>

ብርቅዬው ብሔረሰብ!!! (ሳሚ ዮሴፍ)

ብርቅዬው ብሔረሰብ!!!

ሳሚ ዮሴፍ

• 61 ብቻ ሲቀሩ 12ቱ ብቻ ቋንቋውን ይናገራሉ።

• እባብ ለቁጥራቸው መቀነስ አስተዋጽኦ አድርጓል!!!

 
        የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ክልል የ56 ብሔሮች መገኛ ነው። ከነዚህ መካከል 16 ያኽሉ ዋና መናገሻቸውን ጂንካ ከተማን አድርገው በደቡብ ኦሞ ዞን ውስጥ ይኖራሉ። ዞኑ በ8 ወረዳዎች እና የ1 ከተማ አስተዳደር የተከተፈለ ሲሆን ከነዚህ ወረዳዎች “ቀይ አፈር” የተባለች አነስተኛ ከተማን መናገሻቸው አድርገው የሚኖሩት የበና፤ፀማይ እና ብራይሌ ብሔሮች ወረዳ የሆነችው የበና፤ፀማይ ወረዳ አንዷ ነች።
በወረዳው የበና፤ፀማይ ብሔሮች ከፍተኛውን ቁጥር የያዙ ሲሆን ብራይሌዎች በአንጻሩ በመጥፋት ስጋት ላይ ያሉ ብሔሮች ናቸው።
በአሁኑ ሰዓት 61 የብራይሌ ብሔር አባላት ብቻ ሲኖሩ አንጎታ የተባለውን ቋንቋቸውን መናገር የሚችሉት 12 ያህል ብቻ ናቸው።
የብሔረሰቡ አባላት በወረዳው በእንጨቴ ቀበሌ ልዩ ስሙ ገኤ ወንዝ ድሮ ነው በሚባል መንደር ተሰብስበው የሚኖሩ ሲሆን አንድም የብሔረሰቡ አባል ከተጠቀሰው መንደር ውጪ በየትኛውም ስፍራ አይገኝም።
ብሔረሰቡ የተመሠረተበት ምክንያት በተለያዩ አካባቢዎች ድርቅና ርሃብ በመከሰቱ በምግብ ፍለጋ ስምሪት ሲሆን ከሰባት ከማያንሱ ብሔረሰቦች ተሰባስበው የተመሠረተ ነው
እነዚህም:- ኮንሶ፣ ገዋዳ፣ ማሌ፣ ቦና፣ ጋቦ፣ ቦረና እና ኤርቦሬ ናቸው። ለብሔረሰቡ ቁጥር ማነስ ዋንኛ ምክንያቶች ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል በአካባቢው የትምህርትና የጤና ተቋማት በበቂ ሁኔታ አለመገንባታቸው በበርሃማው የአየር ንብረት ምክንያት በሚፈጠሩ መርዛማ እባቦች ተነድፎ መሞት እንዲሁም በከፍተኛ ሁኔታ በወባ ወረርሽኝ እና ሌሎች የጤና እክሎች መጠቃት ይገኙባቸዋል።
እንደ ወረዳው የባህልና ቱሪዝም የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት መረጃ በመጥፋት ላይ ያለው ይህ ብሔረሰብ 3 ባህላዊ የአስተዳደር እርከኖች አሉት።
የበላይ ሆኖ የሚያስተዳድርውና 5 አባላት ያሉት “ባልኮ” ሲሰኝ በተመሳሳይ 5 አባላትን ያቀፈውና የምክትል አስተዳደርነት ስልጣን ያለው አካል ደግሞ “ሙርጃል አፍ” ይሰኛል። “ሙርጃል አፍ” ዋንኛ ሃላፊነቱ በብሔረሰቡ መካከል ችግሮች ሲፈጠሩ ይፈታል ስብሰባዎች ሲኖሩ ባህላዊ መጠጥ (ጨቃ) እንዲዘጋጅ ትእዛዝ ያስተላልፋል።
ሦስተኛው የአስተዳደር እርከን እንደቀደሙት ሁሉ 5 አባላትን ያቀፈ ሲሆን “ጉርማልኮ” ይሰኛል። የዚህ ደረጃ ባለስልጣን መሆኑን ለመለየት “ዘንግ” ይያዛል ዘንጉን የያዙት የሚሰበሰቡት ሜዳ ላይ ሴቶች ድርሽ ማለት አይፈቀድላቸውም። የሜዳው ስም ናቦ ይባላል።
ብራይሌዎች ሦስት የጋብቻ አይነቶች አሏቸው።
የመጀመሪያው “ኢፋም” የተሰኘ ሲሆን በሁለቱ ተጋባዊች ስምምነት የሚፈፀም ነው።
“አይሳት ሻዳል ቤት” የተሰኘው ጋብቻ ደግሞ የውርስ ጋብቻ ነው።
“እዴ ባዶጂካ ኢስማ” ደግሞ በተጋቢ ወላጆች ስምምነት የሚፈፀም ጋብቻ ነው። ወንዱ ለአቅመ አዳም በሚደርስበት ወቅት በሴቷ ጥሎሽ የሚሰጠው አሣ፣ ማር እና ጋቢ ነው።
በብሔረሰቡ የወንድም ሆነ የሴት ግርዛት ነውር ነው።
በብራይሌዎች ዘንድ በለቅሶ ወይም ሃዘን ወቅት ለልጅና ለአዋቂ የሚከናወነው ስርዓት የተለያየ ነው።
አዋቂ ሲሞት አረቄ ተገዝቶ ባህላዊ መጠጥ (ጨቃ) እየተጠጣ ይጨፈራል መሣሪያ ይተኮሳል የሟች ደግ ሥራ በዘፈን ይወደሳል። ይህ ስርዓት እየተከናወነ አንድ ቀን ይታደርና ቀጥሎ ባለው ቀን ግብዓተ መሬቱ ይፈጸማል።
ወጣት ወይም ልጅ ከሞተ ደግሞ እጅግ ይታዘናል አምርረው ያለቅሳሉ የቡና ገለባ (ሸፈሮ ይበላል) አፍልተው ይጠጣሉ ሃዘናቸውን ለመግለጽም አምባር ጨሌና ሌሎችንም ጌጣጌጦቻቸውን ያወልቃሉ፤ ፀጉራቸውንም ይላጫሉ።
ብራይሌዎች በስፋት ለምግብነት የሚጠቀሙት አሣ ነው በአካባቢው ከሚገኘው የወይጦ ወንዝ አሣ በማውጣት የአሣውን ሥጋ እንደ ቋንጣ በመዘልዘል ይመገቡታል። ሙዝ፣ በርበሬና ሽንኩርት ይተክላሉ በባህላዊ ቀፎ ንብ በማርባት በሚያገኙት የማር ምርትም ይታወቃሉ።
ሳሚ ዘብሔረ ኢትዮጵያ
ቸር ይግጠመን
Filed in: Amharic