በነበረውና ተደጋግሞ በሬዴዮ የቀረበው ያ…ተወዳጅ ድራማ ለእኔ በሬዴዮ ድራማ፣ ታሪክ ወደር ያጣሁለት ነው ለማለት እችላለሁ፡፡
 ለዚህ ድራማ መወደድ ከድምፀ መልካምዋ መስታወት አራጋውና ከደራሲው ጌትን ሆኖ ከተጫወተው ሃይሉ ፀጋዬ ጋር ሽመልስ አበራ ጆሮ ያሰማን ረቂቅ ትወና ዋነኛ ምክኒያት ሆኖ ሊጠቀስ ይችላል፡፡
በሌላ የመድረክ ቴአትር ትውስታ የኋልዮሽ፡- በአንድ ወቅት ወሳኝ የመድረክ ፈርጦች አንድ ላይ የተሳተፉበት ቴአትር ወደ መድረክ ቀርቦ ነበር። የቴአትሩ ርዕስ “ትንታግ” የሚል ሲሆን ደራሲው ንጉሴ የሚባሉ አንድ በወቅቱ በባህልና ማስታወቂያ ቢሮ ውስጥ በሃላፊነት የሚሰሩ ሰው ነበሩ፡፡
 በዚህ የመድረክ ቴአትር ላይ ምንጊዜም የማከብራቸውና በመድረክ ችሎታቸው የምደነቅባቸው ሽመልስ አበራ ጆሮ፣ ዓለማየሁ ታደሰና ደበሽ ተመስገን በጋራ ሲተውኑ የተመለከትኩበት ድንቅ አጋጣሚ ነበር፡፡ ቴአትሩ ኢህአዲግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር መቼቱን አድርጎ የቀረበ ሲሆን ሽመልስ አበራ ጆሮ የደርግ ጄነራል፣ ዓለማየሁ ታደሰ ደግሞ ገና ከጫካ የመጣ ታጋይ ሆነው የተወኑበት ነበር፡፡
ይህ ቴአትር ተመልሶ ወደ መድረክ እንደሚመጣ ባለሙሉ ተስፋ ነኝ፡፡ (የቤት ስራውን ደግሞ ለተፈራ ወርቁ-ተስፋ ኢንተርፕራይዝ ሰጥቻለሁ።)
 የሚስት ያለህ… በሽሜ ስቃይ እኔ የምሰቃይበት የመድረክ ቴአትር፡- በብሄራዊ ቴአትር ጎበዝ በምላት አዜብ ወርቁ አማካኝነት በቀረበውና ዘወትር ማክሰኞ ለረጅም ሳምንታት በታየው ቴአትር ላይ የሽሜ ስቃይ እስካሁን ይሰማኛል፡፡
 ይኸውም ቴአትሩ ለሁለት ሰዓታት ከምናምን ደቂቃዎች በመድረክ ላይ ሲቆይና ተዋናዮች ሲፈራረቁ ሽሜ ግን ለአንድም ደቂቃ ከመድረክ ሳይወርድ፣ ላቡ በጀርባው እንደውሃ እየወረደ ድንቅ ትወናውን ያሳየናል፡፡
ድምፁ አንዲትም ሳትደክም፣ ወኔው ሳይከዳው ለረጅም ሳምንታት ከመደረኩ ሳይወርድ በተወነበት በዚህ ቴአትር ላይ ለእርሱ ድካምና ስቃይ እኔ ቴአትሩን ደጋግሜ የተመለከትኩት ተመልካቹ ተሰቃይቻለሁ!
 የሽሜ የመድረክ ቴአትሮችን ብዛት ለመቁጠርና እነርሱንም መተንተን የዚህ ፅሁፌ ዓላማ አይደለም። ይልቁንም ወደ ፊትም ወደ ኃላም እያልኩ የአባቱ ልጅ ሽመልስ አበራ ጆሮን በተለያዩ ማዕዘናት ለማየት እየሞከርኩ እንደሆን አንባቢ ይረዳልኝ፡፡ አሁን ደግሞ ወደ ቅርብ ጊዜው ሰኔ 30 የቪዲዮ ፊልም ልምጣ፡፡
ሽሜ በሰኔ 30 ፊልም፡- ይህን ፊልም በሚቀረፅበት ወቅት የሽመልስ ዓይን ጠፋ የሚል እጅግ አስደንጋጭ ዜና ሰምተን ነበር፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ሽሜ በፊልሙ ላይ የሚጫወተውን ዓይነ-ስውር ገፀ-ባህሪ ፈፅሞ ከራሱ ጋር ለማጣጣም በማሰብ ከውጪ አገር አንድ የዓይንን ጥቁሩን ክፍል(ብሌኑን) የሚሸፍንለትና እውነተኛ ዓይነ-ስውር የሚያስመስለውን ጠብታ ያስመጣል፡፡ ይሄንን ጠብታ ከተቀባ በሁዋላና ፊልሙን ቀርፃ ከመድሃኒቱ ጋር አብሮ በመጣ መድሃኒት ዓይኖቹን መታጠብ ይጠበቅበታል፡፡
ሆኖም መታጠቢያው በድንገት በማለቁ ዓይኑ አልገለጥ ይላል፡፡ ሆስፒታል ተወስዶ በስንት መከራ በተደረገለት ርብርብ ዓይኖቹ ከመጥፋት ሊተርፉ ችለዋል፡፡ ይህ እንግዲህ ለጥበቡ የተከፈለ ታላቅ መስዋትነት ሊባል ይችላል፡፡ ከዚያ መለስ ግን በፊልሙ ላይ ያሳየን ድንቅ ትወና የሽሜን ዕምቅ አቅም እንደገና ምስክር ሆኖ ያሳየን ነው፡፡
መከራ ቻዩ ሽመልስ አበራ ጆሮ፡- ከቀደምት ባለቤቱ ቢጡ ፈቄ ጋር በነበረው አለመግባባት ትዳሩን በመፍታቱና ከልጆቹም ጋር በመለያቱ በሽሜ ላይ የደረሱት የተለያዩ የመንፈስ ስብራቶች መከራ ቻይነቱን ይመሰክራሉ፡፡ የእኛ ህዝብ የጥበብ ሰዎችን ሲወድም ሆነ ሲጠላ በስራዎቻቸው ብቻና ብቻ ሳይሆን በግል ባህሪም ጭምር በመሆኑ “ሽመልስ ልጆቹን ካደ፣ ሲያልፍለት ሚስቱንም ትቶ ሌላ አገባ” የሚሉ ሃሜቶች የወቅቱ የግል ጋዜጦችና መፅሄቶች የፊት ገፆችን ማድመቂያ ርእሰ-ጉዳይ ሆኖ ነበረ፡፡
ይህ የመንፈስ ስብራት አሸንፎት ሽሜ ከመድረክ ወደ ኋላ አላለም፡። እንዲያውም በሳምንት ከ5 ጊዜ በላይ የመድረክ ስራዎች ለህዝብ የሚያቀርብበት ወቅትም ነበር፡፡ ለእርሱ መድረክ የጥበብ ፍላጎቱን መወጫውና የእንጀራ ማግኛ ገመዱ ብቻ ሳትሆን የክፉ ጊዜው መደበቂያውም ናት፡፡
 በበርካታ ፊልሞችና የመድረክ ስራዎቹ የምናውቀውና የምንወደው ተዋናይ ሽመልስ አበራ፤ ከሬዲዮና የቴሌቭዥን ድራማዎች ውጪ በማስታወቂያ ስራዎች ላይ ተሰማርቶ እምብዛም አናየውም፡፡ ለምን?
ማስታወቂያ የማይሰራው ሽሜ፡- ማስታወቂያ በነጋዴዎች አዕምሮ ብቻ ይመራ የሚል ህግ ያለ ይመስል የእኛ አገር ማስታወቂያ አሰሪ ባለንብረቶች፣ የማስታወቂያውን ጥበባዊ ቃና በመዝለል ምርቶቻቸውና አገልግሎታቸው ብቻ ገኖ እንዲወጣላቸው ይፈልጋሉ። ይህ ደሞ ለእኔ አይመቸኝም::
የማስታወቂያ ድርጅቴንም የዘጋሁት በአገራችን የማስታወቂያ አሰራር ላይ የራሴ የሆነ ቅሬታ ስላለኝ ነው ይላል፤ ሽመልስ አበራ በተለያዩ ቃለ-መጠይቆች ማስታወቂያ ላይ ለምን በብዛት እንደማይታይ ተጠይቆ ሲመልስ!
ማጠቃለያ፡- በመድረክና ፊልም ዝግጅት /በአዘጋጅነት/ ብዙም የማይሰራው ሽመልስ አበራ ጆሮ፤ አልፎ አልፎ ተመሳሳይ ገፀ-ባህሪያትን የመጫወት ድግምግሞሽን ከወዲሁ ማስቀረት አለበት፡፡ በተለይ ለቅሶ ያለበትን፡፡
 ድርሰቱ ኬት ይመጣል አትበሉኝና አሁን ሽሜ በደረሰበት የመድረክ ከፍታ የእርሱን ችሎታ ፈፅሞ በሚፈታተኑ፣ ከዚህ ቀደም ተጫውቶአቸው በማያውቃቸው፣ በዓይነታቸውና በይዘታቸው በተለዩ የመድረክ፣ የቴሌቭዥንና የሬዲዮ ድራማ እንድናየው እሻለሁ፡፡ ለዚህም ሽሜ ከበቂ በላይ ልምዱና ችሎታው አለው፡፡ ልክ እንደ ለ “ዕረፍት የመጣ ፍቅር” ገፀ-ባህሪ!
Filed in: Amharic